የ65 ዓመት አዛውንት ናቸው። የተወለዱት በጉራጌ ዞን ቆጠር በተባለ አካባቢ ነው። በጨቅላ እድሜያቸው አባታቸው በመሞታቸው ምክንያት አጎታቸው አዲስ አበባ ይዘዋቸው መጥተው ያደጉት አዲስ አበባ ነው ። እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ ሽመልስ ሃብቴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግማሽ ቀን እየተማሩ ግማሽ ቀን ደግሞ ቤተሰባቸውን እያገለገሉ ተምረዋል ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በካቴድራል ትምህርት ቤት ገብተው እስከ 10ኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ በ1964 ዓ.ም እድሜያቸውን ጨምረው ለጦር ሰራዊትነት ተመለመሉ። በወቅቱ ስለሐረርና ድሬዳዋ ይሰሙት የነበረው መልካም ነገር ያጓጓቸውና በምርጫቸው ሐረር ይመደባሉ። እንዳሰቡት ግን ሐረር ምቹ ሆና አላገኟትም። ተቀጥረው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ በኋላ ሁኔታው ስላልተመቻቸው ለመመለስ ከጦር ሰራዊቱ ጠፍተው ያመልጣሉ። ይሁንና ብዙም ሳይርቁ አማሬሳ ላይ ይያዙና ይታሰራሉ። በጦር ሰራዊቱ ውስጥ 42 ቀናት ከባድ ቅጣት ይቀጣሉ። ይባስ ተብሎም ወደ ኡጋዴን በረሃ ተላኩ።
ዳግመኛ ለልዩ ትምህርት ተብሎ መመዘኛዎቹን ያሟሉ ስለነበር ለልዩ ሃይሉ ተመረጡና ወደ ድሬዳዋ ተመልሰው መጥተው የመማር እድሉን አገኙ። በዚያው የውትድርና ቤት አገልግሎት እየሰጡ ሳለም በሀገሪቱ የስርዓት ለውጥ መጣ። ሙያቸው በአዲሱ መንግስትም ተፈላጊ በመሆኑ አዳዲስ ምልምሎችን እንዲያሰለጥኑ ይመደባሉ። በወቅቱ ደግሞ ከሱማሊያ የሚመጡ ሽምቅ ተዋጊዎችን የሚከላከል ፀረ- ሽምቅ ተዋጊዎችን ለማሰልጠን ተመልሰው ኡጋዴን ይሄዳሉ። በዚያ የማሰልጠን ስራ ላይ ሳሉም ኤልከሬ በተባለ ስፍራ በሰርጎ ገቦች በተጠመደ ቦንብ የነበሩባት ተሸከርካሪ ጋየች፤ እሳቸውም የመቁሰል አደጋ ደረሰባቸው።
በዚህ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ ተመለሱና ማገገሚያ ገብተው ካገገሙ በኋላ ለካራ ማራ ጦርነት እንዲሰለፉ ይመደባሉ። ሆኖም በሚሄዱበት ቀን ዋዜማ በተፈጠረ ፀብ መሃል ተገኝተው ስለነበር ፀጉረ ልውጥ በሚል ይታሰሩና ጉዞው ያልፋቸዋል።
ፖለቲከኛ ሳይሆኑ የፖለቲከኛ እስረኛ ተብለው ሶስት ወር ታስረው ስለነበርም 135 ብር ተሰጥቷቸው ከእስር ይፈታሉ። አመልክተው ፖሊስና ወታደር ይባል በነበረ ማሰልጠኛ ተቋም አሰልጣኝ ሆነው ተመደቡ። በመቀጠልም ተወዳድረው በማለፍ ሆለታ ጦር ትምህርት ቤት ገብተው የውጊያ መረጃ ስልጠና ወሰዱ። በወቅቱ በተቋቋመ ሀገርና ህዝብ ጥበቃ በተባለ መስሪያ ቤት ውስጥ ከሌሎች አምስት ሰልጣኞች ጋር ተመድበው ትግራይና ጎጃም እየተዘዋወሩ አገለገሉ።
በኋላም በተማሩበት የበረራ ደህንነት ትምህርት ምክንያት በኢትዮጵያ አየር መንገድ የመቀጠር እድሉን አገኙ። የደርግ መንግስት በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ መንግስት እስከሚተካ ድረስ በአየር መንገዱ የበረራ ደህንነት ሲያገለግሉ ቆዩ። የመንግስት ለውጥን ተከትሎ መዋቅሩ በመለወጡ በሙያቸው እያገለገሉ መቀጠል ባለመቻላቸው በግል ስራ ላይ ተሰማሩ።
ብዙም ሳይቆዩ በተሃድሶ ሰበብ ለእስር ተዳረጉ። በፈቃደኝነት የቀረበውን ጥሪ አክብረው ለመታደስ ቢገቡም ባላሰቡበት መንገድ ያለአንዳች ፍርድ ወህኒ ቤት ከረሙ። የነበረው መንግስት አለምአቀፍ ተፅዕኖው ሲበረታበት በሰሩበት ትግራይ ክልል ሄደው በህዝብ እንዲዳኙ አደረገ። ሆኖም በድሎኛል ብሎ የሚከስ ሰው በመጥፋቱ ከብዙ እንግልት በኋላ ከእስር ተፈቱ። መከራቸው በዚህ አላበቃም ። ከሰባት ዓመት በኋላ ጠቅላይ አቃቢ ህግ በዛው ጉዳይ ዳግመኛ እንዲታሰሩ ያደርጋቸዋል። በወቅቱ የነበሩት ባለስልጣናት ገንዘብ ሰጥተው እንዲፈቱ ቢጠይቋቸውም ‹‹አሻፈረኝ›› በማለታቸው ያለምንም ይግባኝ የጦር ወንጀለኛ የሚል ታርጋ ተሰጣቸውና ተፈረደባቸው። 1997 ዓ.ም ከእስር ሲፈቱ ነገሮች ሌላ መልክ ያዙ። ከቀድሞው ባለቤታቸው ጋር መግባባት ባለመቻላቸው ተለያዩ። የነበራቸውን ሃብትና ንብረት ሁሉ ለቀድሞው ባለቤታቸውና ለልጆቻቸው አስረክበው እጃቸው ላይ በነበረው 500 ሺ ብር የንግድ ቤት ተከራዩ፣ አነስተኛ ተሽከርካሪ ገዙና ዳግም ወደ ንግዱ አለም ተቀላቀሉ።
ደረጃዋን የጠበቀች ኢትዮጵያን አጉልታ የምታሳይ የባህል ሬስቶራንት ከፈቱ። በጥቂቱ የጀመሯት የባህል ምግብ ቤት ስራ እየተስፋፋች መጥታ ከፍተኛ እውቅናን ማግኘት ቻለች። በዚህ ሁኔታ ንግዳቸውን እያሰፉ ከመጡ በኋላ ያላሰቡት አደጋ ገጠማቸው። ጉልበታቸውንና መዋዕለ ንዋያቸውን ያፈሰሱባት ባህል ቤታቸው በእሳት ጋየች፤ ያፈሩት ንብረት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ወደመባቸው። ለችግሮች እጅ መስጠትን ፈፅሞ የማያውቁት የዛሬው እንግዳችን በጠፋው ነገር ተስፋ ሳይቆርጡ ዳግመኛ ሌላ የባህል ቤት ገንብተው ስራቸውን በአዲስ መልክ ከዜሮ ጀመሩ።
