ኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቱን በመላ አገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ እያሻሻለ ይገኛል። ለዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ ይሰጥ የነበረውን የ4 ጂ አገልግሎትን በርካታ የክልል ከተሞች ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል። አሁንም በበርካታ የክልል ከተሞች የማስፋፋት ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። አገልግሎቱን በተለያዩ አካባቢዎች በማዳረስ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ በበርካታ ከተሞች አገልግሎቱን አስጀምሯል።
ኢትዮ ቴሌኮም እስካሁን ባደረጋቸው የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት ማስፋፊያ ሥራዎች በአዲስ አበባ፣ በደቡብ ምሥራቅ ሪጅን፣ በሰሜን ምዕራብ ሪጅን፣ በምሥራቅ ምሥራቅ ሪጅን፣ በደቡብ ደቡብ ምዕራብ ሪጅን፣ በምሥራቅ ሪጅን፣ በማዕከላዊ ምሥራቅ ሪጅን እና በሰሜን ምሥራቅ ሪጅን በሚገኙ በርካታ ከተሞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
የዛሬ አራት ወር ገደማ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በደቡብ ምሥራቅ ሪጅን በሚገኙት አዳማ፣ ቢሾፍቱ፣ ዱከም፣ ገላን፣ ሞጆ እና አዋሽ መልካሳ አገልግሎቱን ለደንበኞቹ ያደረሰው ኩባኒያው፤ ከደቡብ ምሥራቅ ሪጂን በመቀጠል በሰሜን ምዕራብ ሪጂን የሚገኙ ሰባት ከተሞች ማለትም ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቡሬ፣ ዳንግላ፣ እንጅባራ እና ቻግኒ ሆነዋል።
ከሁለት ወር በፊት ደግሞ በደቡብ ደቡብ ምዕራብ ‘ሪጅን’ ውስጥ በሚገኙ ስድስት ከተሞች ማለትም በወላይታ ሶዶ፣ በአርባ ምንጭ፣ በሆሳዕና፣ በወልቂጤ፣ በቡታጅራ እና በጂንካ የአራተኛው ትውልድ የማስፋፊያ ፕሮጀከቱን አጠናቆ አገልግሎቱን መስጠት ጀምሯል። በሰሜን ምሥራቅ ሪጅን የሚገኙ ሰባት ከተሞች ማለትም ደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያ፣ ሃይቅ፣ ከሚሴ፣ ቆቦ፣ ላሊበላ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አድቫንስድ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ አድርጓል።
ኩባንያው ሰሜን ምሥራቅ ሪጅንን ተጠቃሚ ባደረገበት በሦስት ቀናት ልዩነት ደግሞ በሰሜን ምሥራቅ ምሥራቅ ሪጅን በሚገኙ አራት ከተሞች ማለትም በሠመራ፣ ሎጊያ፣ አሳይታ እና አዋሽ ሰባት ኪሎ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አጠናቆ አገልግሎቱን ማስጀመር ችሏል።
የ4ጂ አገልግሎት የላቀ ፍጥነትና ባንድዊድዝ እንዲሁም አስተማማኝ የዳታ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ የኩባኒያው ደንበኞች አገልግሎታቸውን ዲጂታይዝ ለማድረግ፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና በአጠቃላይ የቴሌኮም አገልግሎት ላይ ያላቸውን ተሞክሮ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ እንደሚያስችላቸው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
በቀጣይነትም ኩባንያው በተመሳሳይ ሁኔታ የዳታ ትራፊክ እድገትና ፍላጎትን መሰረት ባደረገ መልኩ በዕቅድ ይዞ እያከናወናቸው ያሉ የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት የማስፋፊያ ሥራዎችን በማጠናቀቅ በተለያዩ የክልል ከተሞች አገልግሎቱን በቅርቡ ለማስጀመር የሚያስችሉ ቅድመ ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።
የ4ጂ ኤል.ቲ.ኢ አገልግሎት በተስፋፋባቸው ከተሞች የሚገኙ ደንበኞች በአቅራቢያቸው በሚገኝ የኩባንያው የሽያጭ ማዕከል የ3ጂ ሲም ካርዳአቸውን ወደ 4ጂ በነፃ ማሳደግ በ4ጂ የሞባይል ቀፎ አማካኝነት እጅግ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲጠቀሙ ግብዣቸውን አቅርበዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቴሌኮም አገልግሎት መጠቀሚያ መሣሪያ (smart phone) እና የይዘት (content) አቅራቢዎች በመረጃ የበለፀገ ማህበረሰብና ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲሁም አሁን የተዘረጋውን ከፍተኛ ፍጥነት ያለው የሞባይል ኔትወርክ በስፋት ለመጠቀም የሚያስችሉ ዘመናዊ የሞባይል ቀፎዎችና ይዘቶችን ለህብረተሰቡ በስፋትና በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የ4ጂ አገልግሎት በክልል ከተሞች መስፋፋት ለአገሪቱ ዜጎች ህይወት መለወጥ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ። በርካታ ህዝብ በኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን፣ አገልግሎቶች በፍጥነት እና በጥራት እንዲቀርቡ እንዲሁም የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዳይሬክተር ጄነራል ዶክተር አብዮት ባዩ እንደሚሉት የ4ጂ አገልግሎት በክልል ከተሞች መስፋፋት ለሀገር ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ አለው። የ4ጂ መሰረተ ልማት መስፋፋት በተለይም ኢኮኖሚን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጨወታል።
ለዲጂታል ኢኮኖሚ ሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች እንዳሉት የሚያብራሩት ዶክተር አብዮት፤ ከነዚህ ውስጥ አንደኛው የኮምፕዩተር ኔት ወርክ የሚሰራበት የቴሌኮም መሰረተ ልማት ነው። ሁለተኛው መሰሶ መሰረተ ልማቱን የሚሸከም ስልክ ወይም ኮምፕዩተር ሲሆን ሦስተኛው መሰሶ ደግሞ ተጠቃሚው እና ተጠቃሚው የሚያመነጨው ዳታ ነው። እነዚህ ሦስቱ በዲጂታል ኢኮኖሚ ምሰሶ ይባላሉ።
ከዚህ ውስጥ ዋናውና መሰረታዊው የሚባለው መሰረተ ልማቱ ነው። መሰረተ ልማት ሲባል 2ጂ፣ 3ጂ፣ 4ጂ፣ በቀጣይ ደግሞ 5ጂ እያሉ የሚሄዱ ናቸው። እነዚህ የመሰረተ ልማቱን አቅም የሚጠቁሙ ሲሆኑ መሰረተ ልማቱ ከሌለ ምንም ማድረግ አይቻልም። መሰረተ ልማቱ የበለጠ አቅም አለው ማለት የበለጠ መተግበሪያዎችን እና የበለጠ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል ማለት ነው።
ለአብነት ያህል በ4ጂ መሰረተ ልማት የሚንቀሳቀሱ መተግበሪያዎችን በ2ጂ ወይም በ3ጂ ማንቀሳቀስ የማይቻልና እጅግ አዳጋች ነው። በመሆኑም የመሰረተ ልማቱ አቅም እየጨመረ መሄድ ፋይዳው የጎላ ነው። 4ጂ በየቦታው መስፋፋቱ ዲጂታል አገልግሎቶችን በሁሉም ቦታዎች ለማስፋፋት ያስችላል።
ዲጂታል አገልግሎቶች መስፋፋት ደግሞ ሁለት ፋይዳዎች አሉት። አንደኛው የአገልግሎት ጥራት ሲሆን ሁለተኛው ፋይዳው ደግሞ እኩል ተጠቃሚነት ነው። የአገልግሎት ጥራት ሲባል፤ የ4ጂ አገልግሎት ሲስፋፋ በየትኛው የአገሪቱ ክፍል የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ አካላት በጥራት እንዲያቀርቡ ያስችላል።
እንደ ዶክተር አብዮት ማብራሪያ ሁለተኛው ፋይዳው በየትኛው ቦታ ያለ ዜጋ ተመሳሳይ አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችላል። ይህ እኩል ተጠቃሚነትን የሚያሰፍን ነው። በአራቱም ማዕዘን የሚገኝ ዜጋ እኩል ተጠቃሚ ሲሆን ለአገር ኢኮኖሚ እኩል አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል።
