ሎጅስቲክስ ለአንድ ሃገር እድገት እና ቀጣይ ልማት ቁልፍ ሚና አለው። በተለይ የውጭ ንግድ ለመደገፍ መከናወን ካለባቸው ወሳኝ ተግባራት ውስጥ ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጅስቲክስ ስርዓት መዘርጋት በቀዳሚነት ይጠቀሳል። ዘርፉም የንግድ እንቅስቃሴውን ከማነቃቃት ባለፈ አስመጪና ላኪዎች በአለም ገበያ ያላቸውን ተወዳዳሪነት ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ ያሳድራል።
የሎጅስቲክስ ሥርዓት ከመነሻ እስከ መድረሻ ባለው ሂደት የዕቃ፣ የፋይናንስና የመረጃ ፍሰትን አቀናጅቶ፣ አስተሳስሮ የማቀድ፣ የመምራትና የመቆጣጠር አሠራርን የግድ ይላል። በባህሪው የተወሳሰበና ብዙ አካላቶች በአንድነት ተጣምረው የሚሰሩበት ዘርፍ ነው። ጭነቶችን፣ መሠረተ-ልማቶችን፣ በዘርፉ ያለው አሠራርና የሰው ኃይልን አስተሳስሮና ውጤታማ በሆነ መልኩ በማቀናጀት የመምራት ተግባር ብሎም ስልትን ይሻል። ጠንካራ የመረጃና የክትትል አሠራርም ይፈልጋል።
በ2010 ነሃሴ ወር ላይ ይፋ በሆነው የብሄራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ እንደተመላከተውም፣ የሎጅስቲክስ ስርዓት ውጤታማነት መለኪያ በሆኑት ከጊዜና ወጪ አንጻር ሲመዘን የኢትዮጵያ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በትራንዚት ጊዜ፣ በዕቃዎች እና በመርከቦች የወደብ ላይ ቆይታ፣ ጭነት ከወደብ በማንሳት አቅምና በመሰል የሎጅስቲክስ የአፈጻጸም መለኪያዎች በዝቅተኛ ደረጃ ተቀምጣ ረጅም አመታትን አሳልፋለች።
የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ የችግር መገለጫዎች ከሆኑት መካከል የዕቃዎች የወደብ ላይ ቆይታ ከፍተኛነት ወደር የለሽ ነው። ውጪ ንግዱን የሚያጓጉዙ መርከቦች ሳያራግፉ በባህር ላይ ቆመው የሚያሳልፉት ጊዜ ማራገፍ ከሚወስድባቸው ጊዜ ጋር ተዳምሮ 2 እስከ 3 ወራት ይዘልቃል። ይሕም የአገሪቱን የሎጅስቲክስ ጊዜና ወጪ የናረ እንዲሆን አድርጎታል። ተወዳዳሪ አይደለም ከሚል አልፎ ጉዳቱ ከንግድ አጋሮቻችን (ከአቅራቢዎችና፣ የመርከብ፣ ባለቤቶች) ጋር የሚኖር የንግድ ግንኙነት ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ ሲያሳድር ቆይታል።
የተለያዩ ጥናቶችም የሎጅስቲክስ ስርዓት ውጤታማነት መለኪያ በሆኑት ከጊዜና ወጪ አንጻር ሲመዘን የኢትዮጵያ ደረጃ በዝቅተኛ ላይ እንደሚገኝ ይመሰክራሉ። እ.ኤ.አ 2ዐ16 ይፋ የሆነው የዓለም ባንክ የሎጅስቲክስ አፈጻጸም ሪፖርትም ‹‹የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ አፈጻጸም ደረጃ በጣም ዝቅተኛ ነው›› ሲል ይፋ አድርጋል። የወቅቱ የአገሪቱ ደረጃም ከ160 አገራት 126ተኛ ላይ የተቀመጠ ነበር።
ኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ አፈጻጸም ደረጃ በቀላል ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተወዳዳሪ ከሆኑት ሀገሮች ጋር ሲነጻጸርም የመጨረሻ መሆን ብቻ ሳይሆን በብዙ ርቀት ወደ ኋላ የቀረ ነው። አብዛኞቹ ሀገሮች ደረጃቸውን ሲሻሻል ኢትዮጵያ ግን በተቃራኒ እያሽቆለቆለ የሚሄድ ነው።
የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ ጊዜና ወጪ ከዓለምአቀፍ ስታንዳርድ ጋር ሲነጻጸር በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው የተገኘው። በምስራቅ አፍሪካ ከሚገኙ ሀገሮች የሎጅስቲክስ የአፈጻጸም አማካይ ውጤት ጋር ሲነጻጸርም የኢትዮጵያ በአብዛኛዎቹ መለኪያዎች ከእጥፍ በላይ ይበልጣል።
ለዚህ ዝቅተኛ የሎጅስቲክስ አፈጻጸም በምክንያትነት የሚጠቀሱ በርካታ ችግሮች አሉ። ከእነዚህ ችግሮች ትንታኔ በመነሳት የዘርፉን ራዕይና ዓላማ ከማሳካት አንጻርና የሀገሪቱ የሎጅስቲክስ ስርዓት ተወዳዳሪነትን ከማሻሻል አኳያ መሠረታዊ የሆኑና ከፍተኛ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እና ልዩ ትኩረት የሚሹ ቁልፍ ችግሮች ተለይተዋል። ከችግሮቹም አንዱ የገቢ ዕቃዎች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ሂደት ከባንክ ፈቃድ ማግኘት ጀምሮ ዕቃው እስከ መረከብ ድረስ ከሚወስደው አጠቃላይ ጊዜና ወጪ ውስጥ የፋይናንስና የንግድ ሥርዓቱ ድርሻ 65 በመቶ ያህል መሆኑ ነው።
ከዕቃዎቹ የወደብ ላይ ቆይታ አንጻር ሲታይም ከዓለም አቀፍ ስታንደርድ ከ1ዐ እጥፍ በላይ ነው። ለዕቃዎች የወደብ ላይ ቆይታ መራዘም በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋናውን ቁልፉ ችግር ግን የንግድና የፋይናንስ ሥርዓቱ ነው።
የገቢና የወጪ ዕቃዎች ከመነሻ ጀምሮ እስከ መድረሻ ባለው ሂደት ውስጥ በርካታ ተቆጣጣሪና አገልግሎት ሰጪ አካላት አሉ። በእነዚህ ተቋማት የሚጠየቁ በርካታ የሰነዶች፣ የመረጃና የክፍያ ብዛት፣ የሥራ ሂደቱ የሚወስደው ጊዜ የተንዛዛ መሆን፣ ሥራው በሚጠይቀው ልክ በፋሲሊቲ፣ በመሣሪያና በሰው ኃይል የተሟላ ሆኖ አለመገኘት፣ በዋናነት ደግሞ በእነዚህ የሎጅስቲክስ ዘርፍ ተዋናዮች መካከል የተቀናጀ አሠራር አለመኖር ከከፍተኛ ማነቆዎች ተርታ ይጠቀሳሉ።
እቃውን ከባህር ወደብ ለማውጣት የሚፈጸሙ ስነስርዓቶች፤ በመንገድ ለማጓጓዝና በሀገር ውስጥ የጉምሩክ ስነስርዓት ፈጽሞ እቃውን ለማውጣት የሚወስደው ጊዜ በወረቀት ሲታይ እጅግ አነስተኛ ቢመስልም በተግባር ግን ውስብስብ የሆኑ ሂደቶችን የሚያልፍ ነው።
የጉምሩክ አሰራር ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ የሲስተም እና ሌሎች ጉዳዮች የተነሳ የእቃዎች የትራንዚት ሂደት ረጅም ሆኖ ይስተዋላል። ሎጅስቲክስ ዘርፉን የሚመሩና የሚቆጣጠሩ የመንግስት ልዩ ልዩ ተቋማት በዕውቀትና በብቃት ከመምራት አኳያ የተቋማት የማስፈጸም አቅም ማነስ በተጨማሪ ማነቆነት ይጠቀሳሉ።
ውጤታማ እና የተቀላጠፈ የሎጅስቲክስ ስርዓት ከሚፈለገው ግብዓት አንዱ መሰረት ልማት ነው። ይሑንና በዚህ ረገድ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ። የትራንስፖርት አቅርቦትና የትራንስፖርት ማኔጅመንት ችግር፤ የመንገድ ሁኔታ፤ የጭነት ማዕከላት ሁኔታ፣ የወደብ ፋሲሊቲ፣ የመርከብ ማሸጊያዎች፣ የወደብ ዕቃ መገልገያ መሣሪያዎች፣ የዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በመሰል የሎጅስቲክስ የመሰረተ-ልማት ግንባታ ክፍተት ጎልተው ሲጠቀሱ የነበሩ ችግሮች ናቸው።
ታዲያ እነዚህን የዘርፉ ችግርች በማስወገድ በተለይም የአገሪቱን የውጭ ንግድ ልማት ለመደገፍ ቀልጣፋና ውጤታማ የሎጅስቲክስ ሥርዓት መዘርጋት፣ ዝቀተኛ የአፈጻጸም ደረጃዎች መለወጥ እና ከልማት ማነቆነት ማላቀቅ የግድ ይላል።
በዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ወደ ስልጣን ሲመጣ ቅድሚያ ከሰጣቸው የኢኮኖሚ አጀንዳዎች አንዱም የሎጀስቲክስ ዘርፉን ችግሮች በማስወገድ ውጤታማነቱን ማጎልበት ነበር። በዚህም ዘርፉ የሚመራበት ፖሊሲ የጠራ ራዕይና ስትራተጂ ነድፎ በመንቀሳቀስ በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማስወገድ የሚያስችል ስትራተጂ ተነድፏል።
በስትራቴጂውም የሎጅስቲክስ ሥርዓቱን በቀጣይ አሥር ዓመታት ውስጥ ትራንስፎርም ማድረግ ታሳቢ ተደርጓል። በአጠቃላይ ስትራቴጂው የትግበራ አፈፃፀም ሀገራዊ ወጪን ለመቆጣጠርና ብክነትን ለማስቀረት፣ የሎጅስቲክስ ችግር አፈታት ሥርዓት ተኮር እንዲሆን ለማድረግ እንዲሁም ዘርፉን በጠራ ራዕይና አቅጣጫ ለመምራት ያለመ ነው።
በስትራቴጂውም በዓለም አቀፍ የሎጅስቲክስ አፈፃፀም መለኪያ ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ደረጃ ከ 126ኛ ወደ 50ኛ ደረጃ ከፍ ማድረግ፣ ጭነትን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የባንክ ፈቃድ ከመጠየቅ ጀምሮ ዕቃው በአገር ውስጥ እስከ መረከብ የሚወስደውን ጊዜ ከ128 ቀናት ወደ 40 ቀናት መቀነስ፣ ገቢ ዕቃዎች ከመርከብ ከተራገፈበት ቀን ጀምሮ በአገር ውስጥ መረከብ የሚወስደውን ጊዜ ከ46 ቀናት ወደ 7 ቀናት መቀነስ፣ ወጪ ዕቃዎች ከአገር ውስጥ ከባንክ ፈቃድ ጀምሮ ጭነቱ መርከብ ላይ እስኪጫን የሚወስደውን ጊዜ ከ42 ቀናት ወደ 7 ቀናት መቀነስ፣ ግብ ተቀምጣል።
ከዚህ ባሻገር ወደ አገር ውስጥ የሚጓጓዘውን የብትን ጭነት ያለምንም የመርከብ ዲመሬጅ ክፍያ ወደ አገር ውስጥ ማጓጓዝ፣ የገቢ ዕቃዎችን የወደብ ላይ ቆይታ ከ40 ወደ 3 ቀናት መቀነስ፣ ወጪ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጐ የመላክ አፈፃፀምን ከደረሠበት 11 በመቶ ወደ 100በ መቶ ማሳደግ፣ የብትን ጭነት አጓጓዥ መርከቦች በወደብ የባህር ላይ ቆይታን ከ40 ወደ 3 ቀናት መቀነስ፣ እንዲሁም የብሬክ በልክ አጓጓዥ መርከቦች በወደብ የባህር ላይ ቆይታን ከ15 ወደ 3 ቀናት የመቀነስ ግብ ተይዟል።
በዚህ ውጥን ትግበራ በትራንስፖርት ዘርፉ የ2012 ዓ.ም አፈፃፀም ለአብነት ስንመለከትም፣ ወጪ ዕቃዎችን በአገር ውስጥ በኮንቴነር አሽጐ የመላክ አፈፃፀም 52 በመቶ ማድረስ ችሏል። በወደብ የባህር ላይ ቆይታ ከ 40 ወደ 32 ቀናት መቀነስ ተችላል። የገቢ እና ወጪ ሎጅስቲክስ የተሳለጠ ለማድረግ ዲመሬጅ ህግ የጊዜ ስታንዳርዶች (በሚዛን ጣቢያ፣ በጉምሩክ የፍተሻ እና የቁጥጥር ጣቢያ፣ መጫኛ እና ማራገፊያ ቦታዎች አፈፃፀም 100 በመቶ ለማድረስ ታቅዶ 92 ነጥብ 75 በመቶ መድረስ ችሏል። የገቢና ወጪ ጭነትም 19 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ቶን ለማጓጓዝ ታቅዶ 82 ነጥብ 6 በመቶ ማሳካት ተቸሏል።
ባሳለፍነው አመትም የዘርፉ አፈፃፀም የተመዘገቡ ውጤቶች የመኖራቸውን ያሕል ድክመቶችም ተስተውለዋል። የትራንስፖርት አቅርቦትና ማኔጅመንት ችግር፣ ምቹ የሆነ የመሰረተ ልማት አለመኖር፣ የተደራሽነት ችግር፣ የጭነት ማእከላት እጥረት፣ ደረጃውን የጠበቀ የወደብ ፋሲሊቲ አለመሟላት፣ በመንግስትም ሆነ በግሉ ዘርፍ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በባህር ወደቦች የሎጅስቲክ አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎች ዘርፉ እውቀት እና ክህሎት ክፍተቶች ፣ ዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እጥረት፣ የግልፅነት እና ተጠያቂነት አሰራርን ዘርግቶ በችግሩ ስፋት ልክ የማስተካከያ እርምጃ አለመውሰድ፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ ብልሹ አሰራር በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዳይመጣ የተስተዋሉ ሁነኛ ማነቆ ሆነው ተለይተዋል።
በወርሃ መጋቢት የትራንስፖርት ሚኒስቴር ዘርፍ በሚቀጥሉት አስር አመታት የሚመራበትን የአስር አመት መሪ እቅድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የልማት አጋሮችና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች በሸራተን ሆቴል አስተዋውቆ ነበር።