በጥንታዊው ዲማ ጊዮርጊስ፣ በደብረ ኤልያስ እና በመርጦ ለማርያም ያሉ ከአልማዝ፣ ከወርቅ እና ከብር የተሠሩ ቅርሶች በግርምት እስኪያፈዙን ድረስ በስስት ዓይተናቸዋል። ቅርሶቹን ከጠላትና ከሌባ ጠብቀው እስከአሁን ላቆዩዋቸው አባቶች ምስጋና ብቻ ሳይሆን ሽልማትም ይገባቸው ነበር ብለናል። ይሁንና በወጉ እንኳን የሚጎበኝ ሰው ባለመኖሩ አሁንም የቱሪስት ያለህ እያሉ ይጣራሉ። እኔም ዕድሉን አግኝቼ የጎበኘኋቸው በመንግሥት ተቋማት በተዘጋጀ ጉዞ ላይ ተሳትፌ ነው።
‹‹እናንተ ጎብኙ እኛ እንዘግባለን›› በሚል መሪ ሃሳብ ሰሞኑን የኤፌዴሪ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ እና ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በጋራ ያዘጋጁት ሰባተኛው ሀገር አቀፍ የሚዲያ ፎረም መካሄዱ ይታወሳል። በወቅቱ በሚዲያ ፎረሙ የተሳተፍን 74 የምንደርስ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን አባላት በምሥራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ተፈጥሯዊ እና ባህላዊ ቅርሶችን የመመልከት ዕድሉ አጋጥሞናል።
ምንም እንኳን የአካባቢው የቱሪስት ሀብቶች በጎብኚ ድርቅ ቢመቱም አዚያ በቆየንበት አጋጣሚ አንድ ያልጠበቅነው ነገር አጋጥሞናል። ውብ መኪናዎችን ይዘው አስቸጋሪ ፒስታዎችን አቋርጠው የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን በመያዝ የጳጉሜን አስጎብኚ ድርጅት የአካባቢውን ቅርሶች ሲያስጎበኙ ነበር። ይህ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ነውና ሌሎቹም አስጎብኚዎች ሊከተሉት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን መመስከር ይቻላል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ሰፊ የቱሪስት መስህብ እያለው ለምን ሊጎበኝ አልቻለም የሚለው ጉዳይ ብዙ ምክንያቶች አሉት። አካባቢው በአግባቡ አለመተዋወቁ ጎብኚ እንዳይመጣ ካደረጉ ምክንያት መካከል የሚጠቀስ መሆኑን የሚናገሩት የብቸናዋ ነዋሪ ወይዘሮ አስቴር ሙሉነሽ ናቸው። በደብረ ገነት ኤልያስ ያለው የቅኔ ትምህርት ቤት፤ በብቸና ከተማ የሚገኘው ደብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን እና የብቸና ደብር ሙዚየም በውስጣቸው የኢትዮጵያ ነገስታትን አልባሳት፣ ዘውዶች እና ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት ይዘዋል። በተለይ የመርጦ ለማርያም ደብርን ጨምሮ የሚገኙት የንጉሥ ተክለሃይማኖት የራስ ወርቅ፣ የብር ከበሮ እና የነገስታት መጎናጸፊያዎች የኢትዮጵያን ታሪክ ቁልጭ አድርገው የሚያሳዩ በመሆኑ የአገር ውስጥ ጎብኚውንም መሳብ ይችላሉ። ለአጥኚዎችም ትልቅ ግብአት ናቸው።
እንደ ወይዘሮ አስቴር ከሆነ፤ዋሻ አምባ አቡነ ተክለኃይማኖት የአንድነት ገዳም በምሥራቅ ጎጃም ዞን በማቻከል ወረዳ ልዩ ስሙ ኳሽባ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ይገኛል። ገዳሙ ካለው ዋሻ በተጨማሪ ተራራማ ቦታ ላይ የለማ የተፈጥሮ ሀብት አለው። እንዲሁም በተምጫ ወንዝ ላይ የምሥራቅ ጎጃም ዞን እና የምዕራብ ጎጃም ዞንን የሚያገናኘው በክልሉ መንግሥት የተገነባው ከ200 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ተንጠልጣይ ድልድይ ሌላው የአካባቢው ውበት ነው። ይህ ዓይነቱ መዳረሻ በተለይ ድንኳን ጥለው በአካባቢው እየተዘዋወሩ ጊዜአቸውን ማሳለፍ ለሚፈልጉ የውጭ አገር ጎብኚዎች ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። የምሥራቅ ጎጃም የቱሪስት መስህቦች የማስተዋወቅ ሥራ በአማራ ክልል ብቻ ሳይሆን በፌዴራል ደረጃም መከናወን ይኖርበታል። በተለይ በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን ከተሰጠው ቅርሶቹን ተንከባክቦ ለማቆየት ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ገቢ ለመፍጠር የሚያስችል ገንዘብ ማግኘት ይቻላል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ውድዓለም አልማው እንደሚሉት ደግሞ፤ በዞኑ ያለው የቱሪዝም መዳረሻ ከአራተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ያሉትን ታሪኮች ያቀፈ ነው። የኦሪት ዘመን መሰዊያዎች እና የዚያ ዘመን የስነሕንፃ ጥበብ አሻራ ያረፈበት በመርጦ ለማርያም ገዳም የሚገኘው በአራተኛው ክፍለዘመን የነበረው በአብርሃ እና አጽበሃ ቤተክርስትያን ፍርስራሽ የአካባቢው የቱሪስት መስህብ ነው። የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ቤተክርስቲያኑ በዮዲት ጉዲት ዘመን ጥቃት እንደደረሰበት ቢነገርም አሁንም የኢትዮጵያን የስነሕነፃ ጥበብ ሊመሰክር ግድግዳዎቹ ቆመው ይታያሉ።
ሕንፃው ከተሠራባቸው ጥሬ ዕቃዎች መካከል ኖራ እና ድንጋይ ይገኙበታል። የሚሉት ኃላፊዋ፤ በግቢው ውስጥ የሚገኝ ዛፍ ደግሞ በቀድሞ ጊዜ ወደ ቤተክርስቲያኑ የሚያስገባ የውስጥ ለውስጥ መንገድ መሆኑ ይነገራል። በመሆኑም ቦታውን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ የመሰረተ ልማት ችግሮችን መቅረፍ ያስፈልጋል። በተለይ የአስፋልት መንገድ እና ምቹ ማረፊያ በማዘጋጀት የቱሪዝሙን ገቢ ማሳደግ ይገባል።
እንደ ወይዘሮ ውድዓለም ከሆነ፤ ከሚዳሰሱት የአካባቢው ቅርሶች በተጨማሪ የማይዳሰሱ እና ለቱሪስት መስህብ የሚሆኑ ባህሎች አሉ። ከእነዚህ መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የጎጃም ባህላዊ የጋብቻ ስነስርዓት ነው። ጭፈራው እና የሠርገኛው አለባበስ እንዲሁም አጠቃላይ ሁነቱ በተለይ ከአውሮፓ እና አሜሪካ የሚመጡ ጎብኚዎችን ቀልብ የመሳብ ኃይል አለው። በአስተርዮ ማርያም ማለትም በየዓመቱ ጥር 21 ቀን የሚከበረው በዓል ደግሞ የአካባቢው ቱባ ባህል የሚንጸባ ረቅበት ነው። ልክ ጥምቀት በጎንደር እና በአዲስ አበባ ያለውን ድባብ ዓይነት በአስተርዮ ማርያም በተለይ መርጦ ለማርያም እና ብቸና ከተሞች ሰፊ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ የጎዳና ላይ ትዕይንቶችን ያስተናግዳሉ። በመሆኑም የማስተዋወቅ ሥራው በተጠናከረ መንገድ ይቀጥላል።
የኢፌዴሪ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ በበኩላቸው፤ ሁሉም በኢትዮጵያ የሚገኙ የሚዲያ አካላት ቦታዎቹን ለዓለም በማስተዋወቅ ረገድ ትልቅ የቤት ሥራ እንዳለባቸው ይናገራሉ። ከማስተዋወቁ ባሻገር ግን የአካባቢው ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች ባለሀብቶች የዞኑን መስህቦች በማልማት እና ተያያዥ የእንግዳ ማረፊያዎችን በመገንባት መጠቀም እንደሚችል ይገልጻሉ። ህብረተሰቡ፣ የሐይማኖት ተቋማት እና የመንግሥት አካላት በቅንጅት እስከሰሩ ድረስ በቀጣይ ምሥራቅ ጎጃምን ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ አይከብድም፤ ምክንያቱም ሰፊ ሊጎበኝ የሚችል ሀብት ያለው አካባቢ መሆኑን መመስከር ይቻላል። በተለይ ለሐይማኖታዊ ጉዙ የሚመጡ ጎብኚዎችን በመቀበል የአካባቢውን የቱሪዝም ገቢ ማሳደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ቢሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን የካቲት 3/2011
በጌትነት ተስፋማርያም