የትራፊክ አደጋ መዘዝ

በ2016 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ ከሶስት ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸው እና ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት መውደሙን የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት መረጃ ያሳያል። ለአደጋዎች መንስኤ ከሆኑ ምክንያቶች ከ68 በመቶ በላይ የሚሆነው በአሽከርካሪዎች ስህተት ሲሆን፤ ከፍጥነት ወሰን ማለፍ አንዱ ችግር ነው።

ምናልባት አንድ መኪና አደጋ ቢገጥመው የጉዳቱን መጠን በፍጥነት ወሰኑ የሚወሰን መሆኑ ይነገራል። ችግሩን ከመፍታት አንጻር የመንገድ ደህንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ከብሉምበርግ ፒላንትሮፒስ ኢንሼቲብ ጋር በመተባበር ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር የሚደርሰውን አደጋ የሚያሳይ የሚዲያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻ በትናንትናው እለት አስጀምሯል።

በአገልግሎቱ የትምህርትና አቅም ግንባታ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሐንስ ለማ እንደሚናገሩት፤ የመኪና አደጋ እድሜያቸው ከአምስት እስከ 29 የሚገኝ ህጻናት እና ወጣቶች በመግደል ሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋ ከሚባሉ አንደኛ የሚባል ቢሆንም ያን ያህል አልተወራለትም።

እ.አ.አ በ2012 ተሠርቶ በ2023 ይፋ በሆነ መረጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየዓመቱ አንድ ነጥብ 19 ሚሊዮን ሰዎች በመኪና አደጋ ሕይወታቸው ያልፋል። ከ30 እስከ 50 ሚሊዮን የሚጠጉት ደግሞ ከባድ እና ቀላል አደጋ የሚያጋጥማቸው ሲሆን፤ በሚከሰተው የመንገድ ትራፊክ አደጋ ከስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ሀብት ይወድማል ይላሉ።

በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት ታዳጊ ሀገራት የተመዘገበ የመኪና ቁጥር አንድ በመቶ ቢሆንም፤ ነገር ግን ለሞት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ 13 በመቶ ነው። በሠለጠኑት ሀገራት የተመዘገበ የሚኪና ቁጥር 40 በመቶውን የሚሸፍን ሆኖ፤ ለአደጋ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ሰባት በመቶ ብቻ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ዮሐንስ እንደሚገልጹት፤ በ2016 ዓ.ም ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የገባው ተሽከርካሪ ቁጥር 67ሺህ 633 ነው። በዚሁ ዓመት 47 ሺህ 571 ተሽከርካሪዎች አደጋ ደርሶባቸዋል። ይህም በአንድ በኩል መኪናዎች ተገዝተው የሚገቡ ቢሆንም፤ በአደጋ ምክንያት እንደምናጣቸው ያሳያል።

ባለፈው ዓመት በትራፊክ አደጋ 3 ሺህ 111 ዜጎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ከ10 ሺህ ያላነሱ ዜጎች ቀላልና ከባድ አደጋ ደርሶባቸዋል። ከንብረት አንጻር ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል ይላሉ።

በሚከሰቱ የትራፊክ አደጋዎች በስፋት የሚጎዱት ተሳፋሪዎች መሆናቸውን በመግለጽ፤ ተሳፋሪዎች 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚዙ ሲሆን፤ እግረኞች 33 በመቶ እና አሽከርካሪዎች 14 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንደሚይዙ ይገልጻሉ።

የመንገድ ትራፊክ አደጋ መንስኤዎችን የሚያነሱት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ የመጀመሪያው በህብረተሰቡ ሥነባህሪ ሲሆን፤ በዚህም አሽከርካሪዎች ዘንድ ያለ ቸልተኝነት እና የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ሥርዓት ያለመዳበር ችግር ነው። ሌላኛው የአደጋ መንስኤ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር እና የመንገድ ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ።

