የአፍሪካ የእስከ ዛሬ ጉዞ ቀላል አይደለም። በሁሉም ማለት በሚቻልበት ደረጃ ተቀፍዳ የኖረች ሲሆን ከነአካቴውም ከሁለት አገራት ውጪ ሌሎቹ በቅኝ አገዛዝ (አፓርታይድን ጨምሮ) እግር ተወርች ታስረው የኖሩ ናቸው። ነፃነታቸውንም ማግኘት የጀመሩት በ1950ዎቹ፣ አብዛኞቹም ከ60ዎቹ ወዲህ ነው። ይህ ሁሉ ይሁን እንጂ ከነጭ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ሲደረግ የነበረው እንቅስቃሴ አንድም ጊዜ ተስተጓጉሎ አያውቅም። ከፍ ዝቅ፣ መለስ ቀለስ እያለም ቢሆን ትግሉ አልተቋረጠም። እንደ ተጠበቀውም ዛሬ ቢያንስ የእጅ አዙሩን ባንከራከርበትም አፍሪካ ከቅኝ አገዛዙና አፓርታይዱ ስርአት ነፃ ወጥታለች፤ የ”አፍሪካን መቀራመት” ህልምና አጀንዳም መክኗል። ይህ ሁሉ ሲሆን “ፊት ናት መሪ” እንደተባለው ቀዳሚዋ፣ ተምሳሌቷ፣ ፋሺስት ጣሊያንን ማንነቱን ከነልኩ እንዲያውቅ ያደረገችው፤ የአድዋ ድል ባለቤት ኢትዮጵያ ነች፤ የርእዮተ አለም መታገያቸው ያደረጉት “ኢትዮጵያዊነት”ን ጨምሮ።
የዛሬው የአፍሪካ ህብረት (ኤዩ)ን፣ የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (ኦኤዩ)ን የመመስረት ውጥን መሬት እስኪወርድ ድረስ አፍሪካና የነፃነት ታጋዮቿ በርካታ መከራዎችን አልፈዋል። በተለይም የሞኖሮቪያና ካዛብላንካ ብሎክ ተባብለው፤ ለሁለት ተቃራኒ ጎራ ከተሰነጠቁ በኋላ አፍሪካ አለቀላት ተብሎ ነበር። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በያዘችው የገለልተኛነት አቋም ወደ አስታራቂነቱ ሚና በመሄድ ስንጥቁን ደፍናለች። ያ ባይሆን ኖሮ፤ የንጉሱ እጅግ አስገራሚና አስደማሚ የአመራርና የአስታራቂነት ጥበብ ባይኖር ኖሮ … ዛሬ አፍሪካ የምትባል የለችም ነበር የሚለው ለኢትዮጵያ ስለ ባለውለታነቷ ሲባል የተሰጣት ምስክርነት ነው።
የአለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅ (አይኤምኤፍ) እና የአለም ባንክን መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ (በነገራችን ላይ በአይኤምኤፍ ማኔጅመንት ውስጥ “የኢትዮጵያ ዴስክ” እንደነበር፤ ኢትዮጵያም የአይኤምኤፍ እና አለም ባንክ የጋራ ማኔጅመንት ሰብሳቢ/ሊቀመነበር (እ.አ.አ በ1965) በመሆን ድርጅቱን ለአንድ አመት መርታ እንደነበር ያውቃሉ? ድርጅቱስ አ.አ ቢሮ የነበረው መሆኑንስ?) ወደ አፍሪካ አንድነት ድርጅትም ፊቷን በማዞር እንዲመሰረት “ያስገደደች” መስራች አባል ነች። (እዚህ ላይ በቦታው የነበሩትና የዐይን ምስክርነታቸውን የሰጡት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዳሉት አፄ ኃይለሥላሴ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ብዙዎቹ ባለመስማማታቸው ስብሰባው እስከ እኩለ ለሊት ዘልቆ ነበር። በመጨረሻም ሊበተን ሲል ንጉሱ የአዳራሹን በር ወደ ኋላ ይዘው በመዝጋት “ይህንን የመመስረቻ ሰነድ ካልፈረማችሁ አንድ ሰው አይወጣም” በማለት በግድ አስፈርመዋቸው ነው የለቀቋቸው። ሊቀመንበሩና ጸሐፊውም ከኢትዮጵያ ሆኑ። አንዳንዶች ቢክዱትም የንጉሱ ውለታ እዚህ ድረስ ነው፤ “የአፍሪካ አባት” የሚለውም ዝም ብሎ የተገኘ አለመሆኑም ይህ የፕሮፌሰሩ ምስክርነት ያሳያል።)
