አዲስ አበቤዎችን ሰቅዘው ከያዙ የተለያዩ ችግሮች መካከል ዋነኛው የቤት ፍላጎት እና አቅርቦት አለመደራረስ ወይም በሁለቱ መካከል ያለው ሰፊ ክፍተት ተጠቃሽ ነው:: ይህን ችግር ለማቃለል መንግሥት በራሱ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን እያከናወነ ቢሆንም፤ የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር መጨመር እና ከፍላጎቱ ጋር የተመጣጠነ ግንባታ አለመከናወኑ ችግሩ እንዲቀጥል ብቻ ሳይሆን እንዲባባስ አድርጓል::
‹‹በየጊዜው እየጨመረ የመጣው የቤት ኪራይ ዋጋ ሕይወቴን እያመሰቃቀለው ነው›› በማለት ጥያቄያቸውን የጀመሩት አቶ ገብረሚካኤል ጄላን ፤ ቤት የማግኘት ተስፋቸው እየተሟጠጠ መሆኑን ይገልፃሉ:: አቶ ገብረሚካኤል አሁን ላይ የቤት ኪራይ ከፍለው ለሁለት ልጆቻቸው የትምህርት ቤት ወጪ እና የቤተሰብ ቀለብ ለመሸፈን ገቢያቸው በቂ አይደለም:: ስለዚህ የተወሰኑ ለውጦችን ለማድረግ ማለትም ልጆቻቸውን ከግል ትምህርት ቤት አስወጥተው ወደ መንግሥት ትምህርት ቤት ለማስመዝገብ የግድ የጋራ መኖሪያ ቤቱን የሚያገኙበትን ሁኔታ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ:: እዚህ ላይ ቤቱን አለማግኘታቸው እርግጥ ከሆነ አንድም በባንክ ለቤቱ ያስቀመጡትን ገንዘብ አውጥተው ለመጠቀም ይገደዳሉ:: እዚህ አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ከመግባቴ በፊት እባካችሁ የ1997 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎችን ጉዳይ በሚመለከት ጠይቃችሁ አሳውቁኝ በማለት ለዝግጅት ክፍላችን ጥያቄያቸውን አቅርበዋል::
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ አማራጭ የቤት ልማት አቅርቦት ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ታምራት እንደገለፁት፤ የ1997 ዓ.ም ነባር ተመዝጋቢዎች ያለምንም ማወላዳት ቤት ማግኘታቸው አይቀርም:: አሁን የተገነቡት ቤቶች በዕጣ ለ1997ዎቹ ተመዝጋቢዎች የሚተላለፍ ይሆናል:: ለእነርሱ በሙሉ ማለትም ለባለ አንዶችም ሆነ ለባለ ሁለት መኝታ ተመዝጋቢዎች በቂ ቤቶች አሉ:: አሁን ላይ ቀኑን በእርግጠኝነት ለመናገር ቢያዳግትም በቅርቡ ቤቱ የሚሰጥ ይሆናል ብለዋል::
ቀድሞም ‹‹በቅርቡ ይተላለፋሉ›› ተብሎ ነበር:: ነገር ግን የቤቶች ልማት ሲባል ተሰርቶ የሚሰጠው ቤቱ ብቻ አይደለም:: መንገድ፣ የፍሳሽ መስመር፣ መብራት እና ውሃ ያስፈልጋል:: እነዚህ የሚሰሩት በቅንጅት ነው:: ሥራው የሌሎች አካላቶችንም ድርሻ ይጠይቃል:: ከአንድ ወር በፊት የከንቲባ ጽሕፈት ቤት በኃላፊነት የሚመራው ዓብይ የቴክኒክ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሙሉ ለሙሉ ቤቶች ላይ የሚሰራ አንድም ሰው ሳይቀር ሁሉም ወደ ሳይት በመውረድ ሥራውን ከግብ በማድረስ ነዋሪውን የቤት ባለቤት ለማድረግ ታቅዶ ጉብኝት ተደርጓል:: ሆኖም ግን በሚታሰበው ደረጃ በፍጥነት ቤቱን ለማድረስ እክሎች በማጋጠማቸው በታሰበው ፍጥነት ቤቶቹ ለተመዝጋቢዎቹ መሰጠት አልቻሉም:: ለምሳሌ በግንባታዎች አካባቢ ውሃ የለም:: ስለዚህ ከሌላ ቦታ ተጭኖ መጥቶ ግንባታዎች እየተከናወኑ ነው:: ኤሌክትሪክም እንደዚያው ይቆራረጣል:: ያም በግንባታው ፍጥነት ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል:: ሆኖም አሁን ላይ እየተጠናቀቀ በመሆኑ፤ በቅርብ ጊዜ ሁሉም ሰው ቤት ማግኘቱ እንደማይቀር ይናገራሉ::
‹‹የተገነቡት ቤቶች ለ2005 ተመዝጋቢዎች ተደራሽ አይሆኑም:: ለ2005 ተመዝጋቢዎች ደግሞ አማራጭ ሰጥተናል:: ስለዚህ በማህበር ተደራጅቶ የመስራት ፍላጎት ያለው፤ በማህበር እንዲገነባ እና በሚፈልገው ጥራት ቤቶቹን እንዲያገኝ ከፈለገ በማህበር ተደራጅቶ እንዲሰራ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል::›› ካሉ በኋላ፤ ከማህበር ቤት ባሻገር ነገር ግን በፍጥነት ሰርተን በሚቀጥለው ዓመት አብዛኛውን የተመዘገበ ሰውን የቤት ባለቤት የሚሆንበት ሁኔታ እንደሚኖርም ነው የተናገሩት::
እንደአቶ ጳውሎስ ገለፃ፤ መንግሥት ላለፉት 16 ዓመታት የተቀናጀ የቤት ልማት ፕሮግራምን ተግብሯል:: በጊዜው የፕሮግራሙ ዓላማ በዋናነት ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ ቢሆንም፤ የቁጠባ ባህልን ማሳደግ እና የሥራ ዕድል ፈጠራም ታሳቢ ተደርጓል:: ይህ ሲሆን ቤቱን ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የመንግሥት ድጎማ ታክሎበት የቤት ባለቤት ይሆናሉ ተብሎ ታስቦ ነበር:: ነገር ግን ወደ ከተማዋ የሚፈልሰው ሰው ቁጥር በማደጉ እና ባለው የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ ነዋሪ ቁጥር መጨመር ምክንያት መንግሥት በራሱ ብቻ ቤት ገንብቶ የዜጎችን የቤት ፍላጎት ችግር ማቃለል የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል::
‹‹መንግሥት ብቻውን ቤት እየገነባ ለዜጎች መስጠቱ ጫና ፈጥሯል:: ፍላጎቱና አቅርቦቱን ማጣጣም ባለመቻሉ አሁን ላይ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም የግድ ሆኗል::›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ስለዚህ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ፖሊሲና ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ባወጣው ስትራቴጂ እና መመሪያ መሠረት ሌሎች አምስት ዓይነት የቤት ልማት አመራጮች ከ2013 ጀምሮ ለመስራት መታቀዱን እና እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል::
አማራጮቹ በማህበር ቤት ከመገንባት ጀምሮ የኪራይ ቤትን እስከ ማመቻቸት የደረሱ አማራጮችን ተግባራዊ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች በመሰራት ላይ ናቸው:: አንደኛው የማህበር ቤት ሲሆን፤ ሰዎች በጋራ ሆነው የቤት ልማት ፕሮግራሙን ተግብረው የጋራ ችግራቸውን የሚቀርፉበት አሠራር ነው:: በዚህ በኩል ምዝገባም ታካሂዷል ካሉ በኋላ፤ ሁለተኛው አመራጭ ደግሞ public prep partnership (ppp) በመንግሥት እና በግል አጋርነት የሚተገበር የቤት ልማት ፕሮግራም ነው:: ሰሞኑን እንደተሰማው በጋራ ከባለሀብትና ከድርጅቶች ጋር መንግሥት ተቀናጅቶ ፋይናንስ፣ ልምድ እና ቴክኖሎጂ ሌሎችም ነገሮችን የግሉ ዘርፍ ይዞ ሲቀርብ በመንግሥት በኩል ደግሞ መሠረተ ልማት እና የለማ መሬት በማቅረብ የሚተገበርበት አሠራር ነው:: በዚህ የአጋርነት አሠራር፤ ቤቶች ተገንብተው ለመንግሥት ይሰጣሉ:: መንግሥት ደግሞ ለዜጎች ቤት ያስተላልፋል ይላሉ::
ሌላው በመንግሥት እና በግል ሽርክና የሚሰራው ነው:: በመንግሥት በኩል መሠረተ ልማት ኢንፍራስትራክቸር እና የለማ መሬት በማቅረብ የሚከናወን ሲሆን፤ ባለሀብቱ በመቶኛ የተወሰኑ የንግድ ቤቶችን እና የመኖሬያ ቤቶችን ወስዶ ቀሪውን መንግሥት ለዜጎች ቤቶቹን ያስተላልፋል:: የሽርክናው ጥቅሙ መሬት እና መሰረተ ልማቱ በዋጋ ተተምኖ የተቀሩት ቤቶችን መንግሥት በነፃ ስለሚያገኝ ቤቶቹን ለዝቅተኛ ደረጃ ነዋሪው ተጠቃሚ የሚያደረግበት ሁኔታ ይኖራል::
ሌላኛው የኪራይ ቤት አማራጭ ነው:: ሁሉም ቤት ገዝቶ ወይም ለቤት መሥሪያ ቆጥቦ መኖር የሚችል አይደለም:: የዕለት ገቢ ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በኪራይ ቤት የሚያገኙበት ሁኔታ ይመቻቻል በማለት አምስተኛውን አማራጭ በመጥቀስ ሃሳባቸውን ጠቅልለዋል::
በዚህ ገፅ ላይ አንባቢያን በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ጥያቄ የሚያቀርቡበት እና እኛም የሚመለከተውን አካል መልስ ጠይቀን የምናስነ ብብበት ሲሆን፤ ማንኛውም ሰው በስልክ ቁጥር 0111264326 በመደወል ጥያቄ እና አስተያየት ማቅረብ ይቻላል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013