ከሥራ አጥነት ከተሰደድኩ በኋላ፤ መቀመጫዬን ክብሬና ኩራቴ ወደ ሆነችው ሥራዬ ላይ አድርጌ ራሷን “ታላቋ” እያለች መጥራት የሚቀናት “ደመወዜን” ቀንም ማታም አስባታለሁ። አባቴ ያለ እርሷ ማን አለኝ። ምንም እንኳ በ30 ቀን አንዴ ብቻ ተገናኝተን ብንጨዋወትም ትዝታዋ ግን ሠላሳውንም ቀን አብሮኝ ይኖራል። አሁን ግን ትዝታዋ ብቻ ሳይሆን ለረጅም ቀናት በአይነ ስጋ ልንተያይ ነው መሰለኝ ቅዠት ቢጤ ይዞኛል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ የዝቅተኛ የደመወዝ መጠንን የሚወስነው የደመወዝ ቦርድ ሊቋቋም መሆኑን ቢቢሲ የማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር። በዘገባው መሠረት በአሁኑ ወቅት የዝቅተኛ ደመወዝ ወለልን የሚወስነው የደመወዝ ቦርድ ማቋቋሚያ ደንብ የተረቀቀ ሲሆን፣ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች ምክክር ሲደረግበት ቆይቶ ደንቡ ወደሚፀድቅበት ሚኒስትሮች ምክር ቤት ለመላክ በዝግጅት ላይ ነው።
ጎሽ አትሉም ታዲያ። ይሄ እኮ ጮማ ዜና ነው። እንኳን በመንግስት ደረጃ ይሄ ነገር ተነስቶ በፊት ገጽ በቱቦ ቢነሳም ትልቅ ወሬ እኮ ነው። ወር ጠብቆ ደመወዙን ለሚያገኝ ሰራተኛ ይሄን የመሰለ ጮማ ዜና መስማት እንደምን ያስደስታል። ጎበዝ ይህ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ሠራተኞች ደመወዛቸው በህግ ከተደነነገገው በታች እንዳይሆን የሚያደርግ ነው እኮ። ከእንግዲህ ማንኛውም ቀጣሪ ድርጅት ሰራተኛውን ደመወዝ ዝቅ በማድረግ አይበድልም። ነገሩን እንደሰማሁት ተቋማት ሠራተኞቻቸው ለመኖር የሚያስፈልጋቸው መጠን እንዲሁም በሌላ በኩል ኩባንያዎች፣ ተቋማትና አሰሪዎች የመክፈል አቅም ምን ይመስላል የሚለውን ያጤናል አሉ። አረ ደግ አበጁ።
የተባለው የደሞዝ ጉዳይ መሬት ሲነካ የአስማት ኑሮ ደኅና ሰንብች ልንል ነው በቃ። (ድንቄም የሚል አይጠፋም እኮ) ምክንያቱም ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የአንድን ሠራተኛ የኑሮ ደረጃ የቤት ኪራይ፣ መብራት፣ ውሃ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ እንዲሁም ሌሎች ወጪዎች ተደምረው ለአንድ ሰው ኑሮ በአማካይ ምን ያህል ይበቃል የሚለው ከግምት ውስጥ መግባት አለበት። በነገራችን ላይ ደመወዙን የቤት ኪራይ ላይ ብቻ አውለው የሚኖሩ ሰዎች እጅጉን ይገርሙኛል። እኔማ አንዳንዴ የተከራየሁት ቤት እንደ አንዳንድ የአዲስ አበባ ፎቆች ባለቤት ባይኖረው ብዬ እመኛለሁ።
ወዳጄ ምሳ በልቶ እራት መድገም የማይችል ሠራተኛ ቁጥሩ ጥቂት እንዳይመስልህ። በአሁኑ ወቅት አንድ ሺህ ብር እንኳን በኢትዮጵያ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ገበያ ተወጥቶ እንደልብ አይገዛበትም። በእርግጥ ለኔ ቢጤው ምስኪን ቁጥሩ ብዙ ይምሰል እንጂ ቱጃሮች በማይክሮ ሰከንድ ነው ይህችን ብር የሚያጠፏት። ከዚህ አንፃር ይህ ህግ ከወጣ እነዚህ ነገሮች ይለወጣሉ ብለን እንጠብቃለን። ቢያንስ ሌላ ነገር ማድረግ ባይችል በልቶ ማደር እንችላለን።
ይሄን ዜናማ ለብቻዬ ማጣጣም የለብኝም ብዬ ብችኮላ ለራስ በዛብህ ልንግረው ተጓዝኩ። ራስ በዛብህ አንድም የአናቱን ትልቀት በማስመልከት የወጣለት ስም ነው። የሰፈራችን ድንቅ ገጣሚ ነው። ሙዚቀኛም ነው። ብዙ ጊዜ የሰዎችን ማህበራዊ ሁኔታ መሠረት አድርጎ ይዘፍናል። አዲሱን ወሬ ሹክ ልለው ሮጬ እሱ ዘንድ ስደርስ “ኑሮ ተወደደ አወጣ ሚሊዮን ፣የኔ አይነቱን ድሀ ምን ይውጠው ይሆን?” የሚል ዘፈን እያንጎራጎረ ነበር።
