“ሐገሬን ሐገሬን የምትል ወፍ አለች፣
መነሻዋን አይታ መድረሷን ያወቀች።” አለች…
(የህዝብ ግጥም)
ይህን ግጥም መነሻዬ ያደረግሁት ወቅትን እየጠበቁ አንዴ አውሮፓ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ላቲን ካልሆነም አፍሪካን መዳረሻቸውን የሚያደርጉ አእዋፋትን አስቤ ሳይሆን፣ ወቅት ሳይለዩ በዚሁ ሐገር በቅለው ይኸው ተለዋዋጩ የአየር ሁኔታ ሳይበግራቸው፣ የሀገር መለዮ የሆኑትን ድንቅ አእዋፍ በማሰብ ነው።
በአእዋፍ ጥናት ረገድ ይህ የጉዞ ፍልሰት ትውልድን የማቀፀል ግዳዊ የኑሮ ዘይቤና አካሄድ በመሆኑ የሚነቀፍ ባይሆንም፣ ሐገራቸውን የሙጥኝ ብለው የያዙ ዜጎችን ሐሳብ ለማተለቅ ስላሰብኩ ጭምር ነው። ሐገሩ ውሃው አፈሩ፣ የኑሮ ስልቱና ፈሩ፣ ምርቱም ግርዱም ሁሉ ተስማምቷቸው ይኖራሉና፤ ሊመሰገኑ ይገባል። የበለጠ ሊመሰገኑ የሚገባው ደራሽ ውሃ ሞልቶ የወንዙን አፍ እንደሚተርፍ ጠርጎ የሚያመጣቸውና የሚመልሳቸው ደንጋራ ወቅታውያን በመኖራቸው ነው።
እነዚህን ዓይነቱ ወገኖች ችግራቸው የግል ደንጋራነታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎችም የእነርሱን መንገድ እንዲከተሉ የሚገፋፉ ሰባራ ጋሪዎች መሆናቸው ነው። እግሮቻቸውን እየጎተቱና ነጠላቸውን እየሳቡ ሰው ግር ወዳለበት ለመሄድ ይከተላሉ እንጂ፣ “ማን ሞቶ ወደ ማን ለቅሶ ቤት እንደሚሄዱ” እንኳን በወጉ ሳይጠይቁ፣ አባት በሞተበት ቤት፣ “ልጄ ልጄ” እያሉ ሊያለቅሱ የሚችሉ ናቸው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች ወጉ አይቅር ብለው ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ብቅ ካሉ፣ የሚያቀርቡት ሐሳብ ራሳቸውንና ወገናቸውን የሚያጠፋ እንኳን ቢሆን “ልክ ነው፤” ሲሉ ልታገኟቸው ትችላላችሁ።
ለምሳሌ ያህል፣ በዚህና በዚህ የሐገሪቱ ክፍል በወገን ላይ፣ ጥቃት ተፈፀመ ሲባሉ፤ “ታዲያ እነርሱ ምን ሊያደርጉ ወደዚያ አካባቢ ይሄዳሉ?!” ብለው ከመውቀስ የማይመለሱ ግብዞች ናቸው። ይህቺ ሐገር፤ የሁላችንም የሆነችና ኢትዮጵያ በሚል ስያሜ የምትጠራ፣ ሉዓላዊ ሆና ዜጎቿ ሁሉ የሚኖሩባት ሐገረ-መንግስት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እንደሆኑ ይረሳሉ፤ ካልሆነም ማስታወስ አይፈልጉም። ይህቺ ሐገር በህዝቦቿ ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁሉ የሚታወቅ መልክዓ ምድር ያላት መሆኑን ለማሰብ አይፈልጉም። ትህነግ መራሹ መንግስት፣ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ አፀደቅሁ ባለው፣ ሕገ-መንግስትና የክልል አስተዳደር ስር የክልሉ ብሔር