የተጣለው ታሪፍ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ያለው አንድምታ

አሜሪካ የንግድ ሚዛኗን ወይም የንግድ ጉድለቷን ለማመጣጠንና ፍትሐዊ ያልሆነ የንግድ ፖሊሲዋን ለማስተካከል ወደ አሜሪካ ምርቶቻቸውን በሚያስገቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ 100 ሀገራት ላይ ከ10 በመቶ እስከ 46 በመቶ ድረስ ታሪፍ ጥላለች። ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ 10 በመቶ ወይም ዝቅተኛ የተባለው ታሪፍ ከተጣለባቸው ሀገራት መካከል ትገኛለች። ይህ መሆኑ በተለይም ከወጪ ንግዱ ጋር አንጻር ምን ፋይዳ አለው፤ ምንስ ጉዳት ይኖረዋል ስንል የዘርፉን ምሁራን አነጋግረናል።

ታሪፉ ከወጪ ንግዱ አንጻር አወንታዊም አሉታዊም ጎን እንዳለው የሚገልጹት በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ሀብታሙ ለገሰ ፤አወንታዊ ጎኑ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ ታሪፍ የተጣለባት በመሆኗ በአሜሪካ የንግድ ሜዳ ላይ ጥራት ያለውን ምርት ይዛ እስከቀረበች ድረስ ተወዳዳሪነቷን ከፍ ያደርግላታል ይላሉ። በአሜሪካ የጣለችው ታሪፍ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ የተከለከለችውን የአጎዋ ተጠቃሚነት በእጅ አዙር የሚመልሰው እንደሆነም ያስረዳሉ።

የአሜሪካ ታሪፍ የአጎዋ ተጠቃሚ ሀገራትን ጭምር ያካተተ በመሆኑ ሀገሪቱን ከሌሎች ሀገራት እኩል የገበያው ተጋሪ ያደርጋታል የሚሉት መምህሩ፤ በአጎዋ መቅረት ብዙ አምራቾችና ላኪዎች ችግር ውስጥ ወድቀዋል፤ ሠራተኛ እስከመቀነስም ደርሰዋል። በተመሳሳይ ድርጅታቸውን ዘግተው ወደ አጎዋ ተጠቃሚ ሀገራት የተዘዋወሩም ነበሩ። ይህ ታሪፍ ግን ሁሉንም እኩል ያደደረገ በመሆኑ ተወዳዳሪነት ከታሪፍ ውጪ እንዲሆን ያስችለዋል። ኢትዮጵያን የምትወዳደርበትን አማራጭ እንድታይና እንድታሰፋ እድሉን ይፈጥርላታል ይላሉ።

ታሪፉ በከፍተኛ ሁኔታ የተጣለባቸውን እንደ ቬትናምና ቻይና አይነት ሀገራትን ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ከመሳብ አንጻር የማይተካ ሚና አለው የሚሉት መምህር ሀብታሙ፤ አምራቾች መጡ ማለት ደግሞ ለዜጎች የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር.፤ አማራጭ የምርት ሁኔታን ከማስፋት አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ኢትዮጵያ መጥተው ሲያመርቱ የወጪ ገቢው ላይም የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያሳርፍም ይገልጻሉ።

የፖለቲካል ኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ታሪፉ ገቢና የሥራ እድል መፍጠሩን ቢያምኑበትም የውጭ ሀገራት አምራቾችን ስቦ ማስገባቱ እንደ አወንታዊ ጎኑ መወሰድ አለበት የሚለውን ሃሳብ አይቀበሉትም። ምክንያቱም ታሪፉ የውጭ አምራቾች ኩባንያዎችን የመሳብ ሁኔታ ቢኖርም ተጠቃሚነቱ ከኢትዮጵያ ይልቅ እነርሱ ላይ የሚያደላ ነው። ምክንያታቸውም የውጭ ሀገራት አምራቾች ብራንዳቸው ይታወቃል። በዚህም ገዢያቸው ብዙ ነው። በየትኛው ሀገራት በኩል ገበያው ላይ ቢሄዱ ተጠቃሚነታቸው ከፍ ያለ እንደሆነ ያነሳሉ።

