በ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ላይ ካገኘናቸው ወጣቶች አንዷ…..

ሀገረ ኢትዮጵያ ከዘመኑት እኩል ዘምና ከፍ ያለች ሀገር እንድትሆን የቴክኖሎጂ ፋይዳ ከፍተኛ ነው። ይህንኑ በመረዳትም ካደጉት ሀገራት እኩል ለመራመድም ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ላይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የማደግ ዕድል እንዳላት ሀገር ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት እያደረገች ትገኛለች። በሁሉም መስክ ማለትም የማህበራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል፣ ዘመናዊ ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ግብርናን ዘመናዊ በማድረግ በምግብ እራስን ለመቻል፣ ለጤና ብሎም ለወታደራዊ አገልግሎት፣ በአጠቃላይ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ቴክኖሎጂ መሠረታዊ ነገር ነው።

የቴክኖሎጂ አቅም ማደግም ከሀገር ውስጥ አገልግሎትን ከማሻሻል አንስቶ በውጭ ሀገራት ለሚገኙ በዚህ ዘርፍ ያሉ የቴክኖሎጂ ፍላጎቶችን ለማሟላት የራሱን አስተዋፅኦ የሚያደርግ ነው።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥታ እየሠራች መሆኑን በመንግሥት ይገለፃል። የዚሁ አካል የሆነ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ከመጋቢት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ ሰንብቷል። ለሦስት ሳምንታት በዘልቀው ዓውደ ርዕይ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በሌሎች ዘርፍ የተሰማሩ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ‹‹ስታርት አፖች›› ሥራዎቻቸውን በማስተዋወቅ ላይ ሰንብተዋል።

በእለቱ በርካታ ወጣቶች በቴክኖሎጂው ዘርፍ ሥራን ፈጥረው ለውጭ ሀገራት ካምፓኒዎች በማገልገል ዶላር የሚያመጡ ወጣቶች መኖራቸውን ሰማን። እውነት ሀገራችን በዚህ ልክ ሙያተኞች አላት ወይ በማለት ልቤን ሳስጨንቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሜሪካ ውስጥ ለሚገኘው ለማክዶናልድ ለተባለ ምግበ አቅራቢ ተቋም የሚሰሩ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች መኖራቸውን በ‹‹ስታርት አፕ ኢትዮጵያ›› ዓውደ ርዕይ ላይ ተናገሩ። ታዲያ ይህን ተስፋ ሰጪ ጅምር ከግቡ እንዲደርስ ሰዎችን የማብቃት ሥራ ከሚሰሩት መካከል አንዷን ጠጋ ብለን አነጋገርን።

ፍልቅልቅ ወጣት ናት። ቀርቦ ላላያት ይህን ያህል ቁም ነገር ውስጧ የያዘች አትመስልም። ለቃለ ምልልሱ ተስማምተን መናገር ስትጀምር ግን ከእድሜዋ በላይ የበሰለች ሆና አገኘኋት። የሃያ አራት ዓመት ወጣት ስትሆን ገሊላ ደስታ ትባላለች፡፡ የምትሰራው ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውትሶርሲንግ ላይ ነው።

ወጣቷ ኢ-ቴክ በተባለ ድርጅት ውስጥ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውትሶርሲንግ ዲፓርትመንት ኃላፊ ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች። ይህ ድርጅት ለባንኮችና ለተለያዩ ተቋማት በርካታ የሳይበር ደህንነት ሥራዎችን የሚሰራ ነው። የሶፍትዌር ዲቨሎፕመንት፤ ቴሌኮምና ኢንፍራስትራክቸር፤ ኢኮሜርስና ፌንቴክሰ አገልግሎቶችንም እንዲሁ ለተለያዩ ተቋማት ሰጥቷል።

የተቋሙ ዋና ትኩረት የሳይበር ደህንነትና ሶፍትዌሮችን የማበልፀግ ሥራ፤ ቴሌኮምና ኢንፍራስትራክቸር ሥራን ጨምሮ የሚሠራ ሲሆን እሷ የምትመራው ዲፓርትመንት የአውትሶርሲንግ ሥራን ይሠራል። አውትሶርሲንግ ሥራው ከላይ የጠቀስናቸው በተቋሙ የሚሰሩ ሥራዎችን ወደ ውጭው ገበያ ማለትም ወደ አሜሪካ ወደ አውሮፓ ወስዶ እዛ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ማለት ነው።

ወጣቷ እንደምታብራራውም እሷ የምትመራው ዲፓርትመንት ቴክኖሎጂ ላይ ያለውን አቅም በስልጠና በመስጠት በውጭ ሀገራት ያሉ ገበያዎችን ያፈላልጋል፡፡ ወጣቶች ባሉበት ሀገር እንዲሳተፉ በማድረግ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ሥራዎች ወደ ሀገር ውስጥ መጥተው እንዲሠሩ የማድረግ ሥራን ያከናውናል።

ገሊላ በልጅነቷ ግሎሪ የተባለ ኢንተርናሽናል ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ተምራለች። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በካቴድራል ተምራ ያጠናቀቀችው ወጣት በጥሩ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ወጤት አርሲ አሰላ ዩኒቨርሲቲ ገብታ ዓለም አቀፍ ንግድና የመዋዕለ ነዋይ ፈሰስ አስተዳደር ትምህርት ተምራ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተመረቀች። አሁን ሁለተኛ ዲግሪዋን በኢንተርናሽናል ትሬድ ኤንድ ኢኮኖሚክስ እየተማረች ትገኛለች።

የመጀመሪያ ዲግሪዋን እንደተመረቀች ኢንቨስትመንትን የሚያማክር አንድ ተቋም ውስጥ ዳታ አናሊስት በመሆን ነበር ሥራ የጀመረችው። በመቀጠል የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውትሶርሲንግ ዳይሬክተር በመሆን በመሥራት በተማረችው የዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ባለሙያዎችን ለገበያ ማቅረብ ሥራንና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተለያዩ ሥራዎችን ከሚሰሩ አካላት ጋር የማገናኘት ሥራን መሥራት ቀጠለች።

ከነበረችበት የደታ አናሊስስት ሥራ ወጥታ የአውት ሶርሲንግ ሥራ ላይ ስትገባ ወደ ቴክኖሎጂ ለመቅረብ ከፍተኛ እድል እንደፈጠረላት የምትናገረው ወጣት በአንድ ጊዜ ተሰርቶ የሚያልቅ ቋሚ ሠራተኛ ለማያስፈልጋቸው ካምፓኒዎች የሚፈለገውን ሥራ መሥራት የአውትሶርሲንግ ሥራ በማለት ይታወቃል ትለናለች።

አንድ ተቋም የራሱ የሆነ ሶፍትዌር ማበልፀግ ቢፈልግ ቋሚ ሠራተኛን ከሚቀጥር ይህን ሥራ ሥራዬ ብለው ለሚሰሩ ተቋማት ሰጥቶ የሚፈለገውን ሶፍትዌር አስለምቶ የሚጠቀምበት አሠራር ለበርካቶች የሥራ እድል የፈጠረ ተቋማትንም ከተጨማሪ ወጪ የሚያድን መሆኑን ተናገራለች።

አውትሶርሲንግ ሲባል ሰፊ ነገሮችን በውስጡ የያዘ ሲሆነ የቴክኖሎጂ አውትሶርሲንግ ላይ የምትሰራው ወጣት ገሊላ አሁን ባለችበት ተቋም በሀገር ውስጥ ያሉ በርካታ የሶፍት ዌር ኢንጅነሮች በማሰልጠን ላይ ትገኛለች፡፡ ተመርቀው ከተቀመጡት በተጨማሪ በየዓመቱ የሚመረቁና ገበያውን የሚቀላቀሉትንም በማሰልጠን ወደ ሥራ ለማሰማራት ደግሞ የግድ ገበያውን የሚያገናኝ አካል በማስፈለጉ ነው የአውት ሶርሲንግ ሥራ የሚሠሩ ተቋማተ ያስፈለጉት። ሥራው ሥራ ፈላጊውንና ሥራን የማገናኘት ሲሆን የቴክኖሎጂ አቅም ያለውን ሰው በማሰልጠን ብቁ ሰው ለገበያው ማቅረብ እንደሆነ ትናገራለች።

እንደ ገሊላ ገለፃ በሥራው ውስጥ ኦን ሹርና ኦፍ ሹር የሚባል የአውት ሶርስን እስታይል አለ። ይህ ማለት ኦፍ ሹር ከአንድ ሀገር እሩቅ ማለትም ከሚሰራለት ካምፓኒ እሩቅ ሆኖ የሚሠራ ሥራ ሲሆን ኦን ሹር ደግሞ ሥራው አካባቢ ሆኖ መሠራት ማለት ነው። አሁን በአውትሶርሲንግ ሥራው የአውሮፓና የአሜሪካ|ን ገበያ ለመያዘ እየተሞከረ ነው። ይህ ሲባል አንድ የምግብ አቅራቢ ተቋም ትእዛዞችን እየተቀበለ ለሼፎቹ የሚያስተላልፍ የአይቲ ባለሙያ ቢፈለገ አሜሪካ ላይ አንድ ሰው የሚቀጥርበት ገንዘብ አንድ አስረኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ሊያስቀጥረው ከቻለ ተቀጣሪውም በሀገሩ ሆኖ በዶላር እየተከፈለው መሥራት ሲችል ይህ ገበያን የማገናኘት ሥራ ለሥራውም ለሠራተኛውም ጥቅም አለው ማለት ነው።

በየዓመቱ የሚመረቁ የሶፍትዌር ኢንጂነሮች፤ የአይቲ ባለሙያዎችም የዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ያለን ሥራ በመሥራት በሀገራቸው ተቀምጠው ራሳቸውን ጠቅመው ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪን እንደሚያስገኙ ትናገራለች።

የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አውትሶርሲንግ ዓለም አቀፋዊ ሰፊ ገበያ አለው። በብዛት በህንድ የሚገኙ የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች በደቡብ አፍሪካ ያሉ ባለሙያዎች በሥራው ይሳተፋሉ። በእነዚህ ሀገራት የሚኖሩ ባለሙያዎች ከአስር በመቶ ያላነሰ ገቢ ከአውት ሶርሲንግ እንደሚያገኙ የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱ ወጣቷ ትናገራለች።

በሀገር ውስጥ ያሉ የቴከኖሎጂ ባለሙያዎች ሀገሪቱ ያላትን ርካሽ የሰው ጉልበት በመጠቀም የሥራ አጦችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል። በሀገራችን ያለው ታይም ዞን ማለትም ሰዓት አቆጣጠራችን ለብዙ ሀገራት የተመቸ መሆኑ፤ በቴክኖሎጂው የሰለጠኑ ወጣቶች መበርከታቸው በተወሰነ ስልጠና ለገበያው የተስማሙ ብቁ አቅም ያላቸው ወጣቶች መኖራቸው የውጭውን ፍላጎት ለመያዝ ያስችለናል ትለናለች።

በቂ ስልጠናዎች ስለሚሰጡ አዲስ የሚመጣ ቴክኖሎጂን በፍጥነት ተግባብቶና ተረድቶ መሥራት እንደሚቻል የምትናገረው ወጣት አሁን ስልጠናዎችን በቀላሉ በኢንተርኔት ማግኘት በሚቻልበት በዚህ ዘመን በቀላሉ ሰልጥነው ሙሉ አቅማቸውን መጠቀም የሚችሉ ወጣቶችን ማፍራት ይቻላል ብላለች።

