የዩኬው የፓርላማ አባል ቻይናን በመተቸታቸው ከጂቡቲ እንደተባረሩ ተናገሩ

የዩናይትድ ኪንግደም ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባል ቻይና ላይ ባቀረቡት ትችት ጂቡቲ ከመግባት እንደተባረሩ ተናገሩ።

ከቻይና ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያላት ጂቡቲ ከጥቂት ሳምንት በፊት እንዳባረቻቸው ቲም ሎውተን ገልጸዋል።

የምሥራቅ ዎርቲንግ እና ሾረሃምን ግዛቶችን በመወከል የፓርላማ አባል የሆኑት ቲም ሎውተን ጂቡቲ ሲደርስ ከሰባት ሰዓታት በላይ በእስር መቆየታቸውን እና ወደ ጂቡቲ እንዳልገባ ተከልክያለሁ ብለዋል።

ከሶስት ዓመት በፊት በቻይና ማዕቀብ የተጣለባቸው ሎውተን በሁኔታው ብቸኝነት እንደተሰማቸው “በጣም አስፈሪ” እንደነበር ተናግረዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ክሱ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል።

የፓርላማ አባሉ ወደ ጂቡቲ ያቀኑት ለአንድ ቀን ሀገሪቱን ለመጎብኘትና በሀገሪቱ ከተቀመጡትም የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ጋር ለመገናኘት ነበር።

ጂቡቲ ከደረሱ በኋላ እንዳይገቡ እና በሚቀጥለው በረራ ተሳፍረው እንደሄዱም አስረድተዋል።

“ይህ የቻይና ኮሚኒስት መንግሥት እጅ ምን ያህል ረዥም እንደሆነ የሚያሳይ ሌላ ምሳሌ ነው። በተለይም በአንዳንድ አፍሪካ ሀገራት ያላቸው የከፋ ተጽዕኖ አሳሳቢ ነው” ሲሉ ሎውተን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ሆኖም ቻይና እያደረሰችው ያለው መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ተቃውመው ለመናገር በደፈሩ እና ይህንን ለመናገር መድረክ ባጡ ስፍር በሌላቸው ሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው ማስፈራራት ከባድ ስጋት ይፈጥራል” ብለዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ቻይና በሀገሪቱ ላይ “ሃሰተኛ እና የተሳሳተ መረጃ” እያሰራጩ ነው ባለቻቸው ቲም ሎውተንን ጨምሮ በአምስት የፓርላማ አባላት ላይ ማዕቀብ ጥላለች።

ይህም የዩናይትድ ኪንግደም በሀገሪቱ ባሉት ኡጉር አናሳ ሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ አስመልክቶ ለወሰደችው እርምጃ አጸፋዊ የበቀል ምላሽ ነው ተብሏል።

የቀድሞው ሚኒስትር እና ሆም አፌይርስ የተሰኘው መስሪያ ቤት ኮሚቴ አባል ከ27 ዓመታት የፓርላማ ቆይታ በኋላ በቀጣይነት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ በእጩነት እንደማይቀርቡ አስረድተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You