አንጋፋው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ከተመሰረተ፣ ግንቦት 13 ቀን 2013 ዓ.ም፣ 80 ዓመት ሞላው:: በአፍሪካ ውስጥ በሀገር በቀል ቋንቋ እየታተሙ ረጅም ዓመታትን ካስቆጠሩ ጋዜጦች መካከል ‹‹አዲስ ዘመን›› አንዱ ነው:: ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በስደት ከቆዩበት እንግሊዝ ከተመለሱ ከአንድ ወር በኋላ፣ ግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም፣ መታተም የጀመረው ጋዜጣው በተለያዩ ወቅቶች ብዙ ውጣ ውረዶችን አስተናግዶ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል::
በጋዜጣው የመጀመሪያው ዕትም (የግንቦት 30 ቀን 1933 ዓ.ም ዕትም) ላይ እንደሰፈረው፣ ጋዜጣው ‹‹አዲስ ዘመን›› የሚለውን ስያሜ ያገኘው ንጉሰ ነገሥቱ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ሲገቡ ከተናገሩት ንግግር ጋር በተያያዘ ነው::
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ከስደት ከቆዩበት እንግሊዝ ተመልሰው አዲስ አበባ ሲገቡ ለሕዝቡ ባደረጉት ንግግር ‹‹…ከማናቸውም አስቀድሞ ለሁላችሁም ልነግራችሁና ልትረዱት የምፈልገው ይህ ቀን ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የአዲስ ዘመን መክፈቻ መሆኑን ነው:: በዚህም በአዲስ ዘመን ሁላችን መፈፀም ያለብን አዲስ ስራ ይጀመራል …›› ብለው ስለነበር ጋዜጣውም ‹‹አዲስ ዘመን›› ተብሎ ተሰየመ::
‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ከምስረታው ጀምሮ ባለፉት 80 ዓመታት በርካታ ባለሙያዎችን አፍርቷል:: ከእነዚህ ባለሙያዎች መካከል በኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ላይ ስማቸው ገናና ሆኖ የሚጠቀሱት ቁጥራቸው ብዙ ነው:: ጋዜጣው በምስረታው ወቅት የነበሩበትን ችግሮች እያቃለለና ዘመናዊ የጋዜጣ መልክ እንዲኖረው ካደረጉ አንጋፋ ባለሙያዎች መካከል የጋዜጣው የመጀመሪያ ዋና አዘጋጅ የነበሩትን የብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስን እና ጋዜጣው ዘመናዊ የጋዜጣ መልክና ቅርፅ (ይዘት) እንዲኖረው በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱትን የአቶ ነጋሽ ገብረማርያምን አበርክቶዎች በአጭሩ እንዘክራለን::
፩). ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ
ወልደጊዮርጊስ የተወለደው በ1887 ዓ.ም በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ተጉለት እና ቡልጋ አውራጃ፣ ሼሩ ወረዳ፣ ቆላ ጌበላ በሚባል ሥፍራ ነው:: አባቱ አቶ ወልደ ዮሐንስ ደባልቅ፤ እናቱ ወይዘሮ ያደንቁሻል መኩሪያ ይባላሉ። በ1892 ዓ.ም ፊደል መቁጠር ጀመረና በዓመቱ ዳዊትን ደግሞ ጨረሰ:: ዳዊትን ከልሶና የንባብ መጻሕፍትን ደጋግሞ ካጠናቀቀ በኋላ በ1898 ዓ.ም ከአባቱ ጋር ወደ አዲስ አበባ በመሄድ ከአቡነ ማቴዎስ የዲቁና ማዕረግ ተቀበለ::
ለትምህርት ብርቱ ፍላጎት የነበረው ወልደጊዮርጊስ ግን በዚህ ሳይወሰን ‹‹ዲቁናን ብቻ ሙያ አድርጌ መቅረት አልፈልግም›› ብሎ አለቃ ተስፋዬ ወደ’ሚባሉ የዜማ መምህር ዘንድ በመሄድ የተጉለት ዜማን መከለስ ጀመረ። አሁንም ልቡ አላረፈም ነበርና ሰምሳ ወደተባለ አካባቢ ሄዶ ከዜማው ሊቅ ከደብተራ በየነ ዘንድ ትምህርቱን ቀጠለ::
በ1905 ዓ.ም ወልደዮሐንስ ወደ ወረኢሉ ሄዶ ከአለቃ ጸጋ ዘንድ ዜማን፣ ድጓንና ጾመ ድጓን ተማረ:: እየዘረጉ ዘለቁ። የቃል ትምህርቱን (አርያምን፣ ሠልስት ክስተትንና ዋዜማ ምዕራፍን)ም ሙሉ በሙሉ ፈፀመ:: የቃልና የዜማ ትምህርቱንን እንዳጠናቀቀ ለስምንት ወራት ያህል አለቃ ሚካኤል ከሚባሉ ሊቅ ዘንድ ቅኔ ተቀኘ። ቀጥሎም ወደ ጎንደር በማቅናት ለአምስት ዓመታት ያህል ከአለቃ ኅሩይ ፈንታ ጋር የመጻሕፍትን ትርጓሜ በተለይ ደግሞ ሐዲስን ሲማር ቆየ።
