በክፋት ተጠንስሶ በክፋት ያደገው አሸባሪው ህውሓት በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ በፈጸመው ጥቃት ምክንያት የመጨረሻ ግብዓተ መሬቱ ቢፈጸምም አሁንም የቀሩ ርዝራዦች የትግራይ ህዝብ መከራው እንዲበዛና ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳያገኝ በርካታ መሰናክሎችን ሲፈጥሩ ይታያሉ። አሸባሪ ቡድኑ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ካለችው እንስሳ ባነሰ መልኩ ክልሉ የግጭትና የሁከት ማዕከል ሆኖ እንዲታይ በደከመ እስትንፋሱም ቢሆን ከመቃብር ውስጥ ሆኖ ዕኩይ ተግባሩን ለማስቀጠል ቢሞክርም በትግራይ ህዝብና በኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት አሸባሪ ቡድኑ እየመከነ ይገኛል።
የሽብር ቡድኑ ትግራይን የሁከትና የግጭት ማዕከል እንደሆነች አድርጎ ለውጭው ዓለም ለማሳየት ሙከራ ቢያደርግም የትግራይ ህዝብ ለአርባ አራት ዓመታት ከተጫነው ቀንበር ተላቆ ነገን በተስፋ መመልከት ጀምሯል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ክልሉን ሰላምና መረጋጋት የሰፈነበት ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል። በክልሉ የተጀመረውን ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግም አራት ሺ የሚደርሱ የክልሉ ፖሊሶች ስልጠና እየወሰዱ ነው። በህወሓት አሸባሪ ቡድን የተፈጠረውን ብዥታ ለማጥራትም ሁለት ሺ ከሚደርሱ ነዋሪዎች ጋር ውይይት በመደረግ ላይ ነው። አንድ ሺ ሦስት መቶ ወጣቶችም የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስልጠና እየወሰዱ ናቸው።
በህወሓት አሸባሪ ቡድን የፈራረሱ መሰረተ ልማቶችም ተጠግነው ለህዝቡ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል። በአሸባሪ ቡድኑ የተጎዳውና ተቋርጦ የነበረ ከ1 ሺ 25 ኪሎ ሜትር በላይ ኤሌክትሪክ መስመር ተጠግኖ ለህብረተሰቡ ተደራሽ የተደረገ ሲሆን፤ የቴሌኮም መስመሮችም ተጠግነው ለአገልግሎት በቅተዋል። የመማር ማስተማር ሂደቱ ተቋርጦባቸው የነበሩ ትምህርት ቤቶች ዳግም እንዲከፈቱ ለማድረግም ከ195 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል።
ከራሱ አልፎ ለሌሎች ወገኖች መትረፍ የሚችለው የትግራይ ህዝብ የህወሓት አሸባሪ ቡድን በየጊዜው በሚፈጥራቸው ሁከቶችና ግጭቶች ለተለያዩ ሰብዓዊ ቀውሶች ሊጋለጥ ችሏል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይፋ እንዳደረገውም የህወሓት አሸባሪ ቡድን በፈጠረው ቀውስ ምክንያት ላለፉት ስምንት ወራት ክልሉ በዕርዳታ ላይ የተመሰረተ አካሄድን ሲከተል የቆየ ሲሆን፤ አሁን እየታየ ባለው ለውጥ ምክንያት ፊቱን ወደ ልማት አዙሯል። የአሸባሪው ቡድን ርዝራዦች እና ዓለም አቀፍ ደጋፊዎቻቸው በትግራይ ክልል የከፋ ርሃብ ይገባል የሚል ሙሾ ቢያወርዱም በአሁኑ ወቅት ሊታረስ ከሚችለው መሬት 70 ከመቶ በሚሆነው መሬት ላይ የግብርና ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። እነዚህና መሰል የልማት ሥራዎች የትግራይን ህዝብ ተስፋ ከማለምለማቸውም ባሻገር ትግራይን የሁከትና የግጭት ማዕከል አድርጎ ለማሳየት ለሚታትሩት የአሸባሪ ቡድኑ ቅሬቶች እስትንፋሳቸው እንዲቆም የሚያደርጉ ናቸው።
በተለይም ጊዜያዊ አስተዳደሩና የፌዴራል መንግሥት የያዟቸው የሰላምና ልማት አቅጣጫዎች ከተሳኩ አሸባሪ ቡድኑ ህዝቡን የሚያደናግርበት አጀንዳ እንደሚዘጋ ስለሚያውቅ በየጊዜው በርካታ መሰናክሎችን እና ፕሮፖጋንዳዎችን በመርጨት ላይ ይገኛል።
የአሸባሪው ርዝራዦችና የእሱን የጥፋት መስመር የሚከተሉ የውጭ ሀገር ሎቢስቶችና ሚዲያዎች ኢትዮጵያን ለማመስ ቆርጠው የተነሱበት ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን። በማያባራ ሐሰተኛ መረጃና ውንጀላ ኢትዮጵያ ከተያያዘችው የለውጥ መንገድ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሠሩ ይገኛሉ። ይህን ያህል ሰው ተገደለ፤ ይሄን ያህል ሰው ተደፈረ፤ ይሄን ያህል ሰው በሞት አፋፍ ላይ ይገኛል የሚሉ ሐሰተኛ መርዶ ዜናዎችን በማሰራጨት የከሰረ ፖለቲካቸውን እየነዙ ይገኛሉ። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች አሜሪካና አወሮፓ ተቀምጠው ሐሰተኛ ወሬዎችን ከመፍብረክ ባለፈ ለትግራይ ህዝብ ጠብ ያለ ነገር ሲሠሩ አልታዩም።
ለህዝብ ሊሰሩ ይቅርና አሸባሪው ቡድን በፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋምና ጊዜያዊ መጠለያ እንዲያገኙ የሚደረገውን ጥረት ከማገዝ ይልቅ ለማደናቀፍ ሲጥሩም ነው የሚስተዋሉት።
በአጠቃላይም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት በህወሓት አሸባሪ ቡድን ጠብ አጫሪነት የወደመውን የትግራይ አካባቢ መልሶ ለማቋቋም ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ። በተለይም ላለፉት ስምንት ወራት በዕርዳታ ላይ ጥገኛ ሆኖ የቆየውን የክልሉን ህዝብ እራሱ አምርቶ እራሱን እንዲያስተዳድር ለማድረግ እየተደረገ ያለው ጥረት ሁለት ውጤቶችን ይዞ የሚመጣ ነው። አንድም የትግራይን ህዝብ ከተረጂነት አላቆ ለሀገሩ ዕድገት የየበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያደርገው ሲሆን፤ በሁለተኝነት ደግሞ የአሸባሪውን የህውሓት ቡድን ርዝራዦች የመጨረሻ እስትንፋስ ለመቋጨት የሚረዳ ይሆናል።
በአጠቃላይ ታታሪ የሆነው የትግራይ ህዝብ ሰላሙን የሚያውኩት እኩይ ቡድኖች ከተወገዱለት ከራሱ አልፎ ለኢትዮጵያ አጠቃላይ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚችል ህዝብ ስለሆነ በክልሉ የተጀመረው የሰላምና የልማት አቅጣጫ እንዲሳካ ሁሉም የክልሉ ነዋሪና ኢትዮጵያውያን በሙሉ የበኩላቸውን እገዛ ሊያደርጉ ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2013