ሙዚቃና የሰው ሌጅ ባህርይ ኢ-ተነጣጣይ ተዛምዶ እንዳላቸው ይነገራል።ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ሰው አምስት ባህርያት እንዳሉት ይጠቁማሉ።እነሱም ንፋስ፣ እሳት፣ ውሃ፣ አፈር እና ከእንስሳት የሚለዩት ድግሞ ሦስቱ ባህርያተ ነፍስ (አሳቢነቱ፣ ተናጋሪነቱና ሕያውነቱ) ናቸው። እነዚህ ባህርያቱ ከውልደት እስከሞት ድረስ ባለው አንዱ አንዱን እያየለው ይንፀባረቃሉ።
ሙዚቃን ከውልደትና እድገት ጋር ተዛምዶ ባላቸው እንደ ግርዛት፣ ክርስትና፣ ወሊድ፣ ሠርግ፣ ለቅሶ፣ እርቅ ባሉት ይጠቀምበታል።ከስራ ጋር በተያያዘ ኩነቶች እርሻ፣ አጨዳ፣ ውቂያ፣ ከብት ጥበቃ፣ ወፍጮ፣ አደን፣ ጉዞ፤ ማህበራዊ ተቋማት ደቦ፣ ወንፈል፣ ማህበር፣ ማህበራዊ ፌስቲባሎችና ስርዓተ ከበራዎችን፣ የአካባቢውን መስተጋብር፣ ታሪኩን፣ ፍልስፍናውን፣ የኑሮ መሰረቱን፣ ሃሊፊውንና መጻኢውን ይገልጽበታል።
ሙዚቃ፤ የሰውን ሌጅ ባህርይ ቅርፅ (መልክ) ከሚያሲይዙ ነገሮች ውስጥ ቀዲሚው፣ ለሰው ልጅ ከሚያስፈልጉ መሰረታዊ ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ አንዱ ነው።… ሙዚቃ የግለሰቦችን ባህርይ በመግራት የወጡበትን ማህበረሰብ ግንዛቤ እንዲያውቁ ያደርጋል።
ሰዎች በሙዚቃ አማካኝነት በሚያገኙት ግንዛቤ የማህበረሰባቸውን ርዕዮተ ዓለም፣ ስሜቶችን፣ አመለካከቶችን፣ ማህበራዊ ደንቦችን ይጋራሉ።ይህ በተራው በሙዚቃ የሚከወን ትልቅ ልምድ ይፈጥራል።ሙዚቃ የአንድ ማህበረሰብ ሁለንተናዊ ነገር መገላጫው ከሆኑላቸው የአገራችን አካባቢዎች አንዱ ደግሞ ወሎ ነው፡፡
ወሎ በኢትዮጵያ ሰሜን ምስራቅ የሚገኝ በአሁኑ የአስተዳደር መዋቅር በአማራ ክልል በሁለት ዞኖች ማለትም ደቡብ ወሎና ሰሜን ወሎ ተብሎ የተከፈለ ሲሆን፤ ለዘመናት አብረውት የኖሩ የፍቅር፣ ሠላም፣ መቻቻል እና አብሮነት እሴቶች ያለው አካባቢ ተብሎ ይጠቀሳል።በሙዚቃው ዘርፍም ከቅኝት አንስቶ እስከ ከያኒያን ድረስ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል።
በደብረ ብርሀን ዩኒቨርሲቲ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር ጋሻው አይፈራም በወሎ ባህላዊ ሙዚቃዎች ላይ ባደረጉት ጥናት እንዳመላክቱት፤ ወሎ በርካታ ሃገረሰባዊ ልማዶች (social folk customs) ለምሳሌ አድባር፣ ዱዓ፣ (ወዳጃ)፤ ባህላዊ ተቋሞች ሽምግልና፣ ቅሬ፣ አባጋር ያለ ሲሆን፤ እነዚህ ተቋማት ማህበረሰቡን በማስተሳሰር ረገድ ከፍተኛ ሚና አላቸው።አብሮነትና መቻቻል የወሎ ልዩ እሴቶች ናቸው። ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች መቻቻል የሰፈነባት አገር መሆኗን ማሳያው ወሎ ነው።
እንደ መምህሩ ገለጻ፤ ሠላም አንድ ወጥ የሆነ ብያኔ የለውም። የአብሲኒያ ኢንተርኔት መዘገበ ቃላት ሠላም የሚለውን ቃል “አማን፣ ደኅና፣ ደኅንነት፣ ጤና፣ ዕረፍት ፣ ፀጥታ፣ ፍቅር፣ አንድነት፣ ምሥጋና” ሲል እንደሚያብራራው በመጥቅስ ያስረዳሉ።ሠላም “የፍቅር ፍሬ ነገር ያማረ የተወደደ የቀና ነገር ፍቅር አንድነት መስማማት በሀሳብ በሥራ መገባባት ይኼ የኔ ነው ያንተ አይደለም እየተባባሉ አለመቀማማት እንደ አንድ ነፍስ እንደ አንድ ሥጋ መኾን ነው” በማለትም ብያኔዎችን ያጣቅሳሉ።አብዛኞቹ ምሁራን ሠላም ማለት ጦርነት፣ ሁከትና ብጥብጥ አለመኖር በማለት የሚገልጹትንም ፍቺ ይጠቅሳሉ።
ከዚህ አንጻር ሠላም የብያኔ ጉድለት አለበት ሲሉ ያመለክታሉ። ምክንያቱ ደግሞ ሰው ከራሱ እና ተፈጥሮ ጋር የሚያደርገው ግጭት የሠላም ተጻራሪ በመሆኑ ነው ይላሉ።የተለያዩ መዘገበ ቃላት ሠላምን ጦርነት ወይም ውጊያ የማይካሄድበት ሁኔታ ወይም አለመኖር፣ ጦርነት ለማቆም መስማማት፣ የፀጥታ እና እርጋታ መስፈን በማለት እንደሚገልጹት ነው መምህር ጋሻው የሚያብራሩት።
አለቃ ኪዲነ ወልድ ክፍሌ ሠላም የሚለው ቃል “ፍጹም ጤና፣ ዕርቅ፣ ዕረፍት፣ አንድነት፣ ደህንነት፣ ተድላ፣ ደስታ፣ ቡራኬ፣ የምርቃት ቃል፣…” በማለት በይነውታል። የአለቃ ኪዲነ ወልድ ክፍሌ ብያኔ የወሎን የሠላም እሴት ከመግለጽ አኳያም ጉልህ ሚና እንዳለውም መምህር ጋሻው ይገልጻሉ።
አንደኛ ሠላም ፍጹም ጤና በማለት ተርጉመውታል፤ ፍጹም ጤና አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና አዕምሯዊ ጤናን ከማመልከቱም በላይ የአንድ ማህበረሰብ ጤናማ እንቅስቃሴን ያሳያል።ከዚህ አንጻር ወሎ እንደ ማህበረሰብ ጤነኛ ሊያስብሉት የሚችሉ ማሳያዎች አሉት።
ሁለተኛ ሰላም ማለት እርቅ ነው ብለዋል።ፍጹም የሆነ እርቅ ዋልታዎቹ እውነትና ይቀርታ ናቸው።በእርቅ የጠፋው ሰላም ወደነበረበት ይመለሳል፤ ደስታና ሃሴት ይሞላል ሲሉ ያብራራሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ወሎ እርቅ አንዱ መለያው ነው። ቀለል ያሉ በግለሰብ ደረጃ ያሉ ፀቦች ከሁለቱ የግጭት ተዋናዮች አንዱ ‹‹አፉ በለኝ›› ካለ ሠላም ይወርዳል።ከዚህ ውጭ ወሎ ማህበራዊ መሠረት ያላቸው፣ ግጭትን የሚከላከሉ እና የሚፈቱ ተቋማት አሉት።እነሱም አባጋር፣ ቅሬ እና ሽምግልና ናቸው።
ሦስተኛ ሠላም ዕረፍት፣ አንድነት፣ ተድላና ደስታ ነው በማለት ገልፀውታል።ፍጹም ይቅርታ ሲኖር የተለያየው አንድ ይሆናል።አራተኛ ሠላም የምርቃት ቃል ቡራኬ፣ ሰው ሲገናኝና ሲለያይ የሚናገረው ነው በማለት አስቀምጠውታል። ከዚህ አንጻር ወሎ ሠላምን የሚያጎሉ፣ የሚያውጁና የሚያበስሩ የሠላም እሴቶች አሉት። ሲመርቅ ልጄ አቦ በረካ/ኸ/ ሁን፣ ተባረክ፣ ብሩህ ኩን፣ ማሻ አላህ፣ ኸይር ይመልስህ።
