በቀድሞ ከፋ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ አጠራር ጂማ ዞን፣ ቶባ ወረዳ ልዩ ስሙ ኩረቼ በሚባል ወንዝ አቅራቢያ በ1903 ዓ.ም መወለዳቸውን ይናገራሉ።በልጅነታቸው ከብቶችን በማገድ፤ ከፍ ሲሉም በግብርና ስራ ላይ በመሰማራት ቤተሰቦቻቸውን ያግዙ ነበር።ወይፈኖችን እና ፈረሶችን የመግራት ልዩ ተሰጥኦ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ።ከስልሳ እና ሰባ ዓመት የማይበልጥ የፊት ገጽታና የአካል ብቃት ይታይባቸዋል።ቅልጥፍ ያለ ሰውነት አላቸው። ዛሬም የጉልበት ስራ ይሰራሉ፤ ከአርባ ሁለት በላይ ልጆች እና ከመቶ ሰላሳ በላይ የልጅ ልጆችን አይተዋል።ከ1932 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 1995 ዓ.ም ድረስ ሀገራቸውን በውትድርና አገልግለዋል።የኮሪያም ዘማች ናቸው።በሩዋንዳ ሰላም ማስከበር ተልእኮ ተሳትፈዋል።ዛሬም እድሉን ቢያገኙ መከላከያ ሰራዊትን ተቀላቅለው ሀገራቸውን ከባንዳና ከወራሪ የመጠበቅ ጽኑ ፍላጎት አላቸው።የመቶ አስር ዓመቱ እድሜ ባለጸጋ ሌቴናል ኮሎኔል ሪጃል ኡመር።
ሌተናል ኮሎኔል ሪጃል ኡመር በልጅነት እድሜያቸው ለጥቂት ጊዜ ተገደው የጠጡትን ካልሆነ በስተቀር በራሳቸው ፍላጎት ወተት የጠጡበትን ጊዜ አያስታውሱም፤ አስገዳጅ ሁኔታ ካልገጠማቸው ስጋ አይመገቡም።ከስጋ ዘሮች መብላት ከፈለጉ የተቀቀለ የዓሳና የዶሮ ሾርባን ይመገባሉ።በውትድርና ዓለም በነበሩ ጊዜ ስጋ የመብላት አስገዳጅ ሁኔታ ሲገጥማቸው እንኳን ለረሃብ ማስታገሻ ያህል ትንሽ ጥሬ ስጋ ይጎርሳሉ እንጂ በወጉ የተጠበሰ ስጋ አይመገቡም። ወትሮም ስጋ የመመገብ ፍላጎት እንደሌላቸው የሚናገሩት ሌተናል ኮሎኔሉ በይበልጥም ልጅ እያሉ ወላጆቻቸው የሰጧቸው ፍየል ከሞተችባቸው በኋላ የስጋ ጥላቻቸው ይበልጥ እንደጨመረ ይናገራሉ።በዚያን ጊዜ የአንድ ፍየል ዋጋ ከአስራ አምስት እስከ ሃያ አምስት ሳንቲም እንደሚገመት የሚገልጹት አርበኛው የፍየሏ ሞት እንደ ትልቅ ኪሳራ ተሰምቷቸው አዝነው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ሌቴናል ኮሎኔል ሪጃል ኡመር ዘመናቸውን ሁሉ የአትክልት ዘሮችን እየተመገቡ የኖሩ ናቸው።በተለይም በሚኖሩበት አካባቢ ጫካ ውስጥ በቅሎ የሚገኘውን የአውጢና የአረንጪ ቅጠልና ስር (አንጮቴ) እየተመገቡ ያደጉ ናቸው።ቅጠሉ እየተጠበሰ ስሩም እየተቀቀለ ለምግብነት እንደሚውል ይገልጻሉ።ከአካባቢያቸው ርቀው በኖሩባቸው ዓመታትም እንደ ካሮት፣ ጎመንና ቆስጣ የመሳሰሉትን እየተመገቡ ኖረዋል።
ሌቴናል ኮሎኔል ሪጃል ኡመር ፋሺስት ጣሊያን ሁለተኛውን ወረራ ከማካሄዱ በፊት ባለትዳርና የሶስት ልጆች አባት እንደነበሩ ይናገራሉ።የመጀመሪያዋ ባለቤታቸው የትግራይ ተወላጅ ናቸው። ወይዘሮ ትብለጽ አብርሃ ይባላሉ።ቤተሰቦቻቸው በአድዋ ጦርነት ጊዜ ከትግራይ ኮብልለው አጋሮ መኖር የጀመሩ ናቸው።የያኔው ወጣት ሪጃል ወይዘሮ ትብለጽን አግብቶተው የመጀመሪያ ልጃቸውን ተፈሪ ሪጃልን ጨምሮ ሶስት ልጆችን እንደወለዱ ጣሊያ ዳግም ኢትዮጵያን ትወራለች።በአጭር ቀናት የሪጃል አያት የኢጣሊያኖች ሰለባ ይሆናሉ።በአያታቸው ሞት ክፉኛ ያዘኑትና የተቆጡት ኮለኔሉ በአካባቢው የአርበኞችን እንቅስቃሴ የሚመሩትን ጋራዝማች ስሙር አበራን አነጋግረው ልጆቻቸውን እቤት በመተው አርበኞችን ይቀላቀላሉ። ይህ የሆነው በ1932 ዓ.ም ነው።
አርበኞችን ሲቀላቀሉ አጃቸው ላይ የነበረው መሳሪያ ጦር ብቻ ነበር።ጋሻ እንኳን አልነበራቸውም።የአስራ አምስት ቀን ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ደንቢ ወደሚባል አካባቢ ሄደው መፋለም ይጀምራሉ።ትንሽ ጊዜ በጀሌነት ካገለገሉ በኋላ ወደ መደበኛው ጦር ይካተታሉ። ከወራት በኋላ ከግራዝማች ስሙር አበራ ጦር ወደ ራስ ገዳሙ ተክሌ ጦር ይዛወራሉ።በወለጋና በሊሙ ከወራሪው ፋሺስት ጋር ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርጉ ቆይተው የጠላት ሃይል ሲበረታ ከአርበኞች ጋር ወደ ጎንደር ያፈገፍጋሉ።ጎንደር አካባቢ አርበኞች ሃይላቸውን እያሰባሰቡ ጥቃት በመፈጸም ወራሪውን መውጫ መግቢያ ያሳጡታል።በ1933 ዓ.ም የጠላት ኃይል ጅማ ላይ በርትቶ ስለበር ከጎንደር ወደ ጂማ ይሄዳሉ።ከሸዋ የጃገማ ኬሎ ጦር፤ ከሰሜን የራስ እምሩ ጦር ከግራዝማች ስሙር አበራ እና ከራስ ገዳሙ ጦር ጋር በመሆን ጂማን ከጠላት ነጻ ለማውጣት ከፍተኛ ፍልሚያ ያደርጋሉ።ጣሊያኖች በባንዳዎች ድጋፍ ይደረግላቸው ስለነበር ጦርነቱ ቶሎ መጠናቀቅ አልቻለም ነበር። ሴኔ 12 ቀን 1933 ዓ.ም ጂማ ነጻ ትወጣለች።በወቅቱ 8ሺህ 600 የሚሆኑ የኢጣሊያን ወታደሮችና ባንዳዎች ይማረካሉ።ሪጃልና ጓደኞቻቸው ምርከኞችን እየነዱ ወደ አዲስ አበባ በማምጣት ግማሾቹ ሱማሊያ ግማሾቹም እዚሁ እንዲታሰሩ ያደርጋሉ።
ከድል በኋላ አርበኞች እየተመለመሉ በከብር ዘበኛ ውስጥ እንዲካተቱ ይደረጋል።ሪጃል ምንም እንኳን ቁመታቸው አጠር ያለ መሆኑ ለክቡር ዘበኛነት ባያስመርጣቸውም ማንበብና መጻፍ የሚችሉ በመሆኑ ብቻ በክብር ዘበኛ ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል።
ብዙም ሳይቆዩ ከሁለተኛ ሻለቃ ጋር በመሆን ወደ ኮሪያ ይዘምታሉ።ግንቦት 16 ቀን 1943 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ባቡር ተሳፍረው ወደ ጂቡቲ ይጓዛሉ። ከወራት የመርከብ ጉዞ በኋላ ኮሪያ ደርሰው የተሰጣቸውን ግዳጅ በብቃት መወጣት ይጀምራሉ። ከአምስት ዓመት የኮሪያ ቆይታ በኋላ በ1949 ዓ.ም ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ።በኮሪያ ቆይታቸው ከመሰሎቻቸው ጋር ያሳለፉት የመረዳዳት፣ የመተዛዘንና የጀግንነት ታሪካቸው ሁሌም ይታወሳቸዋል።አንድ የሀገራቸው ልጅ ቆስሎ አስራ ሰባት ኪሎ ሜትር ድረስ ተሸክመውት የተጓዙትን በልዩ ሁኔታ ያስታውሱታል።
ሌተናል ኮሎኔል ሪጃል ከኮሪያ ከተመለሱ በኋላ በሶስተኛ አንበሳ ክፍለ ጦር ተመድበው የውትድርና ህይወታቸውን ይቀጥላሉ።ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ የምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ ይሰጣቸዋል።ከዚያም ኦጋዴን አካባቢ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ይቆያሉ።እዚያው እያሉ የሻንበልነት ማዕረግ ያገኛሉ።
ጥቂት ዓመታትን እንዳገለገሉ እድሜቸው ለጡረታ ሲደርስ በ1965 ዓ.ም ጡረታ እንዲወጡ ይደረጋል።ነገር ግን ፊታቸው የልጅ ስለነበርና ፈርጣማ ሰውነት ስለነበራቸው በአለቆቻቸውና በንጉሱ መልካም ፈቃድ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ይደረጋሉ።
ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ አብዮት ይፈነዳና የንጉሱ ሥርዓት አክትሞ የደርግ መንግስት ስልጣን ይቆጣጠራል።በሁኔታው ደስተኛ ያልነበሩት የጦር መኮንን ጡረታቸውን አስከብረው ከደጃዝማች ሻፊ አደም ጋር ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ጂማ ይሄዳሉ።ጂማ ተወልደው ባደጉባት ቶባ ወረዳ ገጠራማ ቦታ መኖር ይጀምራሉ።በወቅቱ እንደ መኢሶን፣ ኢጫት ኢህአፓ፣ ሰደደን የመሳሰሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቋቁመው እርስ በእርስ ይገዳደሉ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
የሱማሊያው መሪ ሲያድባሬ በኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋት እንደጥሩ አጋጣሚ ተጠቅሞ ወረራ ይፈጽማል።በወቅቱ የደርግ ሊቀመንበር የነበሩት ብርጋዴር ጀነራል ተፈሪ በንቲ ‹‹የሀገሪቱ የጦር መኮንኖች የነበራችሁ፣ ጡረታ የወጣችሁ፣ አቅም ያላችሁና እጅ እግራችሁ የሚሰራ በሙሉ እድሜያችሁን ምክንያት ሳታደርጉ አገራችሁን ከጠላት ተከላከሉ›› የሚል ጥሪ ያቀርባሉ።በጡረታ ላይ የነበሩት ሪጃል ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብለው ዳግም ጦሩን ይቀላቀላሉ።ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን በታጠቅ ጦር ማስልጠኛ ከ 300 ሺ በላይ የሚሆኑ ሚሊሻዎችን አሰልጥነው ለውጊያ ያዘጋጃሉ።ኮለኔሉ አሁንም በሶስተኛ ክፍለ ጦር ውስጥ ተመድበው ወደ ግንባር ይንቀሳቀሳሉ።በወቅቱ የሶማሊያ ወራሪዎች 700 ኪሎ ሜትር ድረስ የኢትዮጵያን ድንበር ዘልቀው መግባታቸውን ያስታውሳሉ።በኦጋዴን፣ ጂግጂጋ፣ ቀብሪደሃር፣ ቀብረቢያን በሚባሉ ግንባሮች ፍልሚ ሲያደርጉ ይቆያሉ።
የምስራቁ ጦርነት በድል ከተጠናቀቀ በኋላ ሰራዊቱ ወደ ሰሜን እንዲዘምት ይደረግና እርሳቸውም ወደ ኤርትራ ይሄዳሉ።የጡረታ ደብተራቸውን ለባለቤታቸው ሰጥተው እርሳቸው መደበኛ ደሞዝ ተከፋይ ይሆናሉ።የሻለቃ ማእረግና የአንደኛ ደረጃ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻንም ይሸለማሉ።በርካታ ዓመታትን በወታደርነት ሀገራቸውን ማገልገላቸውን ጠቅሰው ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ ቢጠይቁም ሳይፈቀድላቸው ይቀራል።በሻለቃ ማእረግ እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ ይቆያሉ።እንደገና የሶስተኛ ደረጃ ጀቡዱ ኒሻል ሽልማት ይሰጣቸዋል።
በደርግ የጦር አዛዦች ይፈጸም የነበረው አሻጥር ውጤታማ ሊያደርግ አለመቻሉና የመፈንቅለ መንግስቱ መደናቀፍም በሰራዊቱ መካከል መተማመን ያልፈጠረ ስለነበር በዚህ የተከፉት ሌተናል ኮለኔል ሪጃል በ1982 ዓ.ም የህወሓት ሰራዊትን ይቀላቀላሉ።በኢህአዴግ መንግስት በውትድርና እያገለገሉ እያሉ በ1987 ዓ.ም በተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ስር ታቅፈው ወደ ሩዋንዳ ይሄዳሉ።ከአንድ ዓመት ከስምንት ወር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው በተለመደው ስራቸው ላይ እንዳሉ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ይጀመራል።በዚህ ጦርነትም በአጋዚ ክፍለ ጦር ውስጥ አዋጊ በመሆን ይሳተፋሉ።ከዚያም ወደ 44ኛ ቀጥሎም ወደ 12ኛ ክፍለ ጦር ተዛውረው ያገለግላሉ። ኋላም የረዥም ጊዜ ቆይታ ኒሻን ያገኙና በ1995 ዓ.ም በጡረታ ይሰናበታሉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በሩዋንዳ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ የሬዲዮ ኦፕሬተር ሆነው ሲያገለግሉ እንደሚያውቋቸው ሌተናል ኮለኔል ሪጃል ይናገራሉ።ባድሜ ላይም እንዲሁ በተመሳሳይ ግዳጅ ላይ ሆነው አግኝተዋቸዋል። ሌተናል ኮለኔል ሪጃል ኡመር ኮሪያ፣ ዙምባበዌና ሩዋንዳ በወታደራዊ ተልእኮ መሄዳቸውን፤ ሱዳንና ሶማሊያ በመገኘትም ለሰራዊቱ የሞራል ድጋፍ ለመስጠት መሄዳቸውን ይናገራሉ።
በ1972 ዓ.ም የዝንባቡዌ መንግስት ለኢትዮጵያ ባቀረበው የትብብር ጥሪ መሰረት ኮለኔል ሪጃል ከዝንባቡዌ የመጡ ወታደሮችን በታጠቅ ማሰልጠኛ አሰልጥነው ወደ ዝንባቡዌ ይዘው መሄዳቸውንና በዚያም ሙያዊ እግዛ ማድረጋቸውን ይገልጻሉ።ወታደሩ ሀራሬን ነጻ እንዲያወጣና ለውጤት እንዲበቃ በማድረግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ይናገራሉ።
ሌተናል ኮለኔል ሪጃል ኡመር በአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ መንግስት ሶስት ጊዜ የጀብድ፤ ከአስር ጊዜ በላይ የአገልግሎትና የክብር ኒሻኖችን፤ እንዲሁም አንድ የዋንጫ ሽልማት አግኝተዋል።ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰላምና ጸጥታ አስከባሪነት ኒሻን አግኝተዋል።የኢህአዴግ መንግስት በጡረታቸው ላይ በልዩ ሁኔታ 1ሺህ 200 አርባ ብር እንደጨመረላቸውና በህይወት እስካሉ ድረስ በ12ኛ ክፍለ ጦር በኩል ራሺን እንዲደርሳቸው አድርጓል።
ሌተናል ኮሎኔል ሪጃል ኡመር በርካታ ልጆችን ወልደዋል።የመጀመሪያ ባለቤታቸው ወይዘሮ ትብለጽ የስድስት ልጆች እናት ሲሆኑ ከአስራ አምስት ዓመት በፊት በ90 ዓመታቸው ማረፋቸውን ይናገራሉ።ሌሎች አምስት ሚስቶችም ሞተውባቸዋል።በውትድርና ምክንያት ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ልጆች ከወለዱ በኋላ በተለያዩ ምክያቶች የፈቷቸው በርካታ ሚስቶች እንደነበሯቸው ይናገራሉ።አሁን ሶስት ሚስቶች አሏቸው።አጠገባቸው ያሉትን የሁለትና የአምስት ዓመት ህጻናት ጨምሮ ከአርባ ሁለት ልጅ በላይ አላቸው።አንዷ ባለቤታቸው አሁንም ነፍሰ ጡር መሆናቸውን ይናገራሉ።የመቶ አስር ዓመቱ አርበኛ ወደፊትም ልጅ የመውለድ ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ።የመጀመሪያ ልጃቸው ተስፋዬ ሪጃል የልጅ ልጆች አይቶ ጡረታ ከወጣ ከሃያ ዓመት በኋላ በ86 ዓመቱ እንዳረፈ ነግረውናል።ከመቶ ሰላሳ በላይ ለጆችን፣ የልጅ ልጆችን እና የልጅ ልጅ ልጆችን አፍርተዋል።
ዛሬ ኢትዮጵያ በውጭ ጣልቃ ገቦችና በሀገር ውስጥ ባንዳዎች አደጋ ውስጥ መግባቷ ያስቆጣቸው አባት አርበኛ ቢፈቀድላቸው በዚህ እድሜ ላይ ሆነውም በጦር ግንባር ቢሰለፉ ፈቃደኛ ናቸው።የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ወጣቱ የአባቶቹን አርአያ በመከተል ክብሯን ሳታስደፍር የቆየችውን ሀገሩን ከውስጥ ባንዳዎችም ሆነ ከውጭ ወራሪዎች እንዲጠብቅ ጥሪ አስተላልፈዋል።የእድሜ ባለጸጋው አርበኛ ሌተናል ኮለኔል ሪጃል ኡመር።አሁንም እድሜና ጤናን ያብዛልዎት አልን።ቸር እንሰንብት።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013