የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለረጅም ዓመታት በአለመረጋጋት ውስጥ ካለፉ የዓለም አካባቢዎች አንዱ ነው። አካባቢው ካለው ጂኦ ፖለቲካል ስትራቴጂ ጠቀሜታ አንጻር የብዙዎች አይን ማረፊያም ነው። በተለይም ኃያላኑ ሀገራት በአካባቢው አለን የሚሉትን ጥቅም ለማስከበር ከፍ ያለ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት አካባቢ ነው።
ኃያላኑ ሀገራት በአካባቢው አለን የሚሉትን ስትራቴጂክ ጥቅም ለማስከበር የአካባቢውን ሀገራት መንግሥታት በየጎራቸው በማሰለፍ የሀገራቱን ህዝቦች ለከፋ ስቃይ፣ መከራ፣ ሞትና ስደት ዳርገዋቸዋል። ቀጣናው ከማያቋርጥ የግጭት አዙሪት ውስጥ እንዳይወጣም በአንድም ይሁን በሌላ ጫናዎችን ሲፈጥሩ ቆይተዋል።
አካባቢው ላይ የሚኖሩት ህዝቦች በባህል እና በሃይማኖት የተሳሰሩ ለዘመናት አብረው የኖሩ ከዚያም በላይ አንዳቸው ለአንዳቸው ቤተሰብ የሆኑ ፤ ከፍ ባለ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የተሳሰሩ ናቸው። ዕጣ ፈንታቸው በብዙ የተጋመዱ ህዝቦችም ናቸው። አንዳንዶቹም ቅኝ ገዥዎች ሲቀራመቷቸው በተፈጠረ አዲስ ማንነት የተገነቡ ናቸው።
እነዚህ ህዝቦች የቅኝ አገዛዝን ቀንበር ከፍ ያለ ዋጋ ከፍለው ከጫንቃቸው ላይ መስበር ቢችሉም፤ ወደ አንድነት በመምጣት በጋራ ዕጣ ፈንታቸውን ለመወሰን ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤት ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። ከዚያ ይልቅ ቅኝ ገዢዎች በቀበሯቸው ጊዜ እየጠበቁ በሚፈነዱ ቦምቦች ወደ ግጭት በማምራት አካባቢው የግጭትና የአለመረጋጋት ማዕከል ሆኖ ቆይቷል።
ከነፃነት ማግስት ነባራዊና እውነታ ጋር በተያያዘ የአካባቢው ሀገራት ህዝቦች በዓለም አቀፍ ደረጃ መታወቂያቸው ድህነትና ከዚሁ የሚመነጭ ጉስቁልና፤ ግጭት፣ ሞትና ስደት ሆኗል። ከዚያም አልፎ በአካባቢው ባለው የግጭት አዙሪት ምክንያት በቀጣናው ጠንካራ መንግሥት መመስረት ባለመቻሉ የአክራሪ ቡድኖችና የጽንፈኛ ኃይሎች መፈልፈያ ለመሆን ተገደዋል። ይህም ለሀገራት ህዝቦች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖባቸዋል።
የአካባቢው ሀገራት ህዝቦች ተፈጥሮ የቸረቻቸው፣ ወደ ሀብትነት ሊለወጡ የአካባቢውን መገለጫ በተጨባጭ ሊለውጡ የሚችሉ የተፈጥሮ ሀብት ባለሀብቶች ቢሆኑም ይህን ሀብት ተጠቅመው ዕጣ ፈንታቸውን እንዳይወስኑ ዛሬም ከፍ ባለ የሰላም ተግዳሮት ውስጥ ይገኛሉ። ዜጎቻቸውም በአውሮፓና በአሜሪካ የስደተኝነት ዕድል ለማግኘት ሲዳክሩ ውለው የሚያድሩ ናቸው።
ከሁሉም የሚያሳዝነው የሀገራቱ ህዝቦች ዕጣ ፈንታቸው ከመተሳሰሩ የተነሳ በአንድም ይሁን በሌላ በአካባቢው በተከሰቱ ግጭቶች ማንም ተጠቃሚ ሊሆን አለመቻሉ ነው። ግጭቶቹ ሁሉን የአካባቢው ሀገራት ህዝቦች በአንድም ይሁን በሌላ ከፍ ያለ ዋጋ ከማስከፈላቸውም በላይ የሁሉም ነገዎች ላይ ጭጋግ አልብሰው አልፈዋል።
የአካባቢው ሀገራት ህዝቦች አካባበያዊና ዓለም አቀፋዊ በሆኑ የፖለቲካ ሴራዎች ከነፃነት ማግስት ጀምሮ የተረጋጋ ፖለቲካ መፍጠር ተስኗቸው ላለፉት ስድስት አስርታት አንዳች ባላተረፏቸው ግጭቶች ውስጥ ለማለፍ ተገደዋል። ከቤተሰብነት ወጥተው በጠላትነት እንዲተያዩ፤ ከዚያም አልፈው ወደ ጦርነቶች እንዲገቡም ተደርጓል። በዚህም ብዙ የተስፋ ቀናቶቻችውን አባክነዋል።
ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ዛሬ ላይ በአዲስ የታሪክ ምዕራፍ ውስጥ ይገኛሉ። የቀደመውን የቤተሰብነት ታሪካቸውን በማደስ አዲስ የትብብር እና የጉርብትና የታሪክ ምዕራፍ ውስጥም ገብተዋል። በተለይም በኢትዮጵያ የተጀመረው ለውጥ የቀደመውን ታሪክ በሚለውጥ መልኩ የአካባቢውን ሀገራት ከጠላትነት እና ከመፈላለግ ወጥተው ወደ ቀደመው ቤተሰብነት እንዲመለሱ የሚያግዝ ነው።
ከዚህም በላይ ትርጉም ከማይኖረው የግጭት ማዕከልነት ወጥተን ትርጉም ወደሚኖረው የልማት አጋርነት፤ዕጣ ፋንታችንን በጋራ ወደ መቅረጽ የሚያመጣን ጉርብትናና መተማማን የሚያሻግር ፤ የአካባቢውን ሀገራት ሕዝቦች ከግጭት አዙሪት በማውጣት ለዘመናት ተስፋ ሲያደርጉት ወደ ቆዩት የህዝቦች ብልጽግና የሚወስድ ትክክለኛው መንገድ እንደሚሆን ይታመናል።
ይህ ታሪካዊ እውነታ ከሁሉም በላይ የአፍሪካ ቀንድን የአፍሪካ ክንድ ለማድረግ የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ፈጥሯል። ይህን አጋጣሚ ወደሚጨበጥ ታሪክ ለመለወጥ የአካባቢው ሀገራት መሪዎች ከፍ ያለ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል።
የቀደሙት ያለመተማመንና የግጭት ዓመታት ህዝቦቻችንን ካስከፈሏቸው ዋጋዎች አንጻር ቀጣዮችን ዓመታት ለህዝቦቻችን የካሳ ዓመታት ማድረግ፤ ለዚህም በቂ ዝግጅትና ቁርጠኝነት መፍጠር ይኖርባቸዋል። ከሁሉም በላይ ለአካባቢው ሀገራት ህዝቦች ፍላጎት ለተገዙ አጀንዳዎች ቅድሚያ መስጠትም ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 8/2013