የዛሬ አምስት ወር ገደማ ወደ ስራ የገባውን የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት ፈርመው ተቀብለውታል። ስምምነቱን በርካታ ሀገራት ፈርመው የተቀበሉት ቢሆንም አሁንም የስምምነቱ ፋይዳዎችና ፈተናዎች እንዲሁም የፈተናዎቹ መሻገሪያ ዘዴዎች ዙሪያ የተለያዩ አካላት ሃሳባቸውን በመሰንዘር ላይ ናቸው።
ስለ ፋይዳው የሚናገሩ አካላት ስምምነቱን ለሚደግፉ የተለያዩ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ይናገራሉ። የንግድ ቀጠና ስምምነቱ 90 በመቶውን ታሪፎች በማስቀረት የአፍሪካውያንን የእርስ በርስ ንግድ እስከ ጎርጎሮሳዊው 2034 ድረስ 60 በመቶ በማሳደግ የ3 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር ገበያ መፍጠር ያስችላል ይላሉ። ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ገቢራዊ ሲሆን 30 ሚሊዮን አፍሪካውያንን ከከፋ ድህነት፤ 70 ሚሊዮን የአህጉሪቱን ህዝቦች ደግሞ ከመካከለኛ ድህነት ያወጣል የሚል መከራከሪያዎችን ያቀርባሉ።
ነፃ የንግድ ቀጣናውን የሚተቹ አካላት ደግሞ የተለያዩ መከራከሪዎችን ያነሳሉ። ከሚያነሱት መከራከሪዎች መካከል ጠንካራ አምራቾች የአህጉሪቱን ገበያዎች እንዲቆጣጠሩ እድል የሚፈጥር በመሆኑ የሀገር ውስጥ አምራቾችን ከንግድ ውጪ ያደርጋል፣ የአፍሪካ ሀገራት ተመሳሳይ ምርቶችን የሚያመርቱ በመሆናቸው አቅርቦት እና ፍላጎት መካከል አለመጣጣም እንዲፈጠር ምክንያት ይሆናል። እንዲሁም አህጉሪቱ ምቹ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ሥርዓት ያልተዘረጋበት መሆኑ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች ነው የሚል መከራከሪያዎችን ያቀርባሉ። ይህ ክርክር በቴክኒክ ደረጃ ስህተት ባይሆንም አጭር እይታ ያለው ነው በሚል ይተቻል።
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትም የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ገበያ ዙሪያ ግንዛቤ ለማሳደግ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ውይይቶችን፣ ኮንፈረንሶችን፣ ፎረሞች ተዘጋጅተውም ግንዛቤ እንዲፈጠር ሲሰራ ቆይቷል። በቅርቡም በቀጣናዊ የንግድ ስምምነቱ ምንነት፣ ለኢትዮጵያ የግል ዘርፍ የሚኖረውን ፋይዳዎች እና ተግዳሮቶች እንዲሁም ተግዳሮቶቹ መፈታት ያለባቸው አቅጣጫዎች ተመላክተዋል። በመድረኩ ላይ አፍሴል ኮንሰልተንሲ የተሰኘ ድርጅት በንግድ ስምምነቱ ዙሪያ ያካሄደውን ጥናት አቅርቦ ውይይትም ተደርጎበታል።
የጥናቱ አቅራቢ አቶ ሙሴ ምንዳዬ የንግድ ስምምነቱን ፋይዳዎችና ተግዳሮቶች እንዲሁም የተግዳሮቶቹን መፍትሄዎች አመላክተዋል። ነጻ የንግድ ቀጠናው ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ አምራቾች ተገማችና ሰፊ የገበያ ዕድል እንዲያገኙ ያስችላል። ኢትዮጵያ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው ሌሎች ከታሪፍ ነጻ የንግድ ስምምነቶች አማራጮች ቢኖሩም ዘላቂ አለመሆናቸውን አንስተዋል። አዲሱ የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ግን ዘላቂና አስተማማኝ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ብዙ እንደምትጠቀም ያነሱት አቶ ሙሴ በአግባቡ ከተጠቀመችበት የግሉ ዘርፍ ውድድር ውስጥ እንዲገባ ስለሚያደርግ በገበያ ውስጥ ለመቆየት ጠንክረው እንዲሰሩ ጫና ይፈጥርባቸዋል። ጫና ውስጥ ስለሚገቡም ሀገሪቱ በአፍሪካ ብሎም በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንድትሆን እንደሚያስችላት አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የግል ዘርፍ በነጻ ቀጣና ስምምነት ውስጥ ገብተው ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግዳሮቶችንም አንስተዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የመንግስት ተቋማት የግሉ ኢንዱስትሪዎች የሚፈልጉትን ያህል ድጋፍ ማድረግ አለመቻላቸው፣ ኢንዱትሪዎች እያጋጠማቸው ያለው የሰው ሃይል ፍልሰት፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ፣ የሎጂስቲክስ ችግሮች፣ የተንዛዛ ቢሮክራሲ እና በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸው ምርቶች ከአካባቢው ኢኮኖሚ ጋር ብዙም ቁርኝት የሌላቸው መሆኑ ለዘርፉ ተግዳሮቶች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ሃሳብ አላቸው።
ተግዳሮቶቹን ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል የሚሉት አቶ ሙሴ፤ የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ንዑስ ዘርፍ ፈቃድ ከሚሰጡት ጀምሮ የሎጂስቲክስ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ዓለም አቀፍ ደረጃ የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል፣ በግሉ ዘርፍ መካከል ውድድር እንዲኖር ማድረግ ፣ ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን መሳብ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን አይነት ማብዛት፣ ጥሬ እቃ ወደ ውጭ ከሚላክ ይልቅ እሴት ተጨምሮበት እንዲላክ ማድረግ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና ኢንዱስትሪዎች ትስስርን የማጠናከር ስራ ልዩ ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል።
እንደ አቶ ሙሴ ማብራሪያ፤ የግሉ ዘርፍ ስለ አፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ያለው ግንዛቤ እንዲያድግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት፣ የኢትዮጵያ ምርቱን በአፍሪካ ገበያ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ፎረሞችን ማዘጋጀት፣ ለግሉ ዘርፍ ምቹ ከባቢን መፍጠር፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ በኢንዱስትሪ እና በአርሶ አደር መካከል ቁርኝት እንዲፈጠር ማድረግ፣ ኢንዱስትሪ ሰራተኞች የሚያነሷቸውን የክፍያ ጥያቄዎችን መመለስ እንዲችል ህጉን ማሻሻል ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013