ጨፌ ኦሮሚያ በሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን የሚፈታ በጥናት የታገዘ የተለያዩ ማሻሻያዎችን ያካተተ አዋጅ ሰሞኑን አፅድቋል፡፡ በዚህና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሣ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
አዲስ ዘመን፣ ስለ ማሻሻያው(ሪፎርም) ቢገልጹልን?
ዶክተር ቢቂላ፣ ባለፉት ዓመታት የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በስፋት በህዝብ ይነሱ ነበር፡፡ የህዝቡ ቅሬታ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ቅራኔ ፈጥሯል፡፡ በሀገሪቷ ሁለንተናዊ ለውጥ እንዲመጣም ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው፡፡ መንግሥትም ለነበሩት ጉድለቶች ይቅርታ ጠይቆ በፖለቲካው ለውጥ አምጥቷል፡፡ የለውጥ ሪፎርሙም በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ሳይቀር ተወድሷል፡፡ በፖለቲካው የተመዘገበው ለውጥ በህዝብ አስተዳደር ማሻሻያ መደገፍ አለበት፡፡ ህዝብ በፖለቲካው ያገኘውን እፎይታ በመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥም በተመሳሳይ ይጠብቃል፡፡
በዚሁ መሰረት ለህዝብ ቅሬታ መንስኤ የሆኑ የመልካም አስተዳደርና የአገልግሎት አሰጣጥ ውስኑነቶችና ችግሮች ምን እንደነበሩ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ጥልቅ ጥናት እንዲካድ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት በፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ አማካኝነት ጥናቱ ተካሂዷል፡፡
አዲስ ዘመን፣ የጥናቱ የትኩረት አቅጣጫዎች ምን ነበሩ?
ዶክተር ቢቂላ፣ ጥናቱ ትኩረት ያደረገው በክልሉ ለአገልግሎት ጥራት መጓደልና ለመልካም አስተዳደር ችግር መንስኤ የሆኑ የአደረጃጀት፣ የመንግሥት አሰራር ሥርዓት ችግሮች እንዲሁም የሰው ሀብት፣ የበጀትና የሌሎች ሀብቶች አጠቃቀም ውስኑነቶች ምንድንናቸው? በሚሉ ነጥቦች ላይ ሲሆን፣ በጥናቱ ላይ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጀምሮ እስከ አርሶ አደሩ ያካተተ 4ሺ250 ህብረተሰብ ተሳትፏል፡፡
በጥናቱ መሰረትም አሁን ያለው የመንግሥት አደረጃጀትና መዋቅር እንዲሁም የመንግሥት የአሰራር ሥርዓት ማለትም መንግሥት አገልግሎቱን የሚያስፈጽምበት አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ውስኑነት እንዳለበት፣ የሰው ሀብት አስተዳደሩም ችግር እንዳለበት እና በዚህም የተነሳ በመንግሥት የበጀትና ሀብት አጠቃቀም ላይ ብክነት እንዳለ ተለይቷል፡፡
የጥናት ግኝቱ ያሳየው የዚህ ሁሉ ችግር ድምር መንግሥት ቀላጣፋና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አሰራር እንዳልነበረው ነው፡፡ ካብኔውም በጥናት ግኝቱ ላይ ተመስርቶ አዲስ አደረጃጀትና መዋቅር በክልሉ ላይ እንዲጠና ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት አዲስ አወቃቀር እንዲጠና ተደርጓል፡፡ ስለዚህ በክልሉ አስፈጻሚ አካላትን መልሶ የማደራጀትና ኃላፊነትና ሥልጣናቸውን የመወሰን አዋጅ በጥናት የተደገፈና የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታት የታቀደ ነው ማለት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፣ ስለ ቀጣይ ሥራዎች ቢገልጹልን?