በእኛ በኩል ሲሄዱ ደግሞ ኢትዮጵያዊ አምራቾች ከእነርሱ ጋር ተወዳድረው ለመሸጥ በእጅጉ ይፈተናሉ። ስለሆነም የወጪ ንግዳችን በአብዛኛው በውጭ ዜጋ ይያዝና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታችንን እናጣለን። ሀገሪቱ በራሷ ዜጎች የተገነባ ኢኮኖሚ አይኖራትምም። ነጻነቷን የምትነፈግበትን እድልንም ያሰፋል። ስለሆነም ኢኮኖሚውን ሊቆጣጠር የሚገባው የሀገሬው ሕዝብ መሆን ይኖርበታልና የሀገር ውስጥ አምራችና ላኪዎችን ማበረታታት ከዚህ ሁሉ አዋጪ እንደሆነ አበክረው ይናገራሉ።

አሜሪካ ሃያል ሀገር በመሆኗ ምንም አይነት ታሪፍ ብትጥል ታዳጊ ሀገራትን ተቀብሎ ለዚያ የሚመጥን ሥራ ከመሥራት ውጪ አማራጭ እንደማይኖራቸው የሚናገሩት ተንታኙ፤ ሀገራቱን ታሪፉ ከገበያ ውጪ እንዳያደርጋቸው የበለጠ ማምረትና ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡትን ምርት በጥራትም፤ በእሴት ጭምርም ማስፋት ነው። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ምቹ ነገሮች አሏት። በመሆኑም እርሱን በአግባቡ በመጠቀም የበለጠ ኢኮኖሚዋን እንድትገነባ እድል ይፈጥርላታል ይላሉ።

‹‹ችግር የፈጠራ እናት ናት›› እንደሚባለው ታሪፉ መጣሉ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ዝናብ ጠብቆ ከመሥራት ላልተላቀቁ ሀገራት እጅግ የሚያነቃቃ ነው። ከቀደመው ልምዳቸው ወጥተው በመስኖ ሥራዎች ሁለቴና ሦስቴ ወደ ማምረት እንዲሸጋገሩ ያደርጋቸዋል፤ ወደ ተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ በስፋት እንዲገቡም አድል ይፈጥርላቸዋል። በእሴት ጭመራ ውስጥ የሥራ እድል እንዲሰፋ፤ ጥራት ያላቸው ምርቶች በሀገር ውስጥ ጭምር እንዲመረቱና በዓለም ገበያ ላይ ተመራጭና ተወዳዳሪ አቅራቢዎች እንድንሆንም ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዚህ ታሪፍ ምክንያት የምትወዳደረው ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ብቻ ሳይሆን ዝቅተኛ ታሪፍ ከተጣለባቸው እንደ ብራዚል ካሉ ያደጉ ሀገራት ጋር ጭምር እንደሆነ አመልክተው፤ አሁን የተጣለው ታሪፍ ውድድሩ ከታሪፍ ዝቅና ከፍ ማለቱ አንጻር ብቻ የሚታይ ባለመሆኑ እንደ ሀገር ከገበያ ውጪ የማያደርጉ ተግባራትን ማከናወን የግድ ይለናል የሚሉት መምህሩ፤ ሀገሪቱ ታሪፍ በመቀነሱ ብቻ ተጠቃሚ ትሆናለች ብሎ መውሰድ አይገባም። ጥራቱ ላይ ከምንጊዜውም በላይ መሥራትና ተወዳዳሪ መሆን ይገባታል ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ዋጋ ከጨመረ ፍላጎት መቀነሱ አይቀርም። በዚህም ኢኮኖሚው ላይ ጫና ይፈጠራል። በዚህም በተለይ ለምርት አገልግሎት የሚውሉ ጥሬ እቃዎች ላይ ችግር ያጋጥማቸዋል። ስለሆነም የታሪፉን ጭማሪ የሚመጥን የጥራት ሥራና የእሴት ጭመራ ተግባራትን ማከናወንና የገበያ ተወዳዳሪነትን ማስፋት ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት የግድ እንደሆነም አስረድተዋል። ወደ ውጪ የምንልካቸው ምርቶች ላይ ሌሎች አማራጭ ተግባራትንም ማከናወን እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ወደ ውጪ የምትልካቸው ምርቶች የነዳጅ ወጪን እንኳን እየሸፈነ አይደለም የሚሉት መምህሩ፤ አሁን ላይ በታሪፉ ሊመጡ የሚችሉ ጫናዎችን ወጪና ገቢያችንን ለማመጣጠን የሚያስችል ምርት በማቅረብ መሸፈን እንደሚገባ አንስተዋል። ለዚህም መንግሥት ልዩ ድጋፍና ማበረታቻዎችን ሊያደርግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ምርትን ተገማች ሊያደርጉ የሚችሉ አሠራሮችን መቀየስ፤ ጫና የሚፈጥሩ አሠራሮችን ማሻሻል፤ ምርቶች ጥራት ያላቸውና እሴት የተጨመረባቸው ማድረግ፤ አብዛኛው የምንልከው የግብርና ምርቶችን በመሆኑ አርሶና አርብቶ አደሩ አካባቢ ልዩ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ኢኮኖሚውን ሊደግፉ የሚችሉ እንደ የሥራ ባህል ቅየራ፤ የሰው ኃይልን በአግባቡ መጠቀምን የመሳሰሉ ነገሮች ላይ በስፋት መሥራት ያስፈልጋል የሚሉት ደግሞ የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ናቸው።

