ርእሴ በዛ በብሔራዊ ኀዘን ወቅት (በሊቢያ በአልሻባብ የተቀሉ የሚሌኒየሙ ሰማእታት ወጣቶቻ ችንን አስመልክቶ) በብሔራዊ ትያትር መድረክ ላይ የተነበበው የጌትነት እንየው “እኛው ነን” ነቃሽ፣ ወቃሽና አልቃሽ ግጥም ተፅእኖ እንዳለበት ከወዲሁ መናገር ተገቢ ብቻ ሳይሆን ሰብዓዊነት ነው። በእግረ መንገድም የወቅቱን የገጣሚውንና የታዳሚዎቹን (ከፍተኛ የአገሪቱ ባለስልጣናትን ጨምሮ)፤ እንዲሁም የመላው የኢትዮጵያ ህዝብን ጥልቅ የኀዘን ድባብና ስሜት ማስታወስም እንደዚያው።
ጣትን ከመቀሰር ይልቅ እራስን ወደ ውስጥ ማየትን የሚመክረው “እኛው ነን” ገሳጭ ግጥም በትክክል እንዳስተላለፈው በወቅቱ ለነበረው መከራ የእኛ አስተዋፅኦ የለበትም በማለት ሁሉንም ነገር በሌላው ላይ መደፍደፍ በፍፁም አይቻልም፤ ስህተትንም አይቶ፣ መርምሮና ተረድቶ ለማስተካከል አያስችልም። ይህንን “የግጥሙ መልዕክት በአጭሩ” ተብሎ እንዲያዝልን እያሳሰብን ወደ እራሳችን፤ ወደ ተነሳንበት “እኛው ነን” እንሂድ።
“እኛ” ከ”እነሱ”፣ “እናንተ”፣ … ከመሳሰሉት ቃላት (ምድብ ተውላጠ ስሞች) ይለያል። በደረሰ አደጋም ሆነ ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ጣትን ወደ ሌላው፣ ወደ ውጪ ከመጠንቆል ይልቅ ወደ እራስ፣ ወደ ውስጥ በማየት የችግሩን መንስኤ ፈልጎ ማወቅና መፍትሔውን ማፍለቅ ላይ ማተኮርን የሚያስገነዝብ ነው። እንዲሁም የጋራ ኃላፊነትን፣ የጋራ ተጎጂነትን የሚያመለክት፣ የጋራ ተጠቃሚነትንም የሚያበስር (በሰዋሰው ክፍሉ ተውላጠ ስም) ነው – እኛ። “እኛው ነን” ስንልም እንደዚሁ ኀላፊነቱም ሆነ ተጠያቂነቱ፤ አድራጊዎቹም ሆንን ተደራጊዎቹ፣ ጎጂም ሆንን ተጎጂዎቹ እኛው፤ ተወቃሽም ሆንን ተወዳሽ እኛው መሆናችንንና ላለው፣ ለሚታየው፤ እየሆነ ላለው ሁሉ በቅድሚያ ተጠያቂው እራሳችን መሆናችንን ለማመልከት ነው።
እዚህ ላይ ግን “እኛው ነን” ስንል “እነሱ” ማለትም ድርጊቱን በቀጥታ የፈፀሙትም ሆኑ ያስፈፀሙትን፣ ያሰቡትንም ሆነ ሃሳቡን ወደ መሬት ያወረዱትን፤ የተላኩትንም ሆነ ሹምባሾቹን (“የታሪክ አተላ(ዎች)” ማለት ምን ማለት ይሆን?) ወዘተ ጉዳይ አይመለከትም ማለት አይደለም፤ ይመለከታቸዋል። በመሆኑም በውስጡ እነሱንም ታሳቢ በማድረግ ነው ሃሳብ የምንለዋወጠው ማለት ነው።
እዚህ ላይ ከላይ በገደምዳሜ የተሽከረከርንበትን በቀጥታ ስናቀርበው “እኛው ነን” የተባለበት ምክንያትና ያስከተለው ውጤት ምንድን ነው? የሚል ይሆናል።
ይህን ጽሑፍ “እኛው ነን” በሚል ርዕስ መሰየም ያስፈለገበትም ሆነ በአጠቃላይ ጽሑፉ ውስጥ ለ”እኛው ነን” ከፍ ያለ ስፍራ መስጠት ያስፈለገበት ዐቢይ ጉዳይ አገራችን አሁን ላለችበት ውስብስብና ምስቅልቅል ሁኔታና እውነታ፤ በቦሀ ላይ ቆረቆር እንዲሉ ምንም ሳይኖረን ገና ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ እየወደሙ መሆናቸው (በፊት ሻሸመኔ፣ አሁን ደግሞ አጣዬ)፤ በገዛ አገርና ቀዬአቸው የንፁሐን ደም መፍሰስና ህይወት ማጣት፤ በማያዋጣው ብሄር እየተቧደኑ መጫረስና ሌሎች በርካታ ጥፋቶች ሁሉ ኃላፊነቱ የእኛ ነው፤ ተጠያቂውም እኛው ነን የሚለውን አቢይ ጉዳይ ከስሩ ለማስመር በመፈለግ ነው። የማይረባ ጥያቄ/አጀንዳ አመንጭዎችም እኛው፤ የማይረባ አጀንዳ አራማጆችም እኛው፤ ለማይረባ አጀንዳ ሟቾችም ገዳዮችም እኛው … መሆናችንን ለማሳየት በማሰብ ነው። ከተሳካልንም ገጣሚው “ምናልባት ቢያስፏጨው” እንዳለው ምናልባት ቢያስታግሰን በሚል ተስፋም ጭምር ነው።
ይህ ጸሐፊ በዚህ በ”እኛው ነን” ርዕስ ስር ለተዘጋጀ ጽሑፍ “አይደለንም” በሚለው ተገላቢጦሽ በኩል ለማሰብና “ነን?” ወይስ “አይደለንም?” ከሚሉት በአንደኛው ድምደሜ ላይ ለመድረስ መክሮ “አይደለንም” የሚለው ድምዳሜ ላይ የሚያደርስ አቋም ለመያዝ የሚያስችል በቂ ምክንያት ማግኘት ባለመቻሉ በዚሁ በ”እኛው ነን” በመጽናት እኛኑ በማሄስና እኛኑ በመውቀስ ሃሳብ ላይ ሊፀና ችሏል። ማለትም ለደረሰው፣ ሁሉም እንኳን ባይሆን፣ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የእኛና የእኛው ድርሻ ነው ማለት ነው። ይህንን ለማመን ካስቸገረ፤ እራስን ካስፈለገ እንደ ግለሰብ፣ ካልሆነም እንደ ተቋም፤ ያም ካልሆነ እንደ ዜጋ ቆጥሮ፤ እራስንም ጠይቆና ምላሹንም ከእራስ ለእራስ ሰጥቶ በተገኘው ውጤት መሰረት እራስን መመርመር ነው። ያኔ ሁሉም ግልፅ ይሆናልና በ”እኛው ነን” መስማማት ይቻላል ማለት ነው።
በእርግጥ ጉዳዩ፣ አሁን የገጠመን (ከዚህም ከዚያም) ችግር ከ”እኛ ነን/አይደለንም” የዘለለ የሚመስልበት መልክ አለው። ያ መልኩም ከእኛ “ውጪ” በሆነ ሁኔታ ሌሎች አካላት (ኃያላን) ስለ እኛ ከእኛው በላይ እናውቃለን፤ ለእኛ ከእኛው በላይ እናስባለን ወዘተ ሲሉ መሰማታቸውና ጣልቃ ገብነታቸውም ከኃያልነታቸው ባወረዳቸው መልኩ ጎጃም ካልሄድን፣ ቀበሌ ድረስ ካልወረድን በማለት እስከ መግለጫና እቀባ ድረስ ሲዘልቁ መታየታቸው በቂ ማሳያ ነው።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባለፈው ሰሞን በንዴት ሲናገሩ እንደተሰማው የውጭ ጠላቶቻችን ተነስተውብናል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ካሉ በኋላ የተናገሩት ነው አንገት የሚያስደፋውና የ”እኛው ነን” ማረጋገጫ ሆኖ ከተፍ የሚለው – “ፕራይመርሊ [በዋናነት] ከእኛው ከውስጥ ነው፤ የኛው ሰዎች . . .” ነበር ያሉት። እኛም አሁንም እንላለን እኛው ነን። (ይህ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አነጋገር ይህን ጸሐፊ ያስታወሰው ጉዳይ ቢኖር የደቡብ አፍሪካውን ዘመነ አፓርታይድ አገዛዝ ሲሆን፤ በወቅቱ በእነዛ ሁሉ የስቃይና የመከራ ዘመናት ውስጥ በሆዳቸው ተገዝተው ለነጩ ያደሩና ወገናቸውን ለስቃይ፣ እንግልት፣ ሞት የዳረጉ ደብብ አፍሪካዊያን ነበሩ። በወቅቱ ለደቡብ አፍሪካ ነፃነት ይሟገቱ የነበሩ ደቡብ አፍሪካዊ ምሁራንና ሌሎችም እነዚህን ባንዳዎች የሚገልጹዋቸው ላያቸው ጥቁር ውስጣቸው ግን ነጭ (blacks in white blood) በማለት ነበር። አሁንም የእነዛ ሰዎች ታሪክ በተነሳ፣ በተነገረና በተፃፈ ቁጥር “blacks in white blood” የሚለው ቀዳሚ ቃል ሆኖ ነው የሚነሳው – በራሱ መንገድ “የታሪክ አተላ” የሚለውን በማረጋገጥ።)
የ”እኛው ነን” ሌላው መገለጫ የቋንቋ እውቀታችን ሲሆን እሱም በእኔ፣ እኛ፣ እሱ/ሷ፣ እነሱ … ወዘተ አጠቃቀማችን ነው።
እነዚህ ስሜት ኮርኳሪና በቀጥታ ከሰው ልጅ አጠቃላይ ማንነት ጋር የተያያዙ “ቃላት” አይደለም በእውኑ ዓለም በፈጠራ ዓለም እንኳን ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቁ/የሚሹ፤ በተገኘበት ቦታ ሁሉ የማይደነጎሩ ሆነው ሳለ እኛ ግን “እኛ” እና “እነሱ” እየተባባልን መባላላታችን ለወሬም እማይመች ነውና ሳይቃጠል በቅጠል እያልን ይህም የኛው እንጂ የሌላ አካል ችግር አለመሆኑን ለመግለጽ ነው።
በአጠቃላይ አሁን ላለንበት አጠቃላይ ሁኔታ ተጠያቂዎቹ በቀዳሚነት እኛው ነን፤ በሱዳን ሳይቀር እንናቅና እንደፈር ዘንድ በሩን ወለል አድርገን የከፈትነው እኛው ነን፤ ለግብፅ ነጋ ጠባ ድንፋታ የልብ የልብ የሰጠነው እኛው ነን፤ ሌሎች በቀደዱልን ቦይ እዚህም እዚያም የምንባላው ያለነው እኛው ነን፤ ለማይረባ ሳንቲም ብለን አገርን ያህል ነገር፤ ህዝብን ያክል ወገን አሳልፈን እየሰጠን ያለነው እኛው ነን፤ ኢትዮጵያ ትፍረስ የምንለውም እኛው ነን …። በዚህ ሁሉ መካከል አንድ ደስ የሚል ነገር ቢኖር “ኢትዮጵያ አትፈርስም!!!” የምንለውም እኛው መሆናችን ነው። የእናት ሆድ …
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2013