የዛሬ ሦስት ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ በመንታ መንገድ ላይ ነበረች። በአንድ በኩል ለ27 ዓመታት ያህል በሕዝብ ጫንቃ ላይ የነበረውን ህወሓት መራሹን መንግሥት ለማስወገድ በተቀጣጠለው ሕዝባዊ የተቃውሞ አመጽ አገሪቱ ወደለየለት መበታተንና መፈራስ ታመራለች የሚል ስጋት ነግሶ የነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ አገሪቱን ሲበዘብዝ የኖረው ገዢ ኃይል ተወግዶ ለኢትዮጵያ አዲስ ዘመን ይመጣል የሚል ተስፋም የጨበጡ ብሩህ አሳቢዎችም አልታጡም። ከሦስት ዓመት በኋላ ያለውን የአገሪቱን ለውጥ ስንመለከትም በርካታ ተስፋዎች የፈነጠቁባት አገር እውን እየሆነች መምጣቷን መመስከር ይቻላል።
ከለውጡ በፊት መንታ መንገድ ላይ የነበረች ኢትዮጵያ ዛሬ የብልጽግና ጉዞን ማስኬድ ጀምራለች። በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና ኢትዮጵያ ለምትገነባው ዴሞክራሲ ጎዳና መሠረት የሚጥል ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሳለች። በሌላ በኩል ወደ መኮላሸት ደርሶ የነበረው የህዳሴ ግድብ ግንባታ በበሳል የለውጥ መፍትሄ ከ80 በመቶ በላይ ደርሷል፤ በያዝነው የሐምሌ ወር ሁለተኛው የውሃ ሙሌት ለማከናወንም ዝግጅቶች ተጠናቀዋል። ለዘመናት ሲጓተቱ የቆዩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም በለውጥ ኃይሉ ነፍስ ዘርተው ለፍጻሜ በቅተዋል። በአንድ ወር ከግማሽ ይጠናቀቃል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት የነበረውና ከዘጠኝ ዓመት መጓተት በኋላ የለውጡ መንግሥት ባደረገው ከፍተኛ ርብርብ ለፍጻሜ የበቃው የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው።
የዶክተር ዐቢይ አስተዳደር ፈተናዎችን እየተጋፈጠ የአገሪቱን የወደፊት ዕጣ ፈንታ መወሰን የሚያስችለውን የአረንጓዴ አሻራ በማሳረፍ የነገዋን ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ይገኛል። በመጀመሪያው ዙር 4 ቢሊዮን፤ በሁለተኛው ዙር 5 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል አሻራውን ዘላለማዊ አድርጓል። በመጪው ክረምትም ሰባት ቢሊዮን ችግኖችን ለመትከልም ጉዞውን ጀምሯል። ከዛሬ አልፎ የነገን ትውልድ የሚታደግ ዘመን ተሻጋሪ ሥራ ነው።
የሸገር ልማትና እንጦጦ አስደማሚ የቱሪስት መስህቦችም ለኢትዮጵያ ሕዝቦች በገጸበረከትነት ቀርበዋል። የኮይሻ፤ የጎርጎራና የወንጪ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መጪውን ጊዜ ሊያደምቁና ለአገርና ለሕዝብ ሊጠቅሙ ተዘጋጅተዋል። በአዲስ አበባም ለዘመናት የተጓተቱ የመንገድ መሠረተ ልማቶች ቀን ወጥቶላቸው ዛሬ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነዋል።
ከዚህ ሁሉ የበላይ ሆነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዛሬ ቀን ወጥቶላቸው የዜጎች ኩራት መሆን ጀምረዋል። ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ለመጥራት ሲጠየፉ የነበሩ ገዢ መደቦች በሕዝብ ትግል በመወገዳቸው ዛሬ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማበብ ጀምረዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢትዮጵያን ለ27 ዓመታት ያህል ሲበዘብዝ የኖረውን የህወሓት አሸባሪ ኃይል በማስወገድ የለውጡ መንግሥት ታሪክ ሰርቷል። ከኢትዮጵያም አልፎ ለምሥራቅ አ ፍሪካ ባ ለውለታ ሆኗል ።
ሆኖም ግን የኢትዮጵያን በጎ ጎን ማየት የማይሹ የውጭ ባዳዎችና የአገር ውስጥ ባንዳዎች የተጀመረውን የለውጥ መንገድ ለማኮላሸት ቀን ከሌት እየሰሩ ይገኛሉ። ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማበቡ የሚያሳምማቸው፤ እውነተኛ ምርጫ መካሄዱና ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጎዳና መጀምሯ የሚከነክናቸው ወደ መኮላሸት ደረጃ ደርሶ የነበረው የህዳሴ ግድብ ተፋጥኖ ሁለተኛ ሙሌት ደረጃ መድረሱና ኢትዮጵያ በልማትና በዴሞክራሲ ጎዳና እየገሰገሰች መሆኑ አልዋጥላቸው ያሉ ሴረኞች አገሪቱን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ ያለመታከት እየሰሩ ይገኛሉ። በተለይም ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ መካሄድና የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ውሃ ሙሌት መከናወን ኢትዮጵያ በቀጠናው ላይ ያላትን ተሰሚነት እንደሚያሳደግ የተረዱ ወገኖች አገሪቱ ከዚህ የስኬት ማማ ላይ እንዳትወጣ እየጎተቷት ይገኛሉ።
ይሁን እንጂ እንደወትሮው ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ተባብረው እነዚህን እኩይ ሴራዎች እያከሸፉት ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያን በየዘመኑ የተነሰቡባቸውን የውጭ ባዕዳንና የውስጥ ባንዳዎችን ሴራ በማምከን የእገሪቱን አንድነትና ሉዓዊነት አስጠብቀው እንደዘለቁ ሁሉ የዛሬውም ትውልድ ዳግም ታሪክ ለመስራት መዘጋጀት አለበት። አሁን ያለንበት ወቅት ጨለማው ሊነጋ ጥቂት ጊዜያት የቀሩት መሆኑን ተገንዝበን የምርጫውን ሰላማዊነት በመጠበቅና የህዳሴውን ግድብ ሁለተኛ የውሃ ሙሌት እውን እንዲሆን ሌት ተቀን ዘብ በመቆም ይህ ትውልድ ታሪክ ሊሰራ ይገባል!
አዲስ ዘመን የሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም