የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከሰት በሰዎች ላይ ከፍተኛ የጤና፣ ማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አስከትሏል:: እስካሁን ድረስ ከ 174 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውም ተረጋግጧል:: ከ3 ሚሊዮን 700 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል:: የቫይረሱ ስርጭት ዕለት በዕለት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም በዓለም አቀፉ ማህረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል::
የክትባቱ መገኘት በተለይ ላደጉት አገራት በመጠኑም ቢሆን እፎይታን የሰጠ ቢሆንም ክትባቱን ለሁሉም አገራት የማዳረሱ ጥረት ግን አሁንም ገና ስለመሆኑ ይነገራል:: ክትባቱ በስፋት ባለተዳረሰባቸው ታዳጊ አገራትም ወረርሽኙ እያስከተለ ያለው ሰብአዊ ቀውስ እያየለ መጥቷል:: ክትባቱ በፍጥነት ለነዚህ አገራት ካልተዳረሰ ወረርሽኙ ከዚህም በላይ ሰብአዊ ቀውስ እንዳያስከትል ተሰግቷል::
የዚህ ሰብአዊ ቀውስ ሰለባ እየሆኑ ካሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴቶች ዋነኞቹ ሲሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች በበሽታው አልቀዋል:: ከዚህ በዘለለም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ደርሶባቸዋል:: በወረርሽኙ ምክንያት በርካታ መስሪያ ቤቶችና ፋብሪካዎች ሥራ በማቆማቸውና ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደቦች በመጣላቸው በርካታ ሴቶችም ከሥራ ገበታቸው ተፈናቅለው በቤታቸው ለመቆየት ተገደዋል:: በዚህም ምክንያት ጥቂት የማይባሉት ለፆታዊ ጥቃት ተጋልጣዋል:: ከዚህም ጋር በተያያዘ የዓለም ባንክ ሴቶችን ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱና ወደ ፆታ እኩልነት ጎዳና እንዲጓዙ ዋና ዋና እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ከሰሞኑ ማስጠንቀቁን ሲ ኤን ቢ ሲ ኒውስ አስታውቋል::
ዘገባው ሴቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ እና ወደ ፆታ እኩልነት ጎዳና እንዲመጡ ለማድረግ ከኮቪድ- 19 ወረርሽኝ በኋላ ወሳኝ እርምጃዎች መወሰድ እንዳለባቸው የዓለም ባንክ ማስጠንቀቁን ገልጿል:: ወረርሽኙ አሁን ያሉትን የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቶች ይበልጥ ያባባሰመሆኑንና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሴቶችን ወደ ፊት ለማራመድ ተጨማሪ ጥረቶች እንደሚያስፈልጉ የዓለም ባንክ ቡድን ዓለም አቀፍ ዳይሬክተር ካረን ግሮውን አርብ ዕለት ለ ሲ ኤን ቢ ሲ መናገራቸውንም አስታውቋል::
ወረርሽኙ በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተመሳሳይ ተፅዕኖ ያሳደረ ቢሆንም በወንዶችና በሴቶች ላይ የተለያዩ ተፅዕኖችን ማሳደሩንም ዳይሬክተሯ ማናገራቸውን ዘገባው ጠቅሶ፤ ምን እንኳን በኮቪድ- 19 ምክንያት የሚከሰተው የሞት መጠን በወንዶች ላይ ከፍተኛ ቢሆንም ወረርሽኙ በሴቶች ላይ ጉልህ ማህበራዊና ኢኮኖሚያ ተፅዕኖ ማሳደሩን ግሮውን ለአብነት ማንሳታቸውንም ጠቁሟል:: ይህም የሆነው እንደ እንግዳ ተቀባይነት እና ቱሪዝም ባሉ በኮቪድ-19 ከባድ ጉዳት በደረሰባቸው ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የሴቶች ያልተመጣጠነ ውክልና ከፊል ምክንያት መሆኑን ዳይሬክተሯ መናገራቸውን ዘገባው አመልክቷል::
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሁሌም ጥላ ያጠላ ወረርሽኝ ነው ተብሎ ቢወሰድም ስለ ማገገም ሲታሰብ ግን ጠንካራ ምላሾችን በቦታቸው ላይ ማኖር እንደሚጠይቅ ጋረን ግሮውን መናገራቸውንም ዘገባው ጠቁሟል:: ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትም ቢሆን የዓለም ባንክ ሴቶች ከወንዶች ጋር ያላቸውን የፆታ እኩልነት ለማረጋገጥ 150 ዓመት ሊወስድባቸው እንደሚችል መገመቱም በዘገባው የተመላከተ ሲሆን አሁን ወረርሽኙ የተፈጠረው የጤና ቀውስ ግን የጊዜ ሰሌዳውን እንዳራዘመው አብራርቷል::
እነዚህን ልዩነቶችን ለማጣጣም የክትባት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ዳይሬክተሯ ግሮውን መናገራቸውንና ይህም ሴቶች እድሎቻቸውን እንዲጠቀሙ ሰዓትና ሁኔታዎችን ማመቻቸትን እንደሚያጠቃልል ዘገባው አመልክቷል:: ከዚህ ባለፈ በወረርሽኙ በእጅጉ የተጎዱ ሴቶች በሁለት እግራቸው ቆመው እንዲሄዱና ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ ተጨማሪ የገንዘብ እና የእንክብካቤ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ዳይሬክተሯ አያይዘው መናገራቸውንም ዘገባው አስታውቋል::
ዳይሬክተሯ ‹‹በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል ተጨማሪ መከላከያዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል›› ያሉ ሲሆን በዚህ የወረርሽኝ ወቅት ጎልተው ከታዩ ነገሮች ውስጥ አንዱ የፆታዊ ጥቃቶች መበራከት መሆኑን መናገራቸውንም ዘገባው ጠቅሷል:: ኮቪድ 19 በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ጥላ ያጠላ ወረርሽኝ ቢሆንም ስለማገገም ሲታሰብ ግን ጠንካራ ምላሾችን እና የመከላከያ እርምጃዎችን ማዘጋጀት እንደሚገባ ዳይሬክተሯ መጠቆማቸውንም ዘገባው አመልክቷል::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2013