ይህ ምጡቅ ራስ በዛብህ በተለይ ኑሮ መውደድ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ዘፈኖችን እያገጣጠመ ሲዘፍን ነው የከረመው። ብቻ እንናተ ርዕሰ ጉዳዩን መስጠት ብቻ ነው የሚጠበቅባችሁ። እርሱ እንደምንም ብሎ አገናኝቶ ያዜማል። አንድ ቀን ራስ በዛብህ ተጠየቀ። ይህን ሁሉ ሀሳብ ግን የት ነው የምታከማቸው ተባለ። ራሴ የተፈጠረው ለዚሁ አገለግሎት ነው ብሎ መለሰ።
ይሄ አያልቅበት ያላነሳው፤ ያልዳሰሰው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ …ጉዳዮች የሉም። ሰዎች ለደመወዛቸው የሚያደርጉትን የዘፈን ምርጫ በቅጡ የማሳየት ችሎታ አለው። እኔም ወሬዬን ከመንገሬ በፊት ጥቂት ስለ ደመወዝ የዘፈን ምርጫ እንዲያጫውተኝ ጥያቄዎች አከታተልኩበት።
ሰዎች በተለይ በደመወዝ መውጫ ሳምንት ደመወዛቸው በጠበቁት ቀን ሳይወጣላቸው ሲቀር ምን ብለው ይዘፍኑ ይሆን ብዬ ጠየቅኩት። “ አይኔ እየጠበቀሽ ነው፤ ዛሬስ ዘገየሽ ምነው? መግቢያ መውጫሽን ሳየው ስትጠፊ እጨነቃለሁ።” የሚለውን የወንድሙ ጅራን ዘፈን አለኝ። እንደው መዘግየቷ በዛው ቢቀጥልስ ተቃውሞ ይገጥማት ይሆን እንዴ ራስ በዛብህ? ቀጣዩ የኔ ጥያቄ ነበር።
“የምን ተቃውሞ ነው እቴ” አለ ራስ በዛብህ። ተሳድቦ በዛው ከማስቀረት አሽሞንሙኖ በመጣች ሰዓት መቀበል ነው የሚበጀው አለኝ። እናም ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ደመወዛቸው ብትቀርባቸው እንኳን “ የት አባቱ ክብሬን ተዪው ደኅና በይ እንዳሻሽ እንዳልሽ ይሁና፤ ካንቺ አይበልጥምና”.. ሲሉ መምጫዋን በልምምጥ ይጠባበቃሉ አለኝ። “የማየውም የምሰማዉ ክብሬን ይነካኛል ፣ያም ሆኖ ግን እንደምንም ብችል ይቀለኛል፣ ተለይቼሽ ከሚሰማኝ ስቃይ ይሻለኛል” የሚለውም ስንኝ እንደማይቀራቸው ነው ያጫወተኝ። ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም፤ 30 ቀን እንደምጠብቅሽ አላወቅሽልኝም፤ አንቺን ለመቆጠብ አብዝቼ ብመኝም በዱቤ ታልቂያለሽ አላወቅሽልኝም። ብለው የሚያንቆለጳጵሳትስ መቼ ይጠፋና አለኝ ራስ በዛብህ።
ልክ ደመወዛቸው እጃቸው ላይ ልትገባ ስትል ደግሞ “እንግዳዬ ነሽ የኔ ሰቀቀን እወድሻለሁ ነይ ቀን በቀን” ብለው ሲዘፍኑ፤ እቴጌ ደመወዝ ደግሞ ኑሯችን ስንክሳሩ ሲበዛባት ተመልክታ “በሳማ በቆንጥር በአጋም በጋሬጣ ፣ በእሾህ ተከበሻል በየት በኩል ልምጣ” ስትል መልስ ትሰጣቸዋለች እያለ አጫወተኝ።
አንድም ቀን ደመወዝ ያላገኙና የሰው እጅ በማየት የሚኖሩም እኮ ለደመወዜ ይዘፍኑለታል አለኝ ራስ በዛብህ። እንዴት ደመወዝን ሳያጣጥሙ ሊዘፍኑላት ቻሉ ብዬ ጠየቅኩት። ለመሆኑ ምን እያሉ ነው የሚዘፍኑት ስለው፤ “ሳላያት አረጀሁ ሳላየት አረጀሁ” የሚለውን ነዋ አለኝ። ምን ይሄ ብቻ፤ ቀጠለ ራስ በዛብህ። ሥራ የሌላቸውና ደመወዝን የማያውቁም “ዲሽታ ጊና ደሞዝ የሌ ሥራ የሌ” ብለው ይዘፍናሉ እኮ አለኝ። ከሁሉም ግን አንጀት የሚበሉት ደመወዛቻውን ተቀብለው ወዲያው የሚያጠፉ ሰዎች “ከምኔው ከምኔው ከምኔው ነውሳ፤ ባዶ ኪስ የሆንኩት ያጣሁት ለምሳ” እያሉ የሚዘፍኑት ናቸው ብሎ ሊቀጥል ሲል አቋርጬው የብስራቱን ዜና ልንገርህ አልኩት።
እናም በመቀጠል የሰማሁትን ዜና ለራስ በዛብህ ስነግረው ደስታው ወደር አጣ። ወዲያው ከእንግዲህማ “የአይኔ አበባ መጥታለች የአይኔ አበባ መጥታለች ሰበር ሰካ እያለች። የአጥቢያ ኮከብ ነሽ ወይ የአጥቢያ ኮከብ ነሽ ወይ አንቺ የንጋት ጸሐይ” ሲሉ ያብዱላታል በቃ አለኝ ራስ በዛብህ።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም