ከቤት እመቤትነት እስከ ድርጅት ባለቤትነት

ሰሚራ ሃይረዲንና ሦስቱ ጓደኞቿ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ባለትዳርና የቤት እመቤት ሲሆኑ ተደራጅተው የራሳቸው የግል ሥራ የመሥራት ሃሳብ ነበራቸው። ስለሚሠሩት ሥራ ከመከሩ በኋላ በደንብ እውቀቱ እንዲኖራቸው በማሰብ ከሥራው ጋር አብሮ ሊሄድ የሚችል ሙያ ለመቅሰም ተማሩ። በዚህም የዲዛይኒንግ ሙያ ባለቤቶች መሆን ቻሉ።

የገበያ ጥናት አድርገው የወንዶች ሕጻናት ልብሶች ለማምረት በማሰብ ሥራ ጀመሩ። ከተደራጁ በኋላ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የመሥሪያ ቦታ ሼድና መነሻ ብድር ስላገኙ ሥራቸውን አሃዱ ብለው ጀመሩ።

በ2015 ዓ.ም ሰሚራና ፋጡማ ጨርቃጨርቅና ህብረት ሽርክና ማህበር የተሰኘ ድርጅት መሠረቱ። አሁን ላይ ሥራውን ከጀመሩ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ገደማ ሆኗቸዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ያሳዩት ለውጥና እያስመዘገቡ ያለው ውጤት በተለይ ለሴቶች አርአያ የሚሆን ነው።

ሥራውን አሃዱ ብለው ሲጀምሩ በ100 ሺህ ብር ካፒታል የጀመሩ ሲሆን አሁን ላይ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ማስመዘገብ ችለዋል። ከጥቃቅን ወደ አነስተኛ አምራችነት ተሸጋግረዋል። ከ90 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ቋሚ የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።

ሥራውን ሲጀምሩ ብዙ ሰዎች አትችሉትም ጀምራችሁ ከምታቋርጡ ቢያንስ በትንሹ ጀምሩ ሲሉ ነበር የምትለው ሰሚራ፤ ‹‹ምንም እንኳን ሰዎች ቢያስፈራሩንም እኛ ግን እርስ በርሳችን እየተበረታተንና እየተደጋገፍን ሥራውን በትልቁ ለመጀመር በማሰብ በቁርጠኝነት ለመወጣት ችለናል›› ትላለች።

ወደ ቢዝነሱ ስንገባ ሥራውንም በደንብ ለማወቅ የሌሎች ሴቶች ልምድና ተሞክሮ ለመቅሰም ጥረት ማድረጋቸውን ትገልጻለች። አራት ሆነው ቢደራጁም ሥራውን ሲጀምሩ ለተጨማሪ ስድስት ሰዎች የሥራ እድል በመፍጠር አስር ሆነው መጀመራቸውን ታስታውሳለች።

ከመነሻው የወንዶች ሕጻናት ልብስ ለመሥራት የመረጡት ምክንያት አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ጥራት ያለው ሥራ በመሥራት የበለጠ ውጤታማ ለመሆን በማሰብ እንደሆነ ሰሚራ ተናግራለች። አሁን ላይ ድርጅቱ የወንዶች ሕጻናት ልብስ በማምረት ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በስፋት እያቀረበ መሆኑን ገልጻ፤ ጥራት ላይ ትኩረት አድርገው በመሥራታቸው ምርቶቻቸው የገበያ ተቀባይነት እንዲያገኙና ተደራሽነት በማስፋት ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ባሉ በተለያዩ ክልል ከተሞች የገበያ ትስስር በመፍጠር እያስረከቡ መሆኑን ትገልጻለች።

ሰሚራ እንደምትለው፤ ድርጅቱ አሁን ላይ በወር ከ15ሺ ፍሬ በላይ ልብሶችን ያመርታል። ልብሶቹን ለማምረት ግብዓትነት የሚውሉ ማቴሪያሎችን ከአስመጪዎች በመግዛት ይሠራል። በተጨማሪም በሀገር ውስጥ ባሉ ግብዓቶችም ተጠቅመው የሚሠሩ ጅንስና የመሳሠሉ ጥራት ያላቸው ልብሶች ያመርታል።

