የተወለዱት ከዛሬ 75 ዓመታት በፊት በቀድሞ አጠራር ኤርትራ ክፍለሃገር ልዩ ስሙ አዲሞገቴ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መንደፈራ በሚባል እና አስመራ በሚገኘው ቤተ -ጊዮርጊስ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን ትምህርት ቤቱ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ርቀት ስለነበረው በየቀኑ ለአራት ሰዓታት በእግራቸው ይጓዙ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በተለይም የአባታቸው ግፊትና ድጋፍ ያለውን ተፅዕኖ ተቋቁመው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመሸጋገር እንዳስቻላቸው የሚያስታውሱት እንግዳችን ከአማርኛ ትምህርት ውጪ ሁሉንም ትምህርት ጥሩ ውጤት በማምጣት ነበር ያጠናቀቁት፡፡ በክረምት የሚሰጠውን ትምህርት ተከታትለው ውጤታቸውን በማሻሻል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በህግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ፡፡ ከዚያም በእንግሊዝ ሃገር በታክስ ፖሊሲ ህግና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡በሆላንድ አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡
ከኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር አንድ ክፍል ውስጥ የተማሩት እኚሁ እንግዳችን ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ በኤርትራ ጉዳይ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉና የኤርትራን መገንጠል አጥበቅው ሲቃወሙ የነበሩ ብርቱ ሀገር ወዳድ ሰው ስለመሆናቸው ይነገራል። ከአንደበታቸው የማይጠፋው የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚያሳስባቸው እኚሁ ሰው በተለይም በንጉሡ ዘመን ከተደረገው የተማሪ አብዮት ጀምሮ በሁሉም መንግሥት ስለሀገራቸውና ስለህዝባቸው መብት በጥብቅ ታግለዋል። ከአምስት አሥርተ ዓመታት በላይ በማስተማርና በማማከር ሥራ ላይ የቆዩት እንግዳችን በተለይም አዲስ አበባ ፣ መቀሌ፣ ሲቪል ሰርቢስ እና ዲላ ዩኒቨርሲቲዎች እየተዘዋወሩ በማስተማር አሁን ስልጣን ላይ ያሉ በርካታ አመራሮችን በመቅረፅ ረገድ የጎላ ሚና ስለመጫወታቸው ይነገራል። በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መንግሥት የገንዘብ ፖሊሲ እና የታክስ ህግ አማካሪ አሁን ደግሞ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን መንግስቱ የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ
ከእንግዳችን ጋር ያደረግነውን ቃለምልልስ እንደሚከተለው ይዘን እንቀርባለን።
አዲስ ዘመን፡– እርሶ ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት ጀምሮ ሁሉንም መንግሥታት ሲቃወሙ እንደነበር ይነገራል፤ ይህ የሆነበት የተለየ ምክንያት ካለ ያጫውቱን?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– እኔ በዋናነት በዚህች ሀገር እኩልነትና ፍትህ በተጨባጭ መምጣት አለበት ብዬ የማምን ሰው ነኝ። በዚህ ምከንያት በሁሉም መንግሥታት ላይ የማስተውለውን ህፀፅ ያለአንዳች ይሉኝታና ፍራቻ ተናግሪያለሁ። ፍትህ እንዲመጣም ታግያለሁ። ከሁሉ በላይ ይህች ሀገር የሰው ዘር መገኛ ጥንታዊ ስልጣኔ ያላት ገናና ሀገር በመሆንዋ ዛሬም ደግሞ ድህነትን ታሪክ አድርጋ እንድትኖር ከፍተኛ ፍላጎት አለኝ። በንጉሡ ዘመን የተማሪ ንቅናቄ ስንጀምር ‹‹መሬት ላራሹ›› ብለን ስንታገል የነበረው የሰሜንን ህዝብ ለመርዳት አልነበረም። አብዛኛው መሬት ላልነበረው የኦሮሞ ህዝብ መሬት እንዲያገኝና ራሱ ዳቦ ጠግቦ እንዲኖር ነበር። አሁን ያሉ አዳዲስ መሪዎች ጉዳዩ በእነሱ እንደተጀመረ አድርገው ሲናገሩ ስሰማ በጣም አዝናለሁ። አሁን ላይ ለኦሮሞ ህዝብ እንታገላለን የሚሉ መሪዎች ሳይወለዱ ነው እኛ ለዚያ ህዝብ ስንጮህ የነበረው። ይሄ ብቻ አይደለም፤ ለአማራ ህዝብም ከማንም በላይ አቀንቃኝ ነበርኩ ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም ዘረኝነት የበለጠ እየተስፋፋ ሲመጣ በአጠቃላይ ህብረተሰቡን ለመለያየት የሚደረጉ የፖለቲካ ሁኔታዎች አይጥመኝም ነበር። እኔ ስለኢትዮጵያ የምናገረው ከወጣትነቴ እስካሁን ድረስ በተግባር የተፈተነ ተሞክሮና እውቀቱ ስላለኝ ነው። በተለይም የዘረኝነት ፖለቲካ እየተስፋፋ ሲመጣ እኔ ከነበረኝ ራዕይ ጋር የሚጣጣም ስላልነበረ የነበሩ አመራሮችን አጥብቄ እቃወም ነበር። የአማራ ህዝብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያ ህዝብ ተበድሎ በድህነት የኖረ ህዝብ በመሆኑ ሊነካ አይገባም ስል እሟገት ነበር። በነገራችን ላይ ከህወሓት ሰዎች ጋር ፀረ አማራ በሆነው አስተሳሰብና በኤርትራ መገንጠል ጉዳይ ተጋጭቼያለሁ። ከዚህ በተጨማሪ እናሰፍናለን ያሉት ዲሞክራሲ በተጨባጭ መሬት ላይ ባለመውረዱና ከምንፈልጋት ኢትዮጵያ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ከእነሱ ጋር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ነበረኝ።
በመሰረቱ ጃንሆይንም እቃወም የነበረው ምንም አይነት ልማት ስላልሰሩ ሳይሆን ሁሉም ህዝብ እኩል ማስተዳደር ባለመቻላቸው ነው። እሳቸው በጊዜያቸው የሚጠበቅባቸውን ያህል ሰርተዋል።ግን እንግሊዝ አገር ስለነበሩ የእንግሊዝ የንጉሣዊ አኗኗር ስለሚያውቁ ልክ እንደእነሱ ሆኖ አገር እየመሩ መኖር ፈለጉ ። ግን እኛ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የምንኖር ህዝቦች በመሆናችን ተመሳሳይ ስርዓት በእኛ አገር መገንባት አዳጋች ነው የሆነባቸው። ያም ቢሆን ግን እሳቸው ድህነትን ባያጠፉም ባላቸው አቅም ሰርተዋል። ለእኛ ግን የሚያጠግብ አልነበረም። ሌላ ተጨማሪ ችግር የነበረው እሳቸው በጣም ስልጣን ፈላጊ መሆናቸው ነበር። ሌላውን ሰው አይሰሙም ነበር። በተለይም በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከፌዴሬሽን ወደአህዳዊ አሰራር ለመቀላቀል የተደረገው ዘመቻ በአግባቡ አልተመራም የሚል እምነት አለኝ። እሳቸው ሥልጣናቸውን ለህዝቡ መስጠት የማይፈልጉ በመሆናቸው ‹‹ስዩመ እግዚአብሄር ›› በሚል ዘላለም መምራት ይፈልጉ ስለነበር ህዝብ መብት አልነበረውም። ህገመንግሥቱም ሲተገበር እንደችሮታ ነው እንጂ የተሰጠው ህዝቡ ጠይቆ አልነበረም። በዚህ ምከንያት አለመግባባት ተፈጠረ።
ደርግም ከመጣ በኋላ የሰራቸው በርካታ ጥሩ ስራዎች ቢኖርም ወታደራዊና አምባገነናዊ ስርዓት በመሆኑ የሕዝቡን ትክክለኛ ጥያቄ መመለስ አልቻለም ነበር። በመሰረቱ እኛ ስንታገል የነበረው ለራሳችን አልነበረም። ይልቁንም ለደሃው ህዝባችን ነበር። አሁን ያለው ትውልድ ግን ያልገባው እኛ የታገልነው ለህዝባችን እንጂ ለራሳችን አለመሆኑን ነው። እኔ ይሄ እውነት እንዲታወቅልን እፈልጋለሁ። በእኔ ትውልድ የነበረው አንድ ሦስተኛ የሚሆነው ወጣት ለአብዮቱ ሲል ነው የሞተው። እኔ እንደአጋጣሚ እንግሊዝ አገር ለትምህርት ሄጄ ስለነበር ነው ህይወቴ መትረፍ የቻለው። በውጭ ሀገር ሆነንም ቢሆን ስለሀገራችን በጣም እንቆረቆር ስለነበር እናነብ ነበር። አብዛኞቹ አሁን ላይ ያሉት ፖለቲከኞች ግን የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር በ60ዎቹ ዘመን የነበርነው ወጣቶች እንደፈጠርነው አድርገው ነው የሚያስቡት። ምንአልባት እዚህ ጋር እንድትገነዘቢልኝ የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ መሪዎች ስህተት ሰርተው ሊሆን ይችላል። ከዚያ በኋላ የነበሩ መሪዎች ግን በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስገባት ትክክል አይመስለኝም።
በአጠቃላይ የእኔ ህይወት ሁለት ቆብ ነበረው ማለት ይቻላል።አንደኛው የአባቴን ፍላጎት ለማሟላትና ትምህርት መሰረት መሆኑ ስለሚገባኝ ትምህርቴን ሳላቋርጥ ጎን ለጎንም ከተማሪ ንቅናቄ ጀምሮ በፖለቲካውም መስክም ተሳትፎ አደርግ ነበር። በፖለቲካው እንድሳተፍ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ ይህ ህዝብ ለምንና እንዴት ደሃ ይሆናል የሚል ቁጭት ስለነበረኝ ነው። አሁንም በተፈጥሮ ሃብት የበለፀገች ሀገር ይዘን ለምን እንራባለን የሚለው ነገር እንቅልፍ የሚነሳኝ ጉዳይ ነው። ለ60 ዓመት በላይ ይህች አገር ራሷን መግባ አረቦችንና አውሮፓን ትመግባለች ብዬ አምኜ ስታገል ቆይቼ እስካሁን ስንዴ ለማኞች መሆናችን እንደማንኛውም ሀገር ወዳድ ዜጋ ልቤን ይሰብረዋል። ለምሳሌ እኔ በምኖርባት ቢሾፍቱ ከተማ ሰባት ሃይቆች አሉ። ነዋሪውን ግን አሁንም በጄሪካን እየተሸከመ ነው የሚጠጣው። የአፍሪካ ህብረት መዲና የሆነችው አዲስ አበባም ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ በየዓመቱ እየዘነበላት ለምንስ ነው ውሃ የሚጠማት? የሚሉትን ነገሮች ሳስብ ሁሌም ያሳዝነኛል።