ያልሆነውን “ዜጋ” ሁሉ አግላይና ከማኖር ይልቅ የሚያነውር በመሆኑ፣ ህዝቡ የሚገባውን ነጻነት በነጻነት ማድረግ ብርቅ እንዲሆንበት ተገዷል። ህዝቡ ግን፣ ለዘመናት በኖረበት ወግና ሥርዓት መሰረት እርስ በእርሱ እየተደጋገፈ ነበር የኖረው፤ ያለውም። አሁን ግን አንቀጽና ንኡስ ቁጥር እየጠቀሱ ወደ ማፈናቀልና ማሳደድ የሄዱት ገፊና ተጋፊ ለሆኑ ቡድኖች ጠቋሚ፣ ክፉ፣ የክልል ህግ፣ መንገድ-ሰጪ ሆኖ ስላገኙት ነው።
ከብሄር ድርጅቶችም መሐል አንደኛው ላይ አባላትን ስለመመልመል የወጣውን መስፈርት ቀደም ሲል በማየቴ የተገረምኩበትን ላውጋችሁ። “የድርጅቱ አባል ለመሆን”፡- ይላል፤ 1/ በአባቱ አማራ የሆነ፣ 2/ በእናቱ አማራ የሆነ፣ 3/ በሁለቱም አማራ የሆነ፣ 4ኛው/ ግን አማራ (ብአዴን) መሆን የፈለገ ተብሎ ተጽፎ አይቻለሁ። እርሱም የብአዴን የአባልነት መስፈርት ነበረ። የሌሎቹ ህገ-ክልል ግን በደም ተወላጅነትን ብቻ መስፈርት ያደረገ ነው/ነበረ። ይህ እንዲሆን፣ እነ በረከት ስምኦን ለምን እንደፈለጉት ግልጽ ነው። ለራሳቸው እንዲመቻቸው ለማድረግ እንጂ አማራ ስለሆኑም መሆን ስለፈለጉም አይደለም፤ አልነበረምም። የሚጠሉትን አማራ ልክ ማስገባት የሚቻለው አማራን “ሳይሆኑ ሆኖ”ና አማራን መስሎ እንጂ። በመጨረሻም በምርጫ ባፀደቁት (Nurtured ethnicity) ብሄረሰብ እጅ በወንጀል ተፈርዶባቸው ታስረዋል። ስለዚህ ነገር ብዙ ማለት ቢቻልም ዓላማዬ ያንን ማብራራት ስላልሆነ ልተወውና ወደመሰረተ ጉዳዬ ልሂድ።
ይህንን ያነሳሁት እግረ-መንገዴን ሳይመርጡ እንኳን፣ በልጅ ልጅነት፣ በሚኖሩበት የሶስተኛና አራተኛ ትውልድ ኑሮ በምርጫም አጽድቀው የገቡበት የዘር-ማንዘር ጌጥ ሳያቆነጅም ሳያድንም ሊቀር የቻለው፣ የዘር ቋሳ ያለበት አካሄድ ስለሆነ ነው ማለቴ ነው። የመረጡት መንገድ ቀድሞ እነ በረከትን ብቻ ሳይሆን የዚህ ሁሉ ጥፋትና ድቀት ዋናውን መሐንዲስ “የሆነውን” አቶ ስብሐት ነጋንም አልማረም።
እነዚህ የጠፋቸው ያልኳቸው ወገኖች በሁለት ይከፈላሉ። አንደኛዎቹ ሳያውቁ የጠፉ ሲሆኑ፤ ሌላዎቹ ግን አውቀው ስማቸውን የጠቃቀስኳቸውንና መሰል ጥፉዎችን የሚያስታውስ ነው።
አውቀው ጥፉ የሆኑት፣ ልዩነት ሊፈጥሩ የሚችሉ፣ የነገሮችን ልዩ ልዩነት ለውበት ሳይሆን ለጦርነት የሚያሰናዱ፣ ልዩ ልዩ ጌጥና ፈርጥ፣ ቀለምና ዓርማ፣ ባንዲራና ቅስት እየሰሩ፣ ከሌላው ጋር የምትለዩት በዚህና በዚያ ነው፤ ብለው ከማጥፋታቸው በተጨማሪ አጥፊ ሃሳባቸውን ለማስፈፀም እስከነፍስ ማጥፋት የሚሄዱ፣ ጨለማ የሚመቻቸው፣ በሴራ የደነደኑ፣ በምክንያት የለሽ መካን ሐሳቦች የተጠነጠኑ ክፉ ፅንሶች ናቸው። ልዩ ልዩ ትርክቶችን ነዳፊ፣ የጥላቻ ታሪኮች ፈብራኪ፣ ቁጭትና ማንገብገብ ግባቸው የሆኑ ተረቶች “ፈጣሪ” አካልና ክፍል አቋቁመው የሚሰሩ ናቸው። የሂትለር