ድርጅቱ ተኪ ምርት በማምረት ከውጭ በከፍተኛ ዶላር የሚገባው ምርት በሀገር ውስጥ እየተካ ነው። ጥራት ያለው የተሻለ ምርት እያመረተ በመሆኑ በተለያዩ በሚመለከታቸው አካላት የምስክር ወረቀት ተሠጥቶታል ብላለች።

የግብዓት እጥረት ለመፍታት አቅማቸው በፈቀደ መሠረት ክፍተቶችን እያሟሉ በመሥራት ላይ መሆናቸውን ጠቅሳ፤ በዚህም ለብዙ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠር መቻላቸውን ትጠቁማለች።

ሰሚራ እንዳብራራችው፤ የልብሶቹ ዋጋም የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም ያማከለ ነው። በዋጋ ከውጭ ከሚመጣው አንጻር ሲታይ በግማሽ የሚቀንስና በጥራት የበለጠ ነው። ዋጋቸው እንደየልብስ አይነት የሚለያዩ ቢሆንም ሙሉ ልብሶች ከ800 ብር እስከ ሁለት ሺህ ብር ዋጋ ወጥቶላቸዋል። ቲሸርት ብቻውን ከሆነ ግን ከ300 እስከ 400 ብር ይሸጣል።

የምናመርታቸውን ምርቶች የሚረከቡን ደንበኞች ምርቶቹ የተሻለ ጥራት ስላላቸው በብዛት እንድናመርት ይጠይቁናል የምትለው ሰሚራ፤ ‹‹እኛም ስንጀምር ጀምሮ ጥራት ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው። በተለይ የኢትዮጵያን ምርቶች ጥራት ደረጃ በማሻሻል የተሻለ ማምረት እንደምንችል በምርቶቻችን እያስመሰከርን ነው››ትላለች።

ወደ ሥራ ሲገባ ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ገልጻ፤ ሴቶች በመሆናቸው የማምረቻ ቦታ ከማግኘት ጀምሮ ብዙ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች አጋጥሟቸው እንደነበር ታነሳለች። ሴት እንደምትችል ጠንክረው ሠርተው በማሳየታቸው ለብዙ ሴቶች አርአያ በሆናቸውም ብዙ ቦታዎች ላይ እየተጋበዙ ተሞክሯቸውን እንደሚያከፍሉ ትገልጻለች።

‹‹ሴቶች ስለሆንን ሠርተን አሳይተን፣ አሳምነናል። ሁለት ዓመት ከስድስት ወር በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሚጠበቀው በላይ ለውጥ አምጥተናል፤ ሴቶች መሥራት እንደምችሉ አስመስክረናል ›› ብላለች።

ሴቶች በተሠማሩበት የሥራ ዘርፍ ሁሉ ከወንዶች እኩል መሥራት እንደሚችሉ ራሳቸውንም አሳምነው ሠርተው ማሳየት አለባቸው የምትለው ሰሚራ፤ በማንኛውም ሥራ ዘርፍ ተግዳሮቶች ሊኖሩ ስለሚችሉ ሴቶች ከሁሉ በላይ ሳይፈሩ በሚፈልጉት ሥራ ተሠማርተው አሸንፈው ለመውጣት ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ትላለች።

በቀጣይ ሀገር ውስጥ ያለውን ፍላጎት ለማሟላት በደንብ መሥራት ተደራሽነት ለማስፋት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን የምትገልጸው ሰሚራ፤ ለልብስ መሥሪያ ግብዓት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ከውጭ በማምጣት ሀገር ውስጥ ለማምረት በሂደት ላይ መሆኑ ትገልጻለች። ከዚህ ባሻገርም ምርቶች ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን ጠቁማለች።

በሚቀጥሉት ጊዜያትም የማምረቻ ቦታ ማስፋፊያ ምላሽ የሚያገኝ ከሆኑ ሥራውን በማስፋት ከ500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ድርጅት የመሆን ራዕይ መሰነቃቸው ሰሚራ ትገልጻለች።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You