ቅኔ ጥበብ

ቅኔ አልባ ኪነ ጥበብ፤ ጨው አልባ ምግብ፣ ንብ አልባ ቀፎ ማለት ነው:: እንደ ሁኔታው ጨው አልባ ምግብ እንመገብ ይሆናል፣ ንብ አልባ የንብ ቀፎ ሰቅለንም ንብ እንጠብቅ ይሆናል፤ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ግን፣ ጥበብ ያለ ቅኔ ባዶነት ይጎላባታል:: ለአንዳንዶች ካልሆነ በስተቀር ለብዙሃኑ አፍቃሪዎቿ አሰልቺ ሆና ትታያለች:: ማር ምን ጣፈጠ ተብሎ ምሳ፣ ቁርስ እራት አይበላም ወይንም አይላስም:: ቅቤ ምን ውዱ ማጣፈጫ ቢሆን እንደማር አይላስም:: እንደ ሻይ ወይንም ቡናም አይጠጣም:: ቅኔም እንዲሁ ነው:: ራሱ ጥበብ ሆኖ ሳለ፣ እንደገና ሌላ የአጠቃቀም ጥበብን ይፈልጋል::

ቅኔ በራሱ ጣፋጭ ጥበብ ሆኖ ሲከሰት ለክተው እንደማር ይልሱታል:: ጣፋጩን ቅኔ ለማጣፈጫነት ስንጠቀምበት ደግሞ እንደ ቅቤ ወይንም እንደ ጨው መጥነን ለመደቆስ ልኬቱን የምናውቅበት ሙያ ያስፈልገናል:: የቅኔ መጉደል ኪነ ጥበብን ያደርቃል፣ ልኬት አልባ የሆነ እንደሆንም ወይንና እንቧዩ የማይለይበት ድፍን ይሆናል::

‹ቅኔ› ሲባል ምንድነው? ምን መልክስ አለው? ቅኔ ብዙ ዓይነት፣ ሕቡ መልክ፣ ረቂቅ ባህሪ፣ ውስብስብ ማንነትና ጥልቅ የምንነት መገለጫ ያለው ቃልና አንዳንዴም ምስል ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ ወጣ ያለ ሌላ ይዘት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን:: ረቂቅነቱ እንዳለው የሚከተል ቢሆንም “ቅኔ” አምላክን ማመስገኛ መዝሙር ማለትም ነው:: ‹ቅኔ መናገር› እና ‹ቅኔ መቀኘት› ሁለቱም ለየቅል ናቸው፤ ሁለቱም ግን ጥበብ ናቸው::

የመጀመሪያው ብዙዎቻችን እንደምናውቀው፣ ዘይቤያዊና ፈሊጣዊ መሰል ቃላት የተቀላቀሉበት ነው:: ቅኔ መቀኘት ግን የስሙ ትርጓሜ የመጣበት መንገድም ጭምር ነው:: “ቀነየ” ከሚል የግእዝ ቃል መውጣቱን ሊህቃን ያሰፍሩታል:: ትርጉሙንም ‹አመሠገነ› ማለት ነው ይላሉ:: ታዲያ ብዙዎች የምናውቀው ቅኔ ከማመስገን ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር አለው? ምሥጋናው እንዲሁ በአንደበት ብቻ ሳይሆን በዝማሬ የሚቀርብ ምሥጋና ነው:: ዝማሬ ደግሞ በግጥምና ዜማ የሚሠራ ጥበብ እንደመሆኑ ድልድዩን በዚህ ጋር ልንሠራለት እንችላለን:: በሁለተኛ ፍቺው ገዛ፣ ዘር፣ ጥሬ…መሰል ትርጓሜዎችን ያስቀምጡለታል:: ምናልባት ይሄኛው በቀጥታ የሚቀራረብ ነገር ሳይኖረው አይቀርም::

እንግዲህ ሁለቱንም ቅርጾች ጨፍልቀን አንድ ወጥ ስናደርገው ቅኔ ጥበብ ነው:: በረቂቅ መንገድ ላይ የሚዘረጋ ረቂቅ እርምጃ ነው:: የሚታይ ግን በዋዛ የማይገለጥ፣ የሚቆጠር ግን ውስብስብ አሐዛዊ ቀመር ነው::

ቅኔ ሦስት መሠረታዊ አላባውያን ይገኙበታል:: ሦስቱንም የምናገኘው ግን፤ የመጀመሪያው አላባዊ በሆነው ‹ሕብረ ቃል› ውስጥ ነው:: “ሕብር ቃል” ሲል የቃላት ብዝሃነት ያለበት ግን እንደ አንድ የሚታይ ማለቱ ነው:: በሀገራችን ውስጥ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ላይ ቆመው ሲታዩ ‹ሕብረ ብሔራዊ› እንደምንለው ማለት ነው:: ‹ሀገር ማለት ቅኔ› ካልን ማሳያው አንድም እንዲህ ነው:: በቅኔ ውስጥ ፍጹም የተለያዩ ሁለት ነገሮች (ሰምና ወርቅ) አንድነት ፈጥረው በሕብረ ቃል ውስጥ ስናገኛቸው የሚታየን አንዲት ቃል፣ አንዲት ሀገር ብቻ ትሆናለች:: ልዩነታቸው ውበት ሆኖ እናገኘዋለን:: ቅኔ የመሰለች ሀገር ሕልውናዋ ሕብረ ብሔራዊነት እንደሆነው ሁሉ ቅኔ ጥበብ ይኖር ዘንድም ሕብረ ቃል ወሳኙ ነጥብ ነው::

ሁለተኛው የቅኔ መሠረታዊ ምሰሶ ‹ሰም› ነው:: ሕዝበ ውሳኔን ወይንም የብዙሃኑን ፍላጎት እንደመከተል ማለት ነው:: ለሕብረ ቃሉ ፍቺ ግጥማዊ ቅኔው የያዘው ቀጥተኛው እማሬያዊው ትርጓሜው ይሆናል:: ግጥሙ እንደወረደ፣ ከላይ በግልጽ የተቀመጠና ስለ ቅኔ የሚገባውም የማይገባውም ጭምር በእኩል የሚረዳው ይዘት ያለው ነው:: አንዳንዴ ተራ የመንደር ንግግር ሊመስለንም ይችላል:: ‹አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ፤ ልምጣ ወይ ካንቺ ደጅ?› ምንም ቅኔ ያልነካው ቀለል ያለና ተራ አባባል ነው:: “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ፤ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ጠንከር ያለ ምልከታና ተምሳሌታዊ ዘይቤን የያዘ ቢሆንም፤ በቅኔ ደረጃ ሕብረ ቃል የምንፈልግለት አይደለም:: ቦታና ሁኔታን መሠረት አድርገን እንደቅኔ ልንጠቀመው የሚችልበት አጋጣሚ ቢኖርም እንደ ብዙሃኑ አቀባበል በቀጥታ ሰማዊ ወይንም እማሬያዊ ትርጓሜውን ብቻ የምንስማማበት ይሆናል::

ሦስተኛው የቅኔ መሠረት ‹ወርቅ› ነው:: ወርቅ ደግሞ በቀላሉ የትም የሚገኝ አይደለም:: በዓይናችን ለመመልከት እንኳን አናገኘውም:: ሰሙን ለማወቅ እምብዛም ሕብረ ቃል ላያስፈልገን ይችል ይሆናል፤ ወርቁን ለማግኘት ግን የመጀመሪያው ወሳኝ እርምጃ ሕብረ ቃሉን ማግኘቱ ላይ ነው:: ሕብረ ቃሉን አገኘን ማለት ቢያንስ ወርቅ የሚገኝበትን የከርሰ ምድር አካባቢ ለየን ማለት ነው፤ ወርቁ ላይ መድረስ ግን አይደለም:: ገና ሕብረ ቃሉን መቆፈር፣ አፈሩን ማገላበጥ፣ ወደ አዕምሯችን የቋንቋ ሀብት ክምችት ክፍል መዝለቅ፣ በእርጋታ በምናብ መጥለቅ ግድ ይለናል:: የወርቅ ሳጥኑ ካለበት ደርሰን እየዳሰስነው እንኳን፤ ቅኔው ጠጠር ያለ ከሆነ መክፈቻ ቁልፉን ማግኘት ይኖርብናል:: ያለንን የቋንቋ ሀብት በመጠቀምና እይታችንን በማስፋት ለቁልፉ መገኛ መላ መዘይድ ያስፈልገናል:: በመጨረሻም ፍካሬያዊ ትርጓሜው (ሚስጢሩ) ላይ መድረስ ነው::