ፈተናቸው ግን በዚህ አላበቃም። አዲሱን ቤት ገንብተው ስራ በጀመሩ በስምንት ወሩ ቤቱን ማፍረስ እንዳለባቸው የምታዝ ደብዳቤ ከመንግስት ደረሳቸው። ዳግም በቅርብ ርቀት ላይ ቤት ተከራይተው ስራቸውን በመቀጠል አሁን ከፍ ያለ ዝና እና ተቀባይነት ያገኘው ዮድ አቢሲኒያ የባህል ቤት ተወለደ ። የባህል ቤቷ የናይጂሪያውያን ዳንኤል ኦባሳንጆና የመሳሰሉት ታላላቅ የአፍሪካና የአለም መሪዎችን ኢትዮጵያዊ በሆነ ለዛ አስተናግዳለች።ይህም የኢትዮጵያን ገፅታ ከፍ አድርጋ ለማሳየት አስችሏታል ። በዚህም በቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዚዳንትና ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ‹‹ የባህል አምባሳደር ›› የተሰኘ ማዕረግ እንዲያገኙም ምክንያት ሆናቸዋለች።
በጥቂቱ የተጀመረችውና በብዙ ውጣውረድ ውስጥ አልፋ እዚህ የደረሰችው የባህል ቤት ታዲያ አሁን ላይ አቅማቸውን አጎልብተው እንግዶቻቸውን የሚያሳርፉበትን ሆቴልና አስጎብኚ ድርጅት እንዲከፍቱ አግዛቸዋለች ። በሰው አቅም ለመቋቋም አዳጋች የሆነ የህይወት ፈተና ያለፉት የዛሬው እንግዳችን በቅርቡ በኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ጠንሳሽነት በጥቂት ቦታዎች የተጀመረውን ‹‹ ገበታ ለሃገር›› የተሰኘውን የልማት መርሃ ግብር ለማገዝ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማበርከት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።
በተወለዱበት ቀዬ ሎጅ በመገንባት በቱሪዝሙ ዘርፍ አሻራቸውን ለማሳረፍ በቅርቡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ በተገኙበት መሰረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል። ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሃብት ለአለም ህብረተሰብ ለማስተዋወቅና ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ያስገኛል ተብሎም ተስፋ ተጥሎበታል። የሸገር ፕሮጀክት አካል በሆነው ወዳጅነት ፓርክ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ የባህል ቤት ለመገንባት በዝግጅት ላይ ይገኛሉ። እኛም የዮድ አቢሲኒያ መስራችና ባለቤት አቶ ትዛዙ ኮሬን የዛሬ የዘመን እንግዳችን አድርገናቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ከወታደርነት ወደ ንግዱ አለም ለመግባት ያነሳዎትን አብይ ምክንያት ያስረዱንና ውይይታችንን እንጀምር?
አቶ ትዛዙ፡- በዘርፉ ለመሰማራት በዋናነት ምክንያት የሆነኝ ሀገርን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ነው። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና ባህል ባለቤት ብትሆንም በቱሪዝሙ ዘርፍ ያን ያህል ተጠቃሚ መሆን ያለመቻሏ፤ ከዚያ ይልቅም በድርቅና በችግር ብቻ መታወቋ ቁጭት ፈጥሮብኝ ነው ወደዚህ ስራ የገባሁት። የሀገሬን መልካም ገፅታ ለመገንባትና ልዩ ልዩ ባህሏን ለማስተዋወቅ በነበረኝ ፍላጎት መሰረት ያለኝን አቅም ሁሉ ተጠቅሜ ሰርቻለሁኝ። በዚህም ዛሬም ድረስ የሚያኮራ ስራ በመስራቴ ውጤታማ መሆን ችያለሁ። ያንን ስል ግን እዚህ መድረስ የቻልኩት አልጋ በአልጋ በሆነ መንገድ ነው ማለቴ አይደለም።
ለመቋቋም የሚያዳግቱ በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች አጋጥመውኛል። ድርጅቴ የመቃጠል አደጋ ደርሶበታል። እንደገና ተስፋ ሳልቆርጥ ሰርቼ ገና ሳላገግም በስምንት ወሩ ያለ በቂ ምክንያት በአስቸካይ ፎቅ ካልሰራሁ እንደሚፈርስብኝ ተነገረኝና ፈረሰብኝ። እንደእውነቱ ከሆነ የባህልና ቱሪዝም ስራ የሚሰራና የሚጥር ሰው ሊደገፍ ሲገባው እንዲህ አይነት ጫና ሊደረግበት አይገባም ነበር። ቤቴን ያፈረሰብኝም በወቅቱ የነበረው መንግስት ነበር። የሚገርመው ደግሞ የእኔን የባህል ቤት አፍርሰው ፎቅ አልሰሩበትም። ለሀገር ሃሳቢ የሆኑኩትን ኢትዮጵያዊ አስወጥተው ለአንድ ለሱዳናዊ ነው የሰጡት። የሚገርምሽ ያም ሱዳናዊ የባህል ቤት ነበር የሰራበት። እሱን ወደፊት ታሪክ ይናገረዋል ብዬ ትቼዋለሁ።
ያም ሆኖ ግን ተስፋ ባለመቁረጥ ለሶስተኛ ጊዜ አሁን ያለንበት አደራሽ አቋቋምኩኝ። በመጀመሪያ 500 ካሬ ሜትር ነበር ፤ ከዚያ አንድ ሺ ካሬ ሆነ። እሰፋነውና አሁን 2ሺ500 ካሬ ላይ ደርሷል። በነገራችን ላይ ይህንን ሰፊ አዳራሽ ሮሆቦት እያልን ነው የምንጠራው። ይህም ማለት ሰፊ ቦታ እግዚአብሄር ሰጠኝ፤ አሰፋልኝ ማለት ነው። ይህ አደራሽ ትልልቅ የመንግስት እንግዶችን በማስተናገድ ይታወቃል፡ ከፍተኛ የሚባሉ የውጭ አገራት ባለስልጣናት መጥተዋል።