አለቃ ኅሩይ በዘመኑ የታወቁ የዜማ ሊቅ በመሆናቸው በልዑል አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) በ1916 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ሲታዘዙ ወጣቱን ደቀ መዝሙራቸውን ወልደ ጊዮርጊስ ወልደዮሐንስንም አስከትለው መጡ። ይህ አጋጣሚም ወልደጊዮርጊስ ከአልጋ ወራሹ ጋር እንዲተዋወቅ አደ ረገው::
ወልደጊዮርጊስ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ የግዕዝ መፃሕፍትን ወደ አማርኛ የመተርጎም ሥራ ጀመረ። በ1916 ዓ.ም የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሲተከል ሃይማኖተ አበው እንዲያነብ ተሰጠው። በመቀጠል መጽሐፈ ቄርሎስን እንዲተረጉሙ ከታዘዙ ከሰባት ሊቃውንት ጋር በጽሑፍና በትርጉም በማገዝ አገልግሏል። ይህ ሥራውም ወልደጊዮርጊስ በአልጋወራሹ ዘንድ የበለጠ እንዲታወቅ አደረገው።
ወልደጊዮርጊስ በቋንቋና በጽሑፍ ችሎታው ‹‹የብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ ምክትል አዘጋጅ እንዲሁም ‹‹ከሳቴ ብርሃን ለልበ ጠቢባን›› የተባለ መጽሔት የአማርኛ አቀናባሪ (አርታኢ) በመሆን አገልግሏል። በወቅቱም ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለነፃነት፣ ስለ አንድነት እና ስለ ኅብረት የሚገልጹ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ያሰራጭ ነበር።
ቀደም ሲል በ‹‹ብርሃንና ሰላም›› ጋዜጣ እና በ ‹‹ከሳቴ ብርሃን ለልበ ጠቢባን›› መጽሔት ላይ በጋዜጠኛነት የሰሩት ወልደጊዮርጊስ፤ ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ከኢትዮጵያ ምድር ከተባረረና ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አዲስ አበባ ከገቡ ከአንድ ወር በኋላ የተቋቋመው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኑ:: በላቀ የቋንቋ ችሎታቸውና የሥራ ትጋታቸውም የ‹‹ብላታ››ነት ማዕረግን አገኙ::
ብላታ ወልደጊዮርጊስ ጽሑፎችን በመጻፍ፣ የአርትኦት ስራ በመስራትና የሕትመቱን ሂደት በመከታተል አገልግለዋል። ጋዜጣው ዕለታዊ እንዲሆንም የእርሳቸው የለውጥ ፍላጎትና ተጽዕኖ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወተ ይነገራል። በ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ታሪክ እንደ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ለረጅም ዘመናት በዋና አዘጋጅነት ያገለገለ የለም:: ከ1933 እስከ 1953 ዓ.ም ለሃያ አመታት (የጋዜጣውን 1/4ኛ እድሜ) ያህል የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ በመሆን ሰርተዋል።
በእነዚህ ዋና አዘጋጅ ሆነው በሰሩባቸው 20 አመታት ውስጥ ጋዜጣው እንዲስፋፋና ሙያው እንዲለመድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርገዋል:: ከዚህ በተጨማሪም ‹‹ሰንደቅ ዓላማችን›› እና ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› የተሰኙት ጋዜጦች አዘጋጅ ሆነውም ሰርተዋል:: አንጋፋው ዋና አዘጋጅ ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች አባት›› በመባል የክብር ማዕረግ አግኝተዋል።
በ1954 ዓ.ም. የማስታወቂያ ሚኒስቴር አማካሪ ሆነው ከተሾሙ በኋላ ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት፣ በተለይ ለጋዜጠኝነት መሻሻል፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። ስለሀገር ብልፅግና፣ ስለፍቅርና ስለሥነ- ምግባር የሚሰብኩ ከ24 በላይ መጻሕፍትን ጽፈዋል። ለአብነት ያህልም ‹‹ሥነ ምግባር››፣ ‹‹የወንድ ልጅ ኩራት ለሀገር ሞት››፣ ‹‹ሙያ በልብ››፣ ‹‹ጀግና ሰው ተጋዳይ››፣ ‹‹ክብረ ነገሥት››፣ ‹‹ገፀ በረከት››፣ ‹‹አንተ ሰው››፣ ‹‹አምሐ ፍቅር ወሰላም ታሪክ እና ሥራ››፣ ‹‹የዓለም ጠባይ››፣ ‹‹ከሥራ በኋላ›› የሚሉት ስራዎቻቸው ይጠቀሳሉ::
የዜማና የቅኔ ሊቅ የነበሩት፣ በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱትና የአንጋፋው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የመጀመሪያው ዋና አዘጋጅ ሆነው ለ20 ዓመታት ያህል ያገለገሉት ብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ በ1974 ዓ.ም አርፈው ስርዓተ ቀብራቸው በደብረ ሊባኖስ ተፈፅሟል::
፪). ነጋሽ ገብረማርያም
ነጋሽ የተወለደው በ1917 ዓ.ም አርሲ ውስጥ ነው:: ታላቅ ወንድሙ አቶ አሰፋ ገብረማርያም በስራ ምክንያት ወደ ተለያዩ ስፍራዎች ሲዘዋወሩ እርሱም አብሮ ይንቀሳቀስ ነበር:: በመጨረሻም መዳረሻውን አዲስ አበባ አድርጎ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባ::
በትምህርቱ ጎበዝ የነበረው ነጋሽ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላም ብሪቲሽ ካውንስል (British Council) ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ከፍቶ ስለነበር እዚያ ገብቶ ለሁለት ዓመታት ተምሮ በዲፕሎማ ተመረቀ።
ከዚያም ወደ ጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተመድቦ ለአንድ ዓመት ያህል አስተማረ:: ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ጊዜ ደግሞ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተማሪዎችን ፈትኖ ከሚቀበልበት ቀን ጋር ተገጣጠመ:: ፈተናውን ተፈተነ፤ አለፈ:: በተቋሙም ለሦስት ዓመታ ያህል ተምሮ ሰርቲፊኬት ተቀበለ::
ብዙም ሳይቆይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስለተከፈተ ዩኒቨርሲቲውን ተቀላቀለ:: ለሁለት ዓመታት ያህል እንደተማረ በወቅቱ በወደብ አስተዳደር (Port Administration) ትምህርት የሰለጠነ የተማረ የሰው ኃይል ይፈለግ ስለነበር የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን አጠናቀቀ:: በተግባርም ጅቡቲ፣ ምፅዋ እና ኤደን ባህረ ሰላጤን በመርከብ እየተዘዋወረ የስራውን ሁኔታ ተመለከተ። ሁሉንም ካጠናቀቀ በኋላም ሰርተፊኬት ተቀበለ:: ይሁን እንጂ የስራው አካባቢ ሞቃታማ ስለነበር በስራው ሳይቀጥል ቀረ:: በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለት ዓመታት ሰርቷል::
በመቀጠልም አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ የመረጃ አገልግሎት ቢሮ የቤተ መጽሐፍትና የትርጉም ሰራተኛ በመሆን ተቀጠረ:: በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥም ለሦስት ዓመታት ያህል እንደሰራ የስራ ትጋቱንና አመርቂ አፈፃፀሙን የተገነዘቡት አሜሪካዊ አለቃው «አሜሪካ አገር ለትምህርት እንላክህ ወይንስ ደመወዝ እንጨምርልህ?» የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። ነጋሽም ወደ አሜሪካ ለትምህርት መሄድን መረጠ። በዚህም መሰረትም እ.አ.አ በ1955 ወደ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ አቀና።