ዶክተር ቢቂላ፣ ጥናቱን መነሻ በማድረግ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥራ ይሠራል፡፡ ተበታትነው የነበሩ ተቋማት ወደአንድ ተሰብስበዋል፡፡ ለህብረተሰቡ ያስፈልጋሉ የሚባሉ አዳዲስ ተቋማት ተፈጥረዋል፡፡ አንድ አይነት ሥራ ሲሠሩ የነበሩ ለበጀት፣ ለሰው ሀብት፣ ለተሽከርካሪና ለሌሎችም አጠቃቀም ብክነት ምክንያት የነበሩ የተንዛዙ ተቋማት ወደ አንድ እንዲመጡ ተደርጓል፡፡ ለአርሶ አደሩ፣ ለአርብቶ አደሩ፣ ለከተማ ነዋሪው በአጠቃላይ ለህብረተሰቡ የሚጠቅሙ አዳዲስ ተቋማት ተፈጥረዋል፡፡
በዚህ አደረጃጀት ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ የሚታይበትና የመንግሥት ተደራሽነት ላይ መሰረት ያደረጉ ሥራዎች ይሠራሉ፡፡ መንግሥት ከዚህ ቀደም በገጠርና በከተማ ቀበሌዎች ውስጥ በየእለቱ አገልግሎት የሚሰጥበት ተቋማዊ አደረጃጀት አልነበረውም፡፡ እንዲህ ያለውን የተደራሽነት ችግር በመፍታት ህዝብ በየእለቱ የሚፈልጋቸውን አገልግሎቶች እንዲያገኝ ለማስቻል ተቋማዊ አደረጃጀቱ አስፈልጓል፡፡
አዲስ ዘመን፣ የታችኛውን መዋቅር ለማጠናከር የተሰጠውን ትኩረት ቢያብራሩልን?
ዶክተር ቢቂላ፣ መንግሥት በታችኛው መዋቅር ላይ እግር የለውም የሚል አባባል አለ፡፡ ጥናቱ ያመላከተውም ይህንኑ ነው፡፡ ይህ ማለት በአርብቶ አደሩ፣ አርሶ አደሩና ከተማ ለሚኖረው የህብረተሰብ ክፍል አገልግሎት ሊያገኝባቸው የሚችሉ አደረጃጀቶች፣ መዋቅሮች፣ የሰው ሀብትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮች ከታች ያለው ህብረተሰብ ጋር ተደራሽ አይደሉም፡፡
ፖሊሲና እቅድ የሚያወጡ በክልል ደረጃ አሉ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ በሚኖርበት ወረዳና ቀበሌ ግን በክልል ደረጃ ያሉት አደረጃጀቶች የሉም፡፡ ስለዚህ እላይ ያለው ወረቀት ላይ የተመሰረተ ሥራ ነው የሚሠራው ማለት ነው፡፡ አርሶ አደሩ የሚደገፍበት መዋቅርና አሰራር በሚኖርበት አካባቢ ማግኘት አለበት፡፡ ትምህርት፣ ጤናና ሌሎችንም ማህበራዊ አገልግሎቶች፣ ከተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም እንዲሁም ከሴቶችና ወጣቶች መብትና ተጠቃሚነት በተለይም ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር የተያያዙ አደረጃጀቶች፣ አሰራርና የሰው ኃይል በገጠርና በከተማ መኖር ባለመቻላቸው ህብረተሰቡ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ የአዲሱ አደረጃጀት ትኩረት ይሄን ለማስቀረት ያግዛል፡፡
አዲስ ዘመን፣ ህዝብ በዋናነት ያነሳው የነበረው ቅሬታ ምን ነበር?