ባህላዊ ምግብን ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን ባህላዊ ቱፊቶችን፤ ቋንቋዎቻችንና ቅርሶቻችንም ነው የምናስተዋውቀው። በዚህም ምክንያት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እውቅና ያለው የቀድሞው የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የባህል አምባሰደር ማዕረግ ማግኘት ችለናል። በዚህ ቆይታም አልተወሰንም። ተያያዥነት ያለው ስራ በመሰራት አስበን የአስጎቢኝና የጉዞ ስራዎችን አያይዘን እየሰራን ነው ። ትንሿ ኢትዮጵያ የሚል ስም የሰጠነው እንግዶቻችን የሚያርፉባት ሆቴል ገንብተናል። በዚህም አላበቃንም አሁን ደግሞ በትውልድ መንደሬ አካባቢ ውብ የሆነ ሎጅ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነኝ ። ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚኒስትራችን የጀመሩትን ገበታ ለሀገር መርሃብር እንደአርአያነት በመውሰድ ለምን በእኛስ አካባቢያችን አንገነባም? በሚል ፕሮጀክት ነድፈን ወደ ስራ ገብተናል ። ይህ ፕሮጀክት በእኔም ላይ ተነሳሽነት ፈጥሮ በአካባቢዬ በተፈጥሮም የበለፀጉ ቅርስም የተገኘበት ስፍራ በመሆኑ ቱሪስቶች እንዲጎበኙ የሚያርፉበት ሎጅ ለመገንባት ነው የተነሳነው። እርግጥነው፤ በዚያ አካበቢ አሁን ላይ ኢንቭስት ማድረግ አዋጭነት አለው ተብሎ አይታሰብም፤ ግን ለአካባቢው ተወላጆች የስራ እድል ለመፍጠር ጥሩ አመቺ ሁኔታ ይሰጣል በሚል ነው በድፍረት የገባንበት። ከዚህ በተጨማሪም እንደ የአካባቢው ተወላጅነቴ ለዚያ ማህበረሰብ ምን ሰራሁ? የሚል ጥያቄ ስለነበረኝ ያንን ጥያቄ ይመልስልኛል የሚል እምነት አለኝ ። እርግጥነው መነሻዬ ከዚያ ቢሆንም በሌሎችም የቱሪስት መስህብነት ያላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ ለመስራት ሃሳቡም እቅዱም
አለኝ። ስለዚህ አሁን የደረስንበት ደረጃ በጣም ጥሩ ።
አዲስ ዘመን፡- እርሶ የሚታወቁት በፈተናዎች ሳይበገሩ በታላቅ ፅናት እዚህ በመድረሶት ነው።ከዚህ ሁሉ ፅናት እና ትእግስት ጀርባ ያለውን ምስጢር ቢያካፍሉን ?
አቶ ትዛዙ፡- ከበስተጀርባዬ ምንም አይነት ሚስጥር የለም። መነሻዬም ሆነ መድረሻዬ ተስፋ፤ እምነት፤ ፍቅር ነው። ‹‹በፈተና የሚፀና እሱ የህይወት አክሊል ይደፋል›› እንደሚለው ቅዱስ ቃሉ በህይወቴ ሙሉ እጅግ ተስፋ የሚያስቆርጡ ችግሮች ቢያጋጥሙኝም እምነት፣ ተስፋና ፍቅርን ይዤ በመስራቴ ነው እዚህ መድረስ የቻልኩት። በእኔ እምነት በፍቅር ሁሉንም ነገር ማሸነፍ ይቻላል። እግዚአብሄር ላይ መተማመንም ለውጤት ያበቃል። ደግሞም እኮ በእምነቱ የፀና እና መንፈሰ ጠንካራ የሆነ ሰው በሁሉም ነገር እግዚአብሄር ራሱ ይረዳዋል። ስለዚህ ፈተናዎች በሚያጋጥሙኝ ጊዜ የማመለክተው ለአምላኬ ብቻ ነው። ለሰው አላመለክትም። ምክንያቱም የማምነው አምላክ ፅናትንና ተስፋ አለመቁረጥን በልቤ ውስጥ አስቀድሞ በማኖሩ ነው።
እንደነገርኩሽ በእምነቱ የፀና በመንፈሱ የጠነከረ ሰው ችግሮች ቢያጋጥሙትም መቋቋም እንደሚችል የማምን በመሆኑ ነገሮች ሲበላሹብኝ ነገም ሌላ ቀን ነው ብዬ ነው የምነሳው። በሁሉም ነገር የፈጣሪ እርዳታ እንዳይለየኝ ዘወትር እማፀናለሁ ። እንዳነሳሽው ግን በርካታ ችግሮች አጋጥመውኛል። ችግሮችን ግን ለመቋቋም የቻልኩት ከእስር ቤት ቆይታ ያገኘሁት የመንፈስ እውቀት አቅም ስለሰጠኝ ነው። ለእኔ እስርቤት ሰው እንደሚናገረው ሲኦል ወይም የችግር ቦታ አይደለም። እኔ እስር ቤትን ዝግ ሱባኤ ብዬ ነው የምጠራው። እንደሚታወቀው በኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት አንድ ሰው ሱባኤ ከገባ ከምንም ነገር ነፃ ሆኖ ህሊናውን ሰብስቦ በፆምና በፀሎቱ አምላኩን የሚለምንበት ነው። አሁንም እዛ ቦታ ላይ ስለምበላውና ስለምጠጣው አልጨነቅም፤ ስለስራም አላስብም። ምክንያቱም ደግሞ በመንግስት እጅ ያለሁ በመሆኔና ላደርግም፤ ልጨነቅም ብል የማመጣው ነገር ባለመኖሩ ነው።
እስር ቤት ሳለሁ ፈጣሪ የነበረኝን ደካማ ጎን እየለወጠ መንፈሰ ጠንካራ እንዲያደርገኝ ነበር ስፀልይ የነበረው። በነገራችን ላይ በዚያ ወቅት ያገኘሁት እውቀት የትም የማላገኘው ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እስር ቤት ስትገቢ ከወንጀል ትርቂያለሽ፣ ሌሎች እኩይና በእምነት ፀያፍ ከሆኑ ተግባራት ትርቂያለሽ። ስለዚህ ከዚህ ሁሉ ነፃ የሆነውን ስፍራ ለምንድነው የምንኮንነው? ብዙ ሰው ሲታሰር ፈጣሪውን ያማርራል። እኔ ግን አማርሬው አላውቅም። ምክንያቱም እግዚአብሄር ሊመጣ ካለው አደጋ ሊከልለኝ እንደሆነ አምን ስለነበር ነው።
አሁን ላይ ያለኝን ልምድ ያገኘሁት እዛ ቦታ ላይ ገብቼ ባገኘሁት እውቀት ነው። ፅናቱንም ያገኘሁት ከዚያ ነው። ከዚያ ቤት ያገኘሁት ስንቅ የመንፈስ ጥንካሬ ሰጥቶኝ ለዚህ በቅቻለሁ። ፈተናም ቢያጋጥም ያንን ፈተና ለመወጣት መቻል ይጠበቅብናል። ፈተና ባጋጠመ ቁጥር ፈጣሪን ከማማረር ይልቅ ሁሉንም ነገር ለበጎ ማሰብና ወደ በጎ መቀየር ለስኬት ያበቃል። እርግጥ ነው ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ሰዎች አሉ። ግን የእነሱንም ፈለግ በመከተል ውጤታማ መሆን ችያለሁ።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ማንኛውንም ስራ ሲሰራ ትርፉን ከግምት ውስጥ አስገብቶ ነው። እርሶ ግን ኪሳራ እንደሚያደርስቦት እያወቁ በተለይም የሀገሪቱን ገፅታ ለመቀየርና የህዝቡን ባህል ለማስተዋወቅ ብዙ ሰርተዋል፤ የባህል አምባሳደርነትዎን በተግባር አስመስክረዋል። ይህን የሚያደርጉበት የተለየ ምክንያት ይኖርዎት ይሆን?