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመስረት ብቻ አይደለም፤ ለዘለቄታዊ አፍሪካ አንድነትም ያላደረገችው የለም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1951 ዓ.ም ጀምሮ በየአመቱ ለ50 አፍሪካውያን ነፃ ወጣቶች የትምህርት እድል (ስኮላርሺፕ) ትሰጥ ነበር (ብዙዎቹ የአፍሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከአአዩ የተመረቁ ነበሩ)፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የአፍሪካ ተማሪዎች ህብረት የሚባል ተቋቁሞ ነበር። የቀድሞዎቹን የአአዩ ጥናቶች (ለምሳሌ “ውይይት” እና የመሳሰሉት) አጠቃላይ ትኩረታቸው አፍሪካ ላይ የነበረ ሲሆን ጥናቶቻቸውም ሆኑ ግንኙቶቻቸው አፍሪካን እንደ አንድ አህጉር በማየት መፍትሄዎችን የሚያመለክተ ነበሩ። ይህ ሁሉ ሲሆን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን ታሳቢ ያደረገ ነበር።
“ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የቅርብ ጊዜ ወይም በቅርቡ ወደ ፖለቲካና ኢኮኖሚው ገበያ የተቀላቀለ ጽንሰ ሀሳብ አይደለም፤ ረዥም ጊዜን፣ ከነፃነት ትግል (ፓንአፍሪካኒዝም) ጀምሮ የነበረ፤ እንደውም መካከል ላይ እየተቀዛቀዘ የመጣ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋናዊው ክዋሜ ንክሩሁማ የተቀነቀነ መርህ ሲሆን፣ እድሜ ለኢትዮጵያ ዘንድሮ እንደገና ምናለልባትም በተሻለ መልኩ ወደ አደባባይ ሊወጣና በወሳኝ ጉዳይ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ለማመንጨት ይቻል ዘንድ በኢትዮጵያ በኩል ተስፋ ተጥሎበት ይገኛል።
የ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ጉዳይ ሲነሳ ብዙ ጊዜ የነበረው አስተያየት የአፍሪካ ህብረትን ምንም የማይሰራ ተቋም አደርጎ የማየቱ ጉዳይ ነው። “ለምን?” የሚለው ጥያቄ እስከ ዛሬ በአግባቡ ባይመለስም ዋናው ግን የራሱ፣ የድርጅቱ አባል አገራት ለድርጅቱ መርህም ሆነ ውሳኔዎች ለመገዛት ፍቃደኛ አለመሆን ነው። ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ በሆነ መልኩ የሩዋንዳው ፖል ካጋሚ የህብረቱ ሊቀመነበር በነበሩበት ጊዜ የታዘቡትን “የአፍሪካ አገራት ችግር በህብረቱ የሚተላለፉትን ህጎች፣ ደንቦችንም ይሁን መመሪያዎችን ወደ ተግባር ለመቀየር ፈቃደኝነት ማጣት ነው” በማለት ነበር የገለፁት።
የራሱ ችግር ነበረው ስንል የራሱ አባላት፣ አፍሪካዊ አገራት እራሳቸው ጉዳያችን በእሱ (ኤዩ) አይታይም፤ መፍትሄ የሚሰጡን እነዛው ቅኝ ገዥዎቻችን ናቸው የማለታቸው ጉዳይ ሲሆን፤ እምነታቸውን በራሳቸው ተቋም ላይ ሳይሆን በጌቶቻቸው ላይ መጣላቸው ነው። ለዚህ ደግሞ ማሳያውም ከምንግዜውም በላይ አሁን ያለንበትን የሚያክል የለም፤ እድሜ ለህዳሴው ግድባችን ግብፅና ሱዳንም እራሳቸውን የማፍረስ ተግባራቸውን፤ ኢትዮጵያም ከራሷም አልፋ የአህጉሪቱ የማንነት ተቋም የሆነውን አፍሪካ አንድነትን ከማጠናከርም ባለፈ መልሳ በመገንባት ላይ መሆኗ እየተስተዋለ ነውና በዚህ ጽሑፍ ይህን እንቃኛለን።
(እየተነጋገርን ያለነው የህዳሴ ግድባችንን በተመለከተ ሱዳንና ፊት መሪዋ ግብፅ “እንዴት እንዴት …?” እያሉ ከስራችን ሊያደናቅፉ በማሰብ ለአቤቱታ አለምን (በተለይም አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የተባበሩት መንግስታት ወዘተ) መዞራቸውና “የአፍሪካ ህብረት ይዳኘን ዘንድ አንፈልግም” ማለታቸውን፤ ኢትዮጵያ በበኩሏ ችግሩ ያለው አፍሪካ ውስጥ፤ ሁላችንም ያለነው አፍሪካ ውስጥ፤ የጋራ ድርጅታችን ደግሞ አፍሪካ ህብረት፤ በመሆኑም በነባሩ “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ” መርህ መሰረት ችግሩ ሊታይና ሊዳኝ የሚገባው በዚሁ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ እንጂ ሌላ አካል እኛ መሀል ሊገባ አይገባውም በሚለው ላይ መሆኑን ለማስታወስ ነው።) ለነገሩ እኮ ስነቃላችን “ያ’ገሩን ሰርዶ ባ’ገሩ በሬ” አይደል የሚለው? ይህ የኢትዮጵያ ፍልስፍና ከሆነ፣ ኢትዮጵያ መርሁን አጥብቃ ብትከተል ምን ይገርማል? ምንም።
