(ክፍል ሁለት)
በክፍል አንድ መጣጥፍ በጠቀስሁት
“ WELCOME Back To Kissenger’s World” በሚል ርዕስ በፎሪን ፓሊሲ መጽሔት ባስነበበን ማለፊያ መጣጥፍ ፤ ደግነቱ ይላል ማይክል ሒሽ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ማግስት የተመሠረተው ነጻው ዓለምአቀፍ ሥርዓትና የትበብር መንፈስ እየተፍገመገመም ዛሬ ላይ ደርሷል። ወደፊትም ይቀጥላል። የመንግስታቱ ድርጅት ፣ ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም ፣ የዓለም ባንክ ፣ የዓለም ንግድ ድርጅትና ሌሎች ተቋማት ለዓለምአቀፍ ትብብርና ሰላም የዋሉትን ውለታ ያነሳሳል።
ሆኖም ዋሽንግተን ፣ ቻይናና ራሽያ የየራሳቸውን አመለካከትና ስውር አጀንዳ አስርገው ለማስገባት የሚያደርጉት ትንቅንቅ እነዚህን ተቋማት ሽባ እያደረጓቸው ነው። በጸጥታው ምክር ቤት እስራኤልን በተመለከቱ በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ የወሳኔ ሃሳቦች በአሜሪካ ወይም በአጋሮቿ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ውድቅ ይሆናሉ። እንዲሁም ቻይናና ራሽያ የሚያቀርቧቸውን የውሳኔ ሃሳቦች አሜሪካና አጋሮቿ እግር በግር እየተከታተሉ ውድቅ ያደርጉታል።
እነ ቻይናም እንደዚሁ እያደረጉ የጸጥታው ምክር ቤት የመቧቀሻ መድረክ በማድረግ ሽባ እያደረጉት ነው። መተማመን ቀርቷል። መጠራጠር ነግሷል። በእነዚህ ኃይሎች መካከል እየተፈጠረ ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቶ የቀዝቃዛውን ጦርነት ሀንጎበር ራስ ምታት እየቀሰቀሰ ነው። አሜሪካና ምዕራባውያን በአንድ ወገን ቻይናና ራሽያ በሌላ ወገን ሆነው አፍሪካን ፣ እስያንና ላቲን አሜሪካን ግዳይ የመጣያ መስክ እያደረጓቸው ነው። አሜሪካና ጭፍራዎቿ በሀገራችን ላይ እየተከተሉት ያለው ፍርደ ገምድልነትና ጫና የዚህ ቅጥያ ነው ።
ደግነቱ ይላል ሒሽ ወደ ተነሳበት ነጥብ ሲመለስ ፤ በርዕዮት ዓለም ተከፋፍሎ መቧቀሱ ከቀዝቃዛው ጦርነት ጋር ላይመለስ ተሸኝቷል። ዛሬ ኮምንዝም አልያም ካፒታሊዝም በሚል ጎራ ለይቶ መጠዛጠዝ የለም። ባለፈው ክፍለ ዘመን ንጉሳዊ ፣ አምባገነናዊ ፣ ፋሽስታዊና ኮምኒስታዊ አገዛዞች በዓለም ላይ ያስከትሉትን ጥፋትና ምስቅልቅል ተመልክተናልና። ዛሬም ይላል ማይክል ሒሽ ዴሞክራሲ በጽንፈኝነት ፣ በተጠመዘዘ መረጃና እንደ ራሽያ ባሉ ሀገራት ደባ እየተፈተነ ከፍ ሲልም አይሰራም እየተባለ እየተብጠለጠለ ነው ። ካፒታሊዝም ራሱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ስለአልቻለ የሰው ልጅ ጥያቄ እያነሳበት ነው። ይህ የተወዛገበ የሀገር ቤት ፖለቲካ ነው እንግዲህ አወዛጋቢ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይዞ ብቅ ያለው።
አንድ ጊዜ “አሜሪካ ትቅደም !”ሌላ ጊዜ “አሜሪካ ተመልሳለች!”እያለ የሚወራከበው። ከእኔ ጋር ካልሆናችሁ ከጠላቶቼ ጋር ናችሁ እያለ ጥርስ የሚያፋጨው። ለዚህ ነው የአፍሪካም ሆነ የኢትዮጵያ ጥፋት ከቻይና ጋር መተባበራቸው ሆኖ የተገኘው። ብዙዎቹ ፈቅደውና መርጠው እየተከተሉት ያለው ዓለምአቀፍ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ በውድቀት ቁልቁለት ላይ ነው ከሚል መደምደሚያ ላይ የተደረሰው በዚህ ነው ይላል ማይክል ሒሽ።
የአሜሪካ ክብርና ኃይል እንዲህ እንደዛሬው ተዳክሞ አያውቅም ይላል ሒሽ ፤ በተለይ የአንድ ዙር ፕሬዝዳንት ሆኖ የቀረው የትራምፕ አሜሪካ “እሴቶቼ” የምትላቸውን ዴሞክራሲ ፣ ሰብዓዊ መብትና ነጻነት ችላ ብሎ ከአምባገነኖች ጎን መቆሙ ሳያንስ አድናቂያቸው መሆኑ ፤ እንደ መንግስታቱ ድርጅትና ኔቶ ያሉ ዓለምአቀፍ ድርጅቶችን ማጣጣሉ እና ዛሬ ድረስ ለማመን በሚቸግር ሁኔታ አሜሪካ ኮቪድ 19ኝን መከላከልና መቆጣጠር ተስኗት በወረርሽኙ ሕንድንና ብራዚልን አስከትላ በመያዝና በመሞት 1ኛ መሆኗ ዓለም ስለ አሜሪካ የነበረው አመለካከት እንደገና እንዲያጤን አስገድዷል።
“የጥቁር ህይወት ይገደናል!” የሚለውን ተቃውሞና የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ አስመልክቶ ትራምፕ ያራምደው የነበረ የተለሳለሰና እርስ በርስ የሚጣረስ አቋም በአሜሪካውያን ዘንድ በተለይ በጥቁሮችና በሌሎች ህዳጣን ጥርስ እንዲነከስበትና እንዲናቅ አድርጎታል። ቻይናም የጆርጅ ፍሎይደን ነገር እየጠቀሰች ስለሰብዓዊ መብት የዓለማችን ቃፊር የመሆን የቅስም ልዕለና የለሽም አረፈሽ ተቀመጭ እያለቻት ነው። ከሁሉም በላይ እኤአ የ2020 ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ውጤትን ትራምፕ አልቀበልም ማለቱና ባይደንን እንኳን ደስ አለህ አለማለቱ ይባስ ብሎ ደጋፊዎቹ ካፒቶል ሒለን ወረው ተነጠቀ ያለውን ድምጻቸውን እንዲያስመልሱ በተደጋጋሚ ወትውቶ የተፈጠረው ሁከት የዓለምን ሕዝብ ያስደነገጠ ነበር።
የሰው ዘር በሙሉ ስለአሜሪካ የነበረውን በጎ ገጽታ እንደገና እንዲመረምር መንስኤ ሆኗል። ይህ የአሜሪካ የቁልቁለት መንገድ በጆርጅ ደብሊው ቡሽ ነው የተጀመረው። ካለፉት 20 ዓመታት ወዲህ ልዕለ ኃያልነቷ ጉልበትም ሞገስም እየራቀው ይገኛል። ከጥንታዊው የሮማ አገዛዝ በላይ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ የበላይነት የነበረው የድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት የአሜሪካ ተጽዕኖ እየሟሸሸ መሆኑን የታዋቂው የየል ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪ ፓል ኬኔዲ ይስማማል።
ኬኔዲ አያይዞ አሜሪካ ዓለምአቀፍ የጸረ ሽብር ዘመቻውን የመራችበት አግባብና ሳትቋጭ እንደ ብላቴና ስፌት በውጥን ያስቀረችበትን ማመንታት ሌላው የድክመቷ መባቻ አድርጎ ያሳያል። የከሸፈው የጸረ ሽብር ዓለምአቀፍ ዘመቻ ገጽታዋን ከማጠልሸቱ ባሻገር ኢኮኖሚዋን ክፉኛ ጎድቶታል። የኒውዮርክ የሽርክና ገበያ እንዲወድቅ ፤ ኢኮኖሚው እንዲንኮታኮት አድርጓል። ቻይና አጋጣሚውን ተጠቅማ እድገቷን ለማፋጠን ተጠቅማበታለች። ይህ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲ የቁልቁለት ጉዞ የሐንስ ሞርጌንታው ደቀ መዝሙር የሔነሪ ኪሲንጀርን በነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ዲፕሎማሲን ዳግም እንድናነብር ያስታውሳል ይላል ሒሽ ።