የፕሮፓጋንዳ ክፍል ሐላፊና በብዙዎች ዘንድ የሒትለር ሁለተኛው ሰው፣ ተብሎ የሚገመተው ጎብልስ፣ የጸረ-አይሁድ ትርክቶች ልዩ ክፍል (ዲፓርትመንት) በማቋቋም ከመስራቱ ሌላ፣ በራዲዮ እንዲቀርቡ ያሰራጭና ይቀሰቅስ ነበረ። ያንን የአይሁዶችን የሐሰት ጥፋትና ክፋት የሰማ ጀርመናዊ ሁሉ፣ ባገኘው ዘዴና መሳሪያ አይሁዶችን ለመግደል እንዲነሳሳ የሚያደርግ ሥራ ነበረ የሚያሰራው።
በሐገራችንም፣ ተከስቶ የነበረውና፣ ከጡት መቁረጥ ሐውልትና ከአኖሌ ትዝታዎች ትረካ በተጨማሪ በየጊዜው በየቅስቀሳው መካከል ከድርጅቱ ማኒፌስቶ የሚቀዳ፣ አደንቋሪ ትርክቶች ዛሬም የሚቀርቡት የዚያ እውር ቅስቀሳ ቅጥልጥል ሆኖ ነው። የሚገርመው ከፌዴራል ስልጣናቸው ለቅቀውና ከክልል ስልጣናቸው ተባርረው ወደጫካ በመግቢያ አፋፍ ላይ በነበሩበት ቅጽበትም እንኳን ሳያርማቸው፣ “አፄ ምኒልክ የእኛን ዘር ቁጥር እንዳይበዛ፣ በዚህን ያህል ሚሊዮን ቁጥር ወንዶች ልጆችን ለብቻ መርጠው ሲያኮላሹ ቆይተው ነው፤ ወደ ሸዋ የተመለሱት” የሚል፣ “የራስን አንገት የሚያስደፋ” ትረካ ነው፤ ከንቱ ውንጀላ ነበር አሰምተው የነበረው።
የዲላ ዩኒቨርስቲው መምህር አሰፋ ወዳጆም፣ በእነርሱ ስብሰባ አንድ ሁለቴ ከተካፈለ በኋላም፣ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ፣ እጅግ በመመሰጥ፣ “እኚሁ ምኒልክ የተባሉ ሰው፣ 40 ሺህ “የእኛን” ዘር ገድለው፣ 37 ሺህ በባርነት ፈንግለው ነው፤ ወደሸዋ የተመለሱት” የሚል ነጠላ ዜማ ከመቐለ መልስ ለቅቆ ነበረ። በሌሎች ተሰርቶ፣ የተሰጠውን የተርም ወረቀት እንደሰራ ሰው አፉን አላቅቋል። “መምህር” አሰፋን ባገኘው፣ የምጠይቀው አንድ ጥያቄ ነበረኝ። በወቅቱ ከእነዚያ ፈላሾች እና ገባር ተደራጊዎች ውስጥ የአስሩን ስም አስተካክለህ ትጠራልኛለህን፤ ምክንያቱም ይህ ታሪክ በእውነት ተሰንዶ ከሆነ የተጋዙት ሰዎች ስም ዝርዝር ቢጠፋ የተማረኩ የጦር አዛዦችና የውጊያው ባለታሪኮች ስም አይጠፉምና ደግሞም ቁጥሩን ካወቅክ ስምም አይጠፋህምና እስቲ ንገረን እለው ነበረ።
የጠፋባቸው አካላት፣ የሚቃወሙት አካል፣ “ወፍ ከሰማይ ቢያወርድ” (ምንም ዓይነት አስደናቂና ጠቃሚ ነገር) ለሐገር ቢያደርግ፣ አይደነቁም፤ ወፏን የሆነ ቦታ ተደብቆ ራሱ ነው ያስወረወረው ወይም፣ የአራዊትና አእዋፋት መምሪያ ስራውን አልሰራም፤ ሲሉ ይከስሳሉ እንጂ አያርፉም። ከዚህም ሌላ ደመናን ወደ ዝናብ ቢቀይር “አስማተኛው ያውና መጣ” ብለው በማህበራዊ ሚዲያቸው ከማላገጥ የማይመለሱ ስልጣኔ ፅዩፋን ናቸው። ልክ እንደ ቦኮ ሐራም። ጠልተዋልና ጠላታችን ነው፤ ያሉትን አካል ሁለመና ደጋግመውና እያላዘኑ በጥላቻ ቀለም ይቀቡታል እንጂ መልካምነቱን አይቀበሉም። ዝም እንኳን ማለት ደግ ቢሆን ዝም አይሉም። ሲያውቁ ብርሃኑን አጥፍተዋላ!!
