እንደ ኢትዮጵያውያን የዘመን አቆጣጠር 1888 ዓ.ም፣ ዓድዋ … የቅኝ ግዛት ፍላጎቱን ለማሳካት ኢትዮጵያን የወረራው ዒላማ አድርጎ ገስግሶ የመጣው የኢጣሊያ መንግሥት/ጦር በኢትዮጵያውያን ልዩና ታሪካዊ አንድነት በተሰጠ ምላሽ የሽንፈት ማቁን ተከናነበ። ጣልያኖች ዓድዋ ላይ ድል ከሆኑ በኋላ ለአጭር ጊዜ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ የሚከተሉትን የመስፋፋት ፖሊሲ እንደመግታት ብለው ነበር። ከሽንፈቱ በኋላ አዲስ የተሾመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዲ ሩዲኒ ቀዳሚው ፍራንችስኮ ክሪስፒ ያራምድ የነበረውን ፖሊሲ ሽሮታል፤ ለቅኝ ግዛት ማስፋፊያ የተመደበውን በጀት በግማሽ ቀነሰው፤ ከአድዋ ጦርነት በፊት አንገቱን ደፍቶ የነበረው የፀረ-ኮሎኒያሊስት ቡድን አሁን የልብ ልብ አግኝቶ ኢጣሊያ ከነአካቴው የአፍሪቃን ምድር ለቃ እንድትወጣ ለመጠየቅ ተዳፈረ። ይህ ሁሉ ግን የቆየው ለአጭር ጊዜ ነበር።
ከእንግሊዝ ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም የጋራ ድንበር ያሏቸውን ቅኝ ግዛቶች የምታስተዳድረው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ችላ ብላ መኖር አልቻለችም። ከዓድዋ ሽንፈት 30 ዓመታት በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው አምባገነኑ የፋሺዝም አቀንቃንኝ ቤኒቶ ሙሶሊኒ፣ ራሱን እንደ ሮም የቀድሞው ንጉስ ጁሊየስ ቄሳር በመቁጠርና “የኢጣሊያን ክብር ለዓለም አሳያለሁ” በሚል የረጅም ጊዜ ተስፋ የቅኝ ግዛት ዘመቻውን ሊያሳካ ላይ ታች ማለቱን ተያያዘው። ነገሩ ይህ ብቻ አልነበረም፤ ኢጣሊያውያን በውስጥ ችግሮቻቸው ላይ የነበራቸውን ትኩረት ለማስቀየር፣ እየጨመረ ለመጣው የኢጣሊያ ህዝብ የማስፈሪያ ቦታ ለመፈለግ እንዲሁም በአውሮፓ መድረክ የከሸፈበትን የመስፋፋት ፖሊሲ ለማካካስ ቅኝ ግዛትን አማራጭ አድርጎ ተነሳ። ከሁሉም በላይ ግን ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ሙሶሊኒ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዞረ።
ኢጣሊያ ዓድዋ ላይ የተከናነበችውን ሽንፈት ለመበቀል ለአርባ ዓመታት ያህል ስትዘጋጅ ከኖረች በኋላ በየጊዜው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በባህል መስክ የተፈራረመቻቸውን የሰላምና የትብብር ውሎችና በመንግሥታትቱ ማኅበር አባልነቷ የገባቻቸውን ዓለም አቀፍ ግዴታዎች ሁሉ ‹‹ከእንግዲህ አላውቃቸውም›› አለች። ከብዙ ጊዜያት ዝግጅትና የጠብ አጫሪነት እንቅስቃሴዎች በኋላ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ወረረች።
ይሁን እንጂ መቼውንም ቢሆን በአገሩና በነፃነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፋሺስትን አገዛዝ ‹‹አሜን›› ብሎ አልተቀበለውም። ይልቁንም ጨርቄን ማቄን ሳይል ‹‹ጥራኝ ዱሩ›› ብሎ ለነፃነቱ መፋለም ጀመረ። የኢጣሊያ ወራሪ ኃይልም አንዲትም ቀን እንኳን እፎይ ብሎ ሳይቀመጥ ከአምስት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ ሌላ የሽንፈት ማቅ ለብሶ ከኢትዮጵያ ምድር ተባረረ። ታዲያ በዚህ አስገራሚና አኩሪ የመስዋዕትነት ጉዞ ውስጥ ደማቅ የጀግንነት ታሪክ ከፃፉና ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተጋደሉ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች መካከል አንዱ ቢትወደድ አዳነ መኮንን (አባ ደፋር) ነበሩ።
አዳነ ከአባቱ ከልጅ መኮነን መንገሻ እና ከእናቱ ከወይዘሮ ብዙነሽ አበበ በሚያዝያ ወር በ1887 ዓ.ም በወልቃይት ጠገዴ፣ ዓዴት፣ በተባለ አካባቢ ተወለደ። አዳነ ገና በልጅነቱ ነበር እርሻ ማረስና ተኩስ መተኮስ የተለማመደው። ተኩስ መለማመዱና አነጣጥሮ ተኳሽ መሆን መቻሉ ጎበዝ አዳኝ እንዲሆን አስቻለው። ለአደን ሲወጣ ያለ ግዳይ አይመለስም ነበር። ጦር አዋቂነቱም የአካባቢን ሰው ጉድ ያሰኝ ጀመር። በቅልጥፍናውና በተኳሽነቱ ስሙ የገነነው ወጣቱ አዳነ፤ በወቅቱ የበጌምድር ገዢ የነበሩትን የራስ ጉግሳ ወሌ ሠራዊትን ተቀላቀለ። በወጣቱ አዳነ ቅልጥፍናና የጦር ስልት የተደነቁት ራስ ጉግሳ ወሌ ለአዳነ የቀኝ አዝማችነት ማዕረግ ሰጡት።
ራስ ጉግሳ በሚያዝያ ወር 1922 ዓ.ም በተደረገው የአንችም ጦርነት ከሞቱ በኋላ ቀኛዝማች አዳነ የአርማጭሆ፣ የያይራና አካባቢው ገዢ ሆነው አስተዳድረዋል። ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጥቂት ቀደም ብሎ ቀኛዝማች አዳነ በስሜን በጌምድር የወልቃት ጠገዴን፣ የአርማጭሆንና የሰቲት ሁመራን ድንበር እንዲጠብቁ ተመረጡ። ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሲወር ቀኛዝማች አዳነ ከፊታውራሪ ኃይሉ ፋሪስ፣ ከቀኛዝማች ዓባይ ወልደ ማርያም፣ ከቀኛዝማች መስፍን ረዳ፣ ከቀኛዝማች ገብሩ ገብረ መስቀል እና ከሌሎች ጀግኖች አርበኞች ጋር በመሆንም በዚያ በር ጠላት እንዳይላወስ ማድረግ ችለው ነበር።
ቀኛዝማች አዳነና ጓዶቻቸው የወልቃይት ጠገዴንና አካባውን ሕዝብ በማስተባበርና በመምራት የወራሪውን ጦር እየተፋለሙ ሳለ የወታደርና የመሳሪያ ብልጫ የነበረው የፋሺስት ጦር በግዙፍ ጦር ታግዞና እልህ አስጨራሽ በሆነ ውጊያ ወደ ጎንደር ዘለቀ። ቀኛዝማች አዳነና ሌሎች አርበኞችም ከጠላት ጋር መፋለማቸውን ቀጠሉ።
ቀኛዝማች አዳነ መኮነን የወራሪውን ጦር ለመመከት የወልቃይት ጠገዴ አርበኞችን አሰባስበው ኃይል በማደራጀት መዋጋታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። በሚያዝያ ወር 1928 ዓ.ም የቀኛዝማች አዳነ ጦር ደብዛ በተባለ ስፍራ ላይ የደፈጣ ውጊያ በማድረግ በፋሺስት ጦር ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ ብዙ መሳሪያ መማረክ ችሏል።
