‹‹የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ስልታዊ እቅድ ያስፈልጋል›› – ኢንስትራክተር ሰለሞን ገብረስላሴ

ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)ን ከመሰረቱ ሀገራት አንዷ ብትሆንም አህጉራዊ ውድድሩን ካዘጋጀች ግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥራለች። በመድረኩ በየጊዜው መሳተፍም ከብዷታል። ወደ ውድድሩን አዘጋጅነት ለመመለስ ግን በቅርቡ ለካፍ ጥያቄ ማቅረቧ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ የ2029 አፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅነት ጥያቄ ተቀባይነት ካገኘ ከመሰረተ ልማት ጀምሮ በርካታ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ይህንን በተመለከተም የተለያዩ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን እየሰነዘሩ ይገኛሉ። ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት ስልታዊ እቅድ ተነድፎ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ ከሚናገሩ ባለሙያዎች አንዱ የእግር ኳስ ዳኞች ኢንስትራክተር ሰለሞን ገብረስላሴ ናቸው።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በባለሙያነት፣ በዳኝነትና በኃላፊነት ደረጃዎች ያገለገሉት ኢንስትራክተር ሰለሞን፤ በአሁኑ ወቅት በካፍና ፊፋ ኮሚሽነርነትና የኢትዮጵያ ዳኞች ኢንስትራክተር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት በማቀዷ እንደ እግር ኳስ ባለሙያ መደሰታቸውን የሚናገሩት ኢንስትራክተር ሰለሞን፤ በእግር ኳስ ውስጥ በዳኝነት እና በሌሎች ትልልቅ ደረጃዎች አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን እንድታዘጋጅ አብዝተው ይመኙ እንደነበር ይገልጻሉ። ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግር ኳስ መስራች እንደመሆኗ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ማስተናገድ ብዙ ሀብት፣ በርካታ ባለሙያዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቁመው፤ መንግሥት ለዚህም ትኩረት መስጠት እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡

እንደ እሳቸው አስተያየት፤ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች መካከል ስድስት ደረጃቸውን የጠበቁ ስታድየሞች እና ለልምምድ የሚሆኑ ሜዳዎች ወሳኝ ናቸው። ከመሰረተ ልማት አኳያ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚገኙ ስታድየሞች ቁጥር ውድድሩን ለማስተናገድ ከበቂ በላይ ናቸው። ይሁን እንጂ ደረጃቸውን ለማሻሻል ብዙ ስራ ያስፈልጋል። ይህንን ለመስራትም መንግሥት ቁርጠኝነቱን አሳይቶ እየሰራና አንዳንድ ስታድየሞች እያደሰ ይገኛል፡፡ ውድድሩን ለማዘጋጀትና የሚያስፈልጉትን መሰረተ ልማቶች ለማሟላት የሚቀረው ጊዜ በቂ በመሆኑ፣ በዚህ ጊዜ በጅምር ላይ የሚገኙትን ስታድየሞችን አጠናቆ ውጤታማ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል፡፡ ስኬታማ ውድድር ለማዘጋጀትና እድሉን ለመጠቀም ግን ሁሉም በሙያው መረባረብ አለበት፡፡

መንግሥት ከአምስት ዓመት በኋላ ውድድሩን ለማዘጋጀት ቁርጠኝነቱን ከማሳየት በተጨማሪ፣ ዝርዝር የስራ እቅድ ያዘጋጃል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ኢንስትራክተር ሰለሞን ይናገራሉ። ለዚህም ብዙ ባለሙያዎችን አቅፎ የሚንቀሳቀስ ብሔራዊ የአምስት ዓመት ስልታዊ እቅድ ማዘጋጀት አለበት ይላሉ። ይህም ከወዲሁ እቅዶችን በማውጣት በዛ መሰረት መስራት የሚቻል ከሆነ ውድድሩን የማስተናገድ እድሉን ማሳካት ይቻላል ባይ ናቸው።

ይህንን እውን ለማድረግም በመንግሥት፣ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በባለሙያዎች መካከል ጠንካራ የጋራ ትስስር ፈጥሮ በቅንጅት መስራት ይጠይቃል ይላሉ፡፡ “ስኬታማ ውድድር ለማዘጋጀት በባለሙያዎች መካከል በእቅድ የተደገፈ ቅንጅታዊ ስራ ከወዲሁ መሰራት” አለበት የሚሉት ኢንስትራክተር ሰለሞን፤ በዚህም መሰረት ማን ምን ይሰራል፣ መቼ እና እንዴት የሚሉት ጉዳዮች በእቅዱ ውስጥ ተካተው የጋራ ክንውንና ግምገማ ማድረግ አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡ እግር ኳሱ የሚመለከታቸው አካላትም ለዚህ እጅ ለእጅ ተያይዘው በአንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

እንደ ኢንስትራክተር ሰለሞን ሃሳብ፣ ካፍ ውድድሩን የማስተናገድ እድል ሲሰጥ የዝግጅት ሁኔታውን ደረጃ በደረጃ የሚከታተልበትና የሚገመግምበት ሥርዓት አለው። ለዚያም የሚመጥን ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ የግድ ነው። ከመሠረተ ልማት፣ ሆቴል፣ ትራንስፖርትና እግር ኳስ ሜዳዎችን ከማሟላት ጋር መስፈርቱን በትክክል ለማሟላት ዝግጅቱ የግድ በባለሙያዎች ድጋፍ መታገዝ አለበት። ለዚህም መንግሥት ቁርጠኛ መሆን አለበት።

እግር ኳስ በዓለም ተወዳጅና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚናን የሚጫወት ስፖርት እንደመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ውድድሩን በማስተናገዷ፣ የተሟላ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራን፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ እና የሀገር ገጽታ ግንባታን ለመፍጠር ቁልፍ ሚናን ስለሚጫወት እድሉ ከተገኘ በአግባቡ ልንጠቀምበት እንደሚገባ ኢንስትራክተር ሰለሞን ያስረዳሉ።

ውድድሩን ለማዘጋጀት ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮች ጎን ለጎን ጠንካራና ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባትም ከፍተኛ ጥረት እንደሚጠበቅ የሚናገሩት ኢንስትራክተር ሰለሞን፤ በሁሉም አካባቢዎች የእግር ኳስ ልማት ስራዎችን ለማስፋፋት የሚደረገው ስራ ተጠናክሮ ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት እንቅስቃሴ መጀመር ይኖርበታል ይላሉ። ለዚህም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግንና ሌሎች የሊግ ውድድሮች ጠንካራ እንዲሆን በማድረግ ምርጥ ተጫዋቾችን ማፍራት ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ እምነታቸው ነው።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ሰኞ ኅዳር 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You