ከ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ፍልስፍና (ጆሮ ሳቢ ሀረግ (“The catchall phrase” ይሉታል)) መረዳት እንደሚቻለው ጉዳዩ እራስን ከመቻል ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያለው ነው። ማለትም፣ ባጭሩ አፍሪካ የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳትፈልግ ችግሮቿን እራሷ ትፈታቸዋለች የሚል ነው አጠቃላይ አላማና ግቡ። (ይህ አይነቱ እራስን የመቻል አቋምና ተግባር ደግሞ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም፤ ከበፊት የነበረ ታሪኳ ሲሆን ለዚህም በማስረጃነትም አፄ ምኒልክ “… ችግራችንን እኛው እንፈታዋለን፤ የማንንም እርዳታ አንፈልግም። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሄር ትዘረጋለች።” በማለት ለአውሮፓ ኃያላን የፃፉትን ደብዳቤ፤ እሳቸው እንዳሉትም እራሳችን የተወጣናቸውን ከበድ ከበድ ያሉ ችግሮችን ማስታወሱ ይበቃል።)
ይህን “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን ሰብሰብ አድርጎ የሚገልፅልን በዚህ ፅሁፍ የመጨረሻ ምንጭ አድርገን መጨረሻ ላይ የገለፅነው ጥናት ሲሆን እሱም መርሁ ገና ከቅላፄው ጀምሮ ከመሪዎች እስከ ተራው ዜጋ ድረስ ያሉትን በሙሉ የባለቤትነት ስሜትን የሚቀሰቅስ፣ አገር ወዳድነትንና ጀግንነትን የሚፈጥር አላማ ያለው መሆኑን “The utterance of ‘African solutions to African problems’ aims to stir feelings of ownership and patriotism amongst leaders and ordinary citizens.” በማለት ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል (ልብ እንበል እነ ግብፅ የተጠየፉት ይህንን ነው)፤ ደካማና ጠንካራ ጎኖቹን ከማብራራት ጋር በተያያዘ በርካታ ቁም ነገሮችን ያነሳ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ገፋ ማድረግ ለፈለገም ጠቃሚ ማመሳከሪያ መሆኑን እንጠቁማለን።
ይሁን እንጂ ይህ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው በአንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ዘንድ አያስኬድም የሚል ተቃውሞ ያጋጥመዋል። እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት አንዳንድ ችግሮች አለም አቀፍ ይዘት ያላቸውና አለም አቀፍ መፍትሄንም የሚፈልጉ ሆነው ሳለ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ብቻ ነው የሚያዋጣው ማለት ፈፅሞ የሚያስኬድ አይደለም።
በአፍሪካ የ”ክራይስስ ግሩፕ” ጊዜያዊ ምክትል ፕሬዚዳንትና ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩ ኮምፎርት ኤሮ በጥናታቸው (The Problems with “African Solutions”) እንደገለፁት “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው ጽንሰ ሀሳብ አሰሪ አይደለም፤ ወደ ፊትም አያራምድም። እንደ እሳቸው አባባል አፍሪካ በርካታ ችግሮች (ረሀብ፣ ድህነት፣ ሽብርተኝነት፣ አካባቢያዊ የብሄርና ሀይማኖት ግጭቶች፣ የከፋ ሙስና፣ የተለያዩ በሽታዎች መንሰራፋት ወዘተ) ያሉባት አህጉር ነች፤ እነዚህ ችግሮቿ ደግሞ ከራሷም ባለፈ አለም አቀፍ ትብብሮችንና መፍትሄዎችን የሚፈልጉ ናቸው። ለምሳሌ የአየር ንብረት ለውጥ፣ በሽታዎች (ኤድስ፣ ኮቪድ-19ን የመሳሰሉ ወረርሽኞች …) አፍሪካ የአለም አካል እንደመሆኗ መጠን ለሚገጥሟት ችግሮች አለም አቀፍ መፍትሄዎች ያስፈልጓታልና “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለው እንደገና መፈተሽ ያለበት አስተሳሰብ ነው።
