ከደቡብ አሜሪካ አህጉር ብራዚል፤ ከአፍሪካ ደግሞ ግብፅ ለግብርናቸው በአብዛኛው የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንደሚጠቀሙ አለም ያወቀው ሀቅ ነው። በእድገት የገሰገሱ አብዛኛዎቹ ሀገራትም ከኬሚካል ማዳበሪያ ከተፋቱ ከሰላሳ አመት በላይ ሆኗቸዋል። ከዚህ በተቃራኒ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ደግሞ የኬሚካል ማዳበሪያ ላይ የሙጥኝ ብለዋል። በዚህም ምክንያት ተደጋጋሚ የአፈር ለምነት ችግር ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል። ይህንንም ተከትሎ የግብርና ምርታቸው ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ መጥቷል።
ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ ነው። የአብዛኛው የሃገሪቱ ማህበረሰብ ኑሮም በግብርና ላይ ተመስርቷል። ግብርናው የሀገሪቱ ዋነኛ የኢኮኖሚ ሞተር የመሆኑን ያህል ግን ዘርፉን ሊያሳድጉ የሚችሉ የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች ሲቀርቡ እምብዛም አይታዩም። አብዛኞቹ የንግድ የፈጠራ ሃሳቦች የሚያተኩሩትም በሌሎች ዘርፎች ላይ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚያደርገው ሽግግር አዝጋሚ ለመሆኑም የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ድርቅ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።
በሌላ በኩል ግብርናውን የሚያዘምኑ በርካታ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በየጊዜው ቢቀርቡም ቴክኖሎጂዎቹ በራሳቸው በግብርናው ስራ ላይ የራሳቸውን አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደራቸው አልቀረም። ለአብነት እንኳን አርሶ አደሩ በየአመቱ ከመንግስት ተቀብሎ ጥቅም ላይ የሚያውላቸው የኬሚካል እህል ማዳበሪያዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግብርናው ላይ በጎ ያልሆነ ተፅእኖ አሳድረዋል።
በቅርቡ በፌዴራል ስራ እድል ኮሚሽን አዘጋጅነትና በማስተር ፋውንዴሽን ድጋፍ ‹‹ብሩህ›› በተሰኘው የንግድ ፈጣራ ሃሳብ ለውድድር ቀርቦ ለሽልማት የበቃው የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት ለአርሶ አደሩ የማቅረብ ሃሳብ ግን ይህን ችግር የሚቀርፍ ይመስላል። በተለይ ደግሞ የአፈር ለምነትን በመጠበቅ ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አኳያ አስተዋፅኦው የጎላ መሆኑ ተነግሮለታል።
የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ ከሃሳብነት በዘለለ መሬት ላይ ወርዶ ቢሰራበት ውጤት ሊያመጣ የሚችል በመሆኑ ከሌሎች ሃያ የንግድ ፈጠራ ውድድሮች መካከል አንዱ ሆኖ ተመርጧል። ለግብርና ጥቅም ላይ የሚውለውን አርተፊሻል ማዳበሪያ በተፈጥሮ የሚተካ መሆኑና የውጪ ምንዛሬን ከማዳን ባሻገር የተፈጥሮ ስነ-ምህዳርን የሚጠብቅ በመሆኑ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ተፈጥሯዊ የግብርና ምርትን ከመጨመር አኳያም የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ተነግሮለታል።
አቶ እሱባለው ነጋ የእኛው ለኛው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ የግል ኩባንያ ባለድርሻና የንግድ ፈጠራ ሃሳቡ አመንጪ ናቸው። ተወልደው ያደጉትም በደቡብ ጎንደር ሀሙስ ወንዝ አካባቢ ነው። በሞያቸውም የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ መምህር ሲሆኑ በልጅነታቸው ሞዴል አርሷደር የነበሩት አባታቸው በአንድ ወቅት የኬሚካል እህል ማዳበሪያ ይዘው ወደማሳቸው ሲመለሱ ያያሉ። አባታቸው በመጀመሪያው አመት በዚሁ ማዳበሪያ በቆሎ ዘርተው ጥሩ ምርት ማግኘታቸውንም ይመለከታሉ።
በቀጣዩ አመትም በማሳቸው ላይ በኬሚካል ማዳበሪያ በቆሎ ደገሙ። ይሁንና ምርታቸው እንደመጀመሪያው ሊሆን አልቻለም። በፊት ከነበረው ምርት በግማሽ ቀነሰ። ይህን የተመለከቱት አቶ እሱባለው በግዜው ልጅ በመሆናቸው ችግሩ ምን እንደነበር በቅጡ አልተገነዘቡም። የኋላ ኋላ ነፍስ እያወቁ ሲመጡና ትምህርትም ሲቀስሙ ምርቱ የቀነሰበትን ምክንያት ማጤን ጀመሩ። በተለይ ወደ ሜካኒካል ኢንጂነርንግ ትምህርት ዘርፍ ከገቡ በኋላ የአባታቸው ምርት የቀነሰበት ምክንያት የኬሚካል ማዳበሪያ በመጠቀማቸው መሆኑን አረጋገጡ።
የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ሲከታተሉ የመመረቂያ ጥናታዊ ፅሁፋቸውን በኬሚካል ማዳበሪያ ማስወገድ ፕሮጀክት ላይ አተኩረው ሰሩ። በኬሚካል ማዳበሪያ ዙሪያ ያላቸውንም ሃሳብ በሚገባ አበሰሉ። የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታውን አጠናቀው ወደ ደብረማርቆስ ከተመለሱ በኋላ ሃሳቡን ለማጎልበት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ቡድን ፈጠሩ። ከአባታቸው የተረከቡትን መሬት ለቀጣዩ ትውልድ በምን መልኩ ማስረከብ እንዳለባቸው ሲያውጠነጥኑም የኬሚካል ማዳበሪያን በተፈጥሮ የመቀየር ሀሳብ መጣላቸው።
ሃሳቡንም ለጓደኞቻቸው አካፍለው እኛው ለኛው የተሰኘውን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ የንግድ ፈጠራ ሃሳብ ጠነሰሱ። ሃሳቡም ለውድድር ቀርቦ ከሃያ ምርጥ የንግድ ፈጠራ ሃሳቦች መካከል ተመርጦ የ200 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆነ።
አቶ እሱባለው እንደሚሉት በአሁኑ ግዜ የአለምን 16 ነጥብ 2 ከመቶ ያህል ህዝብ የአፍሪካ አህጉርን ይወክላል። የአሁጉሩ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢም በግድ ተጎትቶ አንድ ከመቶ ደርሷል። ይህም የአህጉሩ ህዝብ በብድር እየኖረመሆኑን ያሳያል። ኢትዮጵያም ብድራቸውን መመለስ ከማይችሉ ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች። የተለያዩ የግብርና ምርቶችንም ከውጪ ሀገራት እያስገባች ትገኛለች። የግብርናው ዘርፍ የሀገሪቱ ዋነኛ ኢኮኖሚ ከመሆኑ አኳያ ለዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አናሳ በመሆኑ በተፈለገው ልክ የግብርና ምርቶችን ማምረት አልተቻለም። ለዚህም የኬሚካል ማዳበሪያ በስፋት ጥቅም ላይ መዋል ትልቁን አስተዋፅኦ አበርክቷል።
የኬሚካል ማዳበሪያ የአፈርን ለምነት ከአመት አመት እየቀነሰ ከመሆኑም ባሻገር የውሃ ብክለትንም እያስከተለ ይገኛል። የኬሚካል ማዳበሪያዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ የአረም ማጥፊያ መድሃኒቶችም በተመሳሳይ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስገድድ በመሆኑ በግብርና ምርቶች ላይ የተለያዩ ችግሮችን አስከትሏል። በሌሎች እፅዋቶች ላይም ተመሳሳይ ተፅእኖ አሳድሯል። ሰዎች የሚመገቧቸው ምግቦችም በአብዛኛው በኬሚካል ማዳበሪያ የበቀሉ በመሆናቸው ለተለያዩ የጤና ችግሮች ሲጋለጡ ይታያል። የህፃናት መቀንጨርም ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሚመጣ ችግር መሆኑ ታውቋል። እነዚህንና መሰል ችግሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባትም የተፈጥሮ ማዳበሪያን የማምረት የንግድ ፈጠራ ሃሳብ በአቶ እሱባለውና ጓደኞቻቸው ትብብር ፈልቋል።
አፈርን በመመገብ ዘላቂነት ያለው የግብርና ምርት በኢትዮጵያ እንዲኖር አቶ እሱባለውና ጓደኞቻቸው የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ሀሳባቸውን ወደ ተግባር የመቀየር እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ይህን የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረትም የግብርና ተረፈ ምርቶችንና በከተሞች አካባቢ የሚታዩ ቆሻሻዎችን በግብአትነት ለመጠቀም አስበዋል። በአዲስ አበባ እንኳን በየቀኑ 550 ኩንታል ቆሻሻ የሚጣልናከዚህ ውስጥ ደግሞ 60 ከመቶ ያህሉ ተፈጥሯዊ በመሆኑ የንግድ ፈጠራ ሃሳቡን እውን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እንዳለም ተረድተዋል።
በተመሳሳይ የሃዋሳን፣ አዲስ አበባን፣ ባህር ዳርንና ደብረማርቆስን ከተሞች ቆሻሻን መጠቀም ወደ 125 ሺህ 521 የኢትዮጵያ መሬትን መመገብ እንደሚቻልም አረጋግጠዋል። ዋናው ጉዳይ ግን ቆሻሻውን ወደ ተፈጥሮ ማዳበሪያ የመቀየሩ ተግባር በመሆኑ ማዳበሪያውን የሚያመርት ማሽን ዲዛይን ስራ አጠናቀዋል።