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በዚሁ መድረክ ላይ እንደተናገሩት፣ ትራንስፖርት ለአገሪቱ እድገትና ብልፅግና የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ የትኛውም የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፍ የወደፊት እርምጃ ያለ ትራንስፖርት አገልግሎት ሊታሰብ አይችልም። የመንገድ፣ የባቡር፣ የአየርና ሌሎችም የትራንስፖርት ልማቶችን ማጠናከር ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ አዳዲስ የገበያ እድሎችን ለመፍጠር፣ የዋጋ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥና ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለማሳደግ ወሳኝ ነው።
መሪ እቅዱ ዘርፉ የተቀናጀ፣ በተደራሽነት ረገድም ፍትሃዊና ሁሉን አካታች መደረጉ ፈጣንና የተሟላ ምላሽ ይሠጣሉ የተባሉትን ጉዳዮች በሰፊው ያካተተ እና የወደፊት እይታ ያለው መሆኑን አስገንዝብዋል።
ሌላኛው የመድረኩ ተሳታፊ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፣ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በተለይ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው አረጋግጠዋል።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፍን ማቀላጠፍ ለብሔራዊ ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስፈላጊ ስለመሆኑን አፅእኖት ሰጥተው ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ‹‹የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፉን ማቀላጠፍ ለብሔራዊ ልማትና ኢኮኖሚያዊ እድገት አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን። ለዚህም ነው በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዘርፍን የኢትዮጵያ ብልጽግና ራዕይ ትኩረት እያደረግን ያለነውም››ብለዋል::
የኢትዮጵያ ብልጽግና ራዕይን ትኩረት በማድረግ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የባለፉት ሶስት ዓመታት አበይት ክንውኖችን ገልጸዋል። አገር አቀፍ የትራንስፖርት እና አገር አቀፍ ሎጂስቲክስ ፖሊሲዎች፤ ብሄራዊ ሎጂስቲክስ ስትራቴጂ እና ሞተር-አልባ የትራንስፖርት ስትራቴጂዎች መነደፋቸውን ገልጸዋል።
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃም ፣ በአጠቃላይ ሁለት ሺህ 721 ኪሜ የአስፋልት መንገድ ተገንብቷል። ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባትና ወደ ውጭ የመላክ ሎጂስቲክስ ሂደት በ17 ሚሊዮን ቶን በላይ ደርሷል። ይህም በኢትዮጵያ የንግድ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።
የመርከብ የወደብ ቆይታ ጊዜ ከ40 ወደ 12 ነጥብ 75 ቀናት ቀንሷል። ለንግድና ሎጀስቲክስ ፍሰት መሻሻል የኢትዮ-ኬንያ አንድ ማቆሚያ ድንበር መተላለፊ ተከፍቷል። ከ26 በላይ የኢንተርኔት አገልግሎቶች ለህዝብ ተዋውቀዋል። በቴክኖሎጂ የታገዘ የሀገር አቋራጭ የህዝብ ማመላለሻ ትኬት ስርዓት ተጀምሯል።
በአስር አመቱ የትራንስፖርት መሪ እቅድ የአገሪቱ አጠቃላይ የመንገድ ሽፋን አሁን ካለበት ከ144 ነጥብ 027 ኪሎ ሜትር ወደ 245 ነጥብ 942 ለማሳደግ፣ የአገሪቱን የገቢና ወጪ ጭነት አሁን ካለበት 17 ነጥብ 732 ሚሊየን ቶን ወደ 30 ነጥብ 41 ሚሊየን ቶን፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የኤርፖርቶችን ብዛትም አሁን ካለበት 22 ወደ 28 ለማሳደግ ታቅዷል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013