“የምርት ጥራትን በማረጋገጡ ሥራ ከኢትዮጵያ አልፎ ምስራቅ አፍሪካንም ለማካለል ታቅዷል” – ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር

አዲስ አበባ፡- የምርት ጥራት የማረጋገጡ ሥራ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ምስራቅ አፍሪካን ለማካለል ጭምር እቅድ ይዘን እየሠራን ነው ሲሉ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሣሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትየጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ሚኒስትሩ ካሣሁን (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያን ወጪ እና ገቢ ምርት ጥራትና ደረጃዎች በመጠበቅ ረገድ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ተወዳዳሪነቱንም ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ። ጥራት የማረጋገጡ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጂቡቲ እና በራስ ገዟ በሶማሌላንድም አሁን ተጀምሯል። ይህንኑ ተግባር በቀሪዎቹ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራትም ለማካለል እቅድ ይዘን እየሠራን ነው።

ደረጃቸውን ያላሟሉ ምርቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ጥንቃቄ እየተደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መወገድ ያለበት ይወገዳል፤ ወደ መጣበት ሀገር ይመለሳል። አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃዎች የሚባለው ጉዳይ ለድርድር የማይቀርብ ጉዳይ ሆኖ እየተመራ ነው ብለዋል።

የተቋሞቻችንን የፍተሻ፣ የኢንስፔክሽን እና የምርመራ አቅሞቻችንን በማረጋገጡ በኩል 39 በመቶ እድገት አሳይተዋል ያሉት ሚኒስትሩ ካሣሁን (ዶ/ር)፣ የአቅም ችግር የለብንም ብለዋል። በተለይ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ መድቦ የጥራት መንደር ካስገነባ በኋላ ኢትዮጵያ ለገቢ ምርቶቿም ሆነ ለወጪ ምርቶቿ የኢንስፔክሽን፣ የፍተሻ፣ የምርመራና የሰርተፊኬሽን አቅም ከጊዜ ወደጊዜ እየዳበረ የመጣ ጉዳይ መሆኑን ካሣሁን (ዶ/ር) አስረድተዋል። እርሳቸውም የኢትየጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ቦርድ ሰብሳቢ በመሆናቸውም በዚያ አግባብ ደረጃዎች ሲወጡ የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ባስጠበቀ አግባብ እንዲወጡ፣ በዜጎች ኑሮ ላይ፣ በጤናቸው ላይ፣ በሁለገብ ጠቀሜታቸው ዙሪያ ችግር ያለው ምርትና አገልግሎት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ ሰፊ ጥረት እና ክትትል እየተደረገ እንደሆነም አመልክተዋል።

እንደሚኒስትሩ ካሣሁን (ዶ/ር) ገለጻ፤ ጥራት የማረጋገጡ ሥራ ኢትዮጵያ ውስጥ በአግባቡ እየተሠራ ነው። በሁሉም መስክ የሚደረገው ፍተሻ በጣም በተደራጀ እና ዘመናዊ በሆነ ላቦራቶሪ ነው። ብዙ ቅርንጫፍም አለው። በመሆኑም ጥራት የማረጋገጡ ሥራ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም። ጎረቤት ወደ ሆኑት ጂቡቲና በራስ ገዟ ሶማሌላንድም አሁን ተጀምሯል። በቀጣይ ይህንኑ ተግባር ወደ ሌሎቹ ምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ለማሳደግ የሚሠራ ይሆናል።

የጥራት ቁጥጥርን በተመለከተ ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ሁለት አይነት ደረጃዎች አሏት ያሉት ሚኒስትሩ፤ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃዎች እና አስገዳጅ ያልሆኑ ናቸው። አስገዳጅ ያልሆኑ ከ12 ሺህ በላይ ያሉ ሲሆኑ፣ አስገዳጅ የሆኑ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ደግሞ 396 ናቸው። እነዚህ የወጡ ደረጃዎች በደረጃዎች ካውንስል አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ደረጃዎች ቦርድ ከወጡ በኋላ ይህን ሊተገብር የሚችል የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና አገልግሎት ድርጅት በሁሉም መስክ ፍተሻ የሚያደርግበት ላቦራቶሪ በጣም የተደራጀ እና ዘመናዊ እንደሆነ አብራርተዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም በፌዴራል መንግሥት የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት የወጪና ገቢ ንግድ እቃዎችን ጥራት የመቆጣጠር፣ ተፈላጊውን የደረጃ መስፈርት የማያሟሉ የንግድ እቃዎች ከሀገር እንዳይወጡ ወደ ሀገርም እንዳይገቡ የመከታተል ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑ የሚታወስ ነው።

አስቴር ኤልያስ

አዲስ ዘመን ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You