እንዲህ ዓይነቶቹ ሐገር ሲመሩ፣ በወጥመድ ስጋት እንደምትደነብር ቆቅ፣ ደንብረው ህዝብ እያስደነበሩ፣ ነገን እያስጠረጠሩና ሐገር እያስመረሩ ነው። ጠላት ያዝኩ ካሉ፣ በብዙው ዘንድ የሚወደድን ሰው ነው የሚይዙት። “ወንበዴ ያዝን” ካሉ አቅመ ደካማ ሽማግሌና የማያስተውል ወጣት ግራ-ገብ ደንጋራ ይዘው ነው የሚያደናግሩት። የጠፋባቸው ሐገር ሲመሩ የሚመሩት፣ ህዝብ ሳይሆን የቆሙለት ግብ ነው የሚያሳስባቸው። አጣምረው ለማዋሃድ ሳይሆን አጋብተው ለማፋታት ውል ያረቅቁና እርሱንም “ሕገ-መንግስት” የሚሉ ናቸው። በዚህ ህግ ጥላ ስር የሚሰደድ እና የሚጋጭ እንጂ፣ የሚሰበሰብ ህዝብ አይኖርም። እንደ አውሬ ተፈራርቶ፣ ኮሽ ባለ ቁጥር እንደ ብሆር ተደናብሮ ነው የሚኖረው። የሐገርን ህልውና ከተጋቢ ግለሰቦች ፈቃድ ጋር ሲያመሳስሉ፣ አፋቸውን ያዝ አያደርጋቸውም። ናይጄሪያ ከ120 በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች አሏት ነገር ግን በሐገሪቱ ህገ-መንግስት ውስጥ ዋናው ወንጀል ከሐገር ለመገንጠል መሞከር፣ ማስተባበርና ለዚህ ዓላማ ጦር መስበቅ ነው። በሐገር ክህደት ወንጀል የሚያስከስሰው። ህንድ ከአምስት መቶ በላይ ቋንቋዎችና ዘዬዎች ያሏት ሐገር ናት፤ ነገር ግን ከህንድ ለመገንጠል ማቀድ በሐገር ክህደት ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው። በአለም ላይ በሌሎች ሐገሮች ሁሉ፣ ወንጀል ተደርጎ የሚታይ ሥራን የሕገ-መንግስቷ መሰረት እንደሆነ ደንግጋ ያለች ሐገር የእኛ ሐገር ብቻ ናት። እንዲህ ያለ ሌላ ሐገር ካለ ንገሩኝና አስተምሩኝ።
ታዲያ አጥፊውን ሕግ – ሕግ አድርገው የወሰዱና፣ ሲያውቁ የጠፉ ሰዎች በታሪክ ውስጥ ትልቁን ጥፋት ማጥፋታቸው ብቻ ሳይሆን የዋህ ጥፉዓንን መፈልፈላቸው ጭምር ነው የሚያስደንቀው። ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ከህይወት ይልቅ ሞትን፤ ከመልካምነት ይልቅ ክፋትን የመረጡትን እነዚህን ነው “የተከደነባቸው” የሚላቸው።
ሌላኛዎቹ ጥፉዎች ከላይ እንደገለጽኩት በእዚህ ዓይነቱ ጠለፋ ውስጥ ግራ ተጋብተው የጠፉ ናቸው። እነዚህ የዋሃን፣ በስሜት የሚነዱ፣ በረሀብና ጥም የተጎዱ፤ ለችግሮቻቸውና ድህነታቸው ሰበብ ሲፈልጉ የሚላከክበት አካል በማግኘታቸው የተጽናኑ ስለሆኑ፣ ለቂም በቀል ፈጣኖች ናቸው። እነዚህ ናቸው “ቹ” ተብለው ሲለቀቁ ሳያቅማሙ በተነገራቸው መንገድ በመሄድ፣ ለጥፋት መሳሪያ የሚሆኑት።