አዲስ ዘመን፡– እርሶም እንዳሉት ኢትዮጵያ ምንም እንኳን የበርካታ ተፈጥሮ ሃብቶች ባለቤት ብትሆንም ዛሬም ከድህነት መውጣት አልቻለችም። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ምንድን ነው ብለው ያስባሉ? መፍትሄውስ?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– እኔም የሚያሳዝነኝ ነገር ይህ ነው። እግዚአብሄር ሁሉን ሰጥቶን እያለ ግን ደሃ ነን። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት መሪዎቻችን ናቸው ብዬ ነው የማምነው። መሪዎች ሀገሪቷንና ህዝቧን እንመራለን ብለው ስልጣን ቢቆናጠጡም እውነተኛ የሕዝብ አገልጋዮች መሆን ባለመቻላቸው ነው ሀገሪቱ በድህነት ውስጥ እንድትቆይ ያደረጉት። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእድሜም ሆነ በትምህርት የላቀ እውቀት ያላቸውና ስለሃገራቸው እንቅልፍ የሚነሳቸው ምሁራን በአገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር መደረጋቸው ህዝቡ ዛሬም በተወሳሰበ ችግር ውስጥ እንዲዳክር ምክንያት እንደሆነ አስባለሁ። አሁንም ስልጣን ላይ ካሉት መሪዎች በላይ በእድሜም ሆነ በእውቀትም የበሰሉ አገር ወዳድ የሆኑ በርካታ ምሁራን አሉ። አንድ መሪ እጅግ በጣም ጎበዝና አርቆአሳቢ ሊሆኑ ይችላሉ። ግን አገር በአንድ ሰው ብቻ አትመራም፤ ሁሉም ጥያቄ በአንድ ግለሰብ አይመለስም። በመሆኑም የሁሉም እውቀትና አስተዋፅኦ ሊኖር ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ሌላው ቢቀር ከበስተጀርባም ሆነው የሚያማክሩ ጥሩና ቅን ሰዎች ያስፈልጋሉ። ይሁንና ብዙውን ጊዜ መሪዎች የሚሞግታቸውና በምክያታዊነት የሚያስብ ሰው አይፈልጉም፤ ይልቁንም እሺ ብሎ የሚታዘዝና የተላላኪነት ስብእና ያለውን ሰው ነው የሚያቀርቡት። እንደእኔ እምነት መሪዎች ተላላኪ አይደለም የሚያስፈልጋቸው፤ጥሩ አማካሪዎች ነው የሚያስፈልጋቸው። እንደእኔ ያሉ በትምህርትም ሆነ በህይወት ተሞክሮ ብዙ እውቀት ያካባቱ ሰዎችን በጊዜው መጠቀም ያለመቻሉ አንድቀን ከነ እውቀታችን ስናልፍ የምትጎዳው አገሪቱ ናት የሚል እምነት ነው ያለኝ።
ከዚሁ ሁሉ በላይ ግን አንድነታችን ያልተጠበቀ በመሆኑ ነው አገራችን ልታድግ ያልቻለችው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ብዙዎቻችን ኢትዮጵያን እንወዳታለን ብለን እርር ኩምትር ብለን እንናገራለን፤ በተግባር ግን አንድነት የለንም። ስለሰላም ብዙ ይወራል። ስለሰላም አስፈላጊነት ሁሉም በየጊዜው ይናገራል። ግን ተግባር የለም፤ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ሰው የለም።
እኔ ከነኮነሬል ጎሹ ወልዴ ጋር ስታገል የነበርኩና የመድህን ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የነበርኩ ሰው ነኝ ። ይህንን ያቋቋምነው ዘረኝነት ለማስፋፋት አይደለም። መጀመሪያ ላይ ኢህአፓን ነበር የምከተለው። ለትምህርት አውሮፓ በነበርኩበት ጊዜ የግራሃይሉን ስናንቀሳቅስ የነበርነው እኔና ጓደኞቼ ነን። አሜሪካም ሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ትግል ይደረግ ነበር። ግን በዚያን ጊዜ የነበሩ የ60 ዎቹ ትውልድ ስህተት አልሰሩም ማለት አይደለም። ብዙ ስህተት ተሰርቷል። ግን ካለማወቅ እንጂ የሀገሩን ጥቅም አሳልፎ የሰጠ አልነበረም።
አዲስ ዘመን፡– አሁን ላይ ያለው ትውልድ በጋራ ጉዳዮች ጭምር አለመስማማት መፈጠሩ ሀገሪቱን ወደየት ሊመራት ይችላል ?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– አስቀድሜ እንደነገርኩሽ ከ50 ዓመት በፊት የኤርትራን መገንጠል እንኳን በፅኑ ስቃወም ነበር። አሁንም እርስበርሳችን መግባባት ያለመቻላችን ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ያሰጋኛል።
ሰሚ በማጣቴም ያሳዝነኛል። እንደአንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር የማስተማርና ትውልዱን የመቅረፅ ግዴታዬን ተወጥቻለሁ ብዬ ባምንም የሚሰማኝ ስላልነበረ የኢትዮጵያ ችግር ደግሞ አብዛኛው ጊዜ በመሳሪያ መልስ ስላላገኘ እስካሁን የምፈልጋትንና የምመኛትን ኢትዮጵያ ለማየት አልታደልኩም። ሃዘንተኛ ነኝ የምለው ለዚህ ነው። እኔ ጠብመንጃ ይዤ አልታገልም። እኔ የምታገለው በሃሳብ ነው። በነገራችን ላይ ብዙ ጊዜ ‹‹የሃሳብ ፍጭት ያስፈልጋል›› ይባላል። ግን ሃሳብ የሚሰማም ሰው የለም። ከወሬ ባለፈ በተግባር መደማመጥ የሚፈልግ የለም። እኔ ባለኝ አቅም ወጣቱን ለማስተማር እሞክራለሁ። ከመናገር ባላይ ግን ምንም ማድረግ አልችልም።