አቶ ትዛዙ፡- ብዙ ጊዜ በሚዲያዎች ስጠየቅ ይሄ ጥያቄ አልተነሳልኝም። የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ግን እውነት ለመናገር የተለየ ስጦታ ወይም ጥንካሬው ስላለኝ አይደለም። ግን እንደነገርኩሽ በስራ አጋጣሚ በቆየሁባቸው ጊዜያቶች ከዘጠኝ ያላነሱ የሞት አደጋዎች አጋጥመውኝ ነበር። ከእነዚህ ከሞት አደጋዎች ውስጥ ተርፌ እዚህ አለሁ። እንደ እውነቱ ከሆነ እኔ በእድሜ አጋማሽ ነበር ልሞት ይገባ የነበረው። እግዚአብሄር እስከዚህ ድረስ ካቆየኝ ግን ትርፍ ኑሮ እየኖርኩኝ ለምን ሀገሬንና ህዝቤን የሚጠቅም ስራ አልሰራም በሚል በተለይም የሀገራችንን ባህል ለአለም ማህበረሰብ በማስተዋወቅ የበኩሌን አስተዋፅኦ ማበርከት እንደሚገባኝ ስለማምን ነው ኪሳራ እንደሚያመጣብኝ እያወኩኝ እንኳን ቢሆን ስራዎችን በድፍረት የምጀምረው።
እንደነገርኩሽ እኔ ከመነሻዬም ጀምሮ ማንንም ተመክቼ ወይም ድጋፍ አግኝቼ አይደለም ወደዚህ ስራ የገባሁት። ሁሉንም ስራ ስጀምር የምማከረው ከአምላኬ ጋር ነው። እኔ በህይወት ዘመኔ ሰው አምኜ ሰው ኖሮኝ፤ ሃብትና ገንዘብ ሰጥቶኝ ወይም ደግሞ በአቋራጭ ሄጄ ያገኘሁት አንድም ነገር የለም። በ1996 ዓ.ም ከእስር ከተፈታሁኝ በኋላ ዳግመኛ ወደ ንግዱ አለም ስገባ ከባዶ ነው የተነሳሁት። በወቅቱ ደግሞ በግል ሕይወቴ ባጋጠመኝ ችግር ማህበራዊ ግንኙነቴም ጥሩ አልነበረም። እርግጥ ነው በወቅቱ የፈጣሪ መልዕክተኞች ብዬ የማስባቸው ሰዎች የተወሰነ መነሻ ገንዘብ ሰጥተውኛል። ከምንም በላይ ግን ያ ገንዘብ ፈጣሪ በረከት ያሳደረበት በመሆኑ ንግዴን ማስፋፋት ችያለሁ፤ ሃብትም ማፍራት ችያለሁ። በመሆኑም ዛሬ ላይ የሰጠኝን አምላክ ማመስገን ስላለብኝ ከእኔ በፊት ንግድ ከጀመሩ ሰዎች ባላነሰ መልኩ እዚህ ደርሻለሁ።
በሌላ በኩል ደግሞ አምላክ ካገኘነው እንድናካፍል እንጂ እንድንርቅ አላዘዘንም። ካገኘሁት ላይ ለማህበራዊ አገልግሎት እሰጣለሁ። በተለይም ወላጆች ለሌላቸው ልጆች ጧሪ ያጡ አረጋውያን ድርጅታችን እገዛ ያደርጋል። ስለዚህ ይህንን ነገር ቆጥሮልን ሊሆን ይችላል ብዬ አምናለሁ። በፈጣሪ እገዛ እዚህ በመድረሴና ቤቱን በበረከት ስለሞላው ነው እኔም ከሰጠኝ ላይ የማካፍለው። በነገራችን ላይ ለእኔ እዚህ መድረስ ሰራተኞቼ ትልቁን ሚና ይወስዳሉ። ድርጅቱ ሲከፈት የነበሩ ሰራተኞች ዛሬም ድረስ አብረውን አሉ። ይህ ሊሆን የቻለው በፍቅር እጅና ጓንት ሆነን በመስራታችንና በመከራና ችግር ጊዜ ስላልተለዩኝ ነው። ለምሳሌ በኮቪድ ጊዜ ሶስት ወራት ቤታችን ተዘግቶ ነበር። ነገር ግን ያባረርነው አንድም ሰራተኛ የለም። ደሞዝም አልተቆረጠባቸውም። ገቢ ባይኖረንም ከባንክ ተበድረን ነው የከፈልናቸው። በአጠቃላይ ከሰራተኞቻችን ጋር እንደቤተሰብና አጋር ሆነን በመስራታችን ነው እዚህ የደረስነው ብዬ አምናለሁ ።
አዲስ ዘመን፡- ድርጅታችሁ ከሌሎች የንግድ ተቋማት በተለየ ከሚሸጠው ከእያንዳንዱ ምግብ ላይ እየቀነሰ የበጎ አድራጎት ስራ ያከናውናል። የንግዱ ማህበረሰብ ከእርሶ ምን ሊማር ይገባል ይላሉ?
