አዲስ አበባ ፡- ወጣቱ በመቃቃርና በመናቆር የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ ተገንዝቦ በመቻቻል፣ በፍቅር፣ በመተባበርና በመደመር መንፈስ ለሀገር አንድነት፤ሰላምና ልማት መቆም እንዳለበት የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አምባሳደር ዓለማየሁ ሸንቁጥ አስታወቁ።ፋሽስት ጣልያን የካቲት 12 ቀን 1929 ዓመተ ምህረት በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸመው የግፍ ጭፍጨፋ የፈጸመችበት የየካቲት 12 ቀን የሰማዕታት መታሰቢያ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ታስቦ ይውላል፡፡
አምባሳደር ዓለማየሁ ሸንቁጥ ዛሬ የካቲት 12 የሚታሰበውን የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን አስመልክቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያን ማሳደግና ማበልፀግ የሚችለውና ዜጎች ከድህነት የሚላቀቁት ከለውጡ ጋር በመራመድና ተግቶ በመስራት ነው ።ለዚህም ወጣቱ በመቃቃርና በመናቆር የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ ተገንዝቦ በመቻቻል፣ በፍቅር፣ በመተባበርና በመደመር መንፈስ ለሀገር አንድነት፤ሰላምና ልማት መቆም ይኖርበታል።
የዛሬ 83 ዓመት የፋሽስት ጣሊያን ጦር አዛዥ ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚኒ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ሰብስቦ ንግግር እያደረገ ባለበት ወቅት አብረሃም ደቦጭና ሞገስ አስግዶም የተባሉት ወጣቶች በወረወሯቸው ቦምቦች ግራዚያኒ መቁሰሉን ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስታውሰው፣ ይህን ተከትሎ፣ ፋሽስቶቹ በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸሙት ለሦስት ቀናት በዘለቀ የግፍ ጭፍጨፋ የ30ሺ የአዲስ አበባና አካባቢዋ ነዋሪዎች ሕይወት መጥፋቱን ገልጸዋል፡፡ ይህን አሳዛኝ ሁነት ትከትሎም የኢትዮጵያ ሰማዕታት ቀን በየዓመቱ የካቲት 12 ቀን እንደሚዘከር አስታውቀዋል፡፡ ዓርበኞች በባዶ እግር ፣ በቆንጥር በዱር በገደሉ በመኖር በሽምቅ ውጊያ ሀገራቸውን ነፃ ለማውጣት ለአምስት ዓመታት መታገላቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰማዕታት ሲታወሱ ወጣቱ በሀገሪቱ እውን የሆነውን ለውጥ ለማስቀጠል መስራት እንዳለበት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰው፣ ‹‹ወጣቱ ድህነትን ተዋግቶና በልማት ላይ ዘምቶ ተባብሮና ተከባብሮ ራሱንም ሀገሩን ከድህነት ነፃ ለማውጣት መጣር ይኖርበታል » ብለዋል።
አባት ዓርበኞች በሽምቅ ጦርነት ጠላትን መረጋጋት አሳጥተው ሲዋጉ በዘርና በመንደር ሳይከፋፈሉ በአንድ መንፈስ ሆነው እንደነበር ተናግረው፣ በዚህም ጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው ሀገራቸውን መጠበቃቸውን ተናግረዋል፡ ፡ወጣቱ በመናቆር የሚመጣው ደም መፋሰስና ሕይወት ማጥፋት መሆኑን በመረዳት ለሰላም ዘብ መቆም ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል ።
የካቲት 12 ቀን ግራዝኒያ በቤተመንግስት የልጁን ልደት ለማክበር ህዝብ ሰብስቦ ንግግር ሲያደርግ ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ በወረወሩበት ቦንብ ቆስሎ በሰጠው ትዕዛዝ በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጭፍጨፋ ተፈጽሟል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2011
ኃይለማርያም ወንድሙ