ግራ የገባቸውና የተደናገሩት ብለን የምንላቸውም ከእነርሱ ወገን የሆኑትን ነው። ከጠፋባቸው አጥፊዎች የሚለዩት ግራ-ገቦቹ ምልሶች በመሆናቸው ነው። ፀፀት የሚሰማቸው፣ ሲበራላቸው በበጎነት የሚመለሱና የበደሉትን ለመካስ የማያመነቱ ገሮች ናቸው።
ግራ-ገቦቹ (ወላዋዮቹ)፣ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን በአጥፊዎቹ ማእበል ሊወሰዱ የሚችሉና ሲያጠፉ በቁጭት ተሞልተው ስለሚወሰዱ የጥፋታቸውን መጠን ለመግለጽ ይከብዳል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ከበራላቸው ሰዎች ጎንም ሆነው ሊገኙ የሚችሉና በዚሁ ገር ጠባያቸው ወደ አጥፊዎቹ ሰፈር፣ በሁኔታዎች ተገፋፍተው ሊገቡ የሚችሉ ሃይሎች ናቸው።
አያቴ ነገር አልጥማት ሲል፣ ደንጋራ ሽሮ የበላ መንገድ ሲጀምር ሆዱን ይቆርጠዋል፤ ትላለች። በጠዋት መንገድ የሚጀምር ሰው በማለዳ ሆዱን ሞልቶ፣ ለስንቁ ውሃ ይዞ ነው መውጣት ያለበት። “ውሃ መንገድ ያስኬዳል” ትል ነበር። ግራ-ገቦች ግን አቋራጭ መንገደኞች ናቸው፣ የስንቅ ውሃ እንደሌላቸው መንገደኞች ይቆጠራሉ። የራሴ የሚሉት ሐሳብም መርህም የላቸውም። ሁኔታው አላምር ሲላቸው ትናንት ያመኑትን ዛሬ ክደው ወደ ሌላኛው ጽንፍ ለመወርወር አያመነቱም። የተነሳ ማእበል ስፍራ ስለሚያስለቅቃቸው ዛሬ ያመሰገኑትን ነገ ይቃወማሉ፤ ዛሬ የተቃወሙትንም ሐሳብ ነገ ሲያወድሱት ብትሰሙ መገረም የለባችሁም። ደንጋሮች መርህ የላቸውም፤ ጥቅሜ ብለው ያሉት ነገር የተነካ ሲመስላቸው በህግ አግባብና በሠላም ነገሩን፣ ከማስፈፀም ይልቅ “እኔ ከቀረብኝ ሁሉም ይቅርበት” በሚል መርህ ሊመሩ ስለሚችሉ አደገኞች ናቸው።
ግራ-የገባቸው “ምን አገባኝ” ማለት ይቀናቸዋል። እኔ ምኑንም አላውቀውም፤ እባክህ ይቅርብኝ ስለሚሉ ሊያድኑት የሚችሉትን መጻኢ ክፉ እጣ ለአጥፊዎች በመተው ሐገርን ለማፍረስ ምክንያት ይሆናሉ። ስለዚህ ግራ-ገብ ብለን የምንጠራው ሃይል፣ በጣም ሰፋ ያለ ስለሆነ ቁጥሩን በቀላሉ አይቶና ንቆ መተው አያስፈልግም። ይህንን ሁዳድ ክፉዎች እንደ ጭዳ በግ ሊያደርጉት ስለሚፈልጉት ያነሳሱታል፤ ይመለምሉታል፤ መሳሪያ አድርገውም ይጠቀሙበታል። የሚፈልጉት ስፍራ ሲደርሱ ግን እንደ ጠቀማቸው ሳይሆን እንደ ማያስፈልግ የሸንኮራ አገዳ፣ አራግፈው