አዲስ ዘመን፡– ታዲያ እርስበርስ መደማመጥ ያላስቻለን ትክክለኛ ምክንያት ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– እኔ እንደሚታየኝ ከሆነ የዘረኝነትና የጎሰኝነት ፖለቲካ ከሚገባው በላይ ልቅ መውጣቱ ነው እርስበርስ እንዳንደማመጥ ያደረገን። እርግጥ ነው ቀድሞ የነበረችው ኢትዮጵያ አህዳዊ ነበረች። አጼ ኃይለሥላሴ የህብረተሰቡን ንቃተ ህሊና ማደጉን ተገንዝበው ሥልጣናቸውን ለቀቅ ቢያደርጉ ኖሮ ይህ ሁሉ ባልመጣ ነበር። ኤርትራም ላትገነጠል ትችል ነበር። ይቅርታ አድርጊልኝና ግን የሁሉም ችግሮቻችን መንስኤ የጎሳና የዘረኝነት ፖለቲካ ነው። የጎሳ ፖለቲካ ደግሞ የመሃይም ፖለቲካ ነው ብዬ ነው የማስበው። አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ። አፄ ምኒልክ የኦሮሞ ሴቶች ጡት ቆርጠዋል ተብሎ አይደለም እንዴ ዛሬም ድረስ በብዙዎች አዕምሮ የማይጠፋ የጥላቻ ነቀርሳ ያወረስነው? ታዲያ አሁንስ በየቦታው የሚደረገው ጭፍጨፋ ምን ያህል ጠባሳ ሊያመጣ እንደሚችል ሰው አይገነዘበውም? እዚህም ሆነ እዚያ የሚሞቱት ኢትዮጵያውን ናቸው። የእኛ ሰዎች ናቸው። ታዲያ ካለፈው ስህተት ለምን መማር እንዳልቻልን ለእኔ እንቆቅልሽ ነው።
እሱ ብቻ አይደለም፤ ጦርነት ለማንም እንደማይበጅ ሁልጊዜ ይነገራል። ግን በተግባር የምናየው ሌላ ነው። እርግጥ ነው የህወሓት መሪዎች ብዙ ስህተት እንደሰሩ አውቃለሁ። ግን እነሱ ብቻ አይደሉም። አብዛኞቹ በኢህዴግ ስር የነበሩ መሪዎች አሁን ብልፅግና ውስጥ ሆነው ምንም እንዳልበደሉና ከደሙ ንፁህ አድርገው ራሳቸውን ሲያቀርቡ በጣም ያሳዝነኛል። በአጠቃላይ እኔ የማምነው መሪነት በዓርአያነትና በተግባር ነው። እኔ የጎሳ ፖለቲካ የትም አያደርሰንም ብዬ ነው የማስበው። አሁን ላይ የነገሰው አስተሳሰብ ይሄ ነው። ይህ በመሆኑ ምንአይነት ኢትዮጵያን እንፍጠር የሚለው ጉዳይ ላይ መግባባት የለም። የጎሳ መሪዎች ተሰብስበው ኢትዮጵያ ይመስርቱ ወይስ ለልማትና ብልፅግና የሚመች ሀገር እንፍጠር ? ድህነትንስ እንዴት ነው የምናጠፋው? በሚሉት ጥያቄዎች ላይ ስምምነት የለንም።
በነገራችን ላይ ሰላም የሚመሰረተው ከወዳጅ ጋር አይደለም። ሰላምና እርቅ መፍጠር የሚቻለው ወዳጅ ከሆኑት ጋር አንድ ፓርቲ መመስረት አይደለም። ይልቁንም ካኮረፉ ፣ ጠብመንጃ ከያዙና ከሸፈቱ ጋር ነው ስምምነት መፍጠር የሚገባን። እኔ ከታሪክ መማር ያለብን ነው የሚመስለኝ። ደርግ ህወሓትና ሻዕቢያ ሁልጊዜ ‹‹በሰላማዊ መንገድ መፍታት ነው የምንፈልገው ›› እያሉ በተግባር ግን ጦርነት ነበር ሲያካሂዱ የነበሩት። ደርግ ሲጠነክር ለእርቅ ያለው ፍላጎት ይቀንሳል። ህወሓትና ሻቢያም ሲጠነክሩ ተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው። በመጨረሻም ችግራቸው በጠብመንጃ ነው የተፈታው። አሁንም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ችግራችንን መፍታት አለብን ብዬ ነው የማምነው። ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በህብረት ልንታገል ልንሰራ ይገባል። አገራዊ መግባባት ያስፈልጋል። አገራዊ እርቅ ያስፈልጋል። ግን ደግሞ ለይስሙላ ሳይሆን ቅንነትን መሰረት ያደረገ ነው መሆን ያለበት። የሃገሪቱን መሰረታዊ ፍላጎት ያገናዘበ፤ የሕዝቡን ጭንቀትና ብሶት መልስ መስጠት የሚችል እውነተኛ ሀገር ወዳድ የሆኑ የህዝብ ተወካዮች ስምምነት ሲደርሱ ነው ሊመጣ የሚችለው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለምርጫው ያለኝን ሃሳብ መግለፅ እወዳለሁ።እርግጥነው ምርጫው መካሄዱ የማይቀር ነው። ግን እንደእኔ አስተያየት አሁን ሀገሪቱ በውስብስብ ችግር ውስጥ ባለችበት ሁኔታ ህዝቡ በተፈናቀለበት፣ ድህንነት በበዛበት ፣ የኑሮ ውድነት በከፋበት ወቅት ለምርጫ መሯሯጥ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። ሀዘንና ጭንቀት ያለን ህብረተሰብ ሰርግ እንደመደገስ ነው እኔ የምቆጥረው።
አዲስ ዘመን፡– እርሶ ይህንን ቢሉም ሌሎች ግን ‹‹ምርጫ ያለመካሄዱ በህዝብ ያልተመረጠ መንግሥት ሀገሪቱ እንድትመራ ማድረግ ወደባሰ ችግር ይከታታል›› ብለው የሚያምኑ ሰዎች አሉ?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– በእኔ እምነት ምርጫው ለሁለት ዓመት ቢተላለፍ ምንም አይነት ችግር አይፈጠርም። አሁንም ቢሆን ምርጫው መሰረታዊ ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም። ይህንን አቋሜን አስቀድሜ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በፅሁፍ ገልጪያለሁ። የሀገራችንን ችግር ለመፍታት ከልባችን የምንፈልግ፣ ለህብረተሰቡ ጭንቀት መልስ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ስልጣን ዋጋ የለውም። አፄ ኃይለሥላሴ የህዝቡን መሰረታዊ ችግር ከመፍታት ይልቅ እንደአምላክ ሲመለኩ ኖረው መጨረሻ ላይ አሟሟታቸው እንኳን አሳዛኝ ነበር። መንግሥቱም በሚያሳዝን ሁኔታ ከአገሩ ተሰዶ ነው ያረጀው። ስልጣን ለእኔ አደንዛዥ እፅ ነው። ስለዚህ እውነት ለማናገር ኢትዮጵያን ለመምራት የሚፈልጉ ሰዎች በእርግጥ ህዝቡን ለማገልገል ቁርጠኝነት ካላቸው በአገር ጉዳይ ላይ አንድ ሊሆኑ ይገባል። አገር እስክትረጋጋና ወደሰላማዊ ሁኔታ እስክትመለስ መጠበቅ ይገባቸዋል ብዬ ነው የማምነው። አሁን ላይ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ እንዴት ዳቦ ጠግቦ ያድራል? እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ነፃ ህክምና ያገኛል? እንዴት ጥራት ያለው ትምህርት ያገኛል? እንዴት ኑሮው ሊሻሻል ይችላል? በሚሉት ጉዳዮች ላይ አይደለም እየተወያዩበት ያለው። ከዚያ ይልቅ እዚህ እዚያም የስልጣን ሹክቻ ነው የሚታየው። በአጠቃላይ ከምንም በፊት መሰረታዊ ፍላጎታችን ሊሟላ ይገባል ብዬ ነው የማምነው። ወደ ተባባሰ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይገባ ማድረግ መቻል አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ኢትዮጵያ አንዴ በሶሻሊዝም አንዴ ደግሞ በገበያ መር ኢኮኖሚ መመሯቷ በኢኮኖሚ እድገቱ ላይ ምን አይነት አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– ውዥንብር ውስጥ የከተተን አንዱ ጉዳይ አሁን ያነሳሽው ነገር ይመስለኛል። ምንአይነት ኢኮኖሚያዊ ስርዓት ነው የሚያስፈልገው የሚለው ነገር አሁንም ያልተግባባንበት ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በነጉሡ ዘመን የካፒታሊዝም ጭላንጭል የነበረበት ዘመን ነው። እኔ እንደማስታውሰው ሐረማያ የእርሻ ኮሌጅ የተማሩ መምህራን ገበያ ተኮር እርሻ ጀምረው ነበር። ከዚያ በኋላ ተቀለበሰና ከንጉሡ የተጠጉ ጥቂት ግለሰቦች ያላአግባብ ከፍተኛ ሃብት ማፍራት ጀመሩ። በእውነቱ ደርግ አረመኔና ገዳይ መንግሥት ቢሆንም እውነተኛ የድሃ ወገን እንደሆነ ነው የማውቀው። ድህነትን ለማጥፋት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሆኔታዎች ላይ እርምጃ ወስዶ ነበር። ነገር ግን ይፈፅማቸው በነበረው ግድያ ህወሓቶች እንዲመጡ አድርጓቸዋል። ኢህአዴግ ከመጣ በኋላ ልማታዊ መንግሥት የሚል አሰራር ነው የመጣው። በነገራችን ላይ ይህ ስርዓት የአቶ መለስ የግል የፈጠራ ውጤት አይደለም። ጃፓን፣ ኮሪያ የመሳሳሉት አገራት በተግባር የሰሩበት ነው። እኛ ኢትዮጵያኖች ዝም ብለን ማድነቅ ስለምንወድ ነው እንደብቸኛ የእድገት አማራጭ አድርገን የተቀበልነው። ያም ሆኖ ቢሰራበት ጥሩ ነው ብዬ ነው የማስበው። ነገር ግን አስተዳደሩ ጥሩ አልነበረም። የተገበርንበትም መንገድ ውጤታማ አላደረገንም። በዋናነት ደግሞ የእኛ የግሉ ዘርፍ በጣም ደካማ ነው። በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር አንከተልም። የምናስተዳደርበት ስርዓትም ሆነ አስተሳሰባችን ወደኋላ የቀረ ነው። ተቋማትም የሉንም።
መንግሥት በብቃትና በውጤታማነት ቢያስተዳድር ኖሮ ልማታዊ መንግሥት ስርዓት አዋጭ ሊሆን ይችል ነበር። ነገር ግን ሙሰኝነቱም በዛ። ይህ ደግሞ ህዝቡ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት እንዲጓደልና ጥላቻ እንዲኖረው አደረገ። ይህንን ስል ደግሞ ጭልጥ ብሎ ወደ ነፃ ገበያ መግባትም ትክክል አይመስለኝም። ይህንን የምልሽ እነእንግሊዝም ሆነ ሌሎች ያደጉት አገራት የመጀመሪያዎቹ ኢንዱስትሪዎች ያቋቋሙት ከአራት መቶ ዓመታት በፊት ነው። ስለዚህ እነሱ የአምስት መቶ ዓመት ልምድ አላቸው። የሁለት መቶ ዓመት የቴክኖሎጂ እምርታ አላቸው።በርካታ ተቋማትን መስርተዋል። የግሉ ዘርፍም ከመንግሥት አቅም በላይ የተጠናከረ ነው። ስለዚህ እነሱ ነፃ ገበያ ቢሉ ይገባቸዋል። የግሉ ዘርፍ ኢኮኖሚውን ሊመራ ይገባል ቢሉም ትክክል ናቸው። እኛ ግን ወደኋላ የቀረን ህዝቦች ነን። በመሆኑም መንግሥት በአግባቡ እየመራ መዋቅሩ ከሙስና የፀዳ ሆኖ ፣ መሪዎች በሥልጣንና በገንዘብ ሳይሰክሩ፤ የህዝብ አገልጋይ ሆነው ድህንነትን ታሪክ ማድረግ ይችላሉ።
አዲስ ዘመን፡– ከለውጡ በኋላ የሃገሪቱ መንግሥት ለኢኮኖሚው ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት እንዴት ያዩታል? በተለይም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ስትራቴጂን መከተል ለአገሪቱ እድገት ያለው ፋይዳ ምንድን ነው?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– ለእኔ ሀገር በቀል የሚባል የኢኮኖሚ ስትራቴጂ አከራካሪ ጉዳይ ነው። ዝም ብሎ በደፈናው አገር በቀል ይባል እንጂ ከውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት እንላቃቀለን ብዬ አላምንም። አብዛኛው ከውጭ የተኮረጀ ነው። አብዛኛው የእጅ አዙር የእውቀት ቀኝ ግዛት አለ ብዬ ነው የማስበው። በመሰረቱ እውነተኛ የሆነ ሀገር በቀል እውቀትና አሰተሰሳብ ያላቸው ምሁራን አላፈራንም። እያስተማርን ያለነው የውጭ ጸሃፍት የፃፉትን ነው። ሌላ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ በአገራችን ገበያ ላይ የሚቀርበው 90 በመቶ የሚሆነው ምርት ከውጭ የመጣ ነው። ይህ ነበራዊ ሁኔታ እያለ የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ስትራቴጂ እንዴት ነው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው? እኛ እንዴት ነው ማንጎ ከዱባይና ከሌሎች አረብ አገራት እያመጣልን አገርበቀል ኢኮኖሚ ተግባራዊ እያደረግን ነው የምንለው?። እኛ ከውጭ የምናስመጣውን ከመተካት ይልቅ የወሬና የመጠጥ ፋብሪካ ማቋቋም ላይ ነው የተያያዝነው። በተለይም መሰረታዊና ስትራቴጂክ የሆነ ምርቶች ከውጭ ነው የሚመጡት። የኢንዱስትሪ ፓርኮቻችን ግብዓቶች አብዛኛው ከውጭ ነው የሚመጣው። ከውጭ ስለሚመጣ ደግሞ የውጭ ምንዛሬው በሀገሪቱ ላይ ተጨማሪ ጫና ነው እየፈጠረ ያለው። ስለዚህ እኛ የሀገራችን ባለሃብቶች በተቻለ መጠን በቴክኖሎጂ፣ በፋይናንስ፣ በአመራር እየደገፍን ማብቃት ይኖርብናል። ይህም ሲባል ግን እውነተኛ ባለሃብቶች ማለቴ ነው። ዝም ብሎ አንዳንድ ጊዜ ከመጣ መሪ ጋር እየተዛመዱ ህዝብ የሚበዘብዙ ሳይሆኑ እውነተኛ አገር ወዳድ ባለሃብቶች ካሉ ቅድሚያ መስጠት ነው ያለብን።
በሁለተኛ ደረጃ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በመሰረታዊነት የህዝቡን የምግብ ዋስትና ሊያረጋግጡ በሚችሉ ምርቶች ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ባይ ነው። ለዚህ ደግሞ ግብርናውን ማዘመን ያስፈልገናል። እኔ በወረቀት ላይ የቀረ ስትራቴጂ ይጠቅመናል ብዬ አላምንም። ወደመሬት መውረድ አለበት። ከዚህ አንፃር ወጣቱን ወደስራ የሚያስገባ ስትራጂ መተግበር ይገባናል። ጥቃቅና አነስተኛ ተቋማትን የምንመራበት ስርዓት ከአደረጃጀቱ ጀምሮ ከብሄርተኝነትና ከወገንተኝነት የፀዳ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወጣት እኩል ተጠቃሚ የሚሆንበትን ስርዓት ማበጀት ያስፈልጋል። እርግጥነው የሀገራችን ችግር ውስብስብ እንደሆነ ይገባኛል። በመሆኑም በሁሉም ደረጃ ተከታታይ የሆነ ውይይት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡–አሁን ላይ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ማስተካከልም ሆነ የዜጎችን የመኖር ህልውና ማረጋገጥ የሚቻለው በምን መንገድ ነው ?