በትግራይ ክልል በተደረገው የህግ የማስከበር ህልውናው ያከተመው አሸባሪው ህወሓት በርካታ ምስቅልቅሎች ፈጥሯል። በዚህም የተነሳ ከሰላም መደፍረስ ጋር ተያይዞ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ሰብአዊና ስነልቦናዊ ተጽዕኖው በነዋሪው ላይ አለመረጋጋትን ፈጥሯል። ይሁን እንጂ የፌደራል መንግስት በአጭር ጊዜያት የህግ ማስከበር ስራውን አጠናቅቆ ክልሉን ወደ ሰላምና መረጋጋት ለመመለስና መልሶ ለመገንባት የተለያዩ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ክልሉ ወደ ነበረበት ሰላምና ደህንነት እንዲመለስ ነዋሪውም በተረጋጋ መንፈስ መደበኛ ተግባሩን እንዲቀጥል የጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሟል። በየደረጃው የአስተዳደር መዋቅሮች በፍጥነት እንዲደራጁ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል። የክልሉን አጠቃላይ ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብቶ በመለየትና መፍትሄ በመስጠት ወደ ስራ ተገብቷል። ሰብአዊ እርዳታና ድጋፍም ተከፋፍሏል።
በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠርና ህዝቡም በተረጋጋ መንፈስ ኑሮውን መምራት እንዲችል የህግና የአስተዳደር አሰራሮች ላይ ማሻሻያ ተደርጓል። ላለፉት ስድስት ወራት ስራ ላይ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና ለሰአት እላፊ የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ለተጨማሪ ጊዜ እንዳይራዘም ተደርጓል።
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ዓላማ በትግራይ ህገ መንግስትና ሌሎች ህጎች ሳይሸራረፉ ለመተግበርና ግዴታውን ለመወጣት የሚችል ተቀባይነት ያለው ህጋዊ አስተዳደር በህጋዊ መንገድ እንዲመጣ ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ማረጋገጥ ነው። በመሆኑም የትግራይ ህዝብ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ክልሉን በዘላቂነት ለማረጋጋት ለሚደረገው ጥረት የድርሻውን መወጣት አለበት።
ክልሉና ህዝቡ ለዓመታት የሚሻገሩ ችግሮች እንዳይገጥሙትና ወደ ነበሩበት ሰላም እንዲመለስ ለማድረግ በሙያና ልምዳቸው ህዝባቸውን ለማገልገል ዝግጁ የሆኑና በህዝብ የተመረጡ የትግራይ ወጣቶች ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ድጋፍ በመስጠት እያገለገሉ ናቸው። ይሁን እንጂ በአሸባሪነት የተፈረጀው የህወሓት ርዝራዦች በክልሉ መረጋጋት እንዳይፈጠር እርሻ እንዳይታረስ፣ ህጻናትና አረጋውያን እንዲራቡ፣ በአጠቃላይ በክልሉ የተረጋጋ ሰላም፣ ልማትና ደህንነት እንዳይሰፍን በኢትዮጵያ ጠላቶች የገንዘብና የሞራል ድጋፍ እየሰሩ ይገኛሉ። ህዝቡ ይሄንን ሴራ ማወቅና መታገል አለበት።
በመላ ትግራይ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም የሰብአዊ ድጋፉና ህይወት የማዳንና የመልሶ ግንባታ ስራው የተሳካ እንዲሆን ህዝቡ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን ይጠበቅበታል። የአሸባሪው ህወሓት የሁል ጊዜ ምኞቱ በትግራይ ውስጥ አለመረጋጋት እንዲፈጠርና የሰብአዊ ድጋፎች በተገቢውና በሚፈለገው መንገድ እንዳይደርሱ እንቅፋት መፍጠር ነው። ይህ ደግሞ ከጥንት ተፈጥሮው የሚመነጭና በዜጎች ስቃይ የዘረፋ ህይወቱን ለማስቀጠል የሚሄድበት የተለመደ የክፋት መንገድ ነው።
ስለሆነም የህዝቡ አንድ ሆኖ መንቀሳቀስ ሰላምን ለማስፈንና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። የትግራይ ህዝብ ወደፊት ያለውን የብልጽግና ብርሀን አርቆ በመመልከት የጸረ ሰላም ኃይሎችን ሴራ ማክሸፍም ይጠበቅበታል። ህዝቡ አንድ ከሆነና ከጊዜያዊ አስተዳደሩና ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን ቆሞ መስራት ከቻለ ችግሩ በአጭር ጊዜያት ይቀጫል። ከዚህም በተጨማሪ ህዝቡ መጪውን የመኸር እርሻ ወቅት በሙሉ አቅም ሰርቶ ቀጣዩን ዓመት ከችግርና ረሀብ ለመውጣት ፊቱን ወደልማቱ አዙሮ ጠንክሮ መስራት ይጠበቅበታል።
ከውስጥም ከውጪም በየአቅጣጫው የሚሰማው የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ቀድሞም ሆነ አሁን ለትግራይ ህዝብ ተጨባጭ ለውጥ አላመጣም። የትግራይን እናቶች ከውሀ ፍለጋና ሸክምም አላላቀቀም፤ ከሴፍቲ ኔት ተረጂነት አላዳነም። አሁንም በሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ሳይደናገርና ሳይዘናጋ በአንድ ልብ ለሰላም፣ደህንነትና መልሶ ግንባታ መነሳት አለበት። ለትግራይ ህዝብ ሰላምና ልማት ከትግራይ ህዝብ በላይ የሚያስብ ማንም አይኖርም።
ዘላቂ ሰላምና ልማት ሊመጣ የሚችለውም በራሱ በህዝቡ ብቻ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለም። የትግራይ ህዝብ ይህን ተረድቶ ፊቱን ወደ ሰላምና ልማት ማዞር የክረምቱን ጊዜ በአልባሌ ሳይሆን በእርሻ ማሳለፍ፣ ለጸጥታና ደህነነት ቋሚ ዘብ መሆኑን በተግባር ማሳየት አለበት።
ከህዝብ የሚደበቅና ከህዝብ የሚያመልጥ ምንም ነገር የለምና በክልሉ ችግር ፈጣሪ የሆኑትን በማጋለጥና ባለመተባበር እንዲሁም በማውገዝና ለህግ በማቅረብ ጭምር የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለመመለስ መስራት ያስፈልጋል። ‹‹ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይመጣም›› እንደሚባለው ሁሉ ከማንም በላይ ለክልሉ ሰላምና ልማት የመጀመሪያው ዘብ ጠባቂ የክልሉ ህዝብ ራሱ ሊሆን ይገባል!
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013