‹‹ሰኔ ግም ››ሲል፤ ‹‹ለመጪው ክረምት›› እየተባሉ የሚዘጋጁ የተለመዱ ስራዎች አሉ። ሰኔ አርሶ አደሩ ወደ መኸር እርሻው የሚገባበት፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የስራ ዕቅዶቻቸውንና በጀታቸውን አጠናቀው የቀጣዩን አመት ስራ ለመጀመር የሚሰናዱበት ነው። ተማሪው ትምህርት አጠናቆ የበጋውን ልፋቱን ውጤት የሚያይበት … ሌላውም እንዲሁ እንደ ግብሩ ለቀጣዩ ስራ የሚዘጋጅበትና ያሳለፈውን የስራ ጊዜውን ውጤት የሚገመግምበት ነው።
የሰኔ መምጣት ብዙ ነገሮችን እንድናስብ ያደርገናል። እንደ ሀገር የዘንድሮ ሰኔ እይታችን ግን ከለመድነው ለየት ይላል። ብዙ አጓጊ ነገሮችም ከፊት ለፊታችን ተደቅነዋል፤ በተለይ አምስት ዋና ዋና ነገሮችን ለመፈጸምና ለማሳካት ዕቅድ ተይዟል።ለዚህም ውጤታማነት ወገባችንን ጠበቅ፣ ጉልበታችንን በርታ፣ አይናችንን ከፈት አድርገን ልንገባበት ይገባል።
ከመጪው የክረምት ስራችን አንዱ ሰኔ 14 ጀምረን የምናካሂደው ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ነው። በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂደን የምንፈልገውን መንግስት የምንመሰርትበት ወቅት ነው። ለዚህም በርካታ የምርጫ ዝግጅቶች ፣ ቁሳቁሶችን የማሟላት እና ሌሎች ስራዎችም በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አማካይነት እየተካሄዱ ይገኛሉ። መራጩ ህዝብም መብቱን ለመጠቀም የሚመራውን ለመምረጥ ካርዱን በእጁ ጨብጦ የምርጫውን ቀን በናፍቆት እየተጠባበቀ ይገኛል። ይሄ የክረምታችን መግቢያ የመጀመሪያ ስራችን ነው።
በሁሉም ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ ያለው፣ የአንድነታችን ፣የታሪካችን መገለጫ የሆነው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው የውሃ ሙሌት የሚካሄድበትና ኢነርጂ ማመንጨት የሚጀምርበት ነው። ይሄንን ጊዜ ኢትዮጵያውያን የሚጠብቁት ዘጠኝ ወሯ ገብቶ ለመውለድ ቀኗን እንደምትጠብቅ ሴት ነው።
የመጀመሪያው የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ ሲበሰር ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ በጭብጨባና በእልልታ በአደባባይ ደስታውን እንደገለጸ ሁሉ፤ የአሁኑን ስኬት የሚጠብቀውም ከዛ ከፍ ባለ ደረጃ ነው። ይሄንን ለማሳካትም ሌት ተቀን ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ሶስተኛው ተጠባቂ ስራችን ደግሞ ሶስተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ማሳካት ነው። የአለም መነጋገሪያ እስከመሆን የደረሰው ምድርን አረንጓዴ የማልበስ መርሀ ግብር ባለፉት ሁለት የክረምት ዓመታት አለምን ባስደመመ መልኩ ተከናውኗል።
በተለይም የአለምን ሪከርድ የያዘው በቀን ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል የቻልንበት ታሪካዊ ቀን የሚዘነጋ አይደለም። በሁለት ዙር በተካሄደው ችግኝ ተከላ ከዘጠኝ ቢሊየን በላይ ችግኝ መትከል ተችሏል። ከዚህም 87 በመቶ መጽደቁ ተገምግሟል። ሀገራችን ወደ ምድረ በዳነት ልትቀየር አፋፍ ላይ በደረሰችበት ሰዓት የተጀመረው አረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ሶስት በመቶ ደርሶ የነበረውን የደን ሽፋን አሁን ወደ 17 በመቶ ከፍ ማድረግ አስችሏል።
የመርሀ ግብሩ የአምስት ዓመት ዕቅድም 20 ቢሊየን ችግኞችን በመላ ሀገሪቱ መትከል ነው። በዘንድሮው የክረምት ወቅት እንደ ሀገር ስድስት ቢሊየን ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል። ጎረቤቶቻችንም አብረውን ለማልበስ ጭምር አንድ ቢሊየን ችግኞችን ለመስጠት ዝግጅቱ ተጠናቋል። የታሰበው የችግኝ ተከላ ስኬታማ እንዲሆንም በችግኝ ተከላውም ሆነ በእንክብካቤ ስራው ህብረተሰቡ በቀናነት ሊተባበር ይገባል።
አራተኛው ትኩረታችን የእርሻ ስራችን ነው። ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ ትኩረት በመስጠት ምንም መሬት ጦም እንዳያድር ሁሉም ሰው በአካባቢው የሚገኝን ክፍት መሬት በማረስ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው። በተቻለ መጠን የምርት ግብአቶችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ እንዲደርሰው እየተደረገ ይገኛል።
አርሶ አደሩም ከምርጫ ፣ ከችግኝ ተከላ፣ ለህዳሴ ግድቡ ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን የእርሻ ስራውን አጠንክሮ መያዝ አለበት። ቀጣዩ አመት የምርት እጥረት ሳይሆን የምርት መትረፍረፍ የሚደመጥበት ለማድረግ ከወዲሁ ጠንክረን መስራት አለብን።
አምስተኛው ትኩረት የሚሰጠው የክረምት ስራችን ደግሞ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን የበጎ አድራጎት ስራዎች እየሰፉ መጥተዋል። በየአካባቢውና በሌሎችም አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጭምር ለአቅመ ደካማ ዜጎች ድጋፍ የማድረግ፣ አቅመ ደካማ የሆኑ ነዋሪዎችን ቤት መጠገን በዋናነት የሚጠቀስ ነው። ይሄ ስራ በክረምቱ ወቅትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
በእድሜ የገፉና አቅመ ደካማ የሆኑ ዜጎች በጉልምስና ዘመናቸው ሀገራቸውን በእውቀት፣ በጉልበትና በሃሳብ አገልግለዋል። የእነዚህን ሰዎች መኖሪያ ቤት፣ መንገዶችንና የፍሳሽ ማውረጃ ቦዮችን በመስራት አካባቢያችንን ንጹህና ጽዱ ማድረግ ይገባል። በተለይ ወጣቱ ለዚህ ንቁ ተሳታፊ መሆን ይጠበቅበታል።
የመጪውን ክረምት ዕቅዶች አስቀምጠንና አእምሯችንን ለስራ ክፍት አድርገን በቅንነት ተባብረን ከተነሳን ሀገራችንን በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው ፣ በልማቱ ፣ በኢኮኖሚ እድገቱ ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድነትን ወደፊት በማምጣት እናሳድጋለን።ለዚህ ደግሞ የክረምት ስራዎቻችን ውጤታማ እንዲሆኑ እንረባረብ !
አዲስ ዘመን ግንቦት 6 ቀን 2013 ዓ.ም