ጠንካሮች ያሸንፋሉ “the strongest will survive” ሲሉ የስኬት ምሳሌዎች ይገልጻሉ።እነዚህ በምድራችን ላይ “ትጋትና የማይረታ መንፈስ ባለቤት መሆን ከዓለማችን መልካም በረከቶች ለመቋደስ አማራጭ የሌለው መንገድ” መሆኑን ይናገራሉ።
የሰው ልጅ በምቾት እና በነጻነት እንዲኖር የተፈጠረ ቢሆንም፣ የመከራና የችግር ድር ዙሪያውን ከበውት የዓለሙ ሁሉ ጩኸት በእርሱ ላይ የሆነ ይመስል ከችግር ዱቄት ተቦክቶና ተጋግሮ ወደዚህኛው ዓለም የሚመጣው በርካታ ስለመሆኑ በምድር ላይ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ካለው ፈተና መረዳት ይቻላል።
ዋናው ቁምነገር ግን ምድር ላይ ስንፈጠር ይዘነው የመጣነው እድል ሳይሆን እርሱን ገርስሰን ለመጣል የሚያስችል መንፈስ የመታደላችንና የመቻል አቅማችን ነው። ትልቁ አቅም በእድልና በድሎት የመፈጠራችን ጉዳይ ሳይሆን “እጣ ፈንታ” በበረከት የሰጠችንን ፀጋ ጠብቆ የማቆየትና በዚያም የመገልገል ብቃታችን ነው። ለዚያም ይመስላል፤ ብልሆች “ምድራችን” በእድል የሚኖርባት ሳትሆን በረከቷን ለማግኘት ትግል የሚደረግባት፣ የተሰጠንን ላለማጣት የምንፍጨረጨርባት በጥቅሉ “ጠንካሮች ብቻ” በፈለጉት መንገድ የሚኖሩባት እንደሆነች የሚናገሩት።
በዛሬው የዝነኞች የእረፍት ውሎ አምድ በመግቢያችን ላይ ያነሳነውን ጉዳይ በምሣሌ የሚያስረዳልንን እንግዳ ይዘንላችሁ መጥተናል። ይህ እንግዳችን የአካል ጉዳተኛ መሆን ሳያግደው፣ የተሰበረውን መንፈሱን ጠግኖ፣ የተሰጠውን ፀጋ ጠብቆ በመረጠው መንገድ ህይወቱን ማሸነፍና ለሌሎች ምሳሌ መሆን ችሏል።
ከጨለማው ወደ ብርሃን
ገና በልጅነቱ ነበር የህይወት ፈተናን እንዲጋፈጥ ያደረገው ህመም ያጋጠመው። ይህ የጤና ችግር ሰውነቱ እንዳይንቀሳቀስና የአካል ጉዳት እንዲያጋጥመው አድርጎታል። በዚህ ምክንያት ለ9 እና 10 ዓመታት በፍፁም ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ወድቆ ራሱን እስከ ማጥፋት ወደ ማሰብ ደረጃ አድርሶት ነበር። ሠዓሊ፣ ደራሲና የአነቃቂ ንግግር ባለሙያ የሆነው አርቲስት ብሩክ የሺ ጥላ!
ይሁን እንጂ በዙሪያው ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን በማየት መንፈሱን አጠንክሮ፣ ራሱን ለማሸነፍ ብዙ ርቀት መጓዝና ስኬታማ መሆን እንደሚችል ለራሱ ነገረው። መፅሃፍትን በማንበብ፣ ህልሙን ለማሳካት ክህሎቱን ለማንቃት ብዙ ለፋ። በወቅቱ ካጋጠመው የህይወት ግብ…ግብ በላይ ከፊቱ ያለው ብሩህ ተስፋ ጎልቶ ታየው። ያን ጊዜ ባጣው ነገር መቆዘም ሳይሆን ባለውና በሚያገኘው በረከት ሃሴት ያደርግና የበለጠ ይበረታ ጀመር። ሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ።
ከፍፁም ተስፋ መቁረጥ ወጥቶ ለሌሎች ምሳሌ መሆን ጀመረ። በ2003 ዓ.ም የሙያ መንገዱ ስነ ጥበብ እንደሚሆን ወስኖ በጠንካራ ሃሳቡ የተከሸኑ የማህበረሰብን አመለካከትና የጥበብ ጥም የሚያረኩ ስራዎችን ወደ አደባባይ ይዞ ወጣ። በሸራዎቹ ላይ ሃሳቡን እያሰፈረ፣ በቀለማት ተስፋን ብሩህ እይታን መግለጥን ተያያዘው። በተለያዩ የአርት ማሳያ ስፍራዎች “ጋለሪ” የመጀመሪያ ፕሮፌሽናል ስራውንም “በአስኒ ጋለሪ” ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን አዘጋጅቶ ከህዝብ ጋር ተዋወቀ።
ሠዓሊ ብሩክ የሺጥላ በመጀመሪያ ስራው ሳያበቃ የተከፈተለትን ቦይ ተከትሎ የስነ ጥበብ ውጤቶቹን ለታዳሚያን ማቅረቡን ተያያዘው። ከበኩር ስራው አራት ወር ያህልን ቆይቶ “13 ወራቶች” የሚል ርዕስ የሰጠውን የግል አውደ ርእይ ማቅረብ ቻለ። ከዚያ “ፍቅር አሸናፊ”፣ “የኔታ”፣ “አመሠግናለሁ” የሚሉ ርዕሶች ያላቸው ተወዳጅ የሆኑና የገዘፉ የስነ ጥበብ ውጤቶችን በአፍሪካ ህብረት፣ ካፒታልና በመሰል ማሳያ ስፍራዎች ማቅረብና በጥበብ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነትን ማትረፍ ቻለ።
