በ19 መዝገቦች ላይ ‹‹የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ተፈጽሟል›› የሚል ሃሳብ ቀረበ

አዲስ አበባ፡- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከቀረቡለትና ከመረመራቸው አቤቱታዎች መካከል በ19 መዝገቦች ላይ ‹‹የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ተፈፅሟል›› በሚል ሃሳብ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

የአጣሪ ጉባዔ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዬሳ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ አጣሪ ጉባዔው በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 82/1/ መሠረት ተቋቁሞ በአንቀፅ 84/1/ መሠረት ለጉባዔው የሚቀርቡትን ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች የማጣራት ሥልጣን ያለው ተቋም ነው። ጉባዔው ማንኛውም ሕግ ወይም የመንግሥት አካል ወይም የባለሥልጣን ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረንና የሚጋጭ ሆኖ ሲያገኘው በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል። የሕገ መንግሥት ትርጉም የማያስፈልገው ሲሆን የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ ይወስናል ብለዋል።

ጉባዔውም በየጊዜው ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች አስተማማኝና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በሁሉ ረገድ ሁለንተናዊ አቅምና አሠራርን በማጎልበት ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ውጤታማ የሚባሉ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

ጉባዔው ባለፉት ዘጠኝ ወራት ‹‹የሕገ መንግሥት መብታችን ተጥሷል፣ የሕገ መንግሥት ትርጉም ይሠጥበት›› በማለት ከቀረቡለት አቤቱታዎች መካከል ከአንድ ሺህ 692 መዝገቦች ላይ ጥናትና ምርምር አድርጓል። ከእነዚህ መካከል አንድ ሺህ 274 አቤቱታዎችች ላይ የውሳኔ ሃሳብ አሳልፏል። ከእነዚህም ውስጥ በ19 የትርጉም አቤቱታዎች ላይ የሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ተፈፅሟል በሚል የውሳኔ ሃሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ልኳል።

እንደ አቶ ደሳለኝ ገለፃ፣ ሕገ መንግሥታዊ ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል ተብለው በጉባዔው ከተለዩ መዝገቦች መካከል የተከሰሱ ሰዎች መብት እና የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሠራም የሚለውን ድንጋጌ የጣሱ እንዲሁም የእኩልነት መብት የሚፃረሩና ከንብረት መብት ጥሰት ጋር የተቆራኙት አብላጫውን ድርሻ ወስደዋል፡፡፡

ጉባዔው ከተመለከታቸው የአቤቱታ መዝገቦች መካከል አንድ ሺህ 1108 በሚሆኑት የሕገ መንግሥት ጥሰት አልተፈፀመባቸው በሚል የውሳኔ ሃሳብ ማሳለፉን የጠቆሙት ኃላፊው፣ 147 መዝገቦች ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ተጠሪዎች ምላሽ እንዲሰጡበት መምራቱንና ቀሪዎቹን መዝገቦችም በጥናትና ምርምር የማጥራት ሂደት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ጉባዔው በአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንቡ መሠረት አቤቱታዎች በቀረበበት ቅደም ተከተል ቢመለከትም በልዩ ትኩረት ቅድሚያ የሚታዩ አቤቱታዎች እንዳሉ ያመላከቱት አቶ ደሳለኝ፣ የሴቶች፣ ህፃናት፣ የአካል ጉዳተኞችን በፍርድ ተከሶ በማረሚያ ቤት ያሉ ጉዳዮችን ቅድሚያ ከሚሰጣቸው መካከል መሆናቸውን ነው ያሳወቁት፡፡

የጉባዔው የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ ፈጣንና ውጤታማ ውሳኔ በመስጠት ሂደት የአቤቱታ አቀራረብ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መሻሻልን የጠቆሙት አቶ ደሳለኝ፣ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ለመደበኛ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለባቸው አቤቱታዎች ለጉባዔው እንደሚቀርቡና ይህ ፈፅሞ ሊታረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

‹‹ለጉባዔው የሚቀርቡ አቤቱታዎችም በቀጥታ በሕገ መንግሥት መብት ጥሰት ላይ ማእከል ያደረጉ መሆን አለባቸው›› ያሉት ኃላፊው፤ ጉባዔው ለውሳኔ አሰጣጥ ቅልጥፍና የሚያግዙ ተግባራትን ለማጎልበት በተለይ የቴክኖሎጂ አሠራርን ለመተግበር ከኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ጋር ስምምነት መፈፀሙንም ገልፀዋል፡፡

የዲጅታል ሥርዓቱ (ሲስተሙ) ዘርግታ ከ70 በመቶ በላይ መጠናቀቁንና ወደ ሥራ ሲገባም የጉባዔው አሠራር ከማቀላጠፍ ባለፈ ተገልጋዮችን የጉዞ እንግልት እንደሚያስቀር ጠቁመዋል፡፡

አቶ ደሳለኝ፣ ኢትዮጵያ የፊታችን ህዳር 2025 (እ.ኤ.አ) 4ኛውን የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ጉባዔ በብቃት ለማስተናገድ አስፈላጊውን ዝግጅት ከወዲሁ እያከናወነች እንደምትገኝ አሳውቀዋል፡፡

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You