“እስቲ ዝምድናህን

ቆጥረህ ንገረኝ

ከወንድም አንተ ነህ

ትዝ የምትለኝ”

በዚህ ግጥም ውስጥ ሰሙ (እማሬው) ለሁላችንም ግልጽ ነው:: ስለ ዝምድናቸው እያወራች ያለችው ሴት ‹ከወንድሞቼ ሁሉ ትዝ የምትለኝ ወንድም አንተነህ› እያለችው እንዳለች እንረዳለን:: ቀጥሎ ግን ወርቁን ፍለጋ ለመውጣት መጓጓዣውን ሕብረ ቃል ማግኘት ነው:: የምንከተለው የብዙሃኑን ይዘት ነውና ከላይ ጀምሮ ይዘቱ ስለዝምድና ስለቤተሰብና ወንድማዊነት ሆኖ ብቻውን ሁለት ትርጉም ሊሰጥ የሚችልን ቃል መፈለግ ነው:: ‹ዝምድናህን› ወስደን ቃሉን ብንቆራርጥ፣ ፊደላቱን ብንበትን ከዝምድና ውጪ የያዘው ሌላ ምንም ትርጉም የለውም:: ስለዚህ ‹ከወንድም› የሚለውን እንፈትሸዋለን:: ከፊትና ከመጨረሻ ቅጥያ ሆነው የተለጠፉትን ፊደላት እንደቅርፊት ብናነሳለት የተቀቀለ እንቁላል አስኳል የመሰለውን ‹ወንድ› የሚል ወርቅ እናገኛለን:: ይህን ቃል ወደ ግጥሙ ወስደን “ከወንድም” በሚለው ቦታ ላይ ብንተካው፣ የግጥሙ ሙሉ ይዘት ተለውጦ እናገኘዋለን:: ‹ስለዝምድና ትስስር› ነው ያልነው ግጥሟ ስለ ጾታዊ የልብ ተጋምዶ ሆኖ ይከሰታል:: “ከወንድ ሁሉ የተለየህ ወንድ ለኔ አንተ ነህ” እያለችው መሆኗን እንደርስበታለን::

ከዚህ ውስጥ የቅኔን ባህሪ ወደ ኪነ ጥበብ ስንመዘው፤ ቅኔ የሀገር ብቻ ሳይሆን የጥበብ ተምሳሌትም ሆኖ እናገኘዋለን:: ኪነ ጥበብ ማለት በገሀድ ላይ ካለ ከአንድ እውነት ተነስተን ድብቅ ወደሆነው የሳጥን ወርቅ የምናደርገው ጉዞ ነው:: በግልጽ ከሚታየውና ከሚነበበው ነገር ውስጥ አንድ ድብቅ ማንነትና ምንነት እንሰውርበታለን:: ለምሳሌ አንድ በመድረክ ላይ እየታየ ያለን ቲያትር እንውሰድ:: ቲያትሩ የሚያስቅ ወይንም የሚያስለቅስ መሆኑ ብቻ ምርጥ ሊያስብለው አይችልም:: የቲያትሩ ደራሲ በመጀመሪያ ‹የዚህ ቲያትር ትልቁ አላማ ምንድነው?› የሚለውን ማወቅና ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል:: በዚህ ጥያቄ ውስጥ ሊያገኘው የሚችለው ምላሽ በዋናነት ሁለት ናቸው::

አንደኛው አስተማሪነቱን አጉልቶ፣ በአንድ ጉዳይ ዙሪያ ተመልካቹን ማስተማርና ግንዛቤ ማስጨበጥ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ልዩ በሆነ ኪነታዊ እይታ ውስጥ ድብቅ የሆነ አጀንዳን ወደ ተመልካቹ አዕምሮ ውስጥ መወርወር ነው:: እንደመጀመሪያው በቀላሉ እውነታውን እንዲረዳው በግልጽ ከማስቀመጥ ይልቅ እውነቱን እንደ ወርቅ ሸሽጎ እየተመራመረ በቁፋሮ እንዲያገኘው የማድረግ ጥበብ ነው:: ጉዳዩ ምንም ይሁን ስለምን፤ ጥበብን ወደ ቅኔ ለውጦ ይበልጥ ጣፋጭና አዕምሮን ኮርኳሪ ያደርገዋል:: እንደወረደ ለማስተማሪያነት የሚያቀርብበትን መንገድ ደግሞ እንደ ሰም ልንመለከተው እንችላለን:: ስለዚህ በቲያትርም ሆነ በፊልም፣ በግጥምም ቢሆን በየትኛውም ስነ ጽሁፋዊ ሥራ ውስጥ ደራሲው የሚሄድበት መንገድ ከሰምና ወርቅ የተለየ አይደለም:: እንደ አስፈላጊነቱና እንደ ሁኔታው ሰም አሊያም ወርቅ አድርጎ ይደርሰዋል::

