በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን እንደሚዘል መረጃዎች ይጠቁማሉ:: ይህ የኅብረተሰብ ክፍል የተሻለ ኑሮ ፍለጋ፤ በፖለቲካ ተጽእኖ፤ ለትምህርት ወዘተ አገሩን ለቆ የወጣና ኑሮውንም በአውሮፓ፣ አሜሪካና በተለያዩ የዓለም አገራት የመሰረተ ነው:: ዲያስፖራው በአብዛኛው ዘመናዊ ዕውቀትን የታጠቀና የተሻለ የገንዘብ አቅም ያለው ቢሆንም ባለፉት 27 ዓመታት ዕውቀቱንና ገንዘቡን አገሩ ላይ የሚያፈስበት ምቹ ሁኔታ ተነፍጎት ቆይቷል::
ዲያስፖራው ባለፉት 27 ዓመታት የነበረውን ጨቋኝ አስተዳደር በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በመቃወምና በአገር ውስጥ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ያለመታከት ድምጹን ሲያሰማ ቆይቷል:: በተለይም የኢህአዴግ መንግሥት የሚፈጽማቸውን የመብት ጥሰቶችንና አፈናዎችን በመቃወም የነበረው ኢፍትሃዊ አገዛዝ በሕዝብ አመጽ እንዲገረሰስ የበኩሉን ሚና ተጫውቷል::
በዶክተር ዐቢይ የሚመራው የለውጥ መንግሥት ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ ዲያስፖራው ቀደም ሲል ከሚታወቅበት መንግሥትን የመቃወምና የመተቸት አካሄድ ተላቆ በተለያዩ ልማቶች ላይ አሻራውን ወደ ማሳረፍ ተሸጋግሯል:: ለህዳሴ ግድብ፤ ለገበታ ለሀገር፤ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍና በየጊዜው ለሚደርሱ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ያለውን ገንዘብ በማዋጣትና በሀሳብና በዕውቀት በመደገፍ አገራዊ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል::
በተለይም በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግ የማስከበር ዘመቻ በመደገፍ ያሳየው አገራዊ ተቆርቋሪነትና አለሁ ባይነት በእጅጉ የሚያስመሰግነው ነው:: አሸባሪው ህወሓት ራሱ ቆስቁሶ በጋየበት የሕግ የበላይነትና የህልውና ዘመቻ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም በአንጸባራቂ ድል ቢጠናቀቅም በውጭ አገራት የሚገኙ የቡድኑ ርዝራዦች የከፈቱት ሀሰተኛ የሚዲያና የኮሚኒኬሽን ዘመቻ ግን መጠነ ሰፊ ነው:: በዚህ የሀሰት ፕሮፓጋንዳም ኢትዮጵያ በውጭው ዓለም ስሟ እንዲጎድፍና ኢትዮጵያውያንም አንገታቸውን እንዲደፉ እስከዛሬም ያላበራ ውርጅብኝ እየደረሰባቸው ይገኛል:: ከዚያም አልፎ ኢትዮጵያ ያልተረጋጋችና ለመፍረስ የቀረበች አገር እንደሆነች አድርጎ በመሳል የውጭ ኃይል ጣልቃ እንዲገባ ግፊትም እየተደረገ ይገኛል::
የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦች የሚያደርጉት አገር የማጠልሸትና ሉዓላዊነትን ለባዕዳን ኃይሎች አሳልፎ የመስጠት ክህደት ያሳመማቸው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀፎው እንደተነካበበት ንብ ከዳርእስከዳር ተንቀሳቅሰዋል:: በዋሽንግተን፣ በጣሊያን፣ በካናዳ ኦታዋ፣ ሞንትሪያል፣ በቶሮንቶ፣ በክችነር፣ በሎንዶን ኦንታሪዮ፣ በኤድመንተን፣ በሊትብሪጅ እና በካልጋሪ ከተሞች ሰፊ የተቃውሞ ሰልፎችን በማድረግ ለአገራችን ያላቸውን ቀናኢነት አሳይተዋል:: በተለይም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግሥት የወሰደውን የሕግ ማስከበር እርምጃ የሉዓላዊነት ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ የአሸባሪው ቡድን ደጋፊዎችና የእነሱ ጥቅም ተጋሪዎች ባናፈሱት ፕሮፓጋንዳ አንዳንድ ዓለምአቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት እውነታውን ባላገናዘበ መልኩ እየወሰዱት ያለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም እውነታውን ለዓለም ማህበረሰብ ለማስረዳት እያደረጉት ያለው ጥረት በታሪክ መዝገብ የሚሰፍር ነው::