በግሩፕ አውደ ርዕይም ከ15 በላይ ስራዎችን እስካሁን ለእይታ አብቅቷል። ሰዎች በሚሰራቸው የጥበብ ውጤቶቹ ብቻ ሳይሆን ያጋጠመውን የአካል ጉዳተኝነት ፈተና እንዲሁም ህመም ታግሎ ድል ያደረገበትን አሸናፊነቱን ያደንቁ ጀመር። ከዚያ ባለፈ በአልችልም መንፈስ የተተበተበው ደካማነት በእርሱ ምሳሌነት እንደሚቻል እያዩ ወደ ትክክለኛው የህይወት መስመር የገቡ በርካቶች ናቸው።
የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ የመፅሃፍ ድርሰት
ብሩክ የብዙ ሃሳቦች ባለቤት ነው። ከአምስት ዓመት በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነት ያተረፈው የስነ ጥበብ ባለሙያና ሠዓሊ ኤሊያስ ስሜ ባዘጋጀው አውደ ርዕይ ላይ ይገኛል። በዚያ ዝግጅት ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስነ ጥበብንና የስዕል ስራዎችን ሽፋን የሚሰጥ የመገናኛ ብዙሃንና ፕሮግራሞች አለመኖራቸውን ይታዘባል።
በዝግጅቱ ላይ ግን “ኒዮርክ ታይምስ” “ከዋሽንግተን ፖስት” እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ጋዜጠኞች ተገኝተው ነበር። ይኼ ጉዳይ ቁጭት ፈጥሮበት ስነ ጥበብ ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ፕሮግራም ከሙያ ጓደኞቹ ጋር ቀርፆ መስራት ጀመረ። በዚህም “አርት ስቶሪያን” ሰዓሊዎችና በአጠቃላይ በስነ ጥበብ ዙሪያ የሚሰሩ ሰዎችን ያነቃቃና አዳዲስ ሃሳቦችን ያቀበሉ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ሰርቶ አስተላልፏል። አሁን ድጋፍ በማጣቱ ለጊዜው ቢያቋርጠውም በጥረቱ እንደሚቀጥል ግን ባለ ሙሉ ተስፋ ነው።
ደራሲና ሠዓሊ ብሩክ ከላይ ባነሳናቸው ሙያዎች ብቻ አልተገደበም። ይልቁኑም ያሳለፈው የህይወት ፈተናና ከባዱን ችግር የተወጣበት መንገድ ብዙዎችን እንደሚያነቃ እምነት ስለነበረው “የኔ ስጦታ” እና “የምስጋና ፀሎት” የሚሉ ርዕስ ያላቸው ስራዎችን ለንባብ አብቅቷል። እነዚህ የስነ ፅሁፍ ውጤቶች ከእርሱ የህይወት ተሞክሮ የተጨለፉ ሲሆን፤ ምንም ያህል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳን ህይወታችንን አሸንፈን ትርጉም ያለው አበርክቶ ትቶ ማለፍ እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው።
የእረፍት ጊዜ ውሎ
ብሩክ ትርፍ ጊዜ አለኝ ብሎ አያምንም። “ሁሉም እኩል ሰዓት ተሰጥቶታል” ይላል።በዚያ ውስጥ “የእረፍት ጊዜ አለ” ብሎ አያምንም። ይሁን እንጂ ከጠንካራ የስራ ውሎና ሳምንት በኋላ ከቤተሰብና ጓደኞቹ ጋር ራሱን በማዝናናት ለመንፈስ ንፅህናውና መነቃቃቱ ቦታ ይሰጣል። ከዚህ ባለፈ “በወጣትነትህ ፈታ ያልክበት ጊዜ ከሌለህ፤ በእርጅናህ ጊዜ የምታስታውሰው ታሪክ አይኖርህም” በሚለው አባባል ያምናል።
ለዚህም ነው ጥሩ ትውስታ የሚፈጥሩለትን የመዝናኛ ጊዜዎች የሚመርጠው። መፅሃፍት ያነባል፣ ሲኒማ ይመለከታል የተለያዩ ቦታዎችን ይጎበኛል። በተለይ አዳዲስ ቦታዎችን መመልከት ያስደስተዋል።
አርቲስት ብሩክ ባህላዊ አልባሳትን ይጠቀማል። ከዚያ ባለፈ በሚዝናናበትም ሆነ የተለያዩ ቦታዎች እንግዳ ሆኖ ሲገኝ በአገር ውስጥ የተመረቱ ዘመናዊም ሆነ ባህላዊ መዋቢያዎችን ይጠቀማል። ለዚህ ምክንያቱ አገሩን መውደዱና ባለሙያዎች የገበያ እድል እንዲፈጠርላቸው ምሳሌ ለመሆን ከመፈለጉ መነሻ መሆኑን አጫውቶን የነበረንን ቆይታ አጠናቀናል። ሠላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2013