“መልሱን ስጡት እንጂ

ለምን ዝም አላችሁ

ተጣርቶ ተጣርቶ

ያ ሰው ሄደላችሁ” ብሎ አንድ አዝማሪ በመሰንቆው በዜማ ቢያንቆረቁር… የሄደው ሰውዬ ቁምነገሩ የሚገኘው ‹ተጣርቶ ተጣርቶ› ከሚለው ላይ ይሆናል:: ሲጣራ የነበረው ሰው፣ ሰው ለማጣቱ ምክንያት ዝምታ ሰፍኖ እንደሆነ ለመግለጽ ‹ዝም አላችሁ› በማለት ያዜመዋል:: የአዝማሪው አባባል በእማሬው ‹ሰውየው ሲጣራ አቤት ባይ አጣ› ለማለት እንደሆን ግልጽ ነው:: ነገር ግን፤ በዚህ ተራ በሚመስል ግጥም ውስጥ አዝማሪው ‹ሰውየው የሞተው ገንዘቡን ጨርሶ በድህነት ነው› እያለን ነው:: ጥበብ እምቅ ኃይል ያላት ናት ስንል አንድም አካሄዷ በቅኔ የታጀበ በመሆኑ ነው::

በዚህ እምቅ ኃይል ውስጥ አዝማሪዎች የተለየ ቦታ አላቸው:: የጥንት ነገሥታት የሕዝባቸውን የልብ ትርታ ለማድመጥና ስለእነርሱ ምን እየተባለ እንዳለ ለማወቅ ሲሹ ጥያቄው “አዝማሪ ምን አለ?” ነው:: አዝማሪ ደግሞ የሚለው ግልጥልጥ ባሉ ቃላቶች አይደለም፤ ትልቁ መሳሪያው ቅኔ ነው:: የጥበብን ሀያልነትና ጥፍጥናዋን የሚገልጠው በቅኔ ነው:: የአንድን አዝማሪ ሙዚቃዊ የግጥም ስንኞች ስናደምጥ ‹ምን ሊል ፈልጎ ነው? ስለማንስ ነው የሚለው?› ብለን መጠየቅና መመራመር ስንጀምር ከአብዛኛው የሚገለጥ አንድ ነገር አናጣበትም::

ድምጽና ማሲንቆውን አዋህዶ ሲያዝናናን በሙዚቃዊ ስሜት ብቻ ከመፍሰስ ይልቅ፣ ከሚያዝናናባቸው ስንኞች በስተጀርባ ያለውን ነገር ለማወቅ የምናደርገው የምናብ ጨዋታ የበለጠ የሚያስደስት ነው:: ቅኔ ማለት የጭንቅላት ጨዋታ የምንጫወትበት ጥበባዊ መሳሪያ ነው:: በአንድ የምሽት ክበብ ውስጥ አዳራሹን ከሞላው ታዳሚ ውስጥ ስለምንና ስለማን እንደሆነ አንዱም ሳያውቀው፤ ሁለት ሰዎች ግን ማዶ ለማዶ ተቀምጠው ለአዝማሪው ግጥም በማቀበል አንዱ ለሌላው መልዕክት ሊሰድና ሁለቱ ብቻ የሚያውቁትን ሚስጥር እንኳን ሊያወሩ ይችላሉ:: ምክንያቱም አንዳንድ ቅኔዎች በአንድ ቡድን ወይንም ከሁለት በላይ በሆኑ ግለሰቦች ውስጥ የሚፈጠሩና እንደ ስለላ ቃላት በኮድ የሚያገለግሉ ሊሆኑም የሚችሉ ናቸው::