በመቀጠልም በኅዳር ወር 1929 ዓ.ም የቀኛዝማች አዳነ ጦር በፋሺስት የጦር ሰፈር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከፍቶ ብዙ ወታደሮችን ገድሎ ጠብመንጃና ጥይት ማረከ። በአርበኞቹ የተበሳጨው የፋሺስት የአካባቢው አስተዳዳሪ ሕዝቡን ትጥቅ ለማስፈታት ሞከረ። ይሁን እንጂ የአካባቢው ሕዝብ የፋሺቶችን ድርጊት ክፉኛ በመኮነን አርበኞቹን በመቀላቀሉ የቀኛዝማች አዳነ ጦር ተጠናከረ።
የፋሺስት የአካባቢው አስተዳዳሪ የአርበኞቹን አመፅ ለማጥፋትና ለመደምሰስ ብዙ የባንዳ ጦር በማሰማራት ላይ እንዳለ በጥቅምት ወር 1930 ዓ.ም በቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራው የወልቃይት ጠገዴ የአርበኞች ጦር ፈጣን የሆነ የደፈጣ ጥቃት አድርሶ ብዙ የፋሺስት ወታደሮችን ደምስሷል። በዚህ ክፉኛ የተበሳጩት ፋሺቶቹ፤ በዚያው ወር ብዙ ጦር አሰባስበው ከአርበኞች ጋር ገጠሙ። የአርበኞቹ ጦር ባለድል ሆነ። ተስፋ ያልቆረጠው የጠላት ጦር ለሦስተኛ ጊዜ፣ በኅዳር ወር 1930 ዓ.ም፣ ከአርበኞቹ ጋር ከባድ ውጊያ አደረገ። አሁንም ድሉ የኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ሆነ።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን የነቀኛዝማች አዳነን የአርበኝነት እንቅስቀሴ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደምሰስ እንዳለባቸው ያመኑት ፋሺስቶቹ ቀደም ሲል ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች ሁሉ ጠንከር ያለ ጥቃት ለመክፈት ወሰኑ። በእቅዳቸው መሰረትም በሁለት አቅጣጫዎች፣ በዓዲ-ረመጥ እና በወገራ በኩል፣ አድርገው የአርበኞቹ መነኻሪያ ወደነበረችው ዓዴት ዘለቁ።
የፋሺስት ሠራዊት ማይ ገና የተባለውን አካባቢ ዙሪያ ገባ ይዞ ነበር። እነቀኛዝማች ደግሞ አካባቢውን ከጠላት ለማላቀቅ ተዘጋጅተዋል። የጠላትን ሠራዊት ለማሸነፍ ይረዳ ዘንድ ውሃውን ቀድሞ መያዝ የእነቀኛዝማች አንደኛው እቅድ ነበር። በዚህ ጊዜ ታዲያ አንዱ የቀኛዝማች አዳነ አርበኛ …
‹‹አዴት ማይ ገና ላይ ካልተሠራ ቤቴ፣
ወንድም አልወለደች መካን ናት እናቴ›› ሲል ጃሎ አለ። ጦሩ ተነሳ፤ምድር ቁና ሆነች። ማይ ገና ላይ ጦርነት ተካሂዶ በሁለቱም በኩል ከፍተኛ እልቂት ቢደርስም ድሉ ግን የአርበኞቹ ሆነ። ይህ ድል በቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራውን የአርበኞቹን ጦር ትልቅ ዝናና ክብር ሰጠው። የአርበኞቹን ቁጥር እጅግ ከፍ አደረገው። የጠላት ጦርም ሽንፈቱን አምኖና አማራጭ አጥቶ ዓዴትን፣ ማይ ገናን፣ ቀራቅርን፣ ጨጓርኩዶንና አካባቢውን ለቆ ወጣ።
በአርበኞቹ ጀግንነትና ቆራጥነት የተገረመው የፋሺቶቹ ጦር መሪ ለጓደኞቹ ‹‹ … የሸፈቱት ሰዎች አምስት ናቸው ብላችሁኝ ነበር፤ እኔ እንደምመለከተው ግን መሬቱም ጭምር ሸፍቷል። ጥይት የሚመጣው ከመሬት ውስጥ ጭምር …›› ብሎ መናገሩን በታሪክ ተጽፏል።
በጀግናው ቀኛዝማች አዳነ መኮነን የሚመራው ጦር ትግሉን በዚህ አላቆመም። ትግሉን በመቀጠል በጥር ወር 1930 ዓ.ም ጠለሎ በተባለው ስፍራ ላይ መሽጎ የነበረውን የጠላት ጦር በአካባቢው ተወላጅ በሆኑት በደጃዝማች ደስታ ማሩ መሪነትና አስተባባሪነት እንዲደመሰስ አደረጉ።
ድሉ እየሰፋ ሄደ። እነቀኛዝማች አዳነ ወደ ደጋው ጠገዴ አመሩ። ጠገዴ ከፋሺቶች ነፃ ወጣች። በቀኛዝማች አዳነ ጀግንነት የተደሰተው የአካባቢው ሕዝብ ተሰብስቦ ‹‹ … ማዕረግ ኖሮዎት ለእኛም ማዕረግ እንዲሰጡን ደጃዝማች ብለን ሹመንዎታል …›› አላቸው። እርሳውም ሹቱን ተቀበሉ፤ለተከታዮቻቸውም ማዕረግ ሰጡ። በሕዝብ የተሰጣቸው የደጃዝማችነት ማዕረግና እርሳቸውም ለአርበኞቻቸው የሰጡት ሹመትና ማዕረግ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በደስታ አፅድቀውላቸዋል።
ታርቆ ክንዴ ጠገዴ ተጉዞ ስለቢትወደድ አዳነ መኮንን ባጠናቀረው ጽሑፉ የነደጃዝማች አዳነን ጀግንነት እንዲህ ሲል ገልፆታል …
‹‹ … ጠገዴ ነፃ ወጣች። የአርበኝነቱ ሥራ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ቀጠለ። የጠገዴ አርበኞች በደጃዝማች አዳነ መኮንን፣ የጃኖራ ቆላ ወገራ አርበኞች በደጃዝማች ሐጎስ ተሰማ፣ የአርማጭሆ አርበኞች በደጃዝማች ብሬ ዘገዬ፣ የጠለሎ አርበኞች በደጃዝማች ደስታ ማሩ፣ የደብረ ሐርያና የቃብትያ አርበኞች በፊታውራሪ መስፍን ረዳ፣ የአውራ አርበኞች ደግሞ በደጃዝማች አያናዬ ቸኮል እየተመሩ ወልቃይትን ከፋሺስቶች ነፃ ለማውጣት ዘመቱ።
የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊትም አዲ ኮኮብ ላይ ሠፍሮ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ አርበኞች ደግሞ ከአዲ ኮኮብ በሥተምሥራቅ በኩል በሚገኘው የማይ ለሞን ተራራን ተጠግተው ሠፈሩ። እነዚያ ጀግና አርበኞች ጠላትን እንዴት መግጠም እንዳለባቸው እየተመካከሩ በሠፈራቸው ቆዩ። ተከዜን ተሻግሮ ስሜን በጌ ምድርን የረገጠው የጠላት ጦር ሲርቅ በባሩድ እሳት ይለበለባል፤ሲቀርብ በሳንጃ ይሞሸለቃል። የሚሆነውን አጥቷል። አርበኛው በማይ ለሞን ተራራ እንደሠፈረ የደጃዝማች አዳነ መኮንን ጦረኛ የነበረ ሥጦት መኮንን የተባለ ጀግና ጦርነት ለመግጠም ቸኩሎ ነበርና በደጃዝማች አዳነ ድንኳን አጠገብ ሆኖ እንዲህ ብሎ አቅራራ …
‹‹ቂርቆስ ማይ ለመሞ የሁለት ፈሪ ሀገር፣
ወይ እነርሱ አይመጡ ወይ እኛ አንሻገር››
‹‹እስኪ ድገመው›› አለ አርበኛው። ደገመው። ጦሩ ፎክሮ ተነሳ። በግራ በኩል የአርማጭሆ አርበኛ በደጃዝማች ብሬ ዘገዬ፤ በቀኝ በኩል የጠለሎ፣ የቀብትያ፣ የደብረ ሐርያ፣ የአቀወርቅና የአውራ አርበኛ በፊታውራሪ መስፍን ረዳና በደጅ አዝማች፤ የጠገዴ አርበኛ በመሐል በደጃዝማች አዳነ መኮንን እየተመራ ውጊያ ገጠመ። በደጃዝማች አዳነ መኮንን የሚመራው ጦር አስቀድሞ ከጠላት ሠፈር ደረሠ። የጠላትን ጦር እስከነባሩዱ ያቅመው ጀመር። ጠላት ማምለጫ አጣ። በቀኝና በግራ የገባው አርበኛ መፈናፈኛ አሳጠው። የጠነከረ ሮጦ አመለጠ። ያልቻለ እጅ ሰጠ። የፈረደበትም እየተነደፈ ሞተ።
ገሪማ ታፈረ በ‹ጎንደሬ በጋሻው› መጽሐፋቸው ‹ … በዚህ እልቂት የጠላት ወታደር ሬሳ አንዱ በአንዱ ላይ ተከምሮ የኑግ ነዶ መስሎ ይታይ ነበር …› ብለዋል። አርበኝነቱ ቀጠለ። እነደጃዝማች አዳነ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራን ነፃ አወጡ። ቀኛዝማች አዳነ ለዚያ አካባቢ ገዢ ሾመው የፋሺስት ጦር ወዳለበት ሌላኛው የስሜን በጌምድር አውራጃ ወደ ዳባት አቀኑ። ድል በድል እየሆኑ ገሰገሱ። ጣልያን ተጨነቀ። ሠራዊቱ በጦር በጎራዴ አለቀ … ››
ደጃዝማች አዳነ በሱዳን ጠረፍ የኢትዮጵያን ድንበር ጠላት እንዳይረግጥ አያሌ ጀብዱዎችን እየፈፀሙ የተከላከሉ አርበኛም ነበሩ። ከፋሺስት ጋር በሚዋጉበት ወቅት ከፋሺቶቹ በማረኩት መትረየስ ‹‹ተመልከት!›› ብለው የኢጣሊያን ተዋጊ አውሮፕላን እንደጣሉም ይነገርላቸዋል። በጀግንነታቸውም
‹‹አዳነ መጣ ጥርሱን አግጥጦ፣
ኧረ መጠጊያ ትንሽ ቁጥቋጦ።
አይቆረጠም የድንጋይ ቆሎ፣
አይወረወር የእሳት አሎሎ፣
ፍቅሩን ነው እንጂ ጠቡን ማን ችሎ›› ተብሎላቸዋል።
የፋሺስት ጦር ጠላት በኢትዮጵያ ምድር በቆየባቸው አምስት ዓመታት ውስጥ ደጃዝማች አዳነ መኮነን በዓዴት፣ በማይገና፣ በቀራቅር፣ በጨጓርኩዶ፣ በጠለሎ፣ በደጀና፣ በዓዲ-ረመጥ፣ በቤተ-ሙሉ፣ በአርማጭሆ፣ በጃኖራ፣ በአጅሬ፣ በጭልጋና በወገራ ከ55 ጊዜያት በላይ ከጠላት ጋር ጦርነት በመግጠም ድል አድርገዋል። የፋሺስት ጦር ከኢትዮጵያ ከተባረረ በኋላም ደጃዝማች አዳነ በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የቢትወደድነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የወገራና ጭልጋ ገዢ ሆነው አካባቢውን አስተዳድረዋል።
ቢትወደድ አዳነ መኮንን በጦር አርበኝነት ከፈፀሟቸው ደማቅ የጀግንነት ገድሎች በተጨማሪ የልማት አርበኛነታቸውም ይጠቀስላቸዋል። የሑመራ የሰሊጥ ምርት እንዲስፋፋ እንዲሁም መንገድን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ሥራዎች እንዲጠናከሩ አድርገዋል።
ቢትወደድ አዳነ በጦርና በልማት አርበኛነታቸው ላከናወኗቸው አኩሪ ተግባራት ካገኟቸው ሽልማቶች መካከል፡-
- የአምስት ዓመት የአርበኝነት አገለግሎት ሜዳሊያ
- የቅዱስ ጊዮርጊስ የጀብዱ ሜዳሊያ
- (የአፍሪካ ኮከብ) የወርቅ መዳሊያ (ከታላቋ ብሪታንያ)
- የቅዱስ ጊዮርጊስ ኒሻን (የፈረሰኛ ደረጃ)
- የዳግማዊ ምኒልክ የክብር ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ
- የሰለሞን የክብር ኮከብ (ባለ አምበል)
- የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የክብር ኮከብ የወርቅ ሜዳሊያ
- የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የወርቅ መዳሊያ … ይጠቀሳሉ።
በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት የስሜን በጌ ምድርን አርበኞችን ከመሩትና አስደናቂ የጀግንነት ተጋድሎዎችን ከፈፀሙት ኢትዮጵያውያን ጀግኖች መካከል አንዱ የነበሩት የጦር ሜዳ ጀግናውና የልማት አርበኛው ቢትወደድ አዳነ መኮነን (አባ ደፋር) በ1970 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013