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– በመጀመሪያ ደረጃ ድህነትን ለማጥፋት ህዝብ ላይ ያተኮረ ፖሊሲ ማውጣት መቻል አለበት። አርሶአደሩ በተጨባጭ የመሬት ባለቤት ማድረግ ያስፈልጋል። አሁን ላይ እየተከተልን ያለነው ከተማ ተኮር ፖሊሲ ባላሃብቱን ከመሬቱ ብቻ ሳይሆን ከኑሮው እያፈናቀለው ነው። ለእርሻ የሚውለውን መሬት ለኢንቨስትመንት እየሰጠን በመጣን ቁጥር የምግብ ዋስትናችን ጥያቄ ውስጥ ነው የሚገባው። ዛሬ መሬቱ የተወሰደበት ገበሬ ነገ ለማኝ መሆኑ አይቀሬ ነው። ይህም ፖሊሲዎቻችን መሰረታዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑ ያስረዳሻል። ከዚህ ባሻገር ሀገሪቱን እየመሩ ያሉትም ሆነ ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች በአገሪቱ ሰላም ሰፍኖ ትክክለኛ ልማት እንዲመጣና ህዝቡ እየተሰቃየበት ያለው የኑሮ ውድነት ችግር መፍታት የሚፈልጉ ከሆነ ታች ድረስ ወርደው ነባራዊ ሁኔታውን መገንዘብ አለባቸው ባይ ነኝ። ምሁራንም የችግሮቹን መንስኤ በተጨባጭ መሬት ላይ ወርደው ማጥናትና መፍትሄ ማምጣት አለባቸው። አሁን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም። አንድአንድ ጊዜ ድርጅቶችን የምናቋቁመው ለማቋቋም ብቻ በሚል እንጂ ትክክለኛ ለውጥ ለማምጣት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ኖሮ አይመስልም። ለዚህ ነው ሁልጊዜ የችግር አዙሪት ውስጥ የምንገባው። ቅንነትም ብዙ አላይም። የስልጣን ሽኩቻ እዚህም እዚያም ይታያል። የሀገራችን መሰረታዊ ፍላጎትና ጥቅም የማስቀደም ሁኔታ ብዙ አላይም። ይህ ጉዳይ ያሳስበኛል፤ እንቅልፍም ይነሳኛል። መሪዎች በእውነት የህብረተሰቡ አገልጋይ መሆን ነው ያለባቸው። ከአገር ይልቅ ራስ ወዳድነት ነው የነገሰው። ይህ እስካለ ድረስ ልማት ማምጣትም ሆነ ህዝቡን ካለበት የኑሮ ውድነት ማላቀቅ አንችልም። አማራጭ ይዞ የሚመጣ መሪ አለመኖሩ ራሳቸው የችግሩ አካል ሆነው ነው የሚታዩት። በመሆኑም ብሔራዊ አንድነት በማምጣት ሰላምና መረጋጋትን ማረጋገጥ ይኖርብናል። በተጨማሪም መንግሥት ለኑሮ ውድነት ምክንያት የሆኑ አካላትን ከራሱ መዋቅር ጀምሮ ማጥራትና እርምጃ መውሰድ ይገባዋል። ጠንካራ ግን ደግሞ አምባገነን ያልሆነ መንግስት ሊኖረን ይገባል። ይህም ማለት የህዝቡን ጥቅም ከማረጋገጥ አኳያ ቁርጠኝነቱንም በተጨባጭ ማሳየት ይኖርበታል። ህብረተሰቡም በስሜት ከመነዳት ይልቅ መንግሥትን የሚጠይቅ መሆን ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን፡– እንደቻይና ሲንጋፖርና ኮሪያ የመሳሉ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለመላቀቅ ምንአይነት የኢኮኖሚ ስርዓት መከተል አለብን ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ፍስሃ ፂዮን፡– በመሰረቱ በመጀመሪያ በዚህች ሀገር ሰላም ማስፈን ይገባናል። ሁሉም ነገር ሊኖር የሚችለው ሰላም ሲኖር ነው። ከዚህ አንፃር አለመረጋጋት መኖሩ በኢኮኖሚው ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ብዬ ነው የማምነው። በሌላ በኩል ምንም አይነት ፖሊሲ ብንቀይስም ሆነ ስትራቴጂ ብንነድፍ አገር ወዳድ መሪም ሆነ ትውልድ ካልፈጠርን ውጤታማ መሆን አንችልም። እነዚህ አንቺ የተጠቀሻቸው ሀገራት ያደጉት አገራቸውን የሚወዱና ለህዝባቸው የሚቆረቆሩ መሪዎች በየደረጃው ስላሏቸው ነው። የመንግሥት አመራሩም ሆነ የግሉ ዘርፍ የራሱን ጥቅም ከማስጠበቅ ባለፈ የህዝቡን ችግር መቅረፍ አይፈልጉም። በተለይም ነጋዴው የህብረተሰብ ክፍል ህዝቡ ያለበትን ችግር ከመረዳት ይልቅ አሁን ያለውን ሁኔታ በመጠቀም በአቋራጭ ለመክበር ነው የሚሮጡት። ከዚሁ ሁሉ ውስብስብ የአመለካከት ችግር በመጀመሪያ መውጣት አለብን።
ወደ ጠየቅሽኝ ጥያቄ ስመለስ ግን ለእኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዚህች ሀገር እድገት ማስመዝገብ የምንችለው ከውጭ የሚመጡትን ግብዓቶች እዚሁ ማምረጥ የምንችልበትን ስርዓት በተጨባጭ ስንፈጥር ነው። ለድሃው የሚሰጡት ተስፋዎች በተጨባጭ ልናያቸው ይገባል። በሌላ በኩል በኢንቨስትመንት ስም ያለአግባብ የምናስገባቸው የውጭ ሀገር ባለሃብቶች እንዲበዘብዙን እድል ሰጥተናቸዋል። በዚህ ጉዳይ ቀድሞ ከነበሩት መሪዎች ጋር ብዙ ተሟግቻለሁ። ባለሃብቶች በብዛት መምጣቸውን እንጂ በሚታይ መንገድ ጥቅም ስለማምጣታቸው የሚያጠና አካል የለም። ለምሳሌ ባሃብቶቹ ተመዝግበው መምጣታቸውን እንጂ ካፒታሉን እንዴት እንዳስገቡ የምናጠናበት መንገድ የለም። ይህንን የምልሽ ደግሞ ከባዶ ተነስቼ አይደለም። በተጨባጭ በጥናት አረጋግጬ ነው። ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው ውሎች ምን ያህል ጠቃሚ ነው የሚለው ነገር አይታወቅም።
አዲስ ዘመን፡– አሜሪካ በኢትዮጵያ መሪዎች ላይ ያደረገችው የጉዞ እገዳ በኢኮኖሚው ላይ ምንአይነት ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል ብለው ያምናሉ?
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– ማዕቀብና እገዳዎች በኢኮኖሚ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድርም፤ ላያሳድርም የሚችልበት ሁኔታ አለ። ምክንያቱም በተለያየ ሀገራት ላይ የተለያየ ውጤት አምጥቷል። እነሱ በይፋ እንዲሁ ማዕቀብና እገዳ ባይጥሉብንም እንኳን በኢንቨስትመንት ስም በገዛ እጃችን ቀኝ እየተገዛን ነው። የማንም ሀገር ባለሃብት ኢትዮጵያ መጥቶ የፈለገውን ሃብት እንዲበዘብዝ እድል ተሰጥቶታል። ይልቁንም አንድ ኢትዮጵያዊ ባለሃብት በፈለገው ክልል ሄዶ ማልማት የሚችልበት እድል አልተሰጠውም። በጥሬ ዕቃም ሆነ በፋይናንስ የእነሱ ጥገኛ ሆነናል። ለዚህ የዳረገን ደግሞ ህብረት የሌለን በመሆኑ ነው። አንድነታችን በመሸርሸሩ ብዙ ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ችግር ፈጥሮብናል። ህብረት ቢኖረን ኖሮ ሱዳንና ግብፅ አይጫወቱብንም ነበር። ለእኔ አሁንም ቢሆን የውጭ ሃይሎችን መከላከልም ሆነ እነሱ የሚያደርጉብንን ጫና መቋቋም የምንችለው አንድነታችንን ስናጠናክር ነው። የእኛ ዋስትና አንድነታችን ነው። ማንም የውጭ ሃይል በእኛ በኩል ክፍተት ከሌለ ሊጎዳን አይችልም። አሁን ላይ 40 ቢሊዮን ብር እዳ አለብን። ይህ ባለበት ሁኔታ ከውጭ ተፅዕኖ ለመላቀቅ ከባድ ነው የሚሆንብን። ለዚህ ነው ውልና ስምምነት ከማድረጋችን በፊት በአግባቡ ልናጤነው ይገባል ያልኩሽ።አሁን በኢንቨስትመንት ስም የሚደረጉ ስራዎች ዛሬ ተፅዕኖዎቻቸውን ባናይ ከአምስትና ከአሥር ዓመት በኋላ ግን ማየታችን አይቀርም።
ከዚህ ጋር አያይዤ መናገር የምፈልገው ነገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን አስመልክቶ ነው። እነሱ በተመቻቸ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ነው ያሉት። ውጭ ሆነው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሃገራቸውንና ህዝባቸውን እየጎዳ ስለመሆኑ ማጤን ይገባቸዋል። ውጭ ያሉ ምሁራን ሩቅ ሆነው ከማውራት በዘለለ ሀገራቸው መጥተው የመፍትሄ አካል ሊሆኑ ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ባሉበት አገርም ሆነው መንግሥታቱ ላይ የተቀናጀ ጫና ማድረግ ይገባቸዋል። ሌላው የምሁራን ሚና ነው። ምሁራን አድርባዮች መሆን የለባቸውም። ለህሊናቸው ማደርና ለኢትዮጵያ ድሃ ህዝብ መቆርቆር ወገንተኝነት ማሳየት መቻል አለባቸው። ሲመክሩም ለሀገርና ለወገን ነው መሆን ያለበት እንጂ የራሳቸውን ጥቅም ለማግበስበስ መሆን የለበትም። ዓላማ ሊኖራቸው ይገባል። የተማርነው ሀገርና ህዝብ ለማገልገል ነው። አምባሳደሮችንም ስራቸውን በአግባቡ ሊሰሩ ይገባል። ኢትዮጵያን ወክለው እስከአሁን ድረስ ለፓርቲ ሳይሆን ለአገራቸውና ለህዝባቸው መስራት ነው የሚገባን። አንዳንድ አምባሳደሮቻችን ብቃት የሌላቸውና መግባባት እንኳን የማይችሉ ናቸው። አሳምነው የሀገራቸውን ጥቅም ሊያስጠብቁ የሚችሉ መሆን ይገባቸዋል።
በአጠቃላይ ህብረት ሲኖረን የማንም አገር ጣልቃ ገብነት ሊኖርብን አይችልም። እኛ በህብረት አገራችን ካሳደግን ሊያሸንፉን አይችሉም። ለምሳሌ እስራኤልን ማንሳት እንችላለን፤ በርካታ ጠላት ሀገራት ከበዋት ሳለ ከየትኛው ሀገር በላይ በሃይልም በአቅምም በልጣ ጠላቶቿን ትመክታለች። ስለዚህ ይህ እገዳ እኛ የምንተባበርና በጋራ የምንሰራና አቅማችን ማሳደግ የምንችል ከሆነ ጉዳት አያደርስብንም።
አዲስ ዘመን፡– ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሠግናለሁ።
ፕሮፌሰር ፍስሃፂዮን፡– እኔም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013