አቶ ትዛዙ፡- እውነት ለመናገር እኛ ስንፈጠር ራቁታችንን ነው የተፈጠርነው። ይህንን አለም ጥለን የምንሄደውም ራቁታችንን ነው። ገንዘብ ይዘን አንሄድም። ሲጀመርም ገንዘብ ይዘን አልመጣንም። እግዚአብሄር ከሰጠነው እንድንሰጥ ያዘናል። እኛ በሰጠን ቁጥር ደግሞ የበለጠ የሰፋና የጨመረ ነገር ነው የሚሰጠን። እኛም ይህንን ለማድረግ ጀምረነዋል። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ከአንድ ምግብ አንድ ብር እንሰጥ ነበር፤ ስራችን እየተስፋፋ ሲሄድና ከብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ወደ ሁለት ብር አሳደግነው። አሁን ደግሞ ሶስት ብር ለማድረግ ተዘጋጅተናል። ይሄ የማይቋረጥ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም ወላጆች የሌላቸውን ህፃናትና ጧሪ ያጡ አረጋውያንን በአመት ቢያንስ አራት ጊዜ እንመግባለን ። ይህንን ነገር ደጋግመን በምንናገርበት ጊዜ ከንቱ ውዳሴ ይሆንብናል ብለን እንሰጋለን። ግን ደግሞ ኖሯቸው እና መንገዱ ለጠፋቸው ሰዎች አርዓያ መሆን እንድንችል የግድ እንናገራለን።
እርግጥ ነው፤ የእግዚአብሄር ቃል ‹‹ቀኝ የሚያደርገውን ግራህ አይወቀው›› ነው የሚለው። በዚህም ምክንያት ሁልጊዜ ስለምናደርገው ድጋፍ ባወራሁኝ ቁጥር እሸማቀቃለሁ። ግን ደግሞ የሰጠ ሰው እግዚአብሄር እንደማያጎልበት ስለማምን እፅናናለሁ። ብዙዎቹ ከእኔ በላይ እንደሚሰጡ እና እንደማይናገሩ አውቃለሁ። ግን እንዳልኩሽ መስጠት እየፈለጉ የሚሰጡበትን መንገድ ላጡ ያበረታታል። ምንአልባት ከዚህ ጋር ተያይዞ የካ ክፍለ ከተማ ላይ አምስት ለሚሆኑ አባወራዎች ቤታቸውን ሙሉ ለሙሉ አፍርሰን በአዲስ መልክ ሰርተንላቸዋል። ክፍለ ከተማው የሰራውን ስራ አይቶ ለሌሎችም ትምህርት ይሰጣል ብሎ ዛሬ በይፋ የቤቶቹን ቁልፍ ይሰጣል።
አዲስ ዘመን፡- በቱሪዝምና ጉዞ ስራችሁ ምን ያህል ውጤታማ መሆን ችላችኋል? ሀገርን ከማስተዋወቅ አልፋችሁ እስራኤል ድረስ ከዚህ ቱሪስቶችን ይዛችሁ በመሄድ በሰራችሁት ስራስ ምን አይነት ተሞክሮ አገኛችሁ?
አቶ ትዛዙ፡- ከሀገር ውስጥ ባሻገር ወደ ቅድስት ሀገር እየሩሳሌም በምናደርገው ጉዞ አጋጣሚውን እንጠቀምበታለን የሚል እምነት አለኝ። ይህም ማለት በዚያ ፕሮግራም ላይ በመላው አለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚገናኙበትን እድል ፈጥረናል። የልምድ ልውውጥ ማድረግ ችለናል። ከዚህም አልፎ የቢዝነስ አጋሮችን መፍጠር ችለናል ብዬ አምናለሁ። እስራኤል የሚኖሩ ፈላሾችና እስራኤላውያን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንዲጎበኙ አመቺ ሁኔታ ፈጥረናል። አጋጣሚውን ለመጠቀም ሞክረናል። በነገራችን ላይ ይሄ በደርግ ጊዜ ይደረግ የነበረውን የህዝብ ለህዘብ ጉዞ ያስታውሰኛል። በኮቪድ ምክንያት በመሃል ተቋረጠ እንጂ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ ይችል እንደነበር አስባለሁ። ዳግም ወደዚህ ስራ ስንመለስ ግን ለሀገራችን የተሻለ ጠቀሜታ የሚያመጣ ስራ እንሰራለን ብዬ አስባለሁ ። ሀገርን፤ ህዝብን፤ ባህልን፤ ቋንቋን የምናስተዋውቅበት እድል ይኖረናል።
አዲስ ዘመን፡- ኮቪድ በንግዱ ዘርፍ በተለይም እንደ እርሶ በባህልና ቱሪዝም ስራ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ላይ ያደረሰው ጫና እንዴት ይገለፃል? የእርሶ ድርጅት አሁን ላይ እያገገመ ነው ማለት ይቻላል?
አቶ ትዛዙ፡- ልክ ነሽ፤ ኮቪድ እኛን ብቻ ሳይሆን የመላውን አለም ኢኮኖሚ አዳክሟል። በተለይ ደግሞ በባህልና ቱሪዝም ላይ የተሰማሩ የንግዱ ማህብረሰብ ክፍሎች ላይ ያሳደረው ተፅእኖ ቀላል አይደለም። አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ሶስት ወር ስንዘጋ መንግስት ሰራተኞች አታባሩ፣ ደመወዝ ክፈሉ ሲለን ድጎማ ሰጥቶን አይደለም። ሌላ ቀርቶ የባንክ ብድር እንድናገኝ ያቀረብነው ተደጋጋሚ ጥያቄ በአግባቡ አልተመለሰም። ባንኮች በምንፈልገው መልክ ወይም በጠየቅነው መንገድ አይደለም የሰጡን። ኮላተራል አስይዙ ነው ያሉን። የሌለውስ ምን ያድርግ? የሚለው ነገር መልስ አልተሰጠበትም።
በአንድ በኩል ሰራተኛ አታባሩ እንባላለን፤ በሌላ በኩል ብድር ማግኘት ካልቻልን ምን ይሆናሉ የሚለው ነገር ብዙም የታሰበበት አይመስለኝም። እኛ ያንን ነገር ስናደርግ ያስቀመጥነው ብር ኖሮን አልነበረም። ንብረት ሸጠንና ተበድረን ነው። ምክንያቱም ህይወት እየጠፋ ነው፤ የተሻለ ነገር እስከሚመጣ ድረስ መተጋገዝና መረዳዳት አለብን ብዬ አምናለሁ። ይህንን ለማድረግ ብዙ መንገድ ሄደናል። እስከ ሶስት ወር ድረስ በዚህ መልክ ከቀጠልን በኋላ ከሰራተኛው ጋር ተመካክረን ሰራተኛው በራሱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ደመወዙን ቀንሶ በራሱ ጥያቄ ነው የቀጠለው። አሁንም ስራ ብንጀምርም የምንፈልገው ደረጃ ደርሰናል ማለት አይደለም። አሁንም ኮቪድ ከምድራችን ስላልጠፋና ተፅዕኖውም ስለቀጠለ ሙሉ ለሙሉ አላገገምንም። በተለይም አስጎብኚ ድርጅታችን አሁንም እየሰራ አይደለም። መንግስት ድጋፍ ሊያደርግልን ይገባ ነበር። በእኛ በኩል እስካሁን የተደረገልን ነገር የለም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ላይ በተወለዱበት ቀዬ ሎጅ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው ያሉት። እስቲ ስለዚህ ፕሮጀክት አጠቃላይ ሁኔታ ያብራሩልን? በተለይ ለዚያ አካባቢ ማህበረሰብ ያለው ፋይዳ ምን እንደሆነ ያስረዱን?