ቅኔ በኪነ ጥበብ ውስጥ ከተምሳሌታዊ ገጽታው ባሻገረ፣ ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት ያለው መሠረታዊ ጉዳይ ነው:: በመጀመሪያ ደረጃ ቅኔ ራሱን የቻለ አንድ የኪነ ጥበብ ዘውግ መሆኑ ነው:: በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በየትኛውም የኪነ ጥበብ ሥራ ውስጥ ያለው ቦታ፣ የጀርባ አጥንት ሆኖ እስከመገለጥ ድረስ ነው:: ያለምንም ገደብ ሥራውን ጠቅልሎ ጉያው ውስጥ እስከማድረግ ድረስ አቅምና መብት አለው:: ነገር ግን፤ የቱንም ያህል ስንጠቀምበት ወሳኙ ነገር አጠቃቀማችን ነው:: ክትፎ በቅቤ ተለውሶ እጅግ ጣፋጭ ምግብ ነው፤ በግማሽ ኪሎ ሥጋ በተዘጋጀ ክትፎ ላይ አንድ ሊትር ቅቤ ብናፈስበት ወይንም አንድ ኪሎ ሚጥሚጣ ብንነሰንስበት ይህን ለመብላት ምራቁን የሚውጥ ያለ አይመስለኝም:: ቅኔም እንዲሁ ነው፤ ከሥራው ጋር በሚሄድ መልኩ ማመጣጠን ያስፈልገዋል:: ኪነ ጥበብ ሰብሮ የሚገባበት ምናብ ፈታኝ በር ቢኖረውም፣ በግዙፍ የአለት ድንጋይ እንደተከረቸመ ዋሻ ግን አይደለም:: ሰዎች ተጠበው የሚገቡበትን እንጂ ከአቅም በላይ የሆነን አለት በጉልበት እንዲፈነቅሉ መጠበቅ የለብንም::

ከኪነ ጥበባት ሁሉ መካከል ቅኔ ቤቱን ሠርቶ ሲደላደል የምንመለከተው በግጥም ውስጥ ነው:: ግጥም ልቡ በቅኔ ፍቅር ሊነደፍና በቅኔ ፍቅር ሊወድቅ ይችላል፤ ቅኔ ግን ያለ ግጥም ከውሀ እንደሚወጣ አሳ ነው:: ምክንያቱም የቅኔ እምቅ ኃይል ያለው በንግግርና በዝርው ጽሁፍ ሳይሆን በግጥም ምጣኔ በተከሸኑ ቃላት ውስጥ ነው:: ‹ቅኔ› ብለን በመዝሙርና በዘፈን እሳቤ ውስጥ ብንመለከተው እንኳን ግጥምና ዜማ ነው:: በሰምና ወርቅ ውስጥም ያለ ግጥም የሚታይ አይደለም:: ምናልባት ቅርጹ ከዚህ ትንሽ ለወጥ ብሎ ልንመለከተው የምንችለው ተምሳሌታዊ አቀራረብ ባላቸው ጥበባት ውስጥ ነው:: ተምሳሌታዊ ውክልና፣ ፈሊጣዊ ሽሙጥ፣ ነቆራዊ አካሄድ…እና በመሰል አገላለጾች ውስጥ ካልሆነ በስተቀር፣ በኪነ ጥበብ ሥራዎች ውስጥም በአመዛኙ ግጥም ተኮር ነው::

ከግጥማዊ ገጽታው ወጣ ብሎ ልንመለከተው የምንችለው አንድም በትውን ጥበባት ውስጥ ነው:: በብዛት በድራማና ቲያትሮች ውስጥ ቅኔውን ከግጥም ጋር ሲሆን የበለጠ ውበት ይኖረዋል:: ለአብነትም እንደ ሙዚቃዊ ተውኔት ባሉት እንዲሁም በቧልታይ:: ከዚያ ውጭ ግን የቅኔን ዳርቻ ሰፋ አድርገን ከተመለከትነው ቅኔ በቃላት ብቻ የሚገለጥ አድርገን መገደብ አይኖርብንም:: ለምሳሌ በልሳን አልባ (አክሽን ሾው) በሚባለው ትወና ውስጥ የሰውነት እንቅስቃሴዎችን፣ ከሁኔታዎች ጋር የሚሄድ የፊት ገጽታ (ፋሻል ኤክስፕሬሽን) እንዲሁም ልዩ ልዩ ቁሳዊ ግብዓቶችን በመጠቀም፣ ያለምንም ንግግር ተምሳሌታዊ ምስሎችን በመከሰት ቅኔያዊ ማድረግ ይቻላል:: መድረክ ላይ እየታየ ያለው ልሳን አልባ ትወና በጥልቀት የተዘጋጀና ስለ አንድ ጉዳይ የሚገልጽ፤ ነገር ግን ተመልካቹ ሊረዳው የሚችለው በምናባዊ ጨዋታ ምርምር አድርጎ ሊሆን ይችላል::