በአሁኑ ግዜም የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማምረቻ ማሽኑን ለመስራት እንቅስቃሴዎች እያደረጉ ቢገኙም ማሽኑን ለመስራት ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ በመሆኑ በካፒታል እጥረት ምክንያት ማዳበሪያውን ማምረት አልቻሉም። እስካሁን ድረስም ወደ ምርት አልገቡም። ይሁንና ማሽኑን ሊተካ በሚችል መልኩ ባህላዊ በሆነ መንገድ የተፈጥሮ ማዳበሪያው ተመርቶ ሙከራ ተደርጎበታል። በዚሁ ማዳበሪያ የበቀለውም ሰብል ለናሙናነት ቀርቦ ጥሩ መሆኑ በሚመለከተው አካል ተረጋግጦላቸዋል።
የኮምፖስቲንግና ግራኑሌተር ማሽኖችን በመፈብረክ የግብርና ችግሮችን ለመፍታትና አስፈላጊውን ንጥረ ነገሮችን በተመሳሳይ መጠን የያዘ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማምረት ሃሳብ ያመነጨው እኛው ለኛው ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ምርቱ የአፈር ለምነትን እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን እንደሚያሻሽል ታምኖበታል። ይሁንና ሃሳቡን እውን አድርጎ ወደ መሬት ለማውረድ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መነሻ ካፒታል ይፈልጋል።
በቀጣዩ አመት ወደ ስራ የሚገባ ከሆነም እ.ኤ.አ በ2022 ብቻ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንደሚያስገባና ከ 512 ሺህ በላይ የተጣራ ትርፍ እንደሚያስገኝ ተተንብዯል። በቀጣዮቹ አምስት አመታትም 4 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። በሰብል ማምረት የተሰማሩ በምስራቅ ጎጃምና በአማራ ክልል ያሉ አርሶ አደሮችም ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል። ከክልሉ ውጪ ያሉ አርሶ አደሮችም የዚሁ ማዳበሪያ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል።
እስካሁን ባለው ሂደት ማሽኑን በመስራት ወደ ስራ ለመግባት ከኩባንያው አባላት 400 ሺህ ብር ተዋጥቷል። በዚሁ የንግድ ፈጠራ ሃሳብም 200 ሺህ ብር ሽልማት ተገኝቷል። ሆኖም ስራውን ለማስጀመር ገንዘቡ በቂ አልሆነም። ከባንክ ገንዘብ ለመበደር በአባላቱ በኩል ሃሳቡ ቢኖርም ከምርቱ የሚገኘው ትርፍ በአመቱ መጨረሻ ላይ በመሆኑ አመቱን ሙሉ ወለድ ለባንክ እየከፈሉ መቆየቱ አስቸጋሪ መሆኑ ተረጋግጧል።
ስለሆነም አባላቱ የሀገራቸውን አፈር እየመገቡ የህብረተሰባቸውን ህልውና መጠበቅ የሚፈልጉ ባለሃብቶችን በር ለማንኳኳት አላማ አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ። የፌደራል የስራ እድል ፈጠራ ኮሚሽንም ሃሳባቸውን እንዲያበስሉ እገዛ አድርጓል። ከዚህ በኋላም ለስድስት ወር ያህል ከሃያ አሸናፊ የንግድ የፈጠራ ሃሳብ አምንጪዎች ውስጥ አስሩ ወደ ንግድ ማበልፀጊያ ከሚገቡት መካከል ከሆኑ ስራውን መሬት ለመውረድ የሚያስፈልገውን የገንዘብ ድጋፍ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህም ካልተቻለ ግን ከታላላቅ ባለሃብቶች ጋር ለመገናኘት የሚደረገው ጥረት ይቀጥላል። ለዚህ ድንቅ የንግድ የፈጠራ ሃሳብ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በአማራ ብሄራዊ ክልል ውስጥ ያሉ ባለሃብቶችም የጣና ሃይቅ ህልውናና ስነምህዳር የሚያሰጋቸው ከሆነ ሃሳቡን ቢደግፉ ለሀገራቸውም ሆነ ለራሳቸውም የተሻለ ትርፍ ያገኛሉ ተብሎ ይታሰባል።
‹‹የተፈጥሮን መፍትሄ መገደብ የለብንም›› የሚሉት አቶ እሱባለው የሰው ልጅ ስለቴክኖሎጂ ምጥቀት ማውራት የሚችለው ተፈጥሮን መረዳት ሲችል ነው። ተፈጥሮን በመገደብ ለግዜው ጥቅም ሊገኝ የሚችል ቢሆንም ከግዜ በኋላ ግን ችግር ይዞ እንደሚመጣ ማሰብ ይገባል። ከዚህ በመነሳትም አብዛኛዎቹ ችግሮች ተፈጥሯዊ በሆኑ መንገዶች ቢፈቱ ጥቅማቸው ዘለቄታዊነት ያለው መሆኑንም ይጠቁማል።
ከድህነት ለመውጣት እያንዳንዱ ሰው በሚችለው አቅም ሁሉ ለሀገሩ አስተዋፅኦ ማድረግ አለበት የሚል ጽኑ እምነት አላቸው ። አስተዋፅኦው በእውቀት፣ በገንዘብ፣ በልምድ አልያም ደግሞ በጉልበት ሊሆን እንደሚችልም ይናገራል። ይህ ከሆነም በዚህ መንገድ ትልቅ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ከደረሰቸው ሀገር ቻይና ጋር መወዳደር እንደሚቻል ይጠቁማሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2013