አቶ ትዛዙ፡- እንደሚታወቀው የጉራጌ ማህበረሰብ ፍፁም በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምንና የሚኮራ ነው። ለዚህም ነው በየትኛውም የሀገሪቱ ጫፍ ድረስ በመሄድ በንግድ ስራ የሚሰማራው። ይህ ትላንት ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም እንደሚቀጥል ጥርጥር የለኝም። እኔም መነሻዬን እዚያ አካባቢ ላድርገው እንጂ እድሜውና ወቅቱ ከፈቀደልኝ ፤ አቅሙ ካለኝ በመላው የአገሪቱ አካበቢ ሎጅም ሆነ ሌሎች የልማት ስራዎችን የማላከናውንበት ምክንያት የለም። ለዚህ ስራ መነሻ የሆኑኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ገበታ ለሀገር በሚል የልማት መርሃ-ግብር ውስጥ ለቱሪስት መስህብነት ከመረጧቸው አካባቢዎች በተጨማሪ እኔ የተወለድኩበት አካባቢ ለምን የእሳቸውን አርአያነት በመከተል የራሳችንን አንገነባም ብዬ ነው የተነሳሁት።
ያ አካባቢ ምንም እንኳን በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ሃብት የታደለ ሆኖ ሳለ ለምን አልታሰበም? የሚል ቁጭት አድሮብኝ ነበር። በመሆኑም ዝም ብዬ መንግስት ላይ ጣት ከመጠቆም ይልቅ ለምን ባለችኝ ትንሽ አቅም እኔ ልጀምረውና ሌሎች አቅም ያላቸው ሰዎች የበለጠ ያሰፉታል በሚል ተነሳሽነት ነው ሎጅ ለመገንባት የተነሳሁት።
የሚገርምሽ ቆጠር ገድራ የተባለው ይህ ቦታ በጥቅጥቅ ደን የተሞላና ውብ ተፈጥሮ ያለው ስነምህዳር ነው። በዚህ ዘመን እንዲህ አይነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖሩ ጥርጣሬ የሚያጭር ስፍራ ነው። በዚያ አካባቢ በጣም ትልቅ ቅርስ ተገኝቶበታል። ይህ ቅርስ ከ600 ዓመት በፊት የኦሪት የመስዋት ማቅረቢያ ዋሻዎችና ፅላቶች ተገኝተዋል። 28 ዋሻዎች እንዳሉ ጥናቶች አመልክተዋል። ከዚያ ውስጥ እስከአሁን ሰባቱ ተገኝተዋል። ተጨማሪ ፍተሻ ቢደረግበት ከፍተኛ የሆነ የቱሪዝም ስፍራ ሊሆን እንደሚችል አምናለሁ። ግን ያ ቦታ እስካሁን አልታየም።
ይህንን ስፍራ ለማስተዋወቅ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯን በዞኑ አስተዳዳሪ አማካኝነት እንዲጋበዙ ተደርጎ ካዩት በኋላ በጣም ነው የተደነቁት። በዚያ አካባቢ ሎጅ መገንባቱ ቱሪስቱን የበለጠ ሊስብና የውጭ ምንዛሬ ለሀገሪቱ ሊያስገኝ እንደሚችል ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። የአካባቢው የተፈጥሮ ውበት ለቀሽው እንድትሄጂ አይፈቅድልሽም። ከዚህም ባሻገር የተፈጥሮ ፈዋሽ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ(ጠበል) የተገኘበት በመሆኑ ሌላ ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ ይሆናል ብዬ አስባለሁ ። ያ ቦታ በጥሩ አያያዝ ቢያዝ የቱሪስት መስህብ መዳረሻ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለኝም። ያንን ሃሳቤን ነው ወደ ተግባር ለመለወጥ እየጣርኩኝ ያለሁት።
ይህ ሎጅ በሁለት ምዕራፍ የሚገነባ ነው ። አጠቃላይ ሎጁ የሚያርፍበት ስፍራ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ነው። እዛ ቦታ ላይ ሰው ሰራሽ ሃይቅ የምንገነባ ሲሆን ዓሳ ማስገሪያ ይኖራል። የአካባቢውን ውብ ስነ-ምህዳር መመልከት የሚያስችል ትልቅ ማማ ይገነባል። ከዚህም ባሻገር ከብት የምናረባበት፤ ንብ የምናንብበት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ስፍራም ይኖረናል። በአጠቃላይ ኤኮ ቱሪዝምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሟላ ግንባታ ነው የሚከናወነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ 33 ሚሊዮን ብር ይዘናል። በሁለተኛው ምዕራፍ 110 ሚሊዮን ብር የሚፈጅ ግንባታ እናከናውናለን ብለን ነው ያቀድነው። የመዋኛ ገንዳዎችና ሌሎችም የመዝናኛ ስፍራዎችን አስፍተን የምንሰራ ነው የሚሆነው። በመጀመሪያው ምዕራፍ ለ35 ቋሚና ለ23 ጊዜያዊ ሰራተኛ የስራ እድል እንፈጥራለን ብለን ነው የምናምነው። አሁን ጀምረነዋል። እርግጥ ነው፤ አሁን ላይ መሰረተ ልማቶች የሉትም ። ከዞኑ አስተዳደር ጋር እየተመካከርን ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እናደርጋለን ። ለመብራትና የውሃ መሰረተ ልማቶች በጋራ የምንገነባ ይሆናል። በበጋም ሆነ በክረምት ሊያስኬድ የሚችል መንገድ እየተሰራ ነው ።
አዲስ ዘመን፡- ከዞኑ የወጡ በርካታ ባለሃብቶች ቢኖሩም የአካባቢውን ማህበረሰብ በተጨባጭ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እምብዛም ሲሰሩ አይስተዋልም። ከዚህ አንፃር ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
አቶ ትዛዙ፡- እንግዲህ የሰው አስተሳሰብ የተለያየ ነው። እኔ የማስበውን ሌላው ሰው ማሰብ አለበት ብዬ አላምንም። እኔ የአካባቢው ህብረተሰብ ቢሻሻል ቢለወጥ ጥሩ ነገር ቢያይ በጣም ደስ ይለኛል። እረካበታለሁም። ምክንያቱም የሰው ደስታ የሚያስደስተኝ ሰው ነኝ። ሌላው ደግሞ ልክ እንደእኔ ቢያስብም ከባንክ ተበድሮ መስራት ሊፈራ ይችላል። የሆነ ሆኖ ግን በቅን ልቦና ለዚያ ማህበረሰብ ኑሮ መለወጥ አስበን ከተነሳን ላይሳካ የማይችልበት ሁኔታ አይኖርም። ፈጣሪም ደግሞ ቅን ልቦናችንን አይቶ እንደሚያግዘን አልጠራጠርም። በመሆኑም ሁሉም በመጠኑና ለአካባቢው የሚያደርገውን ድጋፍና አስተዋፅኦ ማስፋት አለበት ብዬ አምናለሁ።