የአደጋ ድርሻው ሲታይ ከ68 በመቶ በላይ የሚሆነው አደጋ የሚከሰተው በአሽከርካሪዎች ስህተት ምክንያት ሲሆን፤ ከፍጥነት ከወሰን በላይ ማሽከርከር፤ ደርቦ ማለፍ፤ ጠጥቶ ማሽከርከር፤ ቅድሚያ ባለመስጠት እና ሌሎች ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸው። ነገር ግን አሽከርካሪዎች ደርበው በማለፋቸው እና ቅድሚያ ባለመስጠታቸው ሲቀጡ አይታይም ይላሉ።

በሌላ በኩል 14 በመቶ የሚሆነው በተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት ችግር፤ የመንገድ ችግር ደግሞ 11 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ይይዛል። በኢትዮጵያ የመኪና አደጋ ከጨለማ ይልቅ በብርሃን፤ ምቹ በሆኑ መንገዶች፤ በባለ ሁለት አቅጣጫ መንገዶች ላይ ነው በስፋት ይሚከሰተው። በመሆኑም ይህን ችግር ለመፍታት በአሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

ችግሩን ለመግታት የትራፊክ መቆጣጠሪያ ሕግ ማጠናከር፤ አሠራሮችን ማዘመን፤ ለአሽከርካሪዎች ሥልጠና መስጠት እና በሚዲያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራትና አቅጣጫ በማስቀመጥ በአገልግሎቱ በኩል ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።

ከገጠመኛቸው የሚነሱት የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ፤ እንደሚናገሩት፤ በአንድ ወቅት አንድ እናት ልጇን ወደ ትምህርት ቤት አድርሳ ስትመለስ የመኪና አደጋ ገጥሟት ሕይወቷ በማለፉ፤ ልጇን ከትምህርት ቤት የሚያመጣት ሰው ጠፋ።

በዚህ ምክንያት የኢንሹራንስ ኩባንያው እንዲወስዳት ተደረገ የሚሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ በትራፊክ አደጋ ምክንያት በርካታ ህጻናት አሳዳጊ በማጣት ጎዳና ላይ ይወድቃሉ። ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸውን 31 ልጆች አገልግሎቱ በየወሩ ወጪ በማውጣት እያስተማረ ይገኛል ነው ያሉት።

የትራፊክ አደጋ ይህን ያህል ሰው ሞቷል ተብሎ የሚታለፍ ጉዳይ አይደለም። አደገኛ የማህበራዊ ቀውስ ያስከትላል። በዚህ ረገድ ሚዲያዎች የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ቀዳሚ አጀንዳ አድርገው ሲሠሩበት እንደነበረው ሁሉ በትራፊክ አደጋ ላይም በስፋት ሊሠሩ ይገባል ይላሉ።

ለትራፊክ አደጋ ዋናው መንስኤ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር መሆኑን የሚያወሱት ሥራ አስፈጻሚው፤ አደጋውን ለመቀነስ ለዜጎች ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ከዚህ ረገድም የሚዲያ አካላት ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ ይገልጻሉ።

የትራፊክ አደጋ በየዓመቱ የመቀነስ ሁኔታ እያሳየ ቢሆንም፤ የሚጠፋው የሰው ሕይወት እንደመሆኑ ቀጣይ ሥራዎች ያስፈልጋሉ የሚሉት የመንገድ ደህንነት ባለሙያ ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ፤ በአንድ የመኪና አደጋ 20 እና 30 ሰው የሚሞተው ዋነኛው መንስኤው ከፍጥነት በላይ የማሽከርከር ችግር ነው። እንደዚህ አይነት የከፋ አደጋዎች በስፋት የሚደርሱት ደግሞ ከከተማ ውጪ ነው ሲሉ ይገልጻሉ።

የፍጥነት ወሰን ቁጥጥር እየተደረገ ያለው ከተማ ውስጥ ነው የሚሉት ኢንፔክተር አሰፋ፤ ከተማ ውስጥ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ በፍጥነት ለማሽከርከር አመቺ አደለም። ከፍጥነት ጋር በተያያዘ በስፋት ከከተማ ውጪ መሥራት ቢቻል መልካም ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን  ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You