የታሪፉን ሁኔታ አሁን ባለው መንገድ ለማጣጣም አንዱና ወሳኙ ጉዳይ ሀገሪቱ ከውጪ የምታስገባቸውን ምርቶች በሀገር ውስጥ መተካትና ወደ ውጪ የሚላኩትን ምርቶች የተለያዩ ማድረግ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ከዚያ ባሻገር እንደ አፍሪካ ያለውን ሀብት አይቶና ለይቶ ተሳስሮ መሥራት ነው ይላሉ።

ይህ ትስስራቸው የሰው ኃይላቸውንና የተፈጥሮ ሀብታቸውን በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚያቸውን ለመገንባት ያስችላቸዋልም ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የአጎዋ ተጠቃሚ በነበረችበት ወቅት ብዙ አልሚዎች ከተለያዩ ሀገራት መጥተዋል። በዚህም በርካታ የሥራ እድል ተፈጥሯል፤ ምርቶችም በበቂ ሁኔታ ሀገር ውስጥ እንዲገኙ እድል ፈጥሯል። ሆኖም አጎዋ ሲከለከል ግን ብዙዎች ያለ ሥራ እንዲቀመጡ አድርጓቸዋል። በዚያው ልክ ግን ተኪ ምርቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ እድል አመቻችቷል። ስለሆነም ታሪፉን የመቃወም እድል ስለሌለ የሚገኙ አማራጮቾችን በሙሉ ተጠቅሞ የወጪ ንግዱን ማሳለጥ ያስፈልጋል።

ሁለቱም ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የታሪፍ ጭማሪው በቀጣይ ቁጭትን የሚውልድ በመሆኑ ለሥራ እድል ፈጠራው፤ ጥራት ያለው ምርትን ለማምረት፤ ምርታማነትን ለመጨመርና ኢኮኖሚውን ከፍ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ጽጌረዳ ጫንያለው

አዲስ ዘመን ረቡዕ ሚያዝያ 22 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You