አሁን ላይ እንዳልሽው ከዚያ አካባቢ የወጣው የንግዱ ማህበረሰብና ባለሃብት የአካባቢውን ህዝብ የሚጠቅም ስራ ለመስራት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው። ግን ደግሞ ይህ ጥረት አመርቂ ነው የሚባል እንዳልሆነ ግልፅ ነው። በመሆኑም እኔ በግሌ ለእነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች የምመክረው ፈጥኖ ከፍ ያለ ትርፍ የሚያስገኝ ስራ ብቻ ለመስራት መነሳት እንደሌለብን ነው። አሁን በትንሹ ከጀመርን ይለወጣል ብዬ አምናለሁ። እኛ የጀመርነው ነገር በርካታ ሰዎች ሊያሳትፍ የሚችል በመሆኑ አካባቢያችንን ለማልማት ሌሎችም እገዛ ያደርጉልናል ብለን እናምናለን።
በነገራችን ላይ እኔ የትውልድ አካባቢዬ ባለመልማቱ ከሚቆረቆሩ የአካባቢው ተወላጆች አንዱ ነኝ። ለዚህም ነው ለረጅም አመታት‹‹ መስቀል ንዳ በቃ ያንዳ›› በሚል ርዕስ በአካባቢያችን ያለውን የመስቀል አከባበር ባህል በስፋት እንዲተዋወቅ ስሰራ የቆየሁት። እንደሚታወቀው ጉራጌ መስቀልን በልዩ ሁኔታ ነው የሚያከብረው። ለምንድነው የሚያከብረው ብለሽ ብትጠይቂኝ ሰርቶ ያገኘውን እግዚአብሄር እንዲባርክለት የወላጆቹን ምርቃት የሚያገኝበት ስለሆነ ነው ። ሁሉም ለፍቶ ጥሮ ግሮ የሰበሰባትን ነገር ይዞ ቤተሰቦቹ ጋር ይሄዳል። ከብት አርዶ ያበላል፤ ከፍተኛ ምርቃት ያገኛል። ይህንን እድል ምንአልባት ብዙዎቹ አያገኙትም። ብዙዎች ይህንን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባህል የማየት እድሉንም አያገኙም።
ድርጅታችን መስቀልን በአካባቢያችን በሚል ርዕስ ለአንድ ሳምንት ያህል በጉራጌ ማህበረሰብ የሚከበረውን የመስቀልን፣ የዳመራን ጭፈራን የአመጋገብ ስነስርዓትን ያጠናቀቀ መርሃ ግብር በአንድ ቦታ ላይ ታዳሚዎች እንዲመለከቱ የሚያስችል እድል ፈጥረናል ። 364 ቀን ለሀገሬ ኢትዮጵያ፤ አንድ ቀን ላፈራኝ ማህበረሰብ በሚል የግሌ መፈክር በመነሳት ተወላጁም ሆነ ሌላው ህዝብ ያንን ባህል እንዲያውቅና እንዲጎበኝ እድል ፈጥሬያለሁ። ይሄ መርሃ ግብር አሁን ላይ በደንብ ተቀባይነት አግኝቷል። ዞኑም እውቅና ሰጥቶታል። በዚህ መርሃግብር ላይ ከአካባቢው ማህበረሰብ አበላልና ባህል ባሻገር የምርት ውጤቱን የምናሳይበት አውደ ርዕይም ይኖራል። እኛ ይህንን የምናደርገው ገቢ ለማግኘት አልመን አይደለም፤ ነገር ግን ለትውልድ ለአካባቢዬ የበኩሌን አስተዋፅኦ ለማበርከት በሚል ነው።
ይህም ለሁሉም ሰው ተነሳሽነት ስለሚፈጥር ነው የዞኑ አስተዳደርም ሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ትኩረት የሰጡት። የሎጁ መሰረተ ልማት በተቀመጠበት ጊዜም ከጠበቅነው በላይ ሚዲያው ሽፋን ሰጥቶታል። በአጠቃላይ መሰረተ ልማት አልተዘረጋም፤ ቢሮክራሲ አላሰራ አለኝ የሚሉትን ነገሮች ወደ ጎን ትተን ሁላችንም አቅማችን በፈቀደ መጠን መንቀሳቀስ ይኖርብናል። እኔ እውነት ለመናገር አቅሙ ስላለኝ አይደለም ለመገንባት የተነሳሁት። ግን አቅም ያላቸው ባለሃብቶች አሉ። ይህንን በቀላሉ ሊገነቡ ይችላሉ። ምቹ ሁኔታን ሳይጠብቁ ላፈራቸው ማህበረሰብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይገባል። ዞኑም ለአልሚዎች የተሻለ ሁኔታ ፈጥሮ እጁን ዘርግቶ እየጠበቀ ነው። ደግሞ ያንን አካባቢ ለማልማት ብዙ መሰናክል ይገጥማቸዋል ብዬ አላምንም። ስለዚህ ወደዚህ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ጥሪዬን ማቅረብ እወዳለሁ።
በሀገራችን ከቅርብ አመታት ወዲህ የተፈጠረውን በብሔርና በተለያዩ ልዩነቶች መከፋፈሉ እየቀነሰ የመጣና ወደ ልቦናችን የተመለስን ይመስለኛል። እርግጥ ነው፤ የጉራጌ ማህበረሰብ በተለያየ የሀገሪቱ ክፍሎች ለዓመታት ለፍቶ ያፈራው ወድሞበታል፤ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበታል፤ ሞቷል፤ ተሰዷል። ይህ ሁኔታ ግን አሁን ላይ ቀንሷል። ወደፊትም ይጠፋል ብዬ አምናለሁ።ፈጣሪ ፀሎታችንን እስከወዲኛውም ልዩነቶችና መከፋፈሎችን እንዲያስቀርልንና ሀገራችን ሰላም እንዲያደርግልን ነው። ይሆናልም ብዬ ተስፋ ስለማደርግ አሁን በአካባቢዬ የጀመርኩትን በሁሉም አካባቢዎች ለመስራት እንቅፋት ያጋጥመኛል ብዬ አላስብም። እግዚአብሄር በቃችሁ ይበለንና ያለፈው አሰቃቂ ሁኔታ እንዳይደገም ምኞቴ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ አኳያ ባለሀብቶች በተለይም በባህልና ቱሪዝም በስፋት እንዲሰማሩ በመንግስት በኩል ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ትዛዙ፡- እውነት ለመናገር መንግስት ብዙ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚችልበት ሁኔታ ነው ያለው ብዬ አላምንም። ወይም አቅቶታል አልያም ደግሞ ለመስራት ተነሳሽነት ያላቸውን ሰዎችን በአግባቡ እያየ የሚደግፍበት ደረጃ ላይ አልደረሰም። ለምሳሌ ይሄ የምታይው ቤት የኪራይ ቤት ነው። እኛ ደጋግመን ነው የጠየቅነው። እኔ በማስረጃ ላሳይሽ እችላለሁ ። በርካታ የመንግስት ሃላፊዎች ቃል ገብተውልናል። ግን የአንዳቸውም ቃል እስካሁን ተፈፃሚ አልሆነም። ለምሳሌ ባነሳልሽ ኢንጅነር ታከለ ኡማ መጥተው ጎብኝተዋል። የፈረሰብንንም አይተው ‹‹ እኛ የማይፈርሰውን እንሰጣለን፤ በ15 ቀን ውስጥ ፕሮጀክታችሁን ይዛችሁ ቅረቡ›› አሉን። ይዘን ቀረብን ግን ከ15 አልፎ አሁን ሁለት አመት አልፎታል ። እስካሁን መልስ አላገኘንም። እግራችንን ከማድከምና ጫማችንን ከመጨረስ ያለፈ ያየነው ለውጥ የለም።