ይጥሉታል። ከሰራዊቱ አላግባብ የተባረሩትን ተቀናሽ እና “ተልዕኳቸውን የተወጡ” በሚል ተራ ሙገሳ ያበረሯቸውን አባላት ዞር ብለው አላዩዋቸውም፤ ስለዚህም ነው፤ ያኔም ነው፤ እነዚያ አባላት፣ ሊሞቱላት የገቡትን ድርጅታቸውን፣ “ሐሻዊ -ህወሐት” ይሏት፤ የነበረው። በቀኑ መጨረሻም ከሐዘን በስተቀር ያተረፉት ነገር የለም። በመጨረሻም የበራላቸው ደግሞ አሉ።
እነዚህኞቹ፣ ክፉውንና ደጉን የሚለዩ፣ የሚጠይቁ፣ ግብ ተኮር የሆኑ እና በዓላማ የሚመሩ ናቸውና የበራላቸው ስንል ያወቁና የገባቸው ናቸው ማለታችን ነው።
የበራላቸው ወገኖች፣ ከራስ በላይ የሚያስቡ ለሌሎች ደስታ ቀድመው የተሰጡ ፍቅር የሚጋሩና አደራረጋቸው በጥበብ የተሞላ ነው። እነዚህ ወገኖች አስተዋዮች በመሆናቸው ለሐገራቸው የሚጠቅመውን የተገነዘቡና ለህዝቡ ደግነትና መልካም ኑሮ የሚተጉ ናቸው። ቁጥራቸው ቢያንስም ለለውጥ የሚጥሩ፣ ቆራጦችና ሐገር ወዳዶች ናቸው። ልበ-ሰፊ ስለሆኑ አሁናዊ ነገር አያስደስታቸውም፤ ሌላ አድማስ፣ ሌላ ዕድገት ይናፍቃቸዋል። ከአንዱ ከፍታ በኋላ ሌላ ከፍታ እንዳለ ይሰማቸዋል። አይቆሙም ይራመዳሉ፤ ይንቀሳቀሳሉ፤ ያንቀሳቅሳሉም።
የበራላቸው ፍትህን ወዳድ ናቸው፤ ከአቅማቸው በላይ የሆነ ነገር ሲገጥማቸው እንዳልተረዱት ለመናገር አያቅማሙም፤ ሲሳሳቱ በሌላው ሰው ላይ ከማላከክ ይልቅ፣ ራሳቸውን ለስህተቱ ተጠያቂ ለማድረግ የማያመነቱ ናቸው። ከእነዚህ ጋር መስራት መባረክ ነው፤ ጨካኝነት ሲያልፍም አይነካካቸውም።
የበራላቸው ሰዎች ከጨከኑም በድክመታቸው፤ አልፎ…አልፎ በሚጎበኛቸው በክፋታቸውና በሃጢያት በራሱ ላይ ነው። ስለዚህ ሐገር በእነዚህ ዓይነት ሰዎች እጅ ስትገባ ህዝቡ ያርፋል፤ ወልዶ መሳም፣ ማሳደግ ማስተማርና ለወግ ማዕረግ ማብቃት የዕለት ተዕለት ተግባር ሲሆን፤ ተጋብቶ አለመፋታት የሐገር ወግና ልማድ ይሆናል። በዚህ ሐገር የሚኖሩ ሰዎች ጉዟቸው ረዥም፤ እቅዳቸው ሰፊ፣ ራዕያቸው ሩቅ ነውና።
በመጨረሻም ለጠፋባቸው ብርሐን፣ ግራ ለተጋቡ መብሰልና ማስተዋል እንመኛለን። ሐገሬ በቀሪው ዘመኗ በርቶላቸው የሚያበሩ፣ የጠፋባቸውን በጅምላ የማያጠፉ፣ የተደናገሩትን ወደ መልካም ጎዳና በመውሰድ የተለየ የተሻለና መልካም ዓለም ለሰው ልጆች ሁሉ እንዳለ የሚያሳዩ ዜጎቿ እንዲበረክቱ ናፍቆቴም ምኞቴም ነው፤ ደግሞም ይሆናል። ኢንሻላህ!
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም