አዲስ አበባ፡- የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ በፊት የምግብ ደህንነትን ማስጠበቅ የሚያስችል ጥናት ሊጀመር መሆኑ ተገለፀ፡፡ ጥናቱ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም እንደሚሠራ ተመልክቷል፡፡
በእንግሊዝ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብርና በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ድጋፍ በምግብ ደህንነት ላይ ጥናት ለማካሄድ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሰሞኑን ይፋ የተደረገ ሲሆን የሚደረገው ጥናት የዶሮና የአትክልት ምርቶች፣ የወተትና የወተት ተዋፅዎች፣ የምግብ ወለድ በሽታዎች ላይ እንዲሁም የስጋ ውጤቶች ላይ ያተኮረ መሆኑም ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በኩል አዲስ አበባ፣ ሀሮማያና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ጥናት ለማድረግና ለማገዝ እንደተመረጡም ታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ዶክተር አሻግሬ ዘውዱ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ዩኒቨርስቲው በወተትና በወተት ተዋፅኦ ላይ ለሚያደርገው ጥናት በወተት አቅራቢዎች፣ አምራቾችና ተጠቃሚዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን የመለየት ስራ ይከናወናል፡፡
ጥናቱ ሲጠናቀቅ ለወተት አቅራቢዮች፣ አምራቾችና ተጠቃሚዎች የግንዛቤ ሥልጠና እንደሚሰጥ የጠቀሱት ዶክተር አሻግሬ፤ ወተት አቅራቢዎች በምን አይነት መንገድ የወተትን ንፅህና መጠበቅ እንደሚችሉ፣ አምራቾች ደግሞ በምርት ወቅት ማድረግ የሚገባቸው ጥንቃቄ ላይና ተጠቃሚዎች ደግሞ በምን አይነት መንገድ የወተት ውጤቶች መጠቀም እንዳለባቸው ሥልጠና እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡
የዶሮና የአትክልት ምርቶች ላይ ጥናት የሚያደርጉት ዶክተር ክርስቲ ሮሼል በበኩላቸው፤ የምግብ ደህንነትን ለመጠበቅ ቅድሚያ የአትክልት ምግቦች የሚሸጥባቸው ቦታዎች ንፁህ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ምግቡም ሲዘጋጅ ደግሞ እጅ መታጠብ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የዶሮና የአትክልት ምርቶች ላይ የሚደረገው ጥናት በሀረር፣ በሀሮማያና በድሬዳዋ ከተሞች ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቅሰው፤ የአትክልት ምርቶች ተመርተው ተጠቃሚው ድረስ እስኪደርሱ ያሉትን መስመሮች በመለየት መስመሮቹ ላይ የሚታዩ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ የግንዛቤ ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 11/2011
መርድ ክፍሉ