ሌላውና በዚሁ ጽሑፍ ላይ የቀረበው የ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ደካማ ጎን ነው የተባለው ጉዳይ አንዱ የአፍሪካ አገር ሌላውን የአፍሪካ አገር ለራሱ ብሄራዊ (አገራዊ) ጥቅም ሲል መተንኮሱና ወደ ግጭት መግባታቸው ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር አንዳንድ የአፍሪካ አገራት በሌሎች አፍሪካ አገራት ጉዳይ የጣልቃ ገብነት (ኦንተርቬንሽን) ተግባር መፈፀማቸው ነው። በመሆኑም “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” በሚለው መሰረት ብቻ የአፍሪካን ችግሮች እፈታለሁ ማለት የሚያዋጣ አይደለም። አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት የጦር ሀይሎችም በብዙ ጉዳዮች አቅማቸው ያልተጠናከረ መሆኑና ተጠናክረዋል እንኳን የሚባሉት የሚቀሯቸው ነገሮች ያሉ መሆናቸው “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ”ን እንደተፈለገው ዳር ማድረስ አይቻልም። እንደ የተባበሩት መንግስታትን፣ የአውሮፓ ህብረትን ወዘተ ሳይዙ የትም መድረስ አይታሰብም ነው የሚሉት።
እንደ “ይቻላል” ባዮቹ ከሆነ ደግሞ የሚያነሱት መከራከሪያ አላቸው፤ ለዚህም African Peace and Security Architecture (APSA)፣ African Standby Force (ASF)፣ African Capacity for Immediate Response to Crises (ACIRC)፣ AMISOM፣ እና የመሳሰሉት አፍሪካዊ ተቋማት ይህንኑ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ”ን ተግባራዊ ለማድረግ የተቋቋሙ ናቸው፤ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። እነዚህ ተቋማትም ምን ያህል ተሳክቶላቸዋል አልተሳካላቸውም የሚለውን መፈተሽም ተገቢ ነው ሲሉም ነው የ”ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ተገቢነትንና የሌሎችን ጣልቃ ገብነት የሚቃወሙት። ዝርዝሩ ብዙ ነው።
እነዚህ ከላይ በነካ ነካ ያነሳናቸው ጥናቶች የሚሉት ነገር ሊኖር ይችላል፤ ለአለም አቀፍ ችግሮች አለም አቀፍ መፍትሄዎች ማስፈለጋቸውም እርግጥ ነው። በመሆኑም ሁሉንም እንደየ ሁኔታዎች (ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ …)ና ጊዜው፤ አይቶ፣ መዝኖና ፈትሾ ስራ ላይ ማዋል የሚለውን አጥብቆ በመያዝ ተግባራዊ ማድረጉ ተገቢ ይሆናል።
በተለይም እንደነ አሜሪካና ሸሪኮቿ አይነታቱ በሰው አገር ጉዳይ (በተለይም በሉአላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ላይ) በቀጥታ ጣልቃ ገብቼ የምፈልገውን ካላደረኩ ባይ አገራትን ባሉበት ለማስቆምና አፍሪካዊ ሉአላዊነት ለማስከበር፤ ከታች የጠቀስነው መጽሐፍ ላይ “which privileged state sovereignty and the non-interference in the affairs of other countries” በሚል እንደሰፈረው ማለት