ሀገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ካጋጠሟት እልህ አስጨራሽ ችግሮች፤ ችግሮቹ ከወለዱት ግራ መጋባት፣ ግራ መጋባቱ ከወለደው ተስፋ መቁረጥ አንጻር በዚህ ደረጃ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለምረቃ ማብቃት ከፍተኛ ቁርጠኝነት እና የመንፈስ ልእልና የሚጠይቅ ነው። ከችግሮቹ በላይ ሆኖ ማሰብን የሚፈልግ ፣ ለጥቂቶች የተሰጠ ጸጋ ነው ።
ያለፉት ሦስት አመታት በአንድ በኩል በሀገሪቱ ከአንዱ ጫፍ እስከ ሌላኛው ጫፍ ድረስ ሁከትና ትርምስ የሰፈነባቸው ፣ ወሬዎች ፣ሞት ፣ መፈናቀልና ስደት የሆኑባቸው ፤ የጥፋት ሀይሎች በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ የህዝብን ሰላምና አንድነት የተፈታተኑባቸው፤ ከዛም አልፈው ሀገርን እንደ ሀገር አደጋ ውስጥ ለመክተት ባላቸው አቅም ሁሉ የተንቀሳቀሱባቸው ናቸው።
በተሳሳተ ግምትና ስሌት አሸባሪው ህወሓት ከፍ ባለና በታሪካችን ባልታየ መልኩ በፈጠረው ክህደትና ክህደቱ የፈጠረው የሀገር መፍረስ አደጋ መንግስትና ህዝብ ብዙ ዋጋ ለመክፈል የተገደዱበት፤ በዚህም ምክንያት ሰፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ውስጥ የገባንባቸው አመታት ናቸው።
የኮረና ወረርሽኝ አለም አቀፍ ስጋት የሆነበት፣ በተለይም እንደኛ ያሉ ኢኮኖሚያቸው በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ያሉ ሀገራት ህዝቦች ላይ ሊያደርስ የሚችለው አደጋ ከፍ ባለ ድምጽ የተሰማበት ፤ በዜጎች ማህበራዊ መስተጋብር ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በራሱ የበረታ ችግር የሆነበት ነበር ፣አሁንም ነው።
የአንበጣ ወረርሽን ፣ ጎርፍ በራሳቸው ሀገራዊ ነገዎቻችን ላይ ከፍ ያለ ጭጋግ መፍጠር የቻሉበት፣ በህዝቡ ውስጥ የነበረው የለውጥ ተስፈኝነት በብዙ ተግዳሮት የተፈተነበት ፣ አንዳንዶች ቀናቱን የሀገራችንና የህዝባችን ክፉ ቀናቶች አድርገው የገመቱበትና ከዚህ ግም ታቸው የተነሳም ወደ ትንኮሳ የገቡባቸው አመ ታት ናቸው።
በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር በግልጽም በስውርም በተያያዙ ምክንያቶች ያልተገቡ አለም አቀፍ ጫናዎች የተስተዋሉባቸው። ዛቻና ማስፈራሪያ ከዛም አልፎ ክልከላዎች የታዩባቸው ፣ በሀገራችን ታሪክ ውስጥ መሪዎች በብርቱ ከተፈተኑባቸው አጋጣሚዎች አንዱና ትልቁ ሊሆን የሚችል ወቅት ነው ያሳለፍነውና እያሳለፍን ያለነው።
እንኳን 100 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብን በለውጥ መንፈስና ባልተረጋጋ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ለሚመራ መንግስት ቀርቶ ፤ ቤተሰብን ለሚመራ አባወራ ቤተሰቡን ቀናትን ማሻገር ትልቅ ተግዳሮት የሆነበት፣ ማህበራዊ ፣ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሀገራዊ አውድ ውስጥ ልማትና የልማት ወሬ ማውራት ለብዙዎች ከፖለቲካ ፍጆታ የማያልፍ የጊዜ መግዣ ዲስኩር ተደርጎ የተወሰደበት ነበር ።
የለውጥ ሀይሉ እነዚህ በራሳቸው እጅግ የሚፈታተኑ ተግዳሮቶች ጨምሮ አሉባልታዎችንና ሀገርና ህዝብን ሊበትኑ የሚችሉ የውሸት ትርክቶችን በብርቱ መንፈስ በጽናት ተቋቁሞ ፣ የህዝቡን የለውጥ ተስፋ በማያጨልሙ፤ ከዛ ይልቅ በለውጡ የበለጠ ተስፈኛ እንዲሆኑ በሚያስችል ቁርጠኝነት ከፍ ያሉ የልማት ስራዎችን አቅዶ ያለ እረፍት በመስራት ዛሬ ላይ ለ ምረቃ እያበቃ ነው።
በሀገሪቱ ስለ ሰላም ከሰላሙ በላይ በሚዜምበት፣ ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖ በሚታይበት ወቅት ግንባታቸው በብዙ ተግዳሮት አመታት ሲያስቆጥሩ የነበሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሳይቀሩ ህይወት ተዘርቶባቸው “እንዲህም ይቻላል እንዴ !” በሚያስብል መልኩ ለፍጻሜ እየበቁ ነው ።
የብዙዎችን ልብ የሰበረ፣ የሀገራዊ ቁዘማ ምንጭ የነበረው፤ ከዚህም አልፎ ጠላቶቻችን በርግጥም “ተመልሰው ተኝተዋል፣ ተዋቸው “ እንዲሉ እድል የሰጣቸው ፣ የታላቁ ህዳስ ግድብ ግንባታ በአዲስ መነሳሳት እና መነቃቃት ወደ ስራ የተገባበት፤ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ተከናውኖ ለሁለተኛው ዙር ሙሌት ብስራት ዋዜማ ላይ እንገኛለን ።
ቁርጠኝነት ካለ የትኛውንም ተግዳሮት መሻገር እንደሚቻል በተጨባጭ የታየባቸው እነዚህ ሦስት የሽግግር አመታት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ የሚሰጣቸው ናቸው። ሀገርን ከጥፋት መታደግ ብቻ ሳይሆን የህዝብን ተስፋ በጭለማ ጭጋግ ውስጥ ማሻገር እንደሚችል የታየበት ነው ።
ዛሬ እየተመረቁ ያሉ ፕሮጀክቶች የለውጥ ሀይሉ ለቃሉ ያለውን ቁርጠኝነት ከማሳየት ባለፈ ሕዝብን ከውስብስብ ችግሮች አውጥቶ እንዴት ወደ ተስፋው ማሻገር እንደሚቻል ለትውልዶች ማስተማሪያ የሚሆን የአዲስ ታሪክ ምእራፍ ጅማሪ ነው።
በዚህ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ችግሮች የቱንም ያህል አቅም ገዝተውና ገዝፈው፣ ሕዝብን እንደ ህዝብ ከተስፋውና አሻግሮ ካየው ብርሀን ሊነጥሉት ቢሞክሩ ፤ የቱንም ያህል ችግር ችግር እየወለደ የችግር ድሪቶ በሀገርና በህዝብ ላይ ጽልመት ቢያጥል፣ ለቃል መታመን ከችግሮች በላይ መሆን እንደሚያስችል በቂ ተሞክሮ የተቀሰመበት ነው። ይህንን ተሞክሮ ይዘን ተስፋችንን አሻግረን ያየነውን ብርሀን እንወርሳለን !
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2013