ኢትዮጵያ በርካታ የእንስሳት ሀብት ያላትና በተለይ በቀንድ ከብት ቁጥር ከአፍሪካ የመሪነት ደረጃን የያዘች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚጠበቀውን ያህል አስተዋጽኦ ማበርከት አልሆነለትም፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም ቆዳን አልፍቶ ሰፍቶ ለተለያዩ አገልግሎቶች የመጠቀም ታሪክ አላት፡፡ ቀደም ባሉት አመታትም አገሪቱ ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከቡና ቀጥሎ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ዘርፍ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡
በአሁኑ ወቅት ግን የአገሪቱ የቆዳ ምርት የቀደመ ዝናውን ማስጠበቅ ተስኖታል፡፡ የኢኮኖሚው ምሰሶነቱን ማስቀጠል አቅቶት የኋልዮሽ ጉዞውን ከጀመረ ዓመታትን አስቆጥራል፡፡ ኢንዱስትሪውም በተለያዩ ችግሮች ተተብትቦ ይገኛል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ከአገር ውስጥ የቆዳ ምርት ማግኘት እንዳልቻሉ እና የምርት ፍላጐትና አቅርቦት እጅግ የተራራቀ መሆኑን ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ምርቱ ተትረፍርፎ እና የሚገዛው ጠፍቶ በየሜዳው ሲጣል ይስተዋላል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለአካባቢ ብክለት ምክንያት ሆኗል፡፡
በተለይም የተለያዩ የቆዳ ፋብሪካዎች በሚበዙባቸው በአገሪቱ አካባቢው የፋብሪካዎቹ ተረፈ ምርት አያያዝ እና አለቃቀቅ ከበርካቶች ዘንድ ቅሬታ ይቀርብበታል፡፡ ከጤና ባሻገር በኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ፋብሪካዎቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ሰፊ ክፍተት ስለመኖሩ ይገለፃል፡፡
ኢንዱስትሪው በዚህ ቅርቃር ውስጥ መውደቁም አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እያሳጣት መሆኑን የሚጠቁመው መንግስት በበኩሉ ዘርፉን ከተበተቡት ችግሮች ለማላቀቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡
የቆዳ ዘርፉ ችግሮች ዙሪያ መለስ እና ውስብስብ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡ በዘርፉ ተዋናዮች ብሎም የምርምር ተቋማት በአንፃሩ፣ ቋጠሮውን መፍታት የሚቻለው በመንግስት ተሳትፎ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ባለድርሻዎችን ባሳተፈ መልኩ የጋራ መፍትሄ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት ፡፡
የዘርፉ ማነቆ የሆኑ የፖሊሲና መመሪያ ችግሮች እንደገና ታይተው ጥልቀት ያለው ምርምርና ጥናት በማድረግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ ሽግግሩን በማፋጠን በአገር ደረጃ የታሰበውን የኢንዱስትሪውን ልማት ተጠቃሚነት ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከቀናት በፊትም መሰረቱን ቼክ ሪፐብሊክ ያደረገው እእአ በ1992 የተመሰረተው (ፒፕል ኢን ኒድ) አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅት ‹‹ኢትዮጵያ በቆዳ ሃብቷ ልክ ልትጠቀም ይገባል፣ ዘርፉን በተለይም ከአካባቢ ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር ከብክለት ለመታደግ እና ለበርካቶች የስራ እድል ለመፍጠር አዲስ ፕሮጀክት ይዤ መጥቻለሁ›› ብሏል፡፡
የፒፕል ኢን ኒድ የፕሮግራሞች አስተባባሪ ሜሮን ውብሸት እንደሚገልፁትም ፕሮጀክቱ ተግባራዊ የሚደረገው በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ ላይ ነው፡፡ ሞጆ ከተማ የተመረጠችው የተለያዩ የቆዳ ፋብሪካዎች ስለሚገኙባት ነው፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ፋብሪካዎች የተለያዩ ችግሮች አሉባቸው፡፡
በተለይም የቆዳ ተረፈ ምርት አያያዝ እና አለቃቀቅ ትክክለኛ መንገድን የሚከተል ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በርካቶቹም ተረፈ ምርቱን የሚያጠራቅሙት ፋብሪካ ውስጥ ነው፡፡ ይህም መጥፎ ጠረንን ጨምሮ ለጤና ጠንቅ የሆኑ እክሎችን ይፈጥራል። ችግሩም ከአካባቢ ህብረተሰቡ ጋር የሚኖርን ግንኙነት በቅሬታ የተሞላ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ አብዛኞቹ ፋብሪካዎችን ለአካባቢ ማህበረሰብ የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ደካማ ናቸው፡፡ የአካባቢ ማህበረሰብም ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡
በዚህ ረገድ በአንድ ማእከል ብቻ 4000 የሚሆኑ የተመዘገቡ ስራ አጥ ወጣቶች ስለመኖራቸው መረጃ ማግኘታቸውን የሚገልፁት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ፣ ማእከሉ የምዝገባ አገልግሎት እንደሚሰጥ መረጃ የሌላቸው ወጣቶችን መመልከት ከታቻለ ደግሞ ቁጥሩ ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡
‹‹ግሪን ጆፕስ›› ወይንም አረንጓዴ ስራ ለወጣቶች የተሰኘውና ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ገንዘብ በ40 ወራት ውስጥ የሚተገበረው ፕሮጀክት ዋነኛ አላማም እነዚህን ችግሮች ማቃለል ከተቻለም በማስወገድ በሞጆ እና በአካባቢው ለሚገኙ ስራ እጥ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ስለመሆኑ ያስገነዝባሉ፡፡
ከቆዳ ፋብሪካዎች፣ ከቴክኒክ እና ሙያ ተቋማት እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከቆዳ ልማት ኢንስቲትዩቱ ጋር በመቀናጀት ተግባራዊ በሚደረገው በዚህ ፕሮጀክትም፣ ስራ እጥ ወጣቶች ከቆዳ ኢንዱስትሪ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባሻገር ተረፈ ምርትን ወደ ጠቃሚ ምርት ቀይረው ገቢ እንዲያገኙ እድል ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ ነው››፡፡
እንደ ፕሮጀክት አስተባባሪዋ ገለፃ ኢትዮጵያ ውስጥ ሙከራዎች ቢኖሩም ተረፈ ምርትን ወደ ጠቃሚ ምርት የመቀየር ተግባር ብዙ አልተለመደም፡፡ ከቆዳ ኢንዱስትሪው የሚወጣው ተረፈ ምርት በርካታ ቢሆንም ሃብት አልተቀየረም ‹‹ይህን ታሪክ በሚቀይረው በዚህ ፕሮጀክትም፣ የተመረጡ አራት ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ። ሴቶች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የተሻለ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል ያሉት የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ሜሮን በሞጆ ከተማ እና አካባቢዋ ከሚገኙ 14 ቆዳ ፋብሪካዎች ጋር በሚሰራው ስራም የዘርፉ አበርክቶ እንደሚጎለብት እና የበርካቶች ኢኮኖሚ እንደሚሻሻል ነው ያስረዱት፡፡
እንደ እርሳቸው ገለፃም፣ የፕሮጀክቱ ውጤታማ ትግበራ እንደ አገር የተያዘውን የስራ እድል ፈጠራ በማገዝ ረገድም ተጨማሪ አቅም ይፈጠራል፡፡ የቴክኒክ አቅምን ለመገንባት በተለይም አገሪቱ የመልሶ መጠቀም ቴክኖሎጂዎች እንድትተገብር አቅጣጫን ያመላክታል፡፡ ከጤና አንፃርም ፋብሪካዎች በአካባቢ ላይ የሚያሳድሩትን መጥፎ ሽታ የማስወገድ አቅምንም ለመፍጠር ያስችላል፡፡
የኦሮሚያ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ንጉሱ ብርሃኑ እንደሚገልፁት በሞጆ አካባቢ የሚገኙ የቆዳ ፋብሪካዎች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተስማሙ አይደሉም፡፡ የተረፈ ምርት አያያዝና አወጋገዳቸው በጣም ደካማ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ ተስፋም ሆነ የመንግስት አቅጣጫ የቆዳው ኢንዱስትሪዎች ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የተዛመዱ እንዲሆኑ ከብክለት የፀዱ እና ከጉዳት ይልቅ ጠቃሚ እንዲሆኑ ነው። የፕሮጀክቱ ትግበራም ብክለትን በማስቀረት ረገድ ከፍተኛ አቅም ከመፍጠር ባሻገር እንደ አገር ከባድ ፈተና የሆነውን የስራ እጥነት ችግር ያቃልላል ብለዋል፡፡
እንደ አገርም ሆነ ክልል በቆዳ ኢንዱስትሪ ከፍተኛ የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት አለ፡፡ ኢንዱስትሪዎቹም የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲቀርብ ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው፡፡ የተለያዩ ተቋማትም ይህን ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ናቸው፡፡ ‹‹እኛም ብቃት ያለው ተወዳዳሪ የሆነ ተገቢውን ክህሎትና እውቀት የጨበጠ የስራ ሃይል በአካባቢ ኢንዱስትሪ ለማቅረብ የተለያዩ ጥረት እያደረግን ነው›› የሚሉት አቶ ንጉሱ፤ በፕሮጀክቱ የሚመረጡ ስራ እጥ ወጣቶችም ተገቢውን እውቀት ጨብጠው ወደ ስራ እንዲገቡ ብሎም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ ነው ያስረዱት፡፡ አቶ ንጉሱ የቆዳውን ኢንዱስትሪ ይበልጥ የማዘመንና የማጎልበት በውጤቱም እንደ አገር ተጠቃሚ ለመሆን ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013