እንደነዚህ ዓይነት <<የስታርት አፕ ኢትዮጵያ>> ዓውደ ርዕይ መከፈቱ ብዙ የማይተዋወቁ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲገናኙ የሚያደርግ ሲሆን በዚህም የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮች እርስ በእርስ ግንኙነት ተችለው እንዲታዩ ያደርጋል ብላለች።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቴክኖሎጂው ዓለም ውስጥ በርካታ እቅም ያላቸው፤ የቴክኖሎጂ እውቀታቸው የላቀ ሴቶች እየተፈጠሩ መሆኑን የምትናገርው ወጣት ገሊላ ሴቶች ቴክኖሎጂን የመረዳት አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ ለዚህ አስተዋፅኦ እንዳለው ትናገራለች።

አሁን ያለው የትምህርት ሁኔታ በተለይም በከተማ አካባቢ ሴቶችን የሚያበቃ ነው። ከቴክኖሎጂ አንድ ነገርን ይዞ በትእግስት የመጨረስ አቅም የላቸውም ሴቶች ናቸው። ሴቶች ይህንን ሥራ መሥራታቸው በራሱ ሌላ አቅም የሚፈጥር ነው።

በሚገርም ሁኔታ ሴቶች አግብተውም፤ ወልደውም ቤት ውስጥ ሆነው መሥራት የሚችሉበት ሥራ የቴክኖሎጂ ሥራ ነው። በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን ትምህርት ማግኘት በእጅ ያለ ስለሆነ በስልክ መማር እና በስልክ መሥራት የሚቻልበት ነገሮች የቀለሉበት ጊዜ ነው።

አንድ እናት የቴክኖሎጂ ባለሙያ ከሆነች ልጅ ወልዳ ቤት መሆን ቢኖርባት ሥራዋን የማቆም ግዴታ የለባትም። ይህም ማለት በቴክኖሎጂ ሥራ ላይ የተሳተፈች ከሆነች ልጇን እየተንከባከበች ከሥራዋ ሳትርቅ መቆየት እንደምትችል ትናገራች።

የቴክኖሎጂ ሥራ የሚሠራው በአእምሮ በመሆኑ ሴቶች እናትነትንና የቤተስብ ኃላፊነትን እየተወጡ ቴክኖሎጂ ላይ መሥራት ይቻላል። ሴትነት የሰጣቸው መልካም ፀጋዎች በጊዜያቸው ወብ ሆነው እንዲቀጥሉ ሴቶች በተሻለ ለቴክኖሎጂ ቅርብ የሆኑ ሥራዎቸን መሠራት አለባቸው የሚል እምነት እንዳላት ትናገራለች።

በዚህ ዘመን ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች የበዙበት፤ ወጣቱ መማር የሚፈለግ፤ የሚጓጓ ወጣት ያለበት ዘመን ነው። ሴቶቹም ወደፊት የመግፋት፤ አዲስ ነገር የማግኘት ጉጉታቸው የላቀ በመሆኑ የመፍጠር እና አዲስ ነገር የማግኘት ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ያንን ደግሞ ሊደግፉ የሚችሉ ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ በመሆኑ ሀገሪቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የምታገኘው ጥቅም እየላቀ የሚመጣበት ተስፋ ይታየኛል ብላለች።

በሀገሪቱ በርካታ ሶፍትዌር ኢንጂነሮች መገኘታቸው፤ ሥራ ፈጣሪዎች መበራከታቸው፤ በቀደመ ጊዜ ከነበረው በተለየ ለቴክኖሎጂ ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ መስክ ወደፊት እንደምትራመድ አመላካች ነው፡፡

ከታላላቆቹ እኩል መራመድ እንችል ዘንድ፤ እየተፈጠረ ያለውን የቴክኖሎጂ ግብዓት የታጠቀ ትውልድ ማፍራት አስፈላጊ ነው። ስለዚህም አሁን ስታርት አፖችን ለማበረታታት የተወሰደው ዓይነት ገንቢ አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል በሚል ሃሳባችንን በዚሁ ቋጨን፡፡ ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You