ሰውዬው በአንድ የቤተሰብ ትልቅ ሰርግ ላይ ውሏል:: በሰርጉ በጣም ተደስቶበታል:: በተለይ ከብዙ ጊዜ በኋላ ባገኘው ጠጅ ተደስቷል:: በዚህ ዘመን ይህን አይነት ጠጅ ከየት ተገኘ ብሎ ውስጥ አዋቂ ያላቸውን ጠየቀ:: በትእዛዝ በተዋቂ ጠጅ ቤት የተሰራ መሆኑ ተነገረው:: እቤት ያሉትን እንግዳ አያቱን አስቦ ነው:: ያው ጠጅና አባቶች ይተዋወቁ አይደል:: አስተናጋጆቹ እንደ ምንም ብለው በሀይላንድ እንዲሰጡት ጠይቆ አገኘ::
ጠጁ ቤት ደርሰ:: ሰውዬው ውሎው ጥሩ እንደነበረ እየገለጸ የጠጅን ጣእም ያውቃሉ ያላቸውን አያቱን ሰርፕራይዝ ሊያረጋቸው አስቧል:: ራት መብላታቸውን አረጋግጦም ብርጭቆ እንዲመጣ አዞ ሊከፍተው ሲሞክር ጠጁ መክደኛውን የያዘበትን እጁን ገፍትሮ በመውጣት ቤቱን ጠጅ በጠጅ አረገው:: ማን ይቆጣጠረው:: ርችት በሉት:: ሳሎን ያለ ሰውም ሆነ እቃ ጠጁ ደርሶታል:: ኮርኒሱን ተውት:: ያን ሰሞን ቤቱ ፣ግቢው እቃው ሁሉ ጠጅ ጠጅ እንዳለ ሰነበተ:: ሰውም ጠጂ ቀጂ መስሎ ነው የዋለ የመሸው::
ከዚያ ጠጅ ለጉሮሮ የተረፈው የመዳህኒት ያህል ነበር:: አያቴ እንዲህ አይነት ጠጅ በዚህ ሀገር አለ ሲሉ ነበር ብርጭቆውን ከፍ አርገው መልኩን ጭምር እየተመለከቱ:: እኔ የምለው ጠጅ ይህን ያህል የሚወረወር ከሆነ ፣ በቃ ወደፊት ማስወንጨፊያ አንቸገርም ማለት ነው::
በሀገራችን ጠላ የማር ጠጅና የወይን ጠጅ፣አረቄና ካቲካላ የመሳሰሉት ረዥም ዕድሜ ያስቆጠሩ ባህላዊ መጠጦች ናቸው:: ከወይን ጠጅ በመለስ ያሉት ሁሉም በኢትዮጵያ ብቻ የሚዘጋጁ ናቸው:: እነዚህ አስካሪ ባህላዊ መጠጦች ናቸው:: በልክ ካልተወሰዱ ጉዳት ያስከትላሉ:: ሁሉም ግን የራሳቸው መስፈሪያ አላቸው:: በልክ ካልጠጡ ብቻ አይደለም በልክ ካለበሉስ ቁንጣን አለ አይደል አንዴ:: ሆድ የሚያሳምም::
የፈረንጅ አረቄ በአጼ ምኒሊክ ዘመን ነው ይባላል ወደ ሀገራችን የገባው:: ሰው ያንን አረቄ እየጠጣ እየሰከረ መሆኑን የሰሙት አጼ ምኒሊክ አረቄ አምጪውን ምን አረግሁህ አሉት ይባላል:: እሱም እኔ አረቄውን ባመጣም መለኪያም አንድ ላይ ይዥ መጥቻለሁ አለ ይባላል:: እናም ችግሩ ልክ አለማወቅ ላይ እንጂ መጠጡ ላይ አይደለም::
ደጅ ሆነን ስለጠጅ እናውጋ፤ ደራሲና ጋዜጠኛ ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር በጻፉት አንድ ባህላዊ ትውፊት መጽሐፍ እስከ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን አንድ ተራ ገበሬ የፈለገውን ያህል ሀብት ቢኖረው ከገዛ ቀፎው ማር ቆርጦ ጠጅ ጥሎ መጠጣት አይፈቀድለትም ነበር ሲሉ ገልጸዋል:: ጠጁ ግን በየመኳንንቱ ባላባቱ እልፍኝ ይገኝ ነበር:: በዚህም ምክንያት ጠጅና ወይን ጠጅ ለብቻቸው “ የጨዋ ልጅ መጠጥ “የሚል ስያሜ ወጥቶላቸው ይጠሩ ነበር ይሉናል :: ልብ በሉ እንግዲህ ከመጠጥም አቅም የእከሌና የእከሌ ሲባል::