ዶክተር ቢቂላ፣ ከአደረጃጀት ጋር የሚነሳው ቅሬታ የተደራሽነት ችግር ነው፡፡ በየቄያችን ደርሳችሁ በሚገባ እየደገፋችሁን አይደለም፡፡ ግብርናን በተመለከተ የሚያነሱት የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ፣ የግብአት አቅርቦት ሲሆን፣ የተቋማት የቅንጅት ችግርም በግብርና ሥራቸው ላይ እንቅፋት እየሆነባቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ባለሙያዎች ባለመቀናጀታቸውና ባለመናበባቸው ለግብርናቸው የሚያግዝ ነገር ሳያገኙ እንደሚቀሩ ይገልጻሉ፡፡ ይሄ ከክልል እስከ ቀበሌ በሚዘረጋው አደረጃጀት ይፈታል፡፡ በሥነምግባር የታነጹና የሙያ ክህሎት ያላቸው አገልጋይነትን የተላበሱ የአርሶ አደሩን ችግር ለመፍታት ዝግጁነት ያላቸው ባለሙያዎች በመመደብ የህብረተሰቡን ቅሬታ ለመፍታት ዝግጅት ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፣ የተዘረጋውን አሰራር ተከታትሎ ውጤት ላይ ለማድረስ ምን የመከታተያ ስልት ተቀይሷል?
ዶክተር ቢቂላ፣ አዋጁ ከፀደቀ ገና የቀናት እድሜ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እያንዳንዱ በአዋጁ ላይ የተጠቀሱ ተቋማት ስትራቴጂያዊ አመራር መስጠት በሚያስችል መልኩ የውስጥ አደረጃጀታቸውን ይሠራሉ፡፡ አደረጃጀታቸውም ውስን የሆነ በጀትና የሰው ሀብትን በተቀናጀ በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ለማከናወን የሚያሳይ መሆን አለበት፡፡ በተለይ ለነዳጅ፣ ለአበልና አላግባብ ለሆኑ ወጪዎች የሚመደብ ገንዘብን ማስቀረት ይኖርባቸዋል፡፡
አደረጃጀቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ የሰው ኃይል ምደባ ይከናወናል፡፡ የሰው ኃይል ምደባው ከተከናወነ በኋላ የኦሮሚያ ፐብሊክ ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮና ሌሎች ተቋማት በጋራ ሆነው በጥናቱ የተመላከቱት በተለይ በአገልግሎት የህዝብ እርካታ እና ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው አመኔታን በተመለከተ የድጋፍና የግብረ መልስ መከታተያ ስልት ዘርግተዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት የነበሩ ግኝቶች ላይ በመመስረት የህዝብ ጥያቄዎች መፈታታቸውና አለመፈታታቸው ክትትል ይደረጋል፡፡ በዚህ ወር ግን በሰው ኃይል ምደባና ተቋማትን መልሶ የማደራጀት ሥራ ነው የሚከናወነው፡፡
አዲስ ዘመን፣ ከትግበራው በኋላ ህዝብ ቅሬታ ቢኖረው በምን አግባብ ይፈታል?
ዶክተር ቢቂላ፣ ከዚህ ቀደም ህዝቡ ቅሬታ ሲያቀርብ ቀልጣፋና ተደራሽ ሥርዓት አልነበረም፡፡በዚህ በኩል ያየነው የመንግሥት ተቋማት ለህዝባቸው ክፍት መሆን አለባቸው፡፡ አሰራራቸወም ግልጽ መሆን አለበት። ግብረመልስ የሚቀበሉበት ሥርዓት መዘርጋት ይጠበ ቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ ሁሉም ተቋማት ዕቅዳቸውን፣ አፈጻፀማቸውንና በሥራ ያጋጠማቸውን ችግር ከነመፍትሄው ለህዝብ የሚያቀርቡበት መድረክ ያመቻቻሉ፡፡ በዚህ መልኩ ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ ለመንግሥት ሪፖርት ማቅረብ አይችሉም፡፡
በሪፖርታቸው ስንት የህዝብ መድረክ እንዳዘጋጁ፣ ከምን ያህል የህብረተሰብ ክፍል ጋር ውይይት እንዳካሔዱ፣ በውይይቱ የተነሱ ዋና ዋና ነጥቦች፣ የተነሱትን ነጥቦች ለማሻሻል በግብአትነት መጠቀማቸውን ማካተት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህን የሚከታተል በቢሮው አንድ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሟል፡፡ማንኛውም ተቋም ቢያንስ በሦስት ወር አንዴ ሪፖርት ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ መልኩ ካልተከናወነ ሥራ አልተሠራም ማለት ነው የሚል አቅጣጫ ነው የተቀመጠው፡፡
አዲስ ዘመን፣ ነባር አመራርን በአዲስ መተካት ብቻውን ለውጥ አያመጣም የሚሉ አስተያየቶች ይቀርባሉና በዚህ ላይ ያለዎትን ሀሳብ ቢሰጡን?
ዶክተር ቢቂላ፣ ባለፉት ሦስት ዓመታት የህዝብ ቅሬታ መነሻ የአመራር የመሪነት ጉድለት ነው፡፡ አሁንም በየደረጃው ባሉ የአመራር ምደባ ላይ ውስንነቶች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ውስንነት አለበት የምንለው በእስካሁን አሰራር ስትራቴጂክ በሆነ መንገድ አመራር መርጠን፣ አሠልጥነን፣ አብቅተን ያዘጋጀነው አመራር ስለሌለን ነው፡፡ይሄ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ወደፊትም በክልሉ ይታያል፡፡
ህብረተሰቡ በሚፈልገው አገልግሎት ልክ ችግሮችን እየፈታ የሚሄድ አቅምና የክህሎት ውስንነት በተለይ ደግሞ የአመለካከት ችግር ስላለ ነው አመራሮችን ቶሎ ቶሎ የማስተካከል ሥራ የሚሠራው፡፡የመዋቅር ክለሳው እና የአመራር ምደባው በአንድ ላይ ሲከናወን ይስተካከላል ብለን እናስባለን፡፡በክልላችን ምን አይነት የመሪነት ሚና ያላቸው እና ምን ያህል አመራሮች እንደሚያስፈልጉ ለመወሰን እንዲረዳ ምን መሠራት እንዳለበትም ታይቷል፡ ፡በዚህ ዓመት የሰው ሀብት ልማት ፖሊሲና ስትራቴጅ ይኖረናል፡፡ በስትራቴጅው መሰረት ከተሠራ በሚቀጥሉት ዓመታት አሁን ያሉት ችግሮች ይቀረፋሉ፡፡
አዲስ ዘመን፣ የአመራር ችግር አለ ሲሉ ምን ማለት ነው? ቢያብራሩልን?
ዶክተር ቢቂላ፣ የቁጥር ሳይሆን የጥራት ችግር ነው የነበረበት፡፡ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ 23ሺ ተሿሚዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ በአመራሩ ላይ ብዙ ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡ ክህሎታቸው፣ ሥነምግባራቸው፣ እያደገ የመጣውን የህዝብ አገልግሎት ፍላጎት ቶሎ ተገንዝቦ የመመለስ አቅማቸው ውሱን መሆን፣ ህብረተሰቡን ታች ወርዶ ከልብ የማገልገል ፍላጎት አለመኖር፣ ቶሎ ወደግል ፍላጎት ማድላት፣ ወደ ጎጠኝነት መሄድ፣ በክልሉ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦችንም በአንድ ላይ አቅፎ እኩል ያለማገልገል፣ በእቅድ ያለመመራት የመሳሰሉት ችግሮች ይነሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ በታችኛው መዋቅር ባለው አመራር ላይ በተደጋጋሚ ያጋጠመ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፣ በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮችን ከቦታ ወደ ቦታ የማዘዋወር ሁኔታ ነበር፣ ይህስ እንዴት ታይቷል?
ዶክተር ቢቂላ፣ ክልሉ አመራሮቹን በአቅም ግንባታና በተለያየ መንገድ በማብቃት ብዙ ወጭ አድርጎባቸዋል፡፡ አንድ አመራር አንድ ቦታ ጥፋት አጥፍቶ ሌላ ቦታ እንዲመደብ ሲደረግ ጥፋቱን ሌላ ቦታ እንዲደግመው ለማድረግ አይደለም፡፡ በነበረበት ውጤታማ ካልሆነ ውጤታማ በሚሆንበት ቦታ እንዲሠራ ይደረጋል፡፡ ከበጎ አስተሳሰብ ጭምር መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ በቅርቡም ከፍተኛ ቁጥር ያለው አመራር በክህሎቱ እንዲሠራ ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፣ በፈጻሚዎች በኩልም የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ይነሳል፡፡ ይሄስ እንዴት ተመልሷል?
ዶክተር ቢቂላ፣ ሠራተኛው ግዴታውን ብቻ እንዲወጣ ሳይሆን መብቱም አብሮ ይታያል፡፡ ውስንነቶች ቢኖሩም በተቻለ መጠን ድጋፍ አድርጓል፡፡ የክልሉ የመንግሥት ቢያንስ እያንዳንዱ ሠራተኛው የመኖሪያ ቤት እንዲኖረው በካብኔ ተወስኗል፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ለሚኖሩ ሠራተኞች ከቤት ወደ ስራ የሚያደርስ የትራንስፖርት አገልግሎት በማመቻቸት ድጋፍ አድርጓል፡፡ ከአንዴም ሦስት ጊዜ የደመወዝ ማሻሻያ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሁሉ ቢደረጉም ሠራተኛውን ያረካ ሥራ ተሠርቷል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ኢኮኖሚው ሲሻሻል ሠራተኛውን የሚበረታታበት እድል እንዳለ አብሮ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን፣ የአቅም ግንባታ ላይስ ምን ታስቧል?
ዶክተር ቢቂላ፣ የሠራተኛውን አቅም ለማጎልበትና የትምህርት ደረጃውን ለማሻሻል እስከ ሁለተኛ ዲግሪ የሚያስተምር «ኦሮሚያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ» ባቱ ከተማ ላይ ተቋቁሟል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ወደ 34 የሚሆኑ የርቀት ትምህርት መስጫና 16 ቦታዎች ላይም የቅዳሜና የዕሁድ የትምህርት ፕሮግራም አለው፡፡ እስካሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ ተምሯል፡፡ ከአምና ጀምሮ ደግሞ የክልሉ አመራር በተለያዩ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ ተደርጓል፡፡ ከ23 ሺ አመራሮች 44 በመቶ የሚሆኑት ዲፕሎማና ከዲፕሎከማ በታች በመሆናቸው በትምህርት ማብቃቱ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
አዲስ ዘመን፣ ከሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ጋር በተያያዘ ችግሮች ነበሩ፡፡ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶክተር ቢቂላ፣ ክልሉን ሲፈትኑት ከነበሩት ችግሮች አንዱ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ነው፡፡ራሱን ላጋለጠ በተቀመጠ የምህረት ጊዜ 6ሺ447 ሠራተኛ በሚመጥነው የሥራ ቦታ ተመድቧል፡፡በተለያየ መንገድ በተደረገ ጥቆማ ደግሞ ሰነድ እየተጣራ ነው፡፡ ክስም የተመሰረተባቸውና በእስር ላይም ያሉ አሉ፡፡ አዲስ ተቀጣሪ የትምህርት ማስረጃው የሚጣራበት አሰራር በመዘርገጋቱ ከዚህ በኋላ ችግሮች አይኖሩም።
አዲስ ዘመን፣ በመጨረሻ ከተጀመረው አዲስ አሰራር ምን ይጠበቃል?
ዶክተር ቢቂላ፣ የህዝብ እርካታን እያረጋገጡ በመሄድ የነበረውን ቅሬት ማስቀረት ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን፣ ለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡
ዶክተር ቢቂላ፣ እኔም አመሰግናለሁ
ለምለም መንግሥቱ