በጎርፍ ከ80 ሰዎች በላይ የሞቱባት ኬንያ የትምህርት ቤቶች መክፈቻ በሳምንት አዘገየች

በጎርፍ ከ80 ሰዎች በላይ የሞቱባት ኬንያ የትምህርት ቤቶች መክፈቻ ዕለትን በሳምንት አዘገየች።

አውሎ ንፋስ በቀላቀለ ዝናብ ምክንያት በጎርፍ የተጥለቀለቀችው ኬንያ ትምህርት ቤቶችን መክፈት ለተማሪዎቹ እና ሰራተኞቹ ስጋት መሆኑን ገልጻለች።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላው ሀገሪቷ ያሉ ትምህርት ቤቶች በጎርፍ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ኤዚኪየን ማሾጉ እሁድ እለት ባወጡት መግለጫ አስፍረዋል።

“በከፍተኛ ሁኔታ እየጣለ ያለው ዝናብ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የጎርፍ አደጋን የመከላከል እርምጃ ከመውሰዱ በፊት የተማሪዎችን እና የሰራተኞችን ህይወት አደጋ ላይ መጣል የማይታሰብ ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።

በኬንያ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለሁለተኛ መንፈቅ ዓመት ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም መከፈት ቢኖርባቸውም በጎርፍ ምክንያት የሚከፈቱበት ጊዜ ወደ ሚያዝያ 28 ቀን ተራዝሟል።

አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለው የሚገኙ ነዋሪዎች መጠለያ ሆነዋል።

ቅዳሜ ዕለት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 13 አስከሬኖች መገኘታቸውን ተከትሎ በጎርፍ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 83 አድርሶታል። በቀጣዮቹ ቀናትም የከፋ ዝናብ እንደሚጥል ከመጠበቁ ጋር ተያይዞ የሟቾች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሏል።

ከሞቱት በተጨማሪ በጎርፍ አደጋ ከ130 ሺህ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት የገለጹ ሲሆን በርካቶች ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል ተብሏል።

ኬንያን ጨምሮ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መነሻው ከፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ በሆነው እና በአካባቢ በሚፈጠር የውሃ ሙቀት መጨመር በሚከሰተው ኤልኒኖ የአየር ክስተት ምክንያት በከፋ ዝናብ ተመትተዋል።

በዚህም ምክንያት ኬንያን ጨምሮ ጎረቤቶቿ ብሩንዲ እና ታንዛንያ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል።

በብሩንዲ ከ100 ሺህ ሰዎች በላይ ሲፈናቀሉ፣ በታንዛንያ ደግሞ ቢያንስ 150 ሰዎች ሞተዋል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You