የዘውዳዊው ሥርዓት ተገርስሶ ወታደራዊ ሥርዓት እንደ ቆመ/ ስልጣን እንደ ያዘ/ ጠጅ በቤተመንግሥት ግቢና ደጅ የነበረው ክብር እንዲቆም ተደረገ፤ የበዝባዥ ርዝራዥ መጠጥ ነው ተባለ:: ኅብረተሰባዊነትን በሚያቀነቅኑት ደርጎች ሳቢያ ጠጅ ድሃ ደጅ ተጣለ::
ጠጅ ከንጉሡ መውረድ ጋር ወደታች እየወረደ መጣ፤ ቃናውና ለዛውም ቀነሰ:: ከማር ተፋታ:: የማር ጠጅ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ነው የሚገኘው፤በባትሪ ተፈልጎ:: ለመአዛው ሲባል ብቻ ማር ዞር ይደረግበት ይሆናል እንጂ ስኳር ሆኗል:: የማር ጠጅ ሲባል እንደተኖረ የስኳር ጠጅ ማለት ብቻ ነው የቀረው:: ግርማው ተስፋ የተባሉ ገጣሚ በአንድ መጽሐፋቸው
ንብ ኑሮ ለውጣ ኑሮዋን ቀየረች
አበባ መቅሰምን ኋላቀር ነው አለች
ዛሬ ተሻሽላ ሥራ መናቅ ትታ
በየጉራንጉሩ ተጋፍታ
ጣፋጭ ወለላዋን ማመንጨቷን ትታ
ስኳር ትልሳለች ብርጭቆ ውስጥ ገብታ …. ሲሉ ገጥመዋል::
በርግጥ ንቦቹ በየሻይና ኬክ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ ብቅ ይላሉ:: ሻይ አላስጠጣም ብለዋል:: ስኳር ለምደዋል፤ እሱ ነው በየሻይ ቤቱ የሚያመላልሳቸው::
ጠጅ ጣፈጥ ስለሚል ጠጪዎችን ያታልላል፤በዚህ ላይ ጨዋታ ሲጨምርበት መታለሉ ይበዛል:: ጣፈጠኝ ብለው ለግተው ለግተው ጠጁ በተራው ከግንድ ሊያላጋቸው ይችላል:: ክፉ ሊያናግር፤ ሊያጣላም ይችላል::
ስለጠጅ ገልጾ ስለ አዝማሪያ ሳይገልጹ መውጣት አይገባም:: ጠጅ ቤት ሲታወስ ማሲንቆ መቺዎችም ይታወሱናል:: ማሲንቆ እየተጫወቱ ጠጅ እየተጎነጩ ገቢ የሚያመነጩት ማለቴ ነው:: ተቀበል ተብሎ ግጥም ተሰጥቶትና የራሱንም አውጥቶ ይዘፍናል:: ባህላዊ ጭፈራውና ዳንኪራው ይቀልጣል::
“ጠጅሽን ጠጣነው ጥንት በማር ዘመን
ዛሬ እያየነው በስኳር ሲመጠን”
“ጠጁን ጥለሽዋል ከሲሚን ከርድ (ከእርድ )
አንዱን የቀመሰ ያሳየናል ድድ “
“ጠጅሽን ጠጣነው ድሮ በማር ሲዘጋጅ
ዛሬ ስኳርሽን ስጭው ለማይበጅ “ የሚሉት ግጥሞች ከማሲንቆ መቺዎች የተገኙ ሲሆኑ ጠጅ ዝናውና ጥራቱም መውደቁን የሚያሳዩ ናቸው::
በአዲስ አበባ ከሚገኙ በርካታ ጠጅ ቤቶች መካከልም በጣም ተዋቂ ጠጅ ቤቶች አሉ:: እነዚህ ጠጅ ቤቶች ለሠርግና ለድግስ ታዘው ያቀርባሉ:: ጠጃቸው የማር በመሆኑ ሰው ተሻምቶ በጀሪካን ጭምር ይገዛቸዋል::