የዓለማችንን ጅኦፖለቲካ ወቅታዊ ሁኔታ ከግንዛቤ ያስገባ ዲፕሎማሲ። የሐንስ ንድፈ ሀሳብ የኪሲንጀር የዲፕሎማሲ ዋልታና ማገር የሆነውን በነባራዊ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ። የቻይናን ተጽዕኖና ቀጣይ እጣ ፈንታ ከግምት ያስገባ ዲፕሎማሲ። ቤሪ ጌዌኒ “The Inevitability of Tragedy” በተሰኘውና የሔኔሪ ኪሲንጀርን ህይወትና የዲፕሎማሲ ፍልስፍና በገመገመበት መጽሐፍ ቻይናን የዘነጋ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በሳሎን ውስጥ ያለን ዳይናሰር አላየሁም እንደማለት ነው ይላል።
ቤሪ ጌዌን ከፍ ሲል በተጠቀሰው መጽሐፍ በዓለም ላይ ሰላምና መረጋጋት እውን እንዲሆን የተበላሸውን የቻይናንና የአሜሪካን ግንኙነት ማስተካከል ያሻል ቢልም መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከዚህ ጋር የሚቃረን ነው። ትራምፕ በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቻይናን ከማጠልሸት አልፎ በቻይና ላይ ተደራራቢ ቀረጥ በመጣል የዓለም የንግድ ድርጅት መርሆዎችን ጥሷል። የኮሮና ቫይረስን የቻይና ቫይረስ እያለ በመጥራት ለሕዝበኝነት የፖለቲካ ፍጆታ አውሎታል። ዓለም ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ እንዲል ፤ ጆ ባይደን ቻይና ምሳችንን እየበላች ነው ሲል ይከሳል። ለአሜሪካ የሚገባውን ሲሳይ ቻይና በሕገ ወጥ መንገድ እየተጠቀመች ነው ለማለት።
የትራምፕም ሆነ የባይደን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መሬት ላይ ባለ እውነታ የማይመራ ለመሆኑ ጥሩ አብነት ነው። ለዚህ ነው ጌዌን አሜሪካ በ1970ዎቹ ማለትም በቬትናም ቀውስ ፣ በአሜሪካ የእርስ በርስ ሁከቱ ፣ ዋተርጌት ፣ የዋጋ ግሽበት ፣ የሸመታ መቀዛቀዝና የስራ አጦች ቁጥር መጨመር ፣ ወዘተረፈ. ቀውሶች በተከሰቱበት ጊዜ እንደ መውጫና የማርያም መንገድ ሆኖ ያገለገለው የሔነሪ ኪሲንጀር የውጭ ግንኙነት ፓሊሲ ነው መፍትሔው የሚለው። ዛሬም አሜሪካ ለምትገኝበት ቀውስ መዳኛው ወቅታዊውን ጅኦፖለቲክስ ፣ የኃይልና የስልጣኔ አሰላለፍን ታሳቢ ያደረገ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ነው። በዚህ ስብራት ነው እንግዲህ ሀገራችንን ጨምሮ አሜሪካ በዓለማችን ላይ እያራመደች ያለችውን ጠንካራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መገምገም፣ መተንተንና አበክሮ መዘጋጀት የሚገባው።
ከድህረ 2ኛው የዓለም ጦርነት አንስቶ በኋላም የቀዝቃዛውን ጦርነት በአሸናፊነት ለደመደመችው አሜሪካ ልዕለ ሃያልነቷን የሚገዳደር እንደ ቻይና ያለ ኃይል ሲመጣ መቀበል ይቸግራል። ይህን ዓለምአቀፍ ነባራዊ ሁኔታ አምና ለመቀበል ዝግጁና ፈቃደኛ አለመሆኗ ነው እንግዲህ አሁን ለምትገኝበት ቅርቃር የዳረጋት። ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፣ እንደ ሱዛን ራይስ ያሉ የባይደን አስተዳደር ሰዎች ተጽዕኖ ለጥቆ አሜሪካ በሀገራችን ላይ ጥርሷን እንድትነክስ ያደረገው ከቻይና ጋር የመሠረተችው ጥብቅ ወዳጅነት ነው። በመላው ዓለም ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ቦታዋን በቻይና መነጠቋ ፤ በአፍሪካ በቀይ ባህርና በአባይ ተፋሰስ ላይ የነበራት የበላይነት ቋፍ ላይ መሆኑ የቆሰለ አንበሳ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ሙሌት አጠናቀቀች ማለት የአጋሯ የግብጽ ጅኦ ፖለቲካዊ ስፍራ አደጋ ይደቀንባታል ብላ ስለምታምን ኢትዮጵያን ማዋከብ የዲፕሎማሲዋ አካል አድርጋዋለች። በተፋሰሱ የኢትዮጵያ የበላይ ሆኖ መውጣት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግብጽ ከአሜሪካና ከእስራኤል ተጽዕኖ ይልቅ በኢትዮጵያው ተጽዕኖ ስር ልትወድቅ ትችላለች ብላ ስለምትሰጋ ከግብጽ ጋር በመቆም የእስራኤል ጥቅም ማስቀጠል መርጣለች። ይሄን ስታደርግ ግን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የማልማትና የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት ጠፍቷት አይደለም። ሒሽ አሜሪካ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር ተናጥባለች የሚለው እኮ ይሄን ነው።
እንደ መውጫ
አሜሪካ ከዓለማችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በቅርቡና በቀላሉ ትታረቃለች ተብሎ አይጠበቅም። ከቻይና ጋር ያላት ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት ልዩነት ወደነጠላ አኅዝ ትሪሊዮን ዶላሮች ዝቅ እያለ መምጣቱን ፤ የቻይና ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ጥራትና ጥልቀት የአሜሪካንን ያህል ባይሆንም ከዓለማችን ሁለተኛው ግዙፍ ኢኮኖሚ መሆኑንና ዓለምአቀፍ ተጽዕኖውም እያደገ መምጣቱን መቀበል አትፈልግም። ምንም እንኳ አሜሪካ ይሄን ጥሬ ሀቅ አምኖ ለመቀበል ብትቸገርም ቻይና በተለይ በኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲና ግንኙነት መሪ ኃይል ሆና ወጣለች። ራሽያም ከድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት ወጥታ ከቻይና ቀጥላ ተጽዕኖ ፈጣሪ ከመሆኗ ባሻገር የአሜሪካን ዴሞክራሲ እስከመገዳደር መድረሷን ፤ በመካከለኛው ምስራቅና በላቲን አሜሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና ብቅ ማለቷን መቀበል ተስኗታል።
ይህ ከነባራዊ ሁኔታ ጋር መናጠብና መፋታት ነው እንግዲህ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እንድታራምድ ያደረጋት። ህወሓት በለኮሰው ጦርነት ጋይቶ አመድ መሆኑን ፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መገለጫና ምልዕክት መሆኑን አምና ለመቀበል የቸገራት። አሜሪካ በቀላሉ ወደ ቀልቧ ትመለሳለች ተብሎ ስለማይጠበቅ በሀገር ውስጥ አንድነታችንን ማጠናከር ፤ ዲፕሎማሲያችንን ማዘመንና ስትራቴጂካዊ እይታ እንዲኖረው ማድረግ ፤ በተናጠል የአሜሪካን ሕዝብ ኢላማ ያደረገ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ የተቀናጀ ጥረት ማድረግ ያሻል ። አሜሪካ ከቬትናም ፣ ከኢራቅና ከአፍጋኒስታን ጓዟን ቀርቅባ እንድትወጣ ያደረጋት የአሜሪካ ሕዝብ ግፊት ነውና ። በኢጋድም ሆነ በአፍሪካ ህብረት ያሉ እድሎችን አሟጦ መጠቀምና ከእነ ቻይናና ራሽያ ጋር ያለን ግንኙነት ማደስና ማጠናከር ያሻል። የኒውኪሊየር የጦር መሳሪያ ስለመታጠቅም አበክረን ልናስብ ይገባል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በሀቀኛና ጀግኖች ልጇቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013