ይሄ ቤት እንደሚታወቀው በርካታ የውጭ ሀገራት ባለስልጣት የሚያስተናግድ፤ ኢትዮጵያን የሚያሳይ የሚያንፀባርቅ የባህል ቤት ነው። እንደው ለአብነት ያህል ብጠቅስልሽ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የደቡብ ኮሪያ ጠቅላይ ሚኒስተር፤ የአየርላንዱ ጠቅላይ ሚኒስተር፣ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና ሌሎችም ተስተናግደውበታል። ከዚህ የተሻለ ቦታ ቢሰጠን የማናለማበት ምክንያት የለም። ልምዱ አለን። አቅሙ እንኳን ባይኖረን መንግስት ሊደግፈን ይገባ ነበር። ምክንያቱም እኛ የምናስተናግዳቸውና የሃገሪቱን ባህል የምናስተዋውቃቸው የመንግስትን እንግዶች ናቸው። እነዚህን ትልልቅ መሪዎች በዚህ ውስጥ ቦታና ሁኔታ ከምናስተናግድ በተሻለ ስፍራና አቅም እንዲሁም ባህላዊ ይዘቱ በጠነከረ ሁኔታ የምናስተናግድበትን ቦታ ሊሰጠን ይገባ ነበር።
እኔ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ ተናገሬ ሁሉም ቃል ገብተውልኝ ነበር ። ግን የፈፀመው የለም። ቤታችን በተቃጠለ ጊዜ ጥያቄ አቅርበናል። በወቅቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የነበሩት አምባሳደር መሃመድ ድሪል ሀዘናቸውን ገልፀው መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ፅፈውልን ነበር። አሁን ያሉትም ሚኒስትር ለከንቲባዋ ፅፈውልናል። እስከአሁን ግን ምንም አይነት ተግባራዊ ምላሽ አላገኘንም። ለዚህ ቤት በዓመት ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ እንከፍላለን። ይህንን ገንዘብ ለሌላ ልማት ብናውለው እኛ ብቻ ሳንሆን አገርንም እንጠቅም ነበር። ስለዚህ ስለጠየቅሽኝ ብቻ ልመልስልሽ እንጂ እስካዘሬ ጠይቀን ምላሽ ባለማግኘታችን በዚህ በኩል ብዙ ተስፋ የሚሰጥ ነገር የለም። ሌላው ይቅርና በኮረና ዘመን ግብዓቶችን ከቀረጥ ነፃ ለማግኘት ጠይቀን አጥጋቢ ምላሽ አላገኘንም። ምንአልባት የእናንተን ጋዜጣ የሚያነብ የመንግስት አካል ጋር ደርሶ የዓመታት ጥያቄያችን ምላሽ ሊያገኝ ይችል እንደ ሆነ ወደፊት የምናየው ነው የሚሆነው።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ አሁን እየጠፋ የመጣውን ኢትዮጵያዊ አንድነት ለመመለስ ምን መሰራት እንዳለበት ይግለፁልን እና ውይይታችንን እንጨርስ?
አቶ ትዛዙ፡- ኢትዮጵያዊነት ለእኔ ብዙ ነገር ነው። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ከደረሰብኝ ነገር የተነሳ እንደብዙዎቹ ጓደኞቼ ከዚህ አገር በተሰደድኩኝ ነበር። በተለይ እኔ አየር መንገድ እሰራ ስለነበር ወደውጭ የመሄዱ እድል ነበረኝ።ከእኔ ጋር ይሰሩ የነበሩ ሰዎች ብዙዎቹ ዜግነታቸውን ቀይረው በስደት አገር እየኖሩ ነው ። ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ ነው። ለሀገሬ የተለየ ስሜት ስላለኝ በምንም ነገር ልለውጣት አልችልም። ለዚህም ነው በተሰማራሁበት ዘርፍ በተግባር የሃገሬን ፍቅር እየተገበርኩኝ ያለሁት።
የምሰራው ስራ ሰዎች እንዲያዩልኝ ብዬ ሳይሆን የምወዳት አገር ከማንም በላይ ልቃ እንድትታይልኝ ስለምፈልግ ነው። አየር መንገድ ስሰራ ሀገሬ ስለምትናፍቀኝ ብዙ በረራዎችን አስቀይሬ ወደሀገሬ የምመለስበት ሁኔታ ነበር። ታስሬ በተፈታሁበት ጊዜ እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ የተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶች የጥገኝነት እድል አቅርበውልኝ ነበር። እኔ ግን ያንን ያልተጠቀምኩት አገሬን ስለምወድ ነው። ፈጣሪ ይመስገን ሀገሬን እጠቅማለሁ ብዬ በተነሳሁበት ዘርፍ ውጤት አምጥቻለሁ።
አሁን ላይ እንዳልሽው የሀገር ፍቅር ስሜት ያለው ትውልድ እየጠፋ ነው ። ከዚያ ይልቅም ልዩነቶቻችን ላይ መሰረት በማድረግ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እርስ በርስ እየተጋጨን ነው ። ይህ ሁኔታ እንደማንኛውም ኢትዮጵዊ ያሳዝነኛል። በተለይ ሀገሬንና ህዝቤን ከልቤ የምወድ ሰው በመሆኔ መከፋፈላችን ያሳስበኛል። በመሰረቱ እግዚአብሄር ሁላችንም በአምሳሉ ሰርቶን ሳለ በዘርና በጎሳ ልንባላ አይገባም ነበር። እግዚአብሄር አንድ ያደረገውን ህዝብ እኛ ልንለያየው አይገባንም። የእግዚአብሄርን መንገድ ስተናል። ዘር ለሰብል ነው፤ እንጂ በእግዚአብሄር አምሳል ለተፈጠረ የሰው ልጅ አይደለም። በመሆኑም ያንን ልዩነትና መከፋፈል እስከወዲያኛው ለማስወገድ የሁላችንም ርብርብ ያሻናል የሚል እምነት ነው ያለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዘመን እንግዳ አንባቢዎችና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ትዛዙ፡- እኔም እንግዳችሁ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 5 ቀን 2013 ዓ.ም