በተለያዩ የዓለም ክፍል የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ መፈክሮችን በማሰማት የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ከመግባትና የማይገባ ጫና ከመፍጠር እንዲቆጠቡ አሳስበዋል:: እነዚህ የኢትዮጵያ ድንቅ ልጆች በተለይ አሜሪካ የጣለችው የባለሥልጣናት ዝውውር ገደብ እውነታ ላይ ያልተመሰረተና የአሜሪካንንና የኢትዮጵያን የቆየ ግንኙነት ያላገናዘበ መሆኑን በመግለጽ ተቃውሟቸውን እያሰሙ ይገኛሉ:: ለሚኖሩበት ግዛት አስተዳዳሪዎችም አሜሪካ የወሰደችው አቋም የተሳሳተ መሆኑን በማስረዳት እና አሜሪካ ከገባችበት ስህተት መንገድ እንድትመለስ በማስገንዘብ የበኩላቸውን የዜግነት ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ይገኛሉ::
ከዚሁ ጎን ለጎንም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ በመግዛት በልማቱም የማይናቅ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ:: በተለይም ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዲያስፖራው ለህዳሴው ግድብ ያለው ተቆርቋሪነትና ድጋፍ በእጅጉ ጨምሮ ታይቷል:: በዘንድሮው ዓመት ዘጠኝ ወራት ብቻ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለህዳሴ ግድብ ከሦስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል::
ለአገሩ ቀናኢ የሆነው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በሰላም እንዲጠናቀቅና አገሪቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛል:: ‹‹ኢትዮጵያ ምረጪ›› የሚል መርህ በመቅረጽም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገር ቤት ያሉ ቤተሰቦቻቸው በምርጫው እንዲሳተፉ የሚያነቃቁበት መርሃ ግብር ሲሆን በዚህ የቅስቀሳ ዘመቻም ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ቅድሚያ በመስጠት የሚፈልጉትን የፖለቲካ ፓርቲ ሰላማዊ በሆነ ሂደት ብቻ እንዲመርጡ የሚያስችሉ መልዕክቶች እየተላለፉበት ይገኛሉ::
በአጠቃላይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ከሀሰተኛ ፐሮፓጋንዳ ለመታደግ እያደረጉት ያለው ጥረት የሚበረታታና በሰው አገር ከኑሮ ጋር ግብግብ እየገጠሙም ቢሆን ለአገራቸው ቅድሚያ እንደሚሰጡ ያሳየ አኩሪ ገድል ነው:: ያለምንም የብሔርና የሃይማኖት ልዩነትም በተለያዩ የዓለም አገራት ያደረጉት ሉዓላዊነትን የማስከበር ተግባርም በታሪክ የሚመዘገብ አኩሪ ተግባር ነው:: ከዚሁ ጎን ለጎንም ለህዳሴው ግድብ እያደረጉት ያለው ድጋፍ በብልጽግና ጎዳና ላይ ለምትገኘው ኢትዮጵያ ትልቅ ስንቅ መሆን ችሏል:: ይህን የዲያስፖራውን ገድል ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ዕውቅና የሚሰጡትና በታሪክ መዝገብ ላይም የሚያሰፍሩት ታላቅ አገራዊ አሻራ ነው!
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2013