የኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚጠይቅ፣ አዋጪ ቴክኖሎጂ የሚፈልግ፣ የተሻለ መሠረተ ልማት የሚያሻውና በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ካፒታልን የሚጠይቅ ዘርፍ ነው:: መንግሥት ይህን ዘርፍ ለማጐልበት በአገሪቱ በተመረጡ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ገንብቷል፤ በመገንባትም ላይ ይገኛል። ከእነዚህ ከተሞች መካከል ደብረብርሃን አንዷ ናት።
ዕድሜ ጠገቧ ከተማ ደብረብርሃን ለብዙ ዘመናት ከዕድገት ተለያይታ የዕድሜዋን ያህል ማደግ ተስኗት ብትቆይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ያንቀላፋችበትን ጊዜ ለማካካስ እየታተረች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅትም አገራዊ ፋይዳቸው የጎላ የኢንቨስትመንት ዘርፎች መዳረሻ እየሆነች መጥታለች።
ከተማዋ በተለይም የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ማዕከል የመሆን ግሥጋሴ ላይ ትገኛለች። በከተማዋ የተገነባው የኢንዱስትሪ ፓርክም የዕድገት ሩጫዋ ዋነኛ ሞተር ሆኗል። በ75 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ፈሰስ የተደረገበት የኢንዱስትሪ ፓርኩም ከሁለት ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ እና በኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ተመርቆ ወደ ሥራ ገብቷል።
የኢንዱስትሪ ሠላም በሰፈነባት ከተማ በተገነባውና አስፈላጊው የውሃ፣ የሃይልና ሌሎችም የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎች የተሟሉላት የኢንዱስትሪ ፓርክ ስምንት ሼዶች አሉት። በሙሉ ወደ ሥራ ሲገባ ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይጠበቃል። የኢንዱስትሪ ፓርኩን በሙሉ አቅም ወደ ሥራ ለማስገባት እና ተጠቃሚነትን ለማጎልበትም ባለሃብቶችን በማስገባት እና እንዲያለሙ በማስተላለፍ ረገድ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ ቆይተዋል።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ዘርፉ በአገራዊ የምርት መጠን ላይም ሆነ በሥራ ዕድል ፈጠራ ያለውን ድርሻ ለማጎልበት በተለይ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የተደቀኑበትን ችግሮች ማቃለል ዋነኛ ትኩረቱ በማድረግ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በአሁኑ ወቅትም በአገር አቀፍ ደረጃ ወደ ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚመጡ የአምራች ዘርፍ ተሳታፊዎች እየጨመሩ መጥተዋል። በደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክም የተለያዩ ባለሃብቶች ወደ ሥራ ገብተዋል። በርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገርም የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ጀምረዋል።
የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ እንደገለፁት ኢንዱስትሪ ፓርኩ ወደ ሥራ ከገባ አንድ ዓመት ያልሞላው ቢሆንም ለ1132 ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩ ባሻገር ምርት ወደ ውጭ በመላክ 17 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘት ችሏል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ከአምስቱ ሼዶች ውስጥ በአንዱ የስፔን ባለሐብት በሹራብ ሥራ ተሰማርቶ እየሠራ ይገኛል። ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ እያስገባ ነው። ሥራ በጀመረ በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ ከሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገባት ችሏል። ፡
የፈረንሣይ ኩባንያ ቡርቱማርት ከ2013 ዓ.ም ጥር ወር ጀምሮ በወር ወደ ሦስት ሺህ ቶን ብቅል በማምረት በየወሩ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ እያስገባ ይገኛል ያሉት አቶ የሺጥላ ኩባንያው ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ወጪን አድኗል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በፈረንሣይ ባለሐብት በሁለት ነጥብ ሦስት ቢሊየን ብር ወጪ ተገንብቶ ባሣለፍነው ዓመት ወደሥራ የገባው ኩባንያ በዓመት ስልሳ ሺህ ቶን ብቅል የማምረት አቅም አለው። ይህም በአገሪቱ ለሚገኙ ከ14 በላይ ለሚሆኑ የቢራ ፋብሪካዎች ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችል ነው።
ድርጅቱ ለምርት የሚያስፈልጉትን ግብዓቶች ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በፈጠረው ትስስር ያገኛል። በዚህም የገበያ ትስስር ከ40 ሺህ የሚሆኑ የደብረ ብርሃን እና አካባቢው አርሶ አደሮች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በመሆን ላይ ናቸው።
ከወራት በፊት የጋዜጣው ሪፖርተር በኢንዱስትሪ ፓርኩ በመገኘት ባደረገው ምልከታ፣ በፓርክ ውስጥ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ቢኖርም በተለይ የባንክ አገልግሎት ዋነኛ ችግር መሆኑን አስተውሏል። ባለሐብቶቹም የሚፈልጉትን አገልግሎት ለማግኘት አዲስ አበባ ለመሄድ መገዳደቸውን ከፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመረዳት ችሏል።
ከሁሉ በላይ ግን 13 ሄክታር መሬት ለሼዶች ግንባታና ለባለሀብቶች የተዘጋጀ ቢሆንም፣ ባለሐባቶቹን በማስገባት እንዲያለሙ ማድረግ ባለመቻሉ መሬቱ ባክኖ ለመቀመጥ መገደዱን ለማወቅ ተችሏል። ፓርኩን በሙሉ አቅም ወደሥራ ማስገባትና ፓርክ ውስጥ በተከለለው ቦታም አዳዲስ ባለሀብቶች ገብተው ማልማት እንዲችሉ የማድረግ ኃላፊነት ያለባቸው የፌዴራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎችም ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል።
የባለሀብቶችን ተሳትፎ በሚመለከት የደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ሙሉጌታ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ውስጥ ከቀሪዎች ሦስት ሼዶች መካከል አንዱን የታይዋን ኩባንያ ይዞታል። ኩባንያውም በአሁኑ ወቅት ሙሉ ለሙሉ የማሽን ተከላ መጨረሱንና በቅርቡ ቅጥር በመፈፀም ወደሥራ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት።
አጠቃላይ የፓርኩን የሥራ ዕድል ፈጠራ በሚመለከት ከደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ፓርኩ በእስካሁኑ ሂደት ለ1132 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013