ኢትዮጵያዊነት ከሚገለፅባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱ ሃገርን መውደድ ነው። አንድ ሰው “እከሌ ኢትዮጵያዊ ነው” ሲባል ሃገሩን ይወዳል የሚል ትርጉምም ይኖረዋል። የኋላ ታሪካችንም ይህንን የሚያጠናክርልን ነው። ኢትዮጵያውያን በውጭው ዓለም ከሚታወቁባቸው መልካም ገጽታዎች ውስጥ አንዱ ለሃገራቸው ያላቸው ቀናኢነት ነውና።
አውሮፓውያን መላውን አፍሪካ በተቀራመቱበት የአፍሪካ የቅኝ ግዛት የጨለማ ዘመንም ኢትዮጵያውያን የሃገራቸውን ሉዓላዊነት ከማስከበር አልፈው ለሌሎች ለጥቁር ህዝቦችም አርአያ መሆን የቻሉት ለሃገራቸው ባላቸው ቁርጠኛ አቋም ነው። በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች ብቸኛ አገር እንድትሆን ማድረግ ችለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የማንንም መብት አልፋ የነካችበት የታሪክ መዝገብ ባይኖርም ድንበሯን አልፈው ሉኣላዊነቷን የተዳፈሩ ሃይሎችን ደግሞ የምትታገስበት የሽንፈት ታሪክ የላትም። በዚህ የተነሳ በተለያዩ የውጭ ሃይሎች ጫና ሲደርሰባት ልጆቿ ከዚህም ከዚያም ተሰባስበው በአንድነት የመቆም ልምዳቸው ከፍ ያለ ነው።
በሃገራችን የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎም ኢትዮጵያውያን ወደ ብልጽግና የሚያደርጉት ጉዞ እንደሚቃና ትልቅ ተስፋ አድርገው መጠባበቅ ሲጀምሩ የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ሃይሎች ይህንን ጉዞ ለማደናቀፍ ተንቀሳቀሱ። በዚህ የተነሳም ባለፉት ሶስት ዓመታት በርካታ ተግዳሮቶች ኢትዮጵያን ሲፈትኗት ቆይተዋል።
መንግስትም እነዚህን ተግዳሮቶች አሸንፎ ለመውጣት ከመላ ሃገር ወዳድ ዜጎች ጋር ከፍተኛ ርብርብ አድርጓል። በዚህ ትግል ውስጥ ከሃገሩ ጎን በመሆን የኢትዮጵያን መፃኢ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ትግል እያደረጉ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንም መካከል በውጭ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ይጠቀሳሉ።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሶስት ሚሊየን የሚልቁ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በውጭ ሃገር ይኖራሉ። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ደግሞ በህጋዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ከነዚህ ውስጥም በትምህርት ደረጃቸውና በሃብታቸውም ከፍ ያለ ደረጃ ላይ የደረሱ ዜጎች ይገኙበታል።
እነዚህ የዲያስፖራ አባላት ቀደም ሲል በነበረው ታሪክም ስንመለከት በሃገራቸው ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በርካታ አዎንታዊ ተግባራትን ሲያከናውኑ የኖሩ ናቸው። በተለይ በኢኮኖሚው ረገድ ወደሃገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ ለሃገራዊ እድገት የራሱን አወንታዊ ሚና እንዲጫወት ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍ ያለ ነው። ከዚህም ባሻገር በፖለቲካውም መስክ የነበራቸው ተሳትፎ ቀላል አልነበረም። ለምሳሌ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በርካታ አሳፋሪ ተግባራትን ሲያከናውን የቆየውን እና ኢትዮጵያ አሁን ለገባችበት ሁለንተናዊ ቀውስ ዋነኛ መንስኤ የነበረው የአሸባሪው ህወሓት አገዛዝ እንዲወድቅ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በዚህ መሰረት በውጭ ሃገር በሚገኙ ሚዲያዎችና በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ስለሃገራቸው መረጃ በመስጠት የውጭው ማህበረሰብ የራሱን ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ችለዋል።
