እስራኤልና ፍልስጥኤም ከሳምንት ለበለጠ ጊዜ የብዙ የመቶዎችን ሕይወት የቀጠፈውን የተኩስ ልውውጥ ሲያካሂዱ ከሰነበቱ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ከጥቂት ቀናት በፊት መስማማታቸው ተነግሯል። ይሁንና የተኩስ አቁም ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዳልተፈፀመ የተለያዩ መረጃዎች ከሁለቱም አቅጣጫ እየወጡ ነው።
በዚህ መሃል የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ፍልስጥኤማውያን እና እስራኤላውያን ተዋጊዎች በየፊናቸው “አሸንፈናል” ማለታቸው ነው። ይህ ደግሞ ግጭቱ ቀጣይነት ሊኖረው እንደሚችል አመላካች ስለመሆኑ በጓዳዩ ዙሪያ አስተያየታቸውን ለሚዲያዎች የሰጡ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኞች ገልጸዋል።
የሁለቱ ወገን ደጋፊዎች የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንዴት ተቀበሉት?
የተኩስ አቁም ስምምነቱ እንደተሰማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን አደባባይ በመውጣት ደስታቸውን የገለፁ ሲሆን የሐማስ ተዋጊ ክንፍ በበኩሉ ድል አድራጊነቱን አውጇል። በእርግጥም የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ ደጋፊ ስለመሆናቸው ጥያቄ የማይነሳባቸው የጋዛ ነዋሪዎች እና የዌስት ባንክ ፍልስጤማውያን የ”አሸንፈናል” ምልክት ሲያሳዩ እንደነበር በማህበራዊ ሚዲያዎች እና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የተላለፉ የሁነቱ ዘጋቢ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከእስራኤል መንግሥት ደጋፊዎችም ቢሆን የድል አድራጊነት ስሜት እንዳለ የሚያሳዩ አዝማሚያዎች እንዳሉ የሚያመላክቱ መረጃዎች ስለመኖራቸው አልጀዚራ ዘግቧል።
ግጭቱ ያገረሽ ይሆን?
አልጀዚራን ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ በጋዛ ሰማይ ላይ አሁንም ድረስ የድሮን ድምፅ እየተሰማ ስለመሆኑ ከቦታው አይተናል የሚሉ ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን ዋቢ አድርገው እየዘገቡ ነው።
የአሜሪካ አምባሳደር በእስራኤል ማርቲን ኢንድያክን ነግረውኛል የሚለው አልጀዚራ ባወጣው ዘገባ “ምንም እንኳ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገ ቢሆንም የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች የመመለስ አዝማሚያ ግን በጣም ዝቅተኛ” መሆኑን ያትታል።
“በእስራኤል እና በፍልስጤም ባለሥልጣናት መካከል የድርድር ዕድል ይኖራል ብላችሁ ነው? የችግሩ አንዱ አካል እኮ ነው። እዚህ ጉዳይ ላይ ከአሁን ቀደምም መሰል ሁኔታ ነበረ። ጥረት አድርገናል። እኔ በበኩሌ በ2014ቱ ተሳትፌያለሁ። ያለ ስኬት ነበር ያበቃው” ብለዋል ሲል የአሜሪካ አምባሳደር በእስራኤል የሆኑትን ኢንድያክን ጠቅሶ ዘግቧል ።
አሁን ላይ ያለውን ሁኔታ በዳሰሳ ዘገባው ሲ.ኤን.ኤን እንዳስነበበው ደግሞ የሐማስ ባለሥልጣናት አሁን ላይ መልካም የሚባል ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል። የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲኖር ላደረጉ የግብጽ እና የኳታር ወገኖች እናመሰግናለን ማለታቸውንም ሲኤንኤን ዘግቧል።
የግጭቱ ክብደት ምን ያህል ነው?
በነበረው የአስር ቀን የአየር ላይ ድብደባ ምክንያት 72 ሺህ በላይ ፍልስጥኤማውያን ከመኖሪያ ቀያቸው ስለመፈናቀላቸው እና በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ተቋማት መስሪያ ቤት እንደተጠለሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያወጣው መረጃ ያመለክታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተኩስ አቁም ስምምነት ከማድረጉ በፊት ባስተላለፉት መልዕክት ጦርነትም ሕግ አለው በማለት የሁለቱ ወገኖች ግጭት ያደረሰውን ሰብዓዊ ኪሳራ ክብደት ገልፀዋል።
“ገሀነም በመሬት ላይ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ላይ በጋዛ ንፁሃን ህፃናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ራሱ ይሆን ነበር” በማለት።
ተመድ በጉዳዩ ዙሪያ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል?
ከምሥረታው ጊዜ ጀምሮ ብዙ የሚባሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶችን በመቀልበስ ሂደቱ ቀዳሚውን ሚና እንደተጫወተ የሚነገርለት ተመድ አሁን ላይ ጠንካራ የሚባል ውሳኔዎችን ሲያሳልፍ አላየንም በማለት የእስራኤል ድርጊትን የሚኮንኑ አገራት ወቀሳ ሲያቀርቡ ነበር።
የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በበኩሉ የሁለቱን ወገኖች ግጭት አጀንዳ በማድረግ በአስር ቀናት ውስጥ አራት ጊዜ ተወያይቷል። ያም ሆኖ ግን አስገዳጅ ውሳኔዎችን ለማሳለፉ አልተሰማም።
የሌሎች አገራት አቋም ምንድን ነው?
አሜሪካም በዚህ ጉዳይ የተለየ አቋም እንደማታራምድ ፕሬዚዳንት ባይደን በቅርቡ ከደቡብ ኮሪያው መሪ ጋር በጥምረት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተፈፃሚነት እንዲኖረው እና ከግጭት ነፃ የሆነ ድርድር እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።
ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ እና ሌሎች የአውሮፓ አባል ሃገራት ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን እንዲያቋርጡ ጥሪ ቢያቀርቡም አስገዳጅ የሆነና ጫና ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ አቋማቸውን የገለፁበት መረጃ ግን እስካሁን ድረስ አልታየም።
በሌላ በኩል ብዙ ጊዜ ከምዕራቡ ሃገራት ጋር በውዝግብ የሚታወሱት ቻይና፣ ቱርክ፣ ሩሲያ እና አጋሮቻቸው ችግሩ እየተባባሰ ያለው በእስራኤል ፀብ አጫሪነት ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው ይህ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤትም ሆነ ሃገሮች በተናጠል በሚወስዱት ሕጋዊ እርምጃ ሊገቱ እንደሚገባ ግጭቱ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሲያሳስቡ እንደነበር ይታወሳል።
የቱርክ መንግሥት በበኩሉ “የአሜሪካ መንግሥት ለእስራኤል እያደረገ ያለውን ፖለቲካዊ ድጋፍ እና የጦር መሣሪያ ሽያጭ በእጅጉ እንዳሳሰበው” ገልጿል። ቲአርቲ ወርልድ እንደዘገበው ከሆነ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን አሜሪካ እና እስራኤል የንፁሃንን ደም ከሚያፋስስ የጦርነት ድግስ ራሳቸውን እንዲያቅቡ ጥሪ አድርገዋል።
የሱፍ እንድሪስ
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2013 ዓ.ም