ፍቅር ሌላኛው የወሎ እሴት ነው። ፍቅር ሁሉንም የሚያስማማ ወጥ የሆነ ብያኔ የለውም የሚሉት መምህር ጋሻው፤ ዓይነቱም ብዙ እንደሆነ ይገልጻሉ።አለቃ ኪዲነ ወልድ ክፍሌ ፍቅር የሚለውን ቃል “ውዴታ፣ ይቅርታ፣ እርቅ፣ ሠላም፣ የልብ አንድነት፣ ሥምምነት፣ ረቂቅ፣ መጣበቅ፣ የሃሳብና የአዕምሮ ሙጫ፣” በማለት የበየኑትን መምህር ጋሻው ይጠቅሳሉ።በዚህ መነሻነት የወሎን ባህላዊ ሙዚቃ የሠላምና የፍቅር እሴት ከመግለጽ አኳያ ያላቸውን ሚና እንመልከት።
ወሎ የቅኝት መፈጠሪያ ከመሆኗም በላይ ብዙ ከያኒያንን አፍርታለች። እጅግ ብዙ የሆኑ የባህል ሙዚቃዎች ያላት ሲሆን፤ ለዚህም እንደ አንዳርጌ ወርቁ (ወሎ)፣ መሠረት በለጠ (እሪኩም ዘመዳ) ዜማ የህዝብ፣ ማሪቱ ለገሰ (ከመከም)፣ አማረ መንበሩ (ደሴ ላይ)፣ መብሬ መንግሥቱ (ወሎ ላይ ያለሽው) የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው። በእነዚህና ሌሎች ሙዚቀኞች የሚቀነቀኑ የወሎ ሙዚቃዎች የወሎን የፍቅር፣ ሠላም፣ መቻቻልና አብሮነት እሴትን ከመግለጽ፣ ውክልና ከመስጠትና ህልው ከማድረግ፣ ከብዝሀነት አንጻር ያላቸው አንድምታ ብዙ ነው።
በተለይ የብዝሀነት ውክልናን ከመስጠትና አካባቢዎችን በማንሳት “እሪኩም” የህዝብ ዘፈን ልዩ ቦታ ይይዛል። እሪኩም በወሎ ላሊበላ የኪነት ቡድን፣ ጌታቸው ዘውዱ፣ ታደሰ አለሙና ሌሎች በአማርኛ እንዲሁም ረመዲን ጭሜሳ በኦሮምኛ የዘፈኑት ሲሆን፤ ሁሉንም የወል አካባቢ ከውበት፣ ፍቅር፣ አብሮነት እና መቻቻል ጋር ያነሱታል።
ለምሣሌ የታደሰ አለሙ እሪኩም ዘፈን የፍቅር ምሳሌ የሆኑትን ጦሳና ቦርከና፤ የወሎ አካል የሆኑ ኬሚሴ፣ ቃሉ፣ ዋድላ፣ ደላንታ፣ አምባሰል፣ ወረባቦ፣ የጁ፣ ቦረና፣ ሳይንት፣ ወልድያ፣ ሰቆጣ፣ ቆቦ፣ ራያ፣ አዘቦን በመጥቀስ የኦሮምኛ ቃላትንም ተጠቅሟል።
ደሴ ላይ ተወልዳ ያደገች ኬሚሴ
ፍቅሯ የሚያድን ነው እንደ ዳማ ከሴ። ሲል አንዳርጌ ወርቁ፤ ሙዚቃና ወሎ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን ለማሳየት በደሴ ተወልዳ በኬሚሴ እንዳደገች መገለጫዋ ፍቅር መሆኑን ያሳያል።
መርሳና ኡርጌሳ ወልድያና ቆቦ
እንዴት ይዘልቀዋል ልቤ አንተን አስቦ
መምከንከን ነው እንጂ እሪኩም እያለ
ወሎ ከወደደ ሸር ተንኮል የለ። በማለት የምታቀነቅነው ደግሞ መሠረት በለጠ ናት።ይህ ስንኝ በወሎየነት ሸር መሸረብ፣ ተንኮል ማሴር እንደሌለ ከማሳየትም በላይ ፍቅር ወይም መውደድ በራሱ መጨረሻ የሆነ ኢ ተለዋዋጭ እሴት መሆኑን ያመለክታል። በተቃራኒው ፍቅርን፣ ፍላጎትን እና ስሜትን ለመግለጽና ለመፈፀም እንደ መሳሪያነት የሚጠቀሙ መኖራቸውንም ያሳያል። በተንኮል የተቃኘ ፍቅር የወሎ እሴት አለመሆኑን ይገልጻል።
ለዛሬው ይብቃን። የወሎን ባህላዊ እሴት የሚገልጹ ሌሎች ሙዚቃዎችን በሌላ ጊዜ ይዘን እንደምንቀርብ ቃል በመግባት እንሰናበት።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2013