ነጋሽ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝቶ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ:: ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ የተቀጠረው የእንግሊዝኛው ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ (The Ethiopian Herald)›› ጋዜጣ ላይ ነበር:: የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ብላታ ግርማቸው ወልደኃዋርያት «… መሻሻል የሚገባው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለሆነ ለምን ወደዚያ አትሄድም? …» የሚል ጥያቄ አቀረቡለት:: ነጋሽም በሚኒስትሩ ሃሳብ ተስማምቶ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ መስራት ጀመ ረ::
የጋዜጣው ስራ ከምስረታው ጀምሮ በልምድና በፍላጎት ብቻ ይከናወን ነበር:: ሰራተኞቹ (ጸሐፊዎቹ) የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩ እንጂ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርትና ስልጠና ያላቸው አልነበሩም:: ታዲያ ይህን አሰራር በመለወጥ የጋዜጣው አቀራረብና ይዘት የሙያ መርሁን የተከተለ ማድረግ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርትን በምዕራቡ ዓለም ተምረው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰው ነጋሽ ገብረማርያም ይጠበቅ ነበር::
በሙያው የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ባለዲግሪ የሆነው ነጋሽ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነቱን ኃላፊነት «የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት አባት» ተብለው ከሚታወቁት ከብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ በመረከብ ወደ አሜሪካ አቅንተው የተማሩትን ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርት ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረታቸውን ጀመሩ:: ክብደት ያላቸውና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜናዎች አጠር ተደርገው የመጀመሪያ ገፅ ላይ እንዲሆኑ፤ ጋዜጣው አቋሙን የሚገልፅበትና ‹‹ርዕሰ አንቀጽ›› የሚል የአማርኛ ስያሜ ያለው ክፍል እንዲኖረው፤ የጋዜጣው ተቋማዊ አድራሻና የአዘጋጁ ስም በጋዜጣው ላይ እንዲገለፅ፤ የጸሐፊዎች ስም (Byline) ከጽሑፉ ርዕስ ቀጥሎ እንዲሰፍር እንዲሁም ጋዜጣው ተጨማሪ አምዶች እንዲኖሩት አደ ረጉ።
ቀደም ሲል በጋዜጣው ላይ ተቀላቅለው ይፃፉ የነበሩት ሃቅ/እውነት (Fact) እና የግል አስተያየት (Opinion) ልዩነት እንዳላቸው በማሳየት፤ ሁለቱ የጽሑፍ ዓይነቶች የየራሳቸው የአጻጻፍ ደንብና ቦታ እንዲቀመጥላቸውም አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ማስታወቂያዎችም ለማስታወቂያ በተመደቡ ገፆች ላይ እንዲወጡ አድርገዋል:: በአጠቃላይ አቶ ነጋሽ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀደም ሲል ከነበረው የይዘትና የአቀራረብ ቁመና በብዙ መልኩ እንዲለወጥና እንዲሻሻል አድርገውታል። የጋዜጣው ለውጥም በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የእለት ጋዜጣው ወደ ማተሚያ ቤት ከተላከ በኋላ አቶ ነጋሽ በቢሮ ውስጥ በሰቀሉት ጥቁር ሰሌዳ ላይ በጠመኔ እየጻፉ ለወቅቱ ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነት ስልጠና ይሰጡ ነበር። ይህ በራሳቸው ተነሳሽነት ያከናወኑት ተግባራቸውም ተወደደ። ጋዜጠኞች በየእለት ስራቸው የሚገጥሟቸውን ሙያዊ ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ሲጠይቋቸው እርሳቸውም ካላቸው ልምድና በውጭ አገር ከቀሰሙት እውቀት በመነሳት ጥያቄዎቻቸውን ይመልሳሉ፤ ዘመናዊ የአጻጻፍ ስልትን ጨምሮ ሌሎች የሙያውን ሕግጋትንም ያስተምሩ ነበር።
የጋዜጣው የፊት ገፅ የንጉሰ ነገሥቱ ምስልና እርሳቸውን የተመለከቱ ጉዳዮች ብቻ በዝርዝር የሚስተናገዱበት የጋዜጣው ክፍል ነበር:: ምንም እንኳ ሹማምንቱ ባይወዱትም አቶ ነጋሽ ይህን አሰራር በመቀየር ጋዜጣው ዘመናዊ/ሙያዊ መንገድን እንዲከተል ጥረት ያደርጉ ነበር:: የአንባቢያን አስተያየቶች በጋዜጣው የውስጥ ገፆች ላይ ቦታ አግኝተው እንዲስተናገዱም ታግለዋል። ከብዙ ጥረት በኋላም አቶ ነጋሽ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የጀመሩት ለውጥ ጋዜጠኞችንም ሆነ የመንግሥት ሹማምንትን እያግባባ ሄደ::
አቶ ነጋሽ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነው ለሁለት ዓመታት ያህል ከሰሩ በኋላ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር እንዲያጠኑ ከተመረጡት ሰዎች መካከል አንዱ ሆነው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛወሩ። ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተመልሰው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን መስሪያ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስኪጅ ሆነው ሰርተዋል:: ዜና አገልግሎትን ከለቀቁ በኋላ ደግሞ ወደ አገር አስተዳደር ሚኒስቴርና የከተማ ልማት መስሪያ ቤት ተዛውረው አገልግለዋል::
አቶ ነጋሽ የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ሆነው በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈቱና ውሳኔ እየሰጡ የራሳቸውን ፕሮግራም ከማቅረብ አልቦዘኑም። «ከምሳ በኋላ» በተሰኘው ፕሮግራማቸው ደግሞ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በማይሰለች አቀራረብ በማቅረብ ሬዲዮ ጣቢያውን ተወዳጅ አድርገውት ነበር። አቶ ነጋሽ በልምድ ሙያውን ለተቀላቀሉ ጋዜጠኞች እውቀታቸውን እያካፈሉ በሂደት ጥሩ ጥሩ ጋዜጠኞች እንዲፈጠሩ ጥረት አድርገዋል።
ጡረታ ከወጡ በኋላም «ነጋዴው» የተሰኘ መጽሔት ሲቋቋም ከሌሎች የሙያው ሰዎች ጋር ሆነው ሰርተዋል:: «የድል አጥቢያ አርበኞች» እና ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› የተሰኙ ትያትሮችን ጽፈው ተውነዋል:: ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› የተሰኘው ትያትር በወቅቱ እጅግ ተወዳጅ ሆኖ ነበር:: «ሴተኛ አዳሪ» በሚል ርዕስ ልብወለድ መጽሐፍም አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል። በጋዜጠኝነትና የሕዝብ ግንኙነት ላይ ያተኮሩ ስልጠናዎችንም ሰጥተዋል::
የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ዘመናዊ መልክ እንዲይዝ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል:: ስርዓተ ቀብራቸውም ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳህሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013