አዲስ ዘመን ጋዜጣ ዛሬ 80 ሻማዎች ተለኩሰውለታል። ስምንት አሥርት ዓመታትን ማስቆጠር የቻለ አባት የህትመት ሚዲያ ሆኗል። ጋዜጣው የተቋቋመውና የመጀመሪያ እትሙንም ይዞ የወጣው ልክ የዛሬ 80 ዓመት ግንቦት 1933 ዓ.ም ነው። አዲስ ዘመን እንኳን ለ80ኛ ዓመት አደረሰህ።
ጋዜጣው የተመሠረተበት ዘመን ታላቅ ታሪካዊ ክንውን የተስተናገደበት ወቅት ነበር ። ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን የወረረውን ፋሽስት ኢጣሊያን ወራሪ ሀይል ለእምስት ዓመታት በዱር በገደል ተዋግተው በ1933 ዓ. ም ድል ባረጉ ማግስት ነው የተጀመረው። የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለሥላሴ ከዚህ ድል ወዲህ ያለውን ብሩህ ዘመን አዲስ ዘመን ብለው ጠርተውታል። የአዲሱን ዘመን መጻኢ ተስፋ እንዲያበስር አዲስ ዘመን ብለው ሰይመውታል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ድምጽ፣ መረጃ፣ ዓይንና ጆሮ ሆኖ እያገለገለ እነዚህን ዘመናት መሻገሩ የኖረበትን እድሜ ያመለክታል። በርካታ ድርጅቶች እየተመሠረቱ ብዙም ሳይቆዩ ሲረግፉ በኖሩባት ሀገር ለእዚህ እድሜ መድረስ ትልቅ ቁም ነገር ነው። እንዲህ እንደ ዛሬው በርካታ መገናኛ ብዙኃን ባልነበሩበት ወቅት መንግሥትንም ህዝብንም ያገለገለ ባለውለታ አንጋፋ ጋዜጣ ነው።
ጋዜጣው በሀገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን እንዲበራከቱ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። የአዲስ ዘመን ጋዜጣ አሻራ በሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃንና ጋዜጠኞቻቸው ላይ ጭምር ያረፈ በመሆኑ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ታሪክ ውስጥ የራሱን ሚና ተጫውቷል፤ እየተጫወተም ይገኛል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በከፍተኛ የለውጥ ሂደት ውስጥ ይገኛል። የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን ሲያከናወን ቆይቷል፤ እያከናወነም ነው። በይዘትም በቅርጽም ለውጦችን እያሳየ ከ80 ዓመቱ ላይ ደርሷል።
የየእለቱን ሁነቶች እየዘገበና ታሪክን እየሰነደ ማቅረቡን አጠናክሮ በመቀጠል ይበልጥ ተነባቢ የሚያደርጉትን ዘገባዎች በትኩረት እየሠራ ነው። በእነዚህ ዘገባዎቹ ሳቢያም በሌሎች ሚዲያዎችና ምሁራን ዘንድም ተፈላጊና ተጠቃሽ መሆን ችሏል ። ይህ ትልቅ ስኬት የለውጡ ትሩፋት ነው ።
በፓለቲካዊ በኢኮኖሚያዊና በማህበራዊ ዘርፎች የሚካሄዱ ሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ተከታትሎ ይዘግባል፤ ትንታኔዎችን ይሰጣል። ፓለቲከኞችን፣ ምሁራንንና የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ በማድረግ መረጃ እየሰጠ፤ ኃላፊነቱን በሚገባ እንዲወጣ እያረገው ከመሆኑ በተጨማሪ በተለያዩ ሚዲያዎችና አካላት ዘንድ ተጠቃሽ ለመሆንም በቅቷል።
ህብረተሰቡ ድረስ በመውረድ የሚያቀርባቸው ሰው ሰው የሚሸቱ ዘገባዎችም ለጋዜጣው ተነባቢነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ እየተለወጠ መምጣቱን ለመመስከር ብዙ የሚቸግር አይደለም።
ለውጦቹ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጣውን ሊያደርስ ያሰበበት ከፍታ ላይ ለማድረስ አሁንም ገና ብዙ ሥራዎች ይጠብቁታል። ያለንበት የሽግግር ወቅት ከመሆኑ አንጻር በሽግግር ወቅት የሚከሰቱ ውዥንብሮችን በማጥራት፣ በእውነተኛ መረጃዎች ላይ በመመርኮዝ የለውጡን መሠረታዊ ሀሳቦች በህብረተሰቡ ውስጥ ከማስረጽ አንጻር ሰፊ ሥራ ይጠብቀዋል።
በጋዜጣው የሚስተዋሉ ለውጦች በአጋጣሚ የመጡ ሳይሆን መንግሥት ለመገናኛ ብዙኃን ከሰጠው ትኩረት፤ የድርጅቱ የቦርድ ሥራ አመራርና የማኔጅመንት አመራሮች እንዲሁም መላው ሠራተኞች እጅና ጓንት ሆነው በመስራታቸው የተገኘ ውጤት ነው ።
ድርጅቱ የጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ ሥራዎች በማስቀጠል የተሟላ ስኬት ለማስመዝገብ የራሱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረው ለማስቻል በቦርዱና በማኔጅመንቱ እየተደረገ ያለውን ጥረት መንግሥት በተገቢው መንገድ ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፈው ይገባል ።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እያጋጠመው ያለውን የህትመት ጥራት መጓደል ፤ ህትመት በወቅቱ አለመድረስ ከዛም በላይ ለህትመት የሚያወጣው ከፍ ያለ ወጪ አጠቃላይ በሆነው ተልእኮው ላይ ከዛም አልፎ በባለሙያዎቹ የለውጥ መነቃቃት ላይ እያሳደረ ያለው አሉታዊ ተጽእኖ ከፍ ያለ ነው ።
የህትመት የመገናኛ ብዙኃን ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ሊሠራቸው የሚገቡ ዘርፈ ብዙ የህትመት ሥራዎችን ለማከናወን የማተሚያ ቤት ባለቤት ያለመሆኑ ጉዳይ ከፍ ያለ ችግር መሆኑ፤ በዘርፉም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ያለውን ጠንካራ የተወዳዳሪነት መንፈስ እየጎዳው እንደሚገኝ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም ።
ለድርጅቱ ሁለንተናዊ እድገት ተግዳሮት የሆነውን የማተሚያ ቤት ችግር መፍታት ተቋሙን ማስፈንጠር ማለት ነው ፤ ተወዳዳሪ ማድረግ ማለት ነው ፣ለሀገር ኩራት የሚሆን አቅም ማጎልበት ማለት ነው ፣ከሁሉም በላይ የተሰጠውን ተልዕኮና ኃላፊነት መወጣት የሚያስችል ሞገስ ማላበስ ማለት ነው።
መንግሥት የድርጅቱ ቦርድና ማኔጅመንት ተቋሙን የማተሜያ ቤት ባለቤት ለማድረግ እያደረጉ ያለውን ጥረት በተገቢ መልኩ በማገዝ የተቋሙ የ80 ዓመት ታሪክ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዲሻገር ማድረግ ፤ እድሜውን የሚመጥን ተቋማዊ ቁመና እንዲላበስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። መንግሥት በሀገር አቀፍ ደረጃ የጀመረው የተቋም ግንባታ የለውጥ ምዕራፍ አካል መሆኑም በአግባቡ ሊታወቅ ይገባል !
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2013