ነው፤ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ”ን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል። “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ”ን ከማለት ባለፈ የመርህ፣ የተግባር፣ የአላማ ሰው (መንግስት) መሆን ይገባል። ይህንንም ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲን በአስተማሪነቱ መውሰድ ይገባል፤ አፍሪካን ማእከል ያደረገውን የንጉስ ኃይለ ስላሴን የሊግ ኦፍ ኔሽን ታሪካዊና ሁሌም አዲስ ንግግርን ጨምሮ (ከላይ የጠቀስነውን የአፄ ምኒልክን ደብዳቤ ይዞ)፤ “ያገሩን ሰርዶ ባገሩ በሬ”ን ደርቦ ማለት ነው።
በ”ኢንስቲትዩት ኦፍ ግሎባል ዲያሎግ” አማካኝነት ከታተመው፣ ከሬሞፊሎ ሎባኬኝ “African solutions to African problems: a viable solution towards a united, prosperous and peaceful Africa?” (2017) መረዳት እንደሚቻለው (ከርእሱ ጀምሮ) “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ” ለአፍሪካ የሚያዋጣ መርህ ሲሆን፤ ችግሩ የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት አፍሪካ ህብረትን በተራቸው በመሩበት አመት የታዘቡትንና ያጋጠሟቸውን ችግር የአፍሪካ አገራትና መሪዎች ከአፍሪካ ህብረት የሚወርደውን ደንብም ይሁን መመሪያ አልያም ጥናትና ምርምሮች ወደ ተግባር ለመቀየር አይፈልጉም በማለት የገለፁት ነውና ይህንን ቁልፍ ችግር በመፍታት በህብረቱ የተያዘውን አጀንዳ 2063ም ሆነ የባእዳን እጅ ጥምዘዛን መቋቋም ይቻላል። “ይቻላል” ስንልም ወደ ሌላ፣ ወደ እማያዋጣ አፍሪካዊ ያልሆነ አካል መጓተቱ ምንም ፋይዳ እንደሌለው በግብፅ (ከአረብ ሊግ ጀምሮ … የሄደችበትን ከመቁጠር ያልሄደችበትን (ካለ) መቁጠሩ ይቀላል)ና ወዳጅ ዘመዶቿ ላይ መታየቱን በመገንዘብ ነው።
ጨርሰን እንውጣ። ከመውጣታችን በፊት ግን ያለንበት ክፍለ ዘመን ከቀድሞዎቹ የሚለይባቸው ነጥቦች እናንሳ። ማለትም ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ነጠላውን ሳይሆን የሰዎችን ሰብአዊ፣ ዲሞክራሲያዊ፣ ፖለቲካዊ መብቶች፤ ሕገ-መንግስትንና ሕገመንግስታዊነትን፤ የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ፤ የህግ የበላይነት፤ እኩልነት፤ ፍትሀዊነት እና በርካታ ሌሎች ጉዳዮችንም እስኪጎብጥ ድረስ ተሸክሞ ነው የመጣው። እነዚህን መሬት አለማውረድም ሆነ ከአለም ህዝቦች ተጠቃሚነት አኳያ ተግባራዊ አለማድረግ ያላደረገውን አካል እጅግ ውድ ዋጋን የሚያስከፍል ሲሆን፤ አፍሪካም እነዚህ ባልተሟሉበት (አንዳንዶቹም ጋ ጭራሹን በሌሉበት) ዝም ብሎ “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ”፤ “አፍሪካ በአለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ድምጽ ሊሰማ ይገባል”፣ አጀንዳ 2063 ወዘተ ቢባል ትርፉ ከኪሳራ ያለፈ አይሆንም። መፈንቅለ መንግስት ዋናውና ኦፊሴላዊው የመንግስታዊ ስራ እስኪመስል ድረስ በየአመቱ በማሊ የሚካሄደውን አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ መግታት ካልተቻለ የአፍሪካ ሁኔታ እንዲሁ በቃላትና ጽንሰ ሀሳቦች ብቻ ለውጥ ያመጣል ብሎ ማንጋጠጥ ምንም ውጤት አይኖረውም። ሌላው ቀርቶ “የአፍሪካ ምርጫ” የሚሉንን ወገኖች አደብ እንኳን አያስገዛምና በዛወርቅ “ፍጠን ፍጠን ፍጠን . . . ፖሊሱ . . .” እንዳለችው መፍጠን ያስፈልጋል።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ሰኔ 1/2013