የመጀመሪያዎቹ አንድ ሺ ቀናት ከእርግዝና የመጀመሪያው ቀን አንስቶ እስከ ሁለተኛ ዓመት የልደት ቀን ያለውን ጊዜ ያጠቃልላል። በእነዚህ ቀናት የሚደረጉ እንክብካቤዎችና የአመጋገብ ሁኔታዎች የህይወታችን ቀሪ ዘመን ላይ ወሳኝ ተፅዕኖ ያሳርፋሉ። በዚህም ምክንያት “ወርቃማዎቹ የመጀመሪያ አንድ ሺ ቀናት” በመባል ይጠራሉ። ሀገራችን ብቁ ምርታማና ጥራት ያለው ትውልድ እንድታፈራ በእነዚህ 1000 ቀናት ላይ ትኩረት ሰጥተን መሥራት ይጠበቃል። እነዚህ ቀናት ወሳኝ እና እጅግ ጠቃሚ የሚሆኑበት ምክንያት ደግሞ፤ የሰው ልጅ ከፍተኛ የሆነ አካላዊ፣ አዕምሯዊ እና የማህበራዊ ክህሎት ዕድገት የሚመዘገብበት በመሆኑ፤ የቀጣይ ህይወታችን መሠረት የሚጣልባቸው በመሆናቸው ነው።
ጤናማ አመጋገብ ለሕፃናት ከ6 ወር እስከ 2 ዓመት
ሕፃናት ስድስት ወር ከሞላቸው በኋላ የእናት ጡት ወተት ለብቻው የምግብ ፍላጎታቸውን ስለማያሟላ ተጨማሪ ሌሎች ምግቦችን መጀመር ይኖርባቸዋል:: ይህ የሆነበት ምክንያት የእናት ጡት ወተት ብቻ ከስድስት ወር በኋላ ለልጆች በቂ ስላልሆነ ነው። አንድ ሕፃን ስድስት ወር ከሞላው በኋላ ተጨማሪ ምግብ መጀመር ተገቢ ይሆናል። ምክንያቱም ከእናት ወተት ወይም ከፎርሙላ በተለይም ብረት (Iron) እና ተጨማሪ ጉልበት የሚሰጡ ነገሮችን ከወተት ብቻ ማግኘት ስለማይችሉ ነው። ነገር ግን የእናት ጡት ወተት ቢያንስ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ሊወስዱ ይገባል። በዚህ የዕድሜ ክልል ሕፃናት እድገታቸው ፈጣን ስለሚሆን በቂ የሆነ ምግብ ካላገኙ ለስውነታቸው የሚሆን በቂ ኃይል (calorie) አያገኙም። በተጨማሪም ሰውነታቸው ለመቀጨጭ እና መቀንጨር ይዳረጋል። በተጨማሪም በሽታን የመከላከያ ኃይላቸው (Immunity) ዝቅተኛ ስለሚሆን ለተለያዩ ኢንፌክሽኖች ተጋላጭ ይሆናሉ።
ሕፃናት ከ6 ወር በፊት ሌሎች ምግቦችን ቢጀምሩ ችግር ይኖረዋል?
ከስድስት በፊት ሌሎች ምግቦችን መጀመር ለተቅማጥ እና ትውከት፣ የጡት ወተት መቀነስ እና የመሳሰሉት ችግሮችን ያስከትላል። በተመሳሳይ ሕፃናት ተጨማሪ ምግቦችን ዘግይቶ ቢጀምሩ ጉዳቱ ያለው ሲሆን፤ ሕፃኑ በቂ የሆነ ክብደት እንዳይጨምር እና የተለያዩ ንጥረ ነገሮች (minerals) እና ቫይታሚን እጥረት እንዲያጋጥመው ያደርጋል። ይሄም የራሱ ከሆነ ከፍተኛ የጤና ችግርን ያመጣል። በየትኛውም የዕድሜ ክልል ዉስጥ ያሉ ሕፃናትም ሆነ አዋቂዎች የተመጣጠነ ምግብ መመገብ ይኖርባቸዋል:: የተመጣጠነ ምግብ ማለት መሰረታዊ የሆኑ የምግብ ክፍሎችን የሚያካትት ነው:: ካርቦሃይድሬት (ኃይል ሰጪ ምግቦች)፣ ፕሮቲን (ሰውነት ገንቢ)፣ የዘይት እና ቅባት ምግቦች፣ ቫይታሚን እና ማህድን (በሽታ ተከላካይ) እና በቂ ወሃ ናቸው። ከእነዚህ ንጥረ ነገሮች በቀን ወስጥ ከ4 ዓይነት ሊያገኝ ይገባል።
ልጆችን እንዴት ተጨማሪ ምግብ እናስጀምራቸው?
ከላይ የተጠቀሱትን የምግብ ዓይነቶች በተለያየ መንገድ ማዘጋጀት ይቻላል። በሀገራችን የተለመደው አሠራር “ምጥን ዱቄት” ይባላል:: ይሄም በውስጡ የተለያዩ የእህል ዘሮችን ማካተት ይቻላል። ለምሳሌ 3 እጁን ከእህል ዘሮች ማለትም የተፈተገ ስንዴ÷ በቆሎ÷ ማሽላ÷ ጤፍ÷ አጃ እና የመሳሰሉትን፤ አንድ እጁን ደግሞ ከጥራጥሬ ዓይነቶች፤ ለምሳሌ ባቄላ÷ ሽንብራ÷ አተር÷ ምስር÷ ኦቾሎኒ አድርገን ማዘጋጀት፤ የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬዎችንም መጨመር እንችላለን።
ተጨማሪ ምግብ ሲጀምሩ በቀን መመገብ ያለባቸው መጠን
* ከ6 – 8 ወር ያሉ:- ከ2 – 3 የቡና ሲኒ። ከአጥሚት ትንሽ ወፈር ያሉ ምግቦች ይመከራሉ::
* ከ9 ወር – 1 ዓመት:- ከ4-5 የቡና ሲኒ። በከፊል ጠጣር (semi solid) ወይም ለስለስ ያለ ገንፎ በቀን ከ4-5 ጊዜ መመግብ ይቻላል።
* ከ1 ዓመት በላይ ግን በሲኒ መለካት አስፈላጊ አይደለም፤ ሆኖም ግን 3 ዋና ዋና የምግብ ሰዓቶችን ጠብቆ በመስጠት፤ እንዲሁም በመሃል በመሃል 2 መክሰሶችን መስጠት ይገባል:: በተቻለ መጠን የታሸጉ ምግቦችን (Processed food) ትተን በተፈጥሮ ከእህል ዘሮች ከተዘጋጁ እና በተለመዶው ምጥን ከሚባሉ ምግቦች ብንጀምር መልካም ነው:: እነዚህ ምግቦች በቀላሉ የሚፈጩ እና በውስጣቸው ከፍ ያለ የብረት ማእድን ስለሚይዙ የደም ማነስን ይከላከላሉ። በተጨማሪም ኃይል ሰጪ (carbohydrate) እና ገንቢ (protein) የሆኑ ምግቦች ናቸው:: የእህል ዘሮችን ከለመዱ በኋላ በስለው የተፈጩ አትክልቶችን ቀስ በቀስ ማስለመድ ተገቢ ነው:: ይህን ምግብ ለማዘጋጀት የእናት ጡት ወተትን ወይም ፎርሙላን መጠቀም እንችላለን። ሌላው ደግሞ በቂ ውሃ መስጠትን አለመዘንጋት ነው። ቤተሰብ ልብ ማለት ተጨማሪ ምግብን መስጠት ያለብን ምን ጊዜም መጀመሪያ በተቻለ መጠን የእናት ጡት ከጠቡ በኋላ መሆን ነው።
ተጨማሪ ምግብ ስናስጀምር ሊደረጉ የሚገቡ ነገሮች
1. ልጆች በመጀመሪያ ምግብ ለመጀመር የሚያስችሉ ምልክቶች እንዳላቸው ማረጋገጥ። ለምሳሌ ጭንቅላታቸውን ሙሉ ለሙሉ መደገፍ አለባቸው። ምግብ ሲያዩ የመዞር ምልክት ያሳያሉ፤ በዚህ ጊዜ ምግብ ማስጀመር ተገቢ ነው።
2. ተጨማሪ ምግብ በምንሰጣቸው ጊዜ ልጆች ደስተኛ እና የተረጋጉ በሚሆኑበት ሰዓት መሆን አለበት።
3. ምግብ ስናስጀምር በአንድ ጊዜ አንድ ዓይነት ምግብ ብቻ ከ3-5 ቀናት መስጠት አለብን። ምክንያቱም አንድ ዓይነት ምግብ ከሰጠናቸው ለምግቡ አላርጂ ከሆኑ እንዲሀም የሚስማማቸውን እና የማይስማማቸውን የምግብ ዓይነት ለይተን ለማወቅ ስለሚረዳን ነው።
4. በመጀመሪያ ትንሽ ትንሽ ወይም ከ1-2 የሾርባ ማንኪያ ብቻ እየሰጠን ምግቡን ማላመድ አለብን። ይህንንም ስንሰጥ ሁል ጊዜ ጡት ካጠባናቸው በኋላ መሆን አለበት። በመጀመሪያ በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ተጨማሪ ምግቡን መስጠት አለብን። ከዚያም ቀስ እያልን በቀን ከ2-3 ጊዜ መስጠት እንችላለን። ቤተሰብ ልብ ሊል የሚገባው የመጀመሪያ ሁለት ወራት ልጆችን የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማዘጋጀት የተለያዩ ጣዕሞችን እንዲያጣጥሙ ለማድረግ እንጂ ብዙ እንዲበሉ መጠበቅ የለበትም።
5. ልጆች በመጀመሪያ ምግብ እምቢ ሊሉ ይችላሉ፤ አንድን ምግብ ልጆች አልወደዱትም ለማለት ቢያንስ ያንን ምግብ ከ10-12 ጊዜ መሞከር አለብን። ትልቅ ትግሥትም ያስፈልጋል።
6. ልጆች ምግብ እንዲመገቡ ማስገደድ የለብንም፤ ነገር ግን በተቻለ መጠን እንዲመገቡ ማበረታታት አለብን።
7. ጣፋጭ ምግቦች ማብዛት የለብንም። ጣፋጭ ምግብ የሚያበዙ ልጆች ማግኘት ያለባቸውን ንጥረ-ነገር አይወስዱም፤ ምክንያቱም ጣፋጭ ምግቦች የምግብ ፍላጎት የመዝጋት ባህሪ ስላላቸው ነው። በተጨማሪ ታፋጭ ምግቦች የሚያበዙ ልጆች ለተለያዩ የጤና ችግሮች፤ ለምሳሌ – ለውፍረት፣ ለስኳር በሽታ ወዘተ የተጋለጡ ናቸው።
8. ዕድሜያቸው እስከ 3 ዓመት ላሉ ልጆች ደረቅ ነገሮች፤ ለምሳሌ እንደ ለውዝ ያልተፈጩ ፍራፍሬ ወዘተ መስጠት የለብንም፤ ምክንያቱም ለትንታ ስለሚያጋልጣቸው ነው።
9. ተጨማሪ ምግብ በጀመርን ጊዜ ምግቡ ላይ ጨው እና ስኳር መጨመር አይመከርም፤ ምክንያቱም ለተለያዩ የጤና ችግሮች ስለሚያጋልጣቸው ነው።
10. የላም ወተት ከአንድ ዓመት በታች ላሉ ሕፃናት ከተቻለ መስጠት የለብንም። ምግብ ለማዘጋጀትም ቢሆን የእናት ጡት ወተት ወይም የቆርቆር ወተትን መጠቀም ይመከራል።
11. ከአንድ ዓመት በታች ላሉ ልጆች ማር መስጠት የለብንም። በተለምዶ አፋቸውን ኮልታፋ ስለሚያደርግ ሳይሆን ክሎስትሪድየም የተባለ ባክቴሪያ ሊገኝበት ስለሚችል እና ይህ ባክቴሪያ መርዛማ ኬሚካል የሚያመነጭ በመሆኑ ከፍተኛ የጤና ችግር ከመሆንም አልፎ ህይወት እስከ መቅጠፍ ሊያደርስ የሚችል አደጋ ስለሚያስከትል ነው።
12. የተለያዩ የለሥላሳ መጠጦችን፣ ጁሶችን (ጁስ ከመስጠት ይልቅ በቤት ውስጥ ፈጭተን ወይም ቆረጥ ቆረጥ አድርገን ብንሰጣቸው የተሻለ መሆኑ ይመከራል)። በቀን ውስጥ አንድ ሕፃን መውሰድ ያለበት የጁስ መጠን ከ120 አስከ 180 ሲሲ መሆነኑን መገንዘብና በዚሁ ልክ ብቻ መስጠት ይገባል።።
ምንጭ፦ ከ”ሀኪም ፌስቡክ” ገጽ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013