ውሸት መቼም ቢሆን የትኛውንም ዓይነት ቀለም ቢቀባና ለእውነት የቀረበና የተጠጋ ቢመስልም ፍጥረታዊ ምንነቱ ተለውጦ እውነት ሊሆን ግን አይችልም። ከዚህ ይልቅ እውነት መስሎ በሄደባቸው መንገዶች ሁሉ የሰውን ልጅ በአጠቃላይ፣ አንድን ማህበረሰብ ደግሞ እንደማህበረሰብ፣ ከዚያም አልፎ አንድን ግለሰብ እንደ ግለሰበር የከፋ ዋጋ ከማስከፈል ያለፈ ፋይዳ ኖሮትም አያውቅም።
ከፍጥረት ጀምሮ እስከ ዛሬዋ ቀን በዘመናት መካከል የተፈጠሩ ውሸቶችና የውሸት ትርክቶች የከሰሩበት እንጂ ያተረፉበት የታሪክ ምዕራፍ የለም። ከዚያ ይልቅ ከሰው ልጅ ፍጥረታዊ ውድቀት ጀምሮ በውድቅት ላይ ውድቀት እየጨመረ ባለንበት ዘመን ውሸት የአደባባይ እውነታ ሆኖ የብዙ ግራ መጋባት ምክንያት ሆኗል።
ከዚያም በላይ ሰዎች የተረጋጋ ሕይወት በመኖር ወደ አሰቡትና ወዳቀዱት እንዳይደርሱ ብሎም በሙሉ ሃሳባቸውና መንፈሳቸው የህይወት ጉዟቸውን እንዳይመሩ አድርጓቸዋል። ከዚያም በላይ እንደሀገር በአንድ ወቅት ታላቅ የነበሩ ፣ የብዙታሪክና ስልጣን ባለቤት የሆኑ ሃገራትን የድንጋይ ክምርና የሰቆቃ ድምፅ ምንጭ አድርጓቸዋል።
ፈጽሞ ለማመን የሚከብዱ የውሸት ትርክቶች ተደጋግመው ከመሰማታቸው የተነሳ የሰሚውን ዕውነት የመለየትና የመቀበል ጥንካሬ ተፈታትነው ፣ እውነት የሆኑ ያህል ተቀባይነት አግኝተው ፣ በእውነት ላይ ልእልና ያገኙ እንስኪመስሉ ቢደርሱም የጉዳዩን ባለቤቶች ከፍ ያለ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ያመጡት ሰብዓዊ ትሩፋት የለም ፣ ወደ ፊትም አይኖርም።
ይህ እውነታ በኛም ሀገር እንደ ሀገር በየዘመኑ ያስከፈለን ዋጋ በቀላሉ የሚሰላ አይደለም። ድንገትም አሁን ያለንበት ተጨባጭ የህይወት እውነታ የዚህ ችግር ድምር ውጤት ሊሆን እንደሚችል ለመገመትም ብዙ የሚከብድ አይደለም። በየዘመኑ የህዝባችንን የተረጋጋ ሕይወት የሚፈታተኑ ውሸቶችና የውሸት ትርክቶች ተፈጥረዋል ፤ በህዝባችንም ውስጥ ተዘርተዋል።
አብዛኛው ሕዝባችን ለመረጃ ያለው ቅርበት ትኩረት እና መረጃን የማጥራት ባህል ዝቅተኛ መሆን የውሸት ትርክቶች ብዙ ዋጋ እንዲያስከፍሉት አድርጓል። ከዚያም ባለይ በህዝባችን ተስፋ ላይ የሚያደቡ ጠላቶቻችን ይህንን ክፍተት እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር ዛሬም ህዝባችንን ከጀመረው የመለወጥ መንገድ ለማደናቀፍ ሌት ተቀን እየሠሩ ነው።
በተለይም ፍጥረታዊ ማንነቱ በውሸትና በውሸት ትርክቶች ላይ የተመሰረተው የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ገና ከፍጥረቱ ፍጥረታዊ መሰረቱን በህዝቦች መካከል አለመተማመንን በሚፈጥሩ፤ ግለሰቦችን ይዘዋቸው ከመጡት ማህበረሰባዊ ማንነት የሚያፋቱ እና የማንነት ግራ መጋባት ውስጥ በሚከቱ የፖለቲካ ተጠቃሚነት ያስገኛሉ ተብለው በተፈጠሩ የውሸት ትርክቶች የተሞላ ነው።
ይህ እውነተኛ ባህሪው የብዙዎችን የፍትህ ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ህልም አምክኗ። ከዚያም በላይ እንደ ሀገር ከፍጥረቱ ጀምሮ ሀገርና ህዝብን ከፍያለ ዋጋ አስከፍሏል። ዛሬ እንዳይመለስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላም ከተቀበረበት መቃብር ቆፍሮ ለመውጣት ደቀ መዝሙሮቹ በአጋራቸው ፍጥረታዊ ባህሪው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
የፍጥረትም ሆነ የዓለም ታሪክ የሚያስተምረን እውነት ምንም ያህል የሞተ ቢመስልና ቢቀበርም መቃብርን ደርምሶ የመውጣትን ፍጥረታዊ ልእልና አለው። ከዚህ በተቃራኒ በፍጥረቱ ሙት የሆነውና በውስጡ ህይወት የሌለው ውሸት ይህን የማድረግ ብቃት የለውም። ሲጀመርም ሙት ነው፤ ሲቀበርም ሙት ነው።
የአሸባሪው ህውሓትም እውነታ ከዚህ የተለየ አይደለም፣ በብዙ የውሸት ትርክቶችና በአነዚህ ትርክቶች በሳቱ ንጹሐን ደም ሕይወት ያለው እስኪመስል ህያው መስሎ ቢቀርብም ፣ እራሱ በፈጠራቸው የውሸት ትርክቶችና ትርክቶቹ በፈጠሩት መታወር ሙት መሆኑን በአደባባይ አሳይቷል።
ይህ አሸባሪ ድርጅትና የጥፋት አጋሮቹ ከለውጡ ዋዜማ ጀምሮ ለውጡንና የለውጡን መንፈስ ለማጠልሸት የሄዱባቸው መንገዶች በውሸትና በንጹሐን ደም ላይ የተመሰረቱ ነበሩ። በፈጠሯቸው የውሸት ትርክቶች መጠንም የብዙ ንጹሐን ደም ፈሷል።
ይህ እውነታ ለብዙዎች የቡድኑ አዲስ የለውጥ ዋዜማ ባህሪው ቢመስላቸውም እውነቱ ግን ከዚህ በላይ የሆነ የፍጥረታዊ ማንነቱ መሰረትና መገለጫ ነው። የሚያሳዝነው ደቀመዛሙርቱ በፍጥረታዊ ማንነቱ ሙት ለሆነው ለአሻባሪው ህወሓት በውሸት ትርክቶች ህይወት ለመስጠት የሚያደርጉት ጥረት ነው።
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ ወቅቶችና በተለያዩ መድረኮች ያደረጓቸውን ተስፋ አለምላሚ ንግግሮች ቆርጠውና ቀጥለው ተስፋ አድራቂ አድርገው ለማቅረብ ያደረጉት ጥረት የቡድኑ ፍጥረታዊ ባህሪ ማሳያ ነው። ከመምህሩ ደቀመዝሙር እንደሚባለው ውሸትና የውሸቱ መንፈስ የቱን ያህል በከፋ መልኩ በደቀመዝሙርቱ ላይ እንዳደረና ሕያው ሆኖ እየተገለጠ መሆኑን በተጨባጭ ያሳየ ነው!
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013