ለውጡን ተከትሎም በውጭ ሃገር የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለውጡን ከመደገፍ ጀምሮ ለሃገራቸው ድጋፍ በማድረግ በርካታ አዎንታዊ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ። በዚህም መሰረት የዲያስፖራ አባላት ለሃገራቸው የሚያደርጉት ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ይገኛል። ከነዚህ ድጋፎችም ውስጥ አንዱ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርጉት ድጋፍ ነው። ለግድቡ ከሃሳብ ባሻገር ቦንድ በመግዛት ጭምር ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
በተለይ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ በግብጽ የሚመሩ አንዳንድ የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና የዓለም ማህበረሰብ እንዲገነዘበው ለማድረግ የዲያስፖራ አባላት የሚያደርጓቸው ድጋፎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ናቸው። በዚህም መሰረት የዲያስፖራ አባላት ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ አስፈላጊነትና ጠቀሜታ እንዲሁም ግድቡ መገንባቱ በሌሎች ሃገራት ላይ ምንም አይነት ጫና እንደማይኖረው የተለያዩ መረጃዎችን በማዘጋጀትና በማሰራጨት፤ በተለይ በአሜሪካ የሚገኙ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ባለሙያዎች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ ቆይተዋል።
በቅርቡም በትግራይ የተካሄደውን ህግ የማስከበር ዘመቻ ተከትሎ አንዳንድ የአሸባሪው ህወሓት አፍቃሪዎች የዓለምን ማህበረሰብ ለማሳሳት የጀመሩትን የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ለማረምና ለዓለም ማህበረሰብ ትክክለኛ መረጃ ለመስጠት በርካታ የዲያስፖራ አባላት ርብርብ ሲያደርጉ ቆይተዋል። በዚህ ሂደት አሁንም ገና ብዙ ስራ የሚጠበቅ ቢሆንም በትክክል ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ወደተሳሳተ አቅጣጫ የገቡ ቡድኖችና ግለሰቦችን ግን መመለስና ትክክለኛ መረጃ እንዲይዝ ማድረግ ተችሏል።
በዚህ ረገድ በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ የሚኖሩ ኢትዮጵያውን ቴክኖሎጂን በመጠቀምና ለተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት መረጃዎችን ለማድረስ የሄዱበት ርቀት የኢትዮጵያዊነት መገለጫ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። እነዚህ ወገኖች ጊዜአቸውንና ጉልበታቸውን ሳይሰስቱ ለሃገራቸው ያደረጉት ድጋፍ ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ስለሃገራቸው ቁርጠኛ አቋም እንዳላቸው ማሳያም ነው።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደተሻለ የብልጽግና ጎዳና ለመውጣት ከፍተኛ ትግል ውስጥ ትገኛለች። ለዚህ ደግሞ ከፊት ለፊቷ ያሉት ሁለት ተግባራት ወሳኝ ናቸው፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት እና ስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ። እነዚህ ሁነቶች በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ከጨለማ ለመውጣትና የተሻለ ኑሮ ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያለመልም ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ እውነተኛ የዴሞክራሲ ስርዓት የሚገነባበት ወሳኝ የለውጥ ምዕራፍ ነው።
ነገር ግን እነዚህን ወሳኝ ሁነቶች ለማደናቀፍ የኢትዮጵያ ጠላቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ሩጫ ላይ ናቸው። ስለዚህ ይህንን ጊዜ ለማለፍና ኢትዮጵያን ለማሻገር እያንዳንዱ ዜጋ ሊረባረብ ይገባል። በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ቀደም ሲልም ጀምሮ የድርሻቸውን እየተወጡ የሚገኙት ሃገር ወዳድ የዲያስፖራ አባላት ሚና የላቀ ነው። በመሆኑም መላው የዲያስፖራ አባላት ኢትዮጵያን ለማዳከምና ከጉዞዋ ለማደናቀፍ የሚጥሩ ሃይሎችን ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በላይ እጅ ለእጅ በመያያዝ የጋራ ሃገራችንን በጋራ ማሳደግ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29 ቀን 2013 ዓ.ም