ወደ ፈረንጅ አገር የተሻገረ ጠጅ ቤት እንዳለም ሰምቻለሁ:: በጀርመን:: “በገና ጠጅ” በሚል ስም ጠጅ ጥለው የሚሸጡ ጀርመናዊት በዶቼ ቬሌ ፕሮግራም መተላለፉን አስታውሳለሁ:: ለዚያውም በጀርመናዊት የሚጣል ጠጅ:: ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉት ቬሊ የሚባሉት እኚህ ወይዘሮ በሸገር የኖሩ ናቸው፤ የሸገርን ጮማ ቆርጠው ጠጁን ጠጥው ያሳለፉበትን ጊዜ ያስታውሳሉ::
የኛ ጠጅ እንደተባለው ጀርመን ከመታየቱ በቀር / እሱንም በቅርቡ ነው የሰማሁት/ እንደ ሌሎች ሀገሮች መጠጦች ባህር ማዶ አልተሸገሩም:: ምናልባት በእቃ በእቃ እየተደረጉ ተወስደው ሊሆን ይችላል:: በእርግጥ እነሱን ለማሻገር ማዘመን ያስፈልጋል:: ካልዘመኑ በቀር ማጓጓዙም ያስቸግራል፤ ሰውዬው እጅ ላይ እንደሆነው ማለቴ ነው:: አየር ማረፊያ ላይ ጣጣ ቢያመጣስ:: መገራት አለበት:: ለነገሩ ካቲካላ እየተሸገረች ነው፤ በንግድ ልክ ግን አይደለም:: ካቲካላ ግን እየተሸገረ መሰለኝ:: በንግድ ልክ ግን አይደለም:: ለቤተሰብ ፍጆታ ::
መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ታላቋ ብሪታኒያ በ2014 ብቻ በአልኮል ኢንዱስትሪው ምርትና ሽያጭ 46 ቢሊየን ፓውንድ የሚያወጣ የአልኮል ማምረት ሽያጭ ተካሂዷል:: ይህም ከአጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት 2 ነጥብ 5 በመቶ ነው:: በሌላ መረጃ ደግሞ በዚህችው ሀገር በ2017 ውስኪ ለውጭ ገበያ በማቅረብ 895 ሚሊየን ፓውንድ ተገኝቷል::
እኛ ግን የአልኮል መጠጦቻችን ወደ ውጪ መላካችንንም ፤ለመላክ ማሰባችንንም እንጃ:: በሀገራችን በተለይ ባህላዊ መጠጦች ምን ያህል እንደሚመረቱ ምን ያህሉ ጥቅም ላይ እንደሚውል ፣ለምን ያህል ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩም የሚታወቅ አይመስለኝም::
እንደ ጠጅ ያሉትን ባህላዊ መጠጦች በዘመናዊ መንገድ የሚመረቱበትን ሁኔታ መፍጠር ፣ለውጨው አለም ማስተዋወቅ ላይ ቢሰራ መልካም ነው:: አሁንም ባለሀብቶቻችን የማር ጠጅ እንደ ውሃ ታሽጎ የሚሸጥበትን መንገድ ያስቡበት:: በአንዳንድ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፐራይዞች ኢግዚቢሽን እንደሚታየው ጠጅ እየታሸገ ለገበያ የሚቀርብበት ሁኔታ ቢስፋፋ መልካም ነው:: እነዚህን ምርቶች የውጭ ዜጎችና ዲያስፖራ ኢትዮጵያውያንም ሊወስዱ ስለሚችሉ የሚመለከተው አካል እነዚህን ኢንተርፕራይዞች ቢደግፋቸው መልካም ነው፤ ማን ያውቃል የውጪ ምንዛሪ ማግኘት አንጀምር ይሆናል:: ይህ ሲሆን ደጅ የተጣለው ጠጅ ቀን ይወጣለታል:: አለዚያ ስንፈዝ ጠጅንም እንደ ጤፍ የእኛ ነው የሚሉ እንዳይመጡ::
ይቤ ከደጃች.ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013