መንግስት ሀገራዊው ለውጥ እውን በሆነበት ወቅት በገባው ቃል መሰረት በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት የሚያስችሉ ስራዎችን መስራቱን ቀጥሏል። ከዚህ በሁዋላ ስልጣን የሚያዘው በምርጫ ብቻ መሆኑን በተደጋጋሚ ከማረጋገጡም በላይ ለእዚህ እውን መሆን የሚያስችሉ መደላድሎችን ፈጥሯል።
ስድስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተከናወኑ ያሉት ተግባሮችም ይህንኑ ያመለክታሉ። ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም ለምርጫው ባስቀመጠው መርሀ ግብር መሰረት እየሰራ ሲሆን፣ ይህንንም እየገመገመና የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች በወቅቱ እያቀረበ ይገኛል። ለዚህም ምርጫውን ለማካሄድ ታስቦ ከነበረው ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም አሳማኝ በሆኑ ምክንያቶች ወደ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲራዘም አድርጓል። ቦርዱ ምርጫው የታለመለትን እንዲያሳካ መሰራቱን ቀጥሏል።
በተራዘመው የድምጽ መስጫ ቀን መሰረት ድምጽ የሚሰጥበት ቀን ከአንድ ወር ያነሰ ጊዜ ነው የሚቀረው። ቀሪው ጊዜ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳቸውን አጠናክረው የሚቀጥሉበት፣ መራጮችም ድምጽ የሚሰጡበትን ፓርቲ ለመለየት በትኩረት ሊሰሩበት የሚገባ አጭር ጊዜ ነው።
ይህን ሁኔታ በተለይ መራጮች በሚገባ ሊገነዘቡት ይገባል። የመራጮች መመዝገቢያ መርሀ ግብር ከመራዘሙ በፊት ለታየው የመራጮች መቀዛቀዝ የተለያዩ ምክንያቶች መጠቀሳቸው አይዘነጋም። መራጮችም በእዚህ በኩል ተጠያቂነት እንዳለባቸው መታወቅ አለበት። ይደርሳል በሚል ምክንያትም ይሁን በዳተኝነት ፈጥኖ አለመመዝገብ ታይቶባቸዋል። ያለፉት ዲሞክራሲያ ነኝ ለማለት የተደረጉ የማስመሰል ምርጫዎች ባሳደሩባቸው አሉታዊ ተጽእኖዎች ሳቢያ ምርጫን ዋና ጉዳይ አለማድረግም ታይቷል።
ይህ ሁኔታ ጨርሶ መለወጥ አለበት። መራጮች ሆይ፤ በምርጫው ድምጽ የምትሰጡት እናንተ እና እናንተ ብቻ ናችሁ። ይህን በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል። ድምጽ መስጠት ያለበት በበቂ እውቀት ላይ ተመስርቶ መሆን ይኖርበታል። በተለይ መራጩ የሚፈልገውና አገር ያሻግራል የሚለውን ፓርቲ ለይቶ ለመምረጥ የፓርቲዎችን ዝርዝር ፕሮግራም ማወቅ ይኖርባቸዋል። ከዚህ አኳያ መራጮች ስለምርጫው በቂ ግንዛቤ ይዛችሁ መምረጥ እንዳለባችሁ እውቁ።
አሁን ወቅቱ ፓርቲዎች ፕሮግራሞቻቸውን የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉበት ነው። መራጮች ከፓርቲዎቹ ቅስቀሳ በመነሳት የምትመርጡትን ፓርቲ ሀሳብ መገንዘብ ይጠበቅባችሁዋል። ግንዛቤ ማስጨበጥ የሚጠበቅባቸው አካላት በሚጠበቀው ልክ አጠገባችሁ ካልመጡ ደግሞ እናንተ በምትችሉት መንገድ ስለምትመርጡት ፓርቲ ወይም የግል ተወዳዳሪ መረጃ በመሰብሰብ ለማጣራት ሞክሩ። ምክንያቱም ለመጪው አምስት ዓመት የእናንተ ድምጽ የሚሆንላችሁ ይህ ግለሰብ ወይም ፓርቲ በመሆኑ ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀሳባቸው ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እያስጨበጡ ስለአለመሆኑ የሚያስገነዝቡ ሁኔታዎች ይታያሉ። ቅስቀሳቸው ሁሉ የሩጫና የይስሙላ ይመስላል። በክርክሩም ላይ ጠንካራ ሀሳብ ይዞ አለመቅረብ እንዲሁም ያቀረቡትንም ሀሳብ በዝርዝር ማስረዳት አለመቻል ይታይባቸዋል። የተሰጣቸውን ነፃ የአየር ሰአትና አምድም በሚገባ እየተጠቀሙበት ካለመሆኑም መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው።
ይህ ሁሉ መራጮች ብዙ ስራ እንዳለባችሁ ያስገነዝባል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚፈለገው ልክ ወደ እናንተ ካልመጡ እናንተም ወደ እነሱ መሄድ ይኖርባችሁዋል።
ልብ በሉ፤ ምርጫው በዋናነት የእናንተ ነው። ጊዜው እየሄደ ነው። ወቅቱ የምርጫና የምርጫ ብቻ ነው። የምርጫን ጉዳይ አጥብቃችሁ ያዙ። በእውቀት ላይ ተመስርታችሁ ለመምረጥ የፓርቲዎችን ሀሳብ ለመረዳት ጥረት አድርጉ።
ያልተማረ ካልሆነ በቀር ቁንስል እውቀት ይዞ በምርጫ ድምጽ መስጠት ውስጥ አይገባም። ለሚያውቅ ሰው በቂ ግንዛቤ መያዝ፣ ለምርጫ ጉዳይ በቂ ጊዜ መስጠትን ይጠይቃል። በቂ ግንዛቤ ይዞ ላልያዘው ማስገንዘብም ይገባል።
በተለይ ወጣቶች በዚህ ወሳኝ ወቅት ህይወታችሁን ብዙም በማይቀይረው የማህበራዊ ሚዲያ ውስጥ ተዘፍቃችሁ የምርጫውን ሂደት ከመከታተል መራቅ የለባችሁም። ሀገር ትልቅ አጀንዳ ይዛ እየሰራች ባለችበት በዚህ የምርጫ ወቅት በማህበራዊ ሚዲያው፣ በጌም እና በመሳሰሉት አልባሌ ጉዳዮች መጠመድ ሀገርን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለማሻገር አይረዳም። ቆም ብላችሁ በማሰብ ጊዜ ሳትወስዱ የምትመርጡትን ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ምክንያቱም ነገ የምትመርጡት ፓርቲ የነገ ህይወታችሁን የሚያሻሽልና የጠራ የስራ ዕድል ፈጠራ ስትራቴጂና ፖሊሲ ያለው መሆን አለበት።
ወጣቶችና ጎልማሶች በምርጫው ከፍተኛ ድምጽ እንደሚኖራቸው ይታመናል። አብዛኞቻችሁ በተለይ ጎልማሶች ባለፉት ምርጫዎች በእጅጉ ከተጎዱት መካከል ትገኛላችሁ። ይህ ዘመን እንዲመጣ ብዙ ዋጋ ከፍላችሁዋል።
ሀገራችን አሁን ለምትገኝበት ለውጥ ዋጋ የከፈላችሁ ሁሉ የከፈላችሁት መስዋዕትነት ትህነግ ማስወገድ ብቻ አይደለም መዳረሻው። ትውልዶች ዋጋ ሲከፍሉበት የቆዩትን ዴሞክራሲያዊ ስርአት እውን የሚሆንበት ሁኔታ መፍጠርም ነው። በዚህ ምርጫ ለእዚህ መሰረት በማኖር አሻራችሁን አሳርፉ።
እናንተ በምትመርጡት ፓርቲ ላይ በቂ ግንዛቤ ይዛችሁ ወደ ድምጻችሁን ስትሰጡ ሁነኛ ፓርቲ ወደ ስልጣን ይመጣል፤ እናንተ ግንዛቤ ስትይዙ ቤተሰብም፣ ጎረቤትም የመንደሩም ነዋሪ በቂ ግንዛቤ ይኖረዋል። ለእዚህም ፓርቲዎች ሀሳባቸውን ይዘው ወደ እናንተ እስከሚመጡ ድረስ አትጠብቁ፤ ወደ እነሱም ሂዱ። ምክንያቱም “ትሻልን ሰድጀ ትብስን አመጣሁ“ እንዳይሆን የሀሳብ የበላይነት ያለውንና የህዝብን ሁለተናዊ ዘላቂ ጥቅም የሚያስጠብቀውን ፓርቲ ለመምረጥ ፓርቲው በክርክር ወቅት የሚያቀርበውን ፕሮግራም በዝርዝር ማወቅ ይጠይቃል።
ይህን ማድረግ ካልቻላችሁ ውዝግብ ውስጥ ትገቡና ጎርፍ ወስዷችሁ መምረጥ የሌለባችሁን ትመርጣላችሁ። አንዴ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ደግሞ ነገሮች ያበቃሉ። ይህ ሲሆን ቁጭት ይከተላል፤ ስህተቱን ማረም የሚቻለው ከአምስት አመት በሁዋላ ነው። ይህ እንዳይሆን የምትመርጡት ፓርቲ ላይ ጥልቅ ግንዛቤ ለመጨበጥ ተነሱ። መራጮች የምትመርጡትን በሚገባ ማወቅ ባላችሁበት ወቅት ላይ ናችሁ። ልብ በሉ ግለሰብ ወይም ፓርቲ አይደለም የምትመርጡት፤ ሀሳቡን ነው። ምክንያቱም ዲሞክራሲን የሚያሰፍነው፣ ልማት የሚያመጣውና ሰብዓዊ መብትን የሚያስከብረው የፓርቲው ፖሊሲና ስትራቴጂ የጠራና ግልጽ ሲሆን ነው። ስለዚህ ምክንያታዊ ሆናችሁ ለመምረጥ የፓርቲዎችን ፕሮግራም በጥልቀት በመገንዘብ ላይ ጠንክራችሁ ስሩ።
ዘካሪያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2013