ሌላ አንድ ማሳያ እንጨምርለትና ስዕልን እንጠቀም:: እያንዳንዱ ስዕል በግጥም ውስጥ ‹ሕብረ ቃል› እንደምንለው ዓይነት ነገር አለው:: አንድን የስዕል ሥራ የተመለከተው ሁሉ በቀላሉ የሚረዳውና ሁሉንም ባማከለ መልኩ ቀለል ተደርጎ የቀረበ ከሆነ መልዕክቱን እንደ ሰም ልንቆጥረው እንችላለን:: እንዲህ ዓይነቶቹ አሳሳሎች በብዛት ታሪካዊና መንፈሳዊ በመሳሰሉ ብዙሃኑን አቀፍ የስዕል ሥራዎች ውስጥ ነገሮች እንደምናውቃቸው ተደርገው ይቀርባሉ:: ነገር ግን ረቂቅ (አብስትራክት) በምንለው የአሳሳል ዘዴ ውስጥ የምንመለከተው ስዕልን በቅኔ የመግለጽ ጥበብ ነው:: ብዙ ሰዎች በተመሳሳይ ጊዜና ቦታ አንድን ስዕል እየተመለከቱ፣ ሁሉም አንድ ዓይነት መረዳት አይኖራቸውም:: ሰዓሊው ጭራሽ ባላሰበበት መንገድ የሚረዱም ይኖራሉ:: የሰዓሊውን ሀሳብ ደርሰውበት፣ በተጨማሪ ሌላ እይታ ሊያክሉበት የሚችሉ ተመልካቾችም አይጠፉም::

በዚህ ረቂቅ አሳሳል ውስጥ ሰዓሊው ረቂቁን የሚያስቀምጥበት አንድ እንደ ሕብረ ቃል ያለ የወርቅ ሳጥን ያስፈልገዋል:: ሰዓሊው ይህንን ሕብረ ቃል ከአንድ ተራራ ፊት የቆመን ዛፍ ሊያደርገው ይችላል:: ስዕሉ ፊት የቆመ ማንኛውም ተመልካች ይህን ዛፍ ይመለከታል፤ እየተመለከተ ያለው ግን ሰሙን እንጂ ወርቁን አይደለም:: የእያንዳንዱ ተመልካች እይታ በስዕሉ ይዘትና መልዕክት ላይ ልዩነትን መፍጠር የሚጀምረውም እዚህ ጋር ነው:: ከዛፉ በስተጀርባ፣ ከተራራው ፊት፣ በመሃከል፣ ከላይና ከታች፣ በግራና በቀኝ፣ በውስጥና በውጭ ባሉ እይታዎች መጠን፣ የወርቅ ሳጥኑ ያለበትን ቦታና ቁልፉን ከዚያም ወርቁንና የነጠረውን የወርቁን መልክና ቅርጽ በማግኘት ረቂቁን ቅኔ ሊፈታው ይችላል::

እኚህ ሁሉም በጥበብ ውስጥ ሊገለጡ የሚችሉ መግነጢሳዊ የቅኔ ኃይል፣ ማንነትና ምንነቶች ናቸው:: በጥበብ ውስጥ የሚገኘውን የቅኔን አድማስ መድረስና ዳርቻውን በልኬት ማስቀመጥ ግን ፈጽሞ ለማንም ያልተቻለ ምትሀት ነው:: ይህቺ ብጣሽ ጽሁፍም ብትሆን ጉዞ ለመጀመር ገና ከባሕሩ ዳርቻ እንደምታሟሙቅ ጀልባ ናት::

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You