ዲጂታላይዜሽን ውጤታማነትን ያረጋግጣል። የውጤታማነት አንዱ መገለጫ ፍጥነት ነው። ነገሮችን በፍጥነት ለማከናወን ይቻላል። ነገሮች በፍጥነት ሲከናወኑ ጊዜ እና ጉልበትን ለመቆጠብ ያስችላል። የውጤታማነት ሌላኛው መገለጫ ጥራት ነው። የ4ጂ መስፋፋት ሌላኛው ጥቅሙ ነገሮችን በጥራትም ማከናወን ማስቻሉ ነው።
የአራተኛ ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት መስፋፋት ሌላኛው ጥቅም ደግሞ በአንድ ጊዜ በርካታ አገልግሎቶችን በብዙ ቦታዎች ለማዳረስ ማስቻል ነው የሚሉት ዶክተር አብዮት ይህም ኢኮኖሚው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
ዋናው ነገር ደግሞ በጣም በርካታ ህዝብ በኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን ያደርጋል። ሁሉም ሰው የድርሻውን አንዲያበረክት እንዲሁም ሁሉም ዜጋ ከኢኮኖሚው የድርሻውን ተጠቃሚ እንዲሆን እንደሚያስችልም ነው ያብራሩት።
ዋናው ቁም ነገሩ የመሰረተ ልማት መስፋፋት አይደለም የሚሉት ዶክተር አብዮት። ዋናው ቁም ነገር ዜጎች መሰረተ ልማቱን ምን አይነት መተግበሪያዎችን ለማንቀሳቀስ ይጠቀሙበታል የሚል ነው ይላሉ። ፈጣን የሆነውን የአራተኛ ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎቶችን ሰው ምን አይነት አገልግሎቶችን ለማግኘት እየተጠቀመበት ነው የሚለው ዋናው ቁም ነገር ነው ይላሉ።
በፌስቡክ እና በሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎች ወሬ ለመቀባበል ለዋዛና ፈዛዛ የሚጠቀምበት ከሆነ ከመሰረተ ልማቱ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበውን ጥቅም ማግኘት አይቻልም የሚሉት ዶክተር አብዮት ነገር ግን ሰው የኢኮኖሚ አማራጮቹን ለማስፋት የሚጠቀምበት ከሆነ የሚጠበቀውን ውጤት ማግኘት እንደሚቻል አብራርተዋል። የኢኮኖሚ አማራጮችን ለማስፋት መጠቀም ይኖርበታል።
ለአብነት ያህል ፌስ ቡክን የውሸት ዜና ለማሰራጨት የምንጠቀምበት ከሆነ እዚህ ግባ የሚባል የኢኮኖሚ ውጤት ላያመጣ ይችላል። በሌላ በኩል ፌስ ቡክን ለሌሎች ጠቃሚ ነገሮች መጠቀም ይቻላል። የንግድ መረጃ ለመለዋወጥ፣ ምርቶችን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። እቃዎችን ለመሸጥ እና ለማስተዋወቅ እንደ ምቹ ሁኔታ መጠቀም ይቻላል።
ብዙ ሰዎች አዳዲስ ሶፍትዌሮችን ማለማት ሳያስፈልጋቸው መሰረተ ልማቱ እና ስልኩ ካላቸው ዋትስአፕ እና ቴሌግራም የመሳሰሉ መተግበሪያዎችን አውርደው ማንኛውንም አገልግሎቶችን መጠቀም ይችላሉ። እቃዎችን ኦን ላይን ለመሸጥ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። ህብረተሰቡ ጠቃሚ ለሆኑ ነገሮች እንዲጠቀምበት ማድረግ ይቻላል። በመሆኑም የህዝቡ አጠቃቀም በጣም ወሳኝነት አለው።
ኢትዮ ቴሌኮም መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ረገድ እየሠራ ያለው ሥራ በጣም ጥሩ ነው። ለዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ ታጥሮ የነበረውን የ4ጂ አገልግሎት ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች ማድረሱ ይበል የሚያሰኝ ነው። አገሪቷ በቴሌኮም ዘርፍ ከፍተኛ ሪፎርም ውስጥ መሆኑዋንም አመላካች ነው።
አብዛኛው ሕዝብ ያለው በገጠር እንደመሆኑ መጠን 4ጂ ከአዲስ አበባ አልፎ ወደ አብዛኛው ሕዝብ ወደ ሚኖርበት ወደ ገጠር መስፋፋቱ ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝ እሙን ነው። የአገር ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማስመዝገብ ያስችላል። ኢትዮ ቴሌኮም ከከተሞች ወረድ በማድረግ በገጠር የበለጠ ለማዳረስ የማስፋፋት እና ጥራቱን የማስጠበቅ ሥራውን ሊገፋበት ይገባል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013