የፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በኦሮሚያ አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

ሁለተኛው የኢትዮጵያ ታዳጊ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት ለአራት ተከታታይ ቀናት በሀዋሳ ስታዲየም ሲካሄድ ቆይቶ በኦሮሚያ ክልል አጠቃላይ አሸናፊነት ተጠናቋል። በውድድሩ ዕድሜያቸው ከ16 እንዲሁም ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ታዳጊ አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች የሩጫ እና የሜዳ ተግባራት ፉክክሮችን ማድረግ ችለዋል። የኦሮሚያ ክልልም በሰበሰበው የሜዳሊያ ብዛትና ነጥብ የውድድሩ አጠቃላይ አሸናፊና የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ችሏል።

በየትኛውም ስፖርት ከታዳጊ የሚጀመሩ ስልጠናዎች ቀጣይነት ያለውን ውጤታማነት ማምጣት እንደሚቻል ይታመናል፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ፖሊሲም ይህንኑ የሚደግፍ እንደመሆኑ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆናቸውን ታዳጊዎች በዚህ ፕሮግራም ታቅፈው እንዲሰለጥኑ፣ የማሰልጠኛ ማዕከላትና አካዳሚዎች ግብዓት እንዲሆኑ ከዚያም ወደ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድኖች እንዲያድጉ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ስልጠናውን ለመመዘን እንዲሁም ታዳጊዎቹ የውድድር ልምድ እንዲያገኙም ውድድሮች በተለያዩ ደረጃዎች ይዘጋጃሉ፡፡

ከእነዚህ መካከል አንዱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ታዳጊ ፕሮጀክቶች አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሲሆን፤ በዚህ ስፖርት የሚሰለጥኑ ታዳጊዎችን ያወዳድራል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ በተደረገው በዚህ ውድድር ላይም በቀጣይ ኢትዮጵያን የማስጠራት አቅም ያላቸው ተስፈኛ ተተኪዎች ታይተዋል፡፡ ለአራት ተከታታይ ቀናት በተካሄደው ውድድርም የኦሮሚያ ክልል ባሳየው ብልጫ የበላይነቱን በመያዝ ዋንጫውን ወስዷል። የውድድሩ ተረኛ አዘጋጅ የሆነው የሲዳማ ክልል በሰበሰባቸው ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ደግሞ በወንዶች ሶስተኛ በመሆን አጠናቋል። በሴቶችም በተመሳሳይ ኦሮሚያ ክልል ከፍተኛውን ነጥብ በማስመዝገብ የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡ የሲዳማ ክልል እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደግሞ ሁለተኛና ሶስተኛ ሆነዋል፡፡

በአጠቃላይ ውጤትም የኦሮሚያ ክልል በሰበሰባቸው በርካታ ሜዳሊያዎችና ነጥቦች ታግዞ የመጀመሪያውን ስፍራ ይዟል። የውድድሩ ድምቀትና ተፎካካሪ የነበረው የሲዳማ ክልል በተከታይነት ውድድሩን ሲያጠቃልል፤ ሌላኛው ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ይዞ የቀረበው የአዲስ አበባ ከተማ ቡድን ሶስተኛ ደረጃን በመያዝ ጨርሷል።

ከእድሜ ጋር በተያያዘ የተለመደው የተገቢነት ችግር ቢስተዋልም በአንጻሩ ታዳጊና ተስፈኛ አትሌቶች በየርቀቱና በሜዳ ተግባራት አበረታች ፉክክሮችን ማድረግ ችለዋል። በውድድሩ ማጠቃለያ ዕለት ከተካሄዱ ውድድሮች መካከል ከ16 ዓመት በታች የሪሌ ውድድር ከፍተኛ ፉክክርን አስተናግዶ ሲዳማ በ3:47:88 በሆነ ሰዓት አንደኛ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል። ማዕከላዊ ኢትዮጵያ 3:88:95 ሰዓት አስመዝግቦ ብር እና ኦሮሚያ 3:49:57 በሆነ ሰዓት በመግባት ሶስተኛና የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ችሏል።

ከ18 ዓመት በታች የድብልቅ ሪሌ ውድድርም እንዲሁ ኦሮሚያ፣ ትግራይ እና አዲስ አበባ ጥሩ ፉክክር በማድረግ ኦሮሚያ 3:38:99 ሰዓት በመግባት ወርቁን ወስዷል። ከፍተኛ ተፎካካሪ የነበረው የትግራይ ክልል በ3:41:60 የብር ሜዳሊያውን ሲወስድ አዲስ አበባ 3:4567 የሆነ ሰዓት አመዝግቦ ነሃሱን ሊወስድ ችሏል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ውድድሩ በደመቀና ባማረ መልኩ ተካሂዶ መጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በሴት አትሌቶች ምልመላና ምርጫ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በአንጻራዊነት ያሳተፏቸው አብዛኛዎቹ አትሌቶች በተገቢው ዕድሜ የተገኙ መሆኑ የውድድሩ ጠንካራ ጎን ነበር። አንዳንድ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በበኩላቸው በተገቢ የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ አትሌቶችን አለማሳተፋቸው የውድድሩ ክፍተት ነበር። ለዚህም እስከ መጨረሻው ክትትልና ምርመራ እንደተደረገና በቀጣይ ክፍተቱ የሚታረምበት ሁኔታ እንደሚኖርም ጠቁመዋል።

በመጀመሪያ ዙር ምርመራ 70 ዕድሜ ያጭበረበሩ አትሌቶች የተለዩ ሲሆን፤ ሌሎች ማስረጃዎች ተይዞ የምርመራ ሥራው እንደሚቀጥል አስረድተዋል። የዕድሜ ማጭበርበር ከዚህ በኋላ እንደይኖር የልየታ ሥራ የሚሰራና ቀጣይ በሚወሰነው መሠረት ሕጉን በማይተገብሩት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ርምጃ ይወሰዳል ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ የሚሰጠውን የዋንጫ ሽልማት በማስቀረት ለአትሌቶች ብቻ ማበረታቻ ሜዳሊያ የሚሰጥም ይሆናል። የሕክምና ባለሙያዎች ቀድመው ክልልና ከተማ አስተዳደር በመሄድ ምርመራ በማድረግ የመለየት ሥራም ሌላኛው የዕድሜ ማጭበርበርን ለመከላከል የሚጠቅም መንገድ ሊሆን እንደሚችልም አስረድተዋል፡፡

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You