ግብርና ሚኒስቴር ቀድሞ መገኘት አይከፋም የሚለውን መርህ በመከተል ለ2013-2014 የምርት ዘመን ዝግጅቱን የጀመረው የ2012-2013 ዓ.ም ምርት ተሰብስቦ ጎተራ እንደገባ መሆኑን ያስታውሳል :: እያደገ የመጣውን የአርሶ አደሩንና ከፊል አርሶ አደሩን የግብአት ፍላጎት ለማሟላትም ቀድሞ መንቀሳቀሱ ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር ለመቀነስ እንደሚረዳም ሚኒስቴሩ ይገልጻል :: ሚኒስቴሩ ለበጀት አመቱ 26 ቢሊዮን ብር መመደቡንም አስታውቋል::
ተጠቃሚዎችም ቀድሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን መስክረዋል :: ካነጋገርናቸው አርሶአደሮች መካከል የሰሜን ሸዋ ዞን ነዋሪዋ አርሶ አደር በላይነሽ ሽብሩ ግብርና ሚኒስቴር ዘንድሮ የማዳበሪያ ፍላጎታቸውን በዞኑ ግብርና ቢሮ በኩል ቀድሞ መጠየቁንና አርሶ አደሩም ፍላጎቱን በወቅቱ ማሳወቁን ነግረውናል ። አርሶአደር በላይነሽ እንዳሉት ግብዓቱ በሕብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ተደራሽ ሆኗል ። ግብዓቱ በጊዜ መድረሱ በበልግ ለተከናወነው የግብርና ሥራና አሁን ለተጀመረው የመኸር ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል ። ግብአቶች ቀድመው መሰራጨት መጀመራቸው ከዚህ በፊት እንደ አፈር ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያለው ግብዓት ቀድሞ ባለመቅረቡ አርሶ አደሩ እርሻውን ከማረስና ቶሎ ወደ ዘር መዝራት ከመግባት ሲስተጓጎል የነበረበትን ሁኔታ ማስቀረት ችሏል።
የባሌ አካባቢ ነዋሪው አርሶ አደር አቶምሳ ገቢሳ እንዳሉትም ቀድሞ ፍላጎት መጠየቁ ፈጥኖ ግብዓቱን ለማቅረብ አስችሏል ። በተለይ የአፈር ማዳበሪያ ከማሳ እርሻ ዝግጅት ጀምሮ ጥቅም ላይ የሚውል እንደመሆኑ ዘንድሮ በሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ቀድሞ የቀረበላቸው መሆኑ በግላቸው የማሳ ዝግጅታቸውን በወቅቱ እንዲያደርጉ አግዟቸዋል ። የስርጭት ሂደቱ እንዲህ በጊዜ መከናወኑ ከዚህ በፊት ግብዓት ስርጭቱ በወቅቱ ባለመድረሱ በእርሻ ወቅት ይገጥሙ የነበሩ መንጠባጠቦችንና መጓተቶችን የሚያስቀር በመሆኑ መለመድ ይገባል ብለዋል።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ግብዓትና ግብይት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ተስፋም ይሄንኑ ነው ያረጋገጡት ። እርሳቸው እንደተናገሩት የአርሶ አደሩን የግብአት አቅርቦት ፍላጎት ሊያሟላ የሚችል አቅርቦት ማከናወን በየምርት ዘመኑ የሚጠበቀውን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አስፈላጊነቱ የጎላ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ መንግሥቱ፤በተያዘው በጀት ዓመት የምርት ዘመን የሦስት ሚሊዮን ኩንታል ግብዓት ፍላጎት ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል :: እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ እንደ አገር ከባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ከተጠቃሚ አርሶና ከፊል አርብቶ አደር ፍላጎት ሲሰበሰብ የቆየ ሲሆን፣ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረትም ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ክልሎች ፍላጎታቸውን ለዳይሬክቶሬቱ አሳውቀዋል ። ይሄ በክልሎች ለምርት ዘመኑ ጥቅም ላይ እንዲውል የቀረበው የማዳበሪያ ፍላጎትም 18 ሚሊዮን 169 ሺህ 216 ኩንታል ሲሆን፣ፍላጎትን መሠረት ባደረገ ግዥ ለመፈጸም ተችሏል :: ፍላጎት ካቀረቡት ክልሎች መካከልም ትግራይ ክልል አንዱ ሲሆን፣ስምንት መቶ ሺ ኩንታል የማዳበሪያ አቅርቦት ጠይቆ ተፈጻሚ ሆኗል :: በተጨማሪም 440 ሺ 169 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ቀድሞ ለክልሉ ቀርቧል::
በምርጥ ዘር አቅርቦት ላይም በተመሳሳይ በትኩረት ተሰርቷል :: በአገር ደረጃ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ዘር ለማቅረብ የታቀደ ሲሆን፣ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ የትግራይ ክልልን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ሥራ ተሰርቷል :: ክልሉ በጠየቀው መሠረት 23 ሺ 221 ኩንታል ምርጥ ዘር ቀርቦለታል ። ሆኖም ክልሉ ያለበትን ወቅታዊና ነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታ በማጤን ከጠየቀው በላይ 30 ሺ 800 ኩንታል የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው ምርጥ ዘሮች እንዲቀርቡለት የተወሰነበት ሁኔታ ነበር ። ከዚህም ውስጥ ስምንት ሺ አምስት መቶ 21 ነጥብ አምስት ኩንታል ምርጥ ዘር በህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ተደራሽ ሆኗል :: ግብአቶቹም በወቅቱ ነው በሥፍራው እንዲደርሱ የተደረገው :: ከተሰራጩት ግብአቶች በተለያዩ ድርጅቶች የተደረጉ ድጋፎች ይገኙባቸዋል :: ከግብዓት ስርጭቱ ጎን ለጎንም አርሶ አደሩ መደበኛ ልማቱን ማስቀጠልና ማልማት ይኖርበታል በሚል ስሜትና አስተሳሰብ ወደ ልማት እንዲገባ በተለየ መልኩ ያላሰለሰ ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል::ተጠናክሮም ይቀጥላል::
የአፈር ማዳበሪያ ፣ ምርጥ ዘርና ኬሚካል ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ማቅረብ ካልተቻለ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፤ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር መግቦ ማሳደር እንደማይቻልም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፤አርሶ አደሩ ባለው ጥቂት መሬት ላይ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ምርቱን ማሳደግ የግድ መሆኑን በመገንዘብ ጊዜውን በተለይም በዋናነት የግብርና ግብዓቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዳለበትም መክረዋል። ግብርና ሚኒስቴር በዚህ በኩል አርሶ አደሩ ግንዛቤ እንዲኖረው የሚያደርግ ትምህርት ከመስጠት ጀምሮ የግብርና ምርት ግብዓቶችን በወቅቱ በማቅረብ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል :: የዘንድሮው ግብዓት አቅርቦትና ስርጭት አፈጻጸም ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንደሆነም አቶ መንግስቱ አስረድተውናል።
‹‹ግብርና ለሀገራችን ክፍለ ኢኮኖሚ ዋናው መሰረት ነው››የሚሉት ዳይሬክተሩ ዘርፉን በግብዓትና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ግብርናን የማሻገር ስራ መሰራት ጊዜ የማይሰጠው ተግባር እንደሆነም አበክረው ይናገራሉ። እንዳከሉት ከዚህ አንፃር ለአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ስርጭቱ ከፌዴራል እስከ ክልል የነበሩ ባለድርሻ አካላትን በማቀናጀት ትኩረት ተሰጥቶት ሲሰራ ቆይቷል ። ተደራሽነቱም ትግራይ ክልልን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ውጤታማ ነበር ። ከስርጭት አኳያ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ተሰብስቦ አርሶ አደሩ እጅ እስኪገባ ድረስ እጅግ ውስብስብና ስራው ላይ ብዙ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት እንደ መሆኑ በጥንቃቄ ለማከናወን ጥረት ተደርጓል ። በሥርዓት ለማሰራጨት በየደረጃው ወቅቱን የጠበቀ መረጃ በመለዋወጥ፣ አሰራሮችን በማዘመን፣ በተፈለገው ወቅት እና ጊዜ በማድረስ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። የአርሶ አደሩን ፍላጎት ለማሟላት ብሎም ምርታማነትን ለመጨመር ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል ብለው ያምናሉ ። በስርጭቱ ወቅት ትግራይ ክልልን ጨምሮ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ ብዙ ፈታኝ አጋጣሚዎች ቢኖሩም ከበፊቱ የተሻለ ስራ ለመስራት መቻሉንም ነው ዳይሬክተሩ አቶ መንግስቱ የገለፁልን ። እንደ አቶ መንግስቱ በተለይ ደግሞ የማጓጓዣ ፣ የመጋዘን፣ የክፍያ፣ ሸራ ፈቺ፣ የማዳበሪያ ኪሎ መቀነስ እና የማዳበሪያ ዓይነትና መጠን ላይ ምንም ዓይነት ጉድለቶች ሳይኖሩ ለአርሶ አደሩ በተፈለገው ወቅት እና ጊዜ ማድረስ በመቻል መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ ቆይተዋል ። በአገሪቱ ባሉ ሁሉም ክልሎች የቀረበውና የተሰበሰበው የማዳበሪያና የምርጥ ዘር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የኬሚካል ግብዓት ፍላጎትም ነበር ። በዚህ መሰረት ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የተለያየ ዓይነትና ይዘት ያላቸው አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሺህ ሊትር ኬሚካል ፍላጎት ቀርቧል :: የኬሚካል ስርጭቱም በአፋር፣ በሶማሌና በአማራ ክልል ቆላማ አካባቢ እንዲሁም በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የተከናወነ ሲሆን፣ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ አኮብኩቦ የነበረውን የአንበጣ መንጋ ፈጥኖ ለመከላከል ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል::ከተለያዩ አቅጣጫዎች በነፋስ ኃይል የሚገባው አንበጣ ዝናብ በሚዘንብበት ወቅት እንቁላል በመጣል፣የሚበላ ካገኘም ይፈለፈልና ሰብል ምርት ላይ፣ በመኖ ዕፅዋትና በሌሎች ምርቶች ላይ ጉዳት ያደርሳል። የኬሚካል አቅርቦትና ስርጭቱ ይሄን ታሳቢ ባደረገ ሁኔታ ነው የተከናወነው::
የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አባዲ ግርማይ እንደሚናገሩትም በክልሉ ከትራንስፖርት አቅርቦት ጀምሮ ብዙ አስቸጋሪና ምቹ ሁኔታዎች ባይኖሩም የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በወቅቱ እንዲደርሱ የተለያየ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል ። የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ማከፋፈል ተግባራት የተጀመሩት በምርት ዘመኑ መግቢያ ሲሆን በዚሁ ሰሞን መጀመሪያ አካባቢ ለምርት ዘመኑ ለማስገባት ከታቀደው 800 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ውስጥ ክልሉ 222 ሺ ኩንታል ማዳበሪያ መረከብ ችሏል። ይሄንኑ ግብዓትም በሕብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የማድረግ ሥራ ሲሰራ ቆይቷል ። ምርጥ ዘርን በተመለከተ ከለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ ለማሰባሰብ ዕቅድ ተይዞ የነበረ መሆኑንም ዶክተር አባዲ አስታውሰዋል።
እንደገለፃቸው በእርግጥ ይሄ የዘገየበት ሁኔታ ነበር።ቢሆንም እንደሚያስታውሱት በዚያው አካባቢ ከታቀደው 97 ሺ ኩንታል 38 ሺ ኩንታል ወደ ትግራይ ክልል የገባበት ሁኔታ ሲኖር በገባበት ፍጥትነትም 70 በመቶ የሚሆነውን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ወደ አርሶ አደሩ የማድረስ ተግባር ተከናውኗል። በምርት ዘመኑ የትግራይ ክልልን ጨምሮ በ12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር ማሳ ላይ የሚሳተፉት አርሶ አደሮች 18 ሚሊዮን መሆናቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።ይገኛል ተብሎ የሚጠበቀውም ምርት 374 ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፣ይሄ የምርት ዘመኑ ሂደት የ10 ዓመቱ ዕቅድ የመጀመሪያ ምዕራፍ እንደመሆኑና ለስኬቱ በተለይ እንደ አገር ከተካሄደው ከግብዓት አቅርቦትና